የዘመናትን እንባ ያበሰ ለውጥ

ለሁለት አስርት ዓመታት በባላንጣነት ሲተያዩ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ዳግም ወደ ሰላማዊ ግንኙነት ተመልሰዋል፡፡የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦችም ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡በተለይም በኤርትራ የቅርብ ዘመድ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራውያን በሁለቱ ሀገራት መካከል ዳግም የተጀመረው ሰላማዊ ግንኙነት እንዳስደሰታቸው በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ የተጀመረው መልካም ግንኙነት አዲስ ዕድል ይዞላቸው እንደሚመጣም ተስፋ ሰንቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያዊ አባትና ከኤርትራዊት እናት የተወለደው ሳሙኤል መንገሻ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት አሉታዊ ተፅዕኖ ካሳረፈባቸው አንዱ ነው፡፡ የ27 ዓመቱ ሳሙኤል ላለፉት 20 ዓመታት እናቱንና የእናቱን ቤተሰቦች አግኝቷቸው አያውቅም፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ሀዘንም ይሁን ደስታ ሳይካፈል መኖሩ ሁሌም ይቆጨው እንደነበር ይናገራል፡፡
‹‹የወጣትነት እድሜ ከቤተሰብ ጋር የመቀራረብ ጊዜ ነው›› የሚለው ወጣት ሳሙኤል ከቤተሰቡ ጋር ባለመቀራረቡ በሕይወቱ ትልቅ ነገር እንዳጣ ይሰማው እንደነበር ይናገራል፡፡ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረው ችግር ተፈትቶ ቤተሰቦቹን ለመገናኘት ሁሌም ይመኝና ይጸልይ እንደነበር ይናገራል፡፡
በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከልዑካኖቻቸው ጋር በኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በሀገራት መካከል የነበረው የጥላቻ ግንብ ፈርሶ ሊያቀራርቡ የሚችሉ ስምምነቶችን መፈፀማቸውን በማየቱም ‹‹ምኞቴ እንደሰመረ ፀሎቴ በፈጣሪ ዘንድ መልስ እንዳገኘ ይሰማኛል›› ይላል፡፡ ለኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአስመራ የተደረገውን አቀባበል ሲመለከት ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት የደስታ እንባ ያነባ እንደነበር ነው ወጣት ሳሙኤል የተናገረው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ኤርትራ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ቤተሰቦቹን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም እስካሁን እንዳላገኛቸው የተናገረው ወጣት ሳሙኤል አሁንም ደጋግሞ ወደ ኤርትራ ስልክ እየደወለ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ስልክ ባይሰራ እንኳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ ሲጀምር ወደ ኤርትራ ሄዶ ቤተሰቦቹን ለማግኘት ማቀዱን ያመለክታል፡፡
እንደወጣት ሳሙኤል ማብራሪያ፤ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ተቋርጦ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዳግም መጀመሩ ለሁለቱ ሀገራት በርካታ ጥቅም አለው፡፡ የሀገራቱ ድንበር ሲከፈት ማሕበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስሩ ይጠናከራል፡፡ በመካከላቸው እንቅስቃሴ ስለሚኖርም የአንዱ ሀገር ዜጋ በሌላ ሀገር መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ እድል ይፈጥራል፡፡ ይህም የሕዝቡ ተጠቃሚነት ይጨምራል፡፡ በሁለቱ ሀገራት እንደሌሎቹ ጎረቤት ሀገራት ሁሉ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ድንበር ተሻግረው መገበያየት መስራት ስለሚችሉ የገበያና የስራ እድል ይፈጥራል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን በተመጣጣኝ ዋጋ የመጠቀም እድል ስለሚኖራት ለኢትዮጵያ በተለይም ከወደብ ኪራይ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ወጣቱ ይናገራል፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ወደብ መጠቀም ከተቻለ የእቃዎች ዋጋ ስለሚቀንስ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኑሮ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይገልጻል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ለተፈጠረው ሰላም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ትልቁን ድርሻ እንደሚ ወስዱ በመግለጽ፤ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በሀገራቱ መካከል ለብዙ ዓመታት የቆየው ጥሩ ያልነበረ ግንኙነት እንዲያበቃ ወስነው የሰላም ጥሪውን መቀበላቸው የሚያስመሰግናቸው ነው ብሏል፡፡
እንደ ሳሙኤል ማብራሪያ፤ ከዚህ በኋላ ዳግም ችግር እንዳይፈጠር ሁለቱም ሀገራት ለውይይት በራቸውን ክፍት አድርገው መነጋገርን ባሕላቸው ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ትናንሽ ችግሮች ላይ ትኩረት ባለማድረግ ሀገራቱ ለፍቅር ላቅ ያለ ቦታ በመስጠት ግንኙነታቸው ዳግም እንዳይበላሽ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ እንደ አጋጣሚ አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን መወያየትና ፍቅርን ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡
ወይዘሮ ልቺያ ጆቫኒ ከኤርትራ በልጅነታቸው የወጡ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ትዳር መስርተው ልጅ ወልደው ይኖራሉ፡፡ እናታቸውን ጨምሮ አብዛኛው ቤተሰባቸው ኤርትራ ውስጥ እንደሚኖር ይናገራሉ፡፡ ኤርትራ ካለ ቤተሰብ ጋር ተገናኝተው እንደማያውቁ የሚናገሩት ወይዘሮ ልቺያ ከቤተሰቦች መካከል በሕይወት ያሉትንና የሞቱትን እንኳን እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የስልክ አገልግሎት መጀመሩን ተከትሎ ወደ ኤርትራ ደውለው ቤተሰብ ማግኘታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ልቺያ፤ ከቤተሰቦቻቸው የተወሰኑትን ማግኘታቸውን በመግለጽ በስልክ የደስታ እንባ ሲያነቡ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡
የልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ልቺያ ልጆቻቸው በኤርትራ ከሚኖር ቤተሰባቸው ጋር ለመገናኘት ከፍተኛ ጉጉት ውስጥ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን የመጀመሪያ በረራ ተጠቅመው ከልጆቻቸው ጋር ወደ ኤርትራ ለመብረር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ሰሞኑን በሁለቱ ሀገራት መካከል የታየውን መልካም ጅማሮ ሲመለከቱ በጣም ደስተኛ እንደሆኑ በመግለጽ ‹‹በአስመራ ጎዳናዎች የነበረውን ሁኔታ በቴሌቪዥን መስኮት ስከታተል አይኖቼ እንባ መቆጣጠር አቅቷቸው ነበር›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ልቺያ ማብራሪያ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው በጎ ግንኙነት ለሀገራቱ ትልቅ ጥቅም ያስገኛል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ ላይ ጥሎ የነበረውን ማዕቀብ እንዲያነሳ ጥያቄ ማቅረባቸው ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርሳቸው መተሳሰብ መጀመራቸውን ማሳያ ነው፡፡ የሁለቱን ሀገራት ሰላም ለማደፍረስ ለሚፈልጉ ኃይሎች እድል ባለመስጠት የተጀመረውን የሰላም ስራ ማስቀጠል አለባቸው፡፡
ወጣት አቤል ገብረ እግዚአብሄር ደግሞ በረሃ አቋርጦ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ሶስት ዓመት እንደሆኑት ይጠቅሳል፡፡ ላለፉት ሶስት ዓመታት ከቤተሰቦቹ ጋር ሳይገናኝ መቆየቱን ጠቅሶ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረው ሰላም እንዳስደሰተው ይገልፃል፡፡ ሰሞኑን ወደ ቤተሰቦቹ ደውሎ ከእናቱና ከሌሎች ቤተሰቦቹ ጋር እንደተገናኘ ያመለክታል፡፡
እንደ ወጣት አቤል ማብራሪያ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ ጉብኝት ያደረጉ እለት የነበረውን ሁኔታ ሲመለከተው ልዩ ስሜት ፈጥሮበታል፡፡ የተፈጠረው ሰላምና ወዳጅነት ወደፊት የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች እንደፈለጉ እየተንቀሳቀሱ የሚሰሩበት እድል ስለሚፈጥር ለሁለቱ ሀገራት ዜጎች ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡
የዛሬ ሶስት ዓመት ኢትዮጵያ ሲገባ ኢትዮጵያውያን ያደረጉለት አቀባበል በጣም ልብ የሚነካ እንደነበር ያወሳው ወጣት አቤል፤ ኢትዮጵያውያንን እንደ ወንድሞቹ እንደሚመለከት ኢትዮጵያንም እንደ ሀገሩ እንደሚያያት ነው ያብራረው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ባይጀምርም በነጻነት እንደፈለገ ወጥቶ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

ዜና ሐተታ
መላኩ ኤሮሴ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።