ቤተክርስቲያኗ በአባቶች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት እየሰራች ነው Featured

አቡነ ማቲያስ መግለጫ በሰጡበት ወቅት አቡነ ማቲያስ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ፎቶ - በገባቦ ገብሬ

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ሶስት ሊቃነ ጳጳስትን ሰይማ እየሰራች መሆኗን አስታወቀች። 

የቤተክርስቲያኒቷ ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱሰ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርዕስ ሊቃነ ጳጳስት ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጉዳይን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ከሐምሌ11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአባቶች መካከል እርቀ ሰላም በማውረድ አለመግባባቱ ፍጻሜ እንዲያገኝ ሶስት ሊቃነ ጳጳስትን ሰይማ እየሰራች ነው።
በውጭ አገር የሚገኙ አባቶችም ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ የቤተክርስቲያኒቷ አንድነት እንዲመለስ ለማድረግ ጥረት እያደረገች መሆንዋን ገልፀው፤ ይህም እውን እንዲሆን ካህናትና ምዕመናን በጸሎት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ የጠፋውን ሰላም ለመመለስ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ቅዶስ ሲኖዶሱ ባካሄዳቸው በአራት ጉባዔዎች ጊዜያት ሊቃነ ጳጳሳትን መድቦ ወደ አሜሪካ በመላክ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል፡፡ ሲኖዶሱ በየዓመቱ በሚያካሂዳቸው ጉበዔዎቹም በሩን ክፍት አድርጎ መቆየቱን አስታውሰው፤ አለመግባባቱን ወደ ሰላም ለማምጣት ባለፈው ጥቅምት በተካሄደው የሲኖዶሱ ጉባዔ ከካህናትና ምዕመናን የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ያቀረበውን የዕርቅ ጥያቄ በአዎንታ መቀበሉን አስረድተዋል።
እንደብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ገለፃ፤ እርቀ ሰላሙ በቤተ ክርስቲያኒቷ ቀኖና መሰረት የሚካሄድ ሲሆን በእርቀ ሰላሙ አጠቃላይ ሂደት ሲኖዶሱ ፍቃድ ከሰጠው አካል ውጭ ሌላ አካል መግለጫ መስጠት ጠቃሚ አይሆንም፡፡
በተመሳሳይ በአገሪቱ በአዲስ መንፈስ የህዝቡን አንድነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፤ በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የነበረው አንድነትና ቤተሰባዊነት ወደ ፍጹም ሰላም ለማምጣት እየተከናወነ ያለውን ጅምር ቤተክርስቲያኒቷ እንድምትደግፍም ገልጸዋል።

አጎናፍር ገዛኸኝ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።