ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ስምምነት የአፍሪካ ቀንድ የኃይል አሰላለፍን እንደሚቀይር ተገለፀ Featured

አቶ መለስ አለም አቶ መለስ አለም ፎቶ፡- ፀሐይ ንጉሤ

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያና ኤርትራ በኩል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ያለመግባባት ከመፍታት ባለፈ፤ የቀጣናውን የኃይል አሰላለፍ እንደሚቀይር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበትን 100ኛ ቀን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከርና አህጉራዊ ውህደት እንዲመጣ እየሰራች ከመሆኗ ባሻገር ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት መፈጸሟ፤ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተደማጭነት እንደሚያሳድገውና የኃይል አሰላለፍን እንደሚቀይረው አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰላም ማስከበር እና አደራዳሪነት ሚና ስላላት ተደማጭነቷን እንደሚያጎላው ጠቁመዋል፡፡ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋር የበለጠ መተማመን በመፈጠሩ እንዲሁም በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ መድረኮች የዲፕሎማሲ ሚናዋ ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚያደርገው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን በቆዩባቸው ቀናት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሥራዎች የተሰሩበት፣ የላቀ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ድል የተገኘበትና ታሪክ የተቀየረበት ነው፡፡ በተለይም ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት የዘለቀውን አለመግባባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንና በኤርትራ መንግሥት ቅን ምላሽ በመሰጠቱ ለዲፕሎማሲ ሥራው ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በአገራቱ መካከል የተደረሰው ስምምነት ያለ ማንም አሸማጋይና ጣልቃ ገብነት የተተገበረ በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡
የሁለቱን አገራት ስምምነት በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ እና ሌሎች አገራትም በተናጠል ድጋፋቸውን መግለጻቸው የዲፕሎማሲ ሥራው ስኬታማነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዲፕሎማሲ ሥራው አገሪቱ የገጠማትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ የተገኘበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥረትም ኢትዮጵያ ያላትን ውክልና ለማስፋት የተሰራው ሥራ በአውሮፓ ዘሄግ ኔዘርላንድስና ዳሬሰላም በታንዛኒያ የቆንጽላ ጽህፈት ቤትና ኤምባሲ መክፈት መቻሏን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለያዩ አገራት በእስር የቆዩ ሦስት ሺ ዜጎችን በማስፈታትና በጠላትነት ተፈርጀው የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ አገር እንዲመለሱ መደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራ ስኬት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለአገሪቱ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ስኬት የውስጥ ሰላምና አንድነት ዋነኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በህዝቡ መካከል የተፈጠረው የሰላምና የአንድነት መንፈስም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በ100 ቀናት ውስጥ ያመጡት ዲፕሎማሲያዊ ለውጥ ‹‹የ100 ቀናት 1001 ስኬቶች›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።