መግለጫው በተሰጠበት ወቅት፤ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ Featured

በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት መጎልበትና እና ዘርፉን ለማዘመን የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን የገበያ ሁኔታ የሚዳስስ ጉባኤ ትናንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የገንዘብ አገልግሎት ስልጠናና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ወልዳይ አምሃ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ በቅርቡ እንደመጀመሩ የሚያበረታታ ቢሆንም አፈፃፀሙ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራትም ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ይገኛል። በዕድሜ አዋቂ ከሆነው ህብተሰብ መካከል ስድስት በመቶ የሚሆነው ብቻ ዲጂታል የገንዘብ ልውውጥ ተጠቃሚ ነው።

እንደ ዶክተር ወልዳይ ገለጻ፤ አገልግሎቱን በማሳደግ በአገሪቱ ያለውን የገንዘብ ልውውጥ ሁሉን ያካተተ ማድረግ ይቻላል። ለእዚህም እ..አ በ2030 በገጠር ቀበሌዎች የሞባይል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን 50 በመቶ ለማድረስ እንዲሁም የሞባይል ባንክ አካውንት ያላቸውን 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል።

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በሞባይል፣ በኢንተርኔት፣ በፖስታና በኤቲኤም ማሽኖች ማከናወን እንደሚቻል ያስረዱት ዶክተር ወልዳይ፤ ከገንዘብ ኖት ንክኪ ነፃ የሆነ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል። የአገሪቷ የባንክ ቅርንጫፎች በማይደርሱባቸውና የመሠረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው የገጠር አካባቢዎች ገንዘብን በወኪል አማካኝነት ለመለዋዋጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነቢል ኬሎ፤ የዲጂታል ቢዝነስ እንዲስፋፋ በማድረግ በኢትዮጵያ ያለውን የፋይናንስ ዕድገት ማፋጠን እንደሚቻል ተናግረዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ህብረተሰቡን በአካባቢያቸው የገንዘብ ልውውጥ ዘዴ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸዋል። በርካታ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ ሰዎችን የገንዘብ ልውውጥ ስርዓት ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

በሞባይል ግብይትና ፋይናንሻል ሥራዎች ላይ አማካሪ ኢግናሲዮ ማስ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በርካቶችን ያካተተ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት አመቺ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች የሞባይል ግብይትን ለማስፋፋት የሄዱት ርቀት እንዳለና የአገልግሎት ክፍያውም ተመጣጣኝ መሆኑን ተናግረዋል። አንድ ሺ ብር ለማስተላለፍ አስር ብር የአገልግሎት ክፍያ የሚፈፀምበት የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ርካሽ እንደሆነና የዲጂታል ፋይናንስ እንዲስፋፋ እንደሚያበረታታ አስረድተዋል።

የቤል ካሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ወኪል ኔትወርክ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ጉልላት እንደገለጹት፤ ሄሎ ካሽ የሞባይል ባንኪንግ የሙከራ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሶማሌ ክልል ላይ ነበር። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች በመስፋፋት 190 ሺ ተጠቃሚዎችንና ሁለት ሺ ወኪል ቅርንጫፎችን ማፍራት ተችሏል። አገልግሎቱ ህብረተሰቡ ተንቀሳቃሽ ስልክን በመጠቀም የባንክ አገልግሎትና የገንዘብ ዝውውርን በአቅራቢያው የሚያገኝበትን አሠራር ፈጥሯል። በዚህም የሞባይል ስልክ በመጠቀም የአገልግሎቱ ደንበኛ ላልሆኑ ሰዎች ገንዘብ ለመላክ ያስችላል።

 

ፀሐፊ ጌትነት ተስፋማርያም

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።