ተቋማቱ ተማሪዎችን አስመረቁ

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲና ቤተል ሜዲካል ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ።

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ33ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸው ተማሪዎች ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ 798 ተማሪዎችን ሲያስመርቅ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አረጋ ይርዳው፤ ዩኒቨርሲቲው በአገሪቱ የማዕድን ዘርፉ እንዲያድግ ለማገዝ የማዕድን ምህንድስና ትምህርት ክፍል ከፍቶ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ማስመረቁን ገልፀዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍም ብቁ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት በቀጣይ አመት በእንስሳት እርባታ ቴክኖሎጂና በአትክልት ፍራፍሬ ምርት

ቴክኖሎጂ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በግብርናውና በማዕድን ዘርፍ ብቁ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃኑ ሲሳይ፤በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ ከተመረቁት 798 ተማሪዎች መካከል አሰራ ሰባቱ በማዕድን ምህንድስና እንዲሁም ሃያ ስምንቱ በሲቪል ምህንድስና ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው የተመረቁ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ሌሎቹ ግን በተለያዩ ነባር የትምህርት መስኮች የተመረቁ ናቸው።

በአሁን ወቅት ዩኒቨርሲቲው ስድስት የድህረ ምረቃና አሰራ ሶስት የቅድመ ምረቃ መርሃ ግብሮች እንዳሉት የጠቀሱት ዶክተር ብርሃኑ፤ ከሃምሳ በላይ አጫጭር የስልጠና ኮርሶች በማዘጋጀት ለተለያዩ ድርጅቶች መሰጠቱን ገለፀዋል፡፡ በቀጣይ አመት በአመራር ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡ በአዳማና በደሴ በሚገኙት የዩኒቨርሲቲው ቅርንጫፎች 222 ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ አመልክተዋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የተለየ አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦች ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ቤቴል ሜዲካል ኮሌጅ ለ11ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 88 ተማሪዎች ትናንት አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኮሌጁ ዲን ፕሮፌሰር ለገሰ ዘርይሁን እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ባለፉት 11 አመታት ውስጥ 1676 ተማሪዎችን በማስመረቅ የሰለጠነ የጤና ባለሙያ ለማፍራት የድርሻውን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ዘንድሮም በክሊኒካል ነርስና በጤና መኮንንነት ካስመረቃቸው 88 ተማሪዎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ 16 ተማሪዎች በሕክምና ዶክትሬት ማስረቁን ጠቅሰዋል። በቀጣይም በ26 ሺ ካሬ ቦታ ላይ የጀመረውን የማስፋፊያ ስራ ሲያጠናቅቅ 1500 ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ አብራርተዋል፡፡ በሕክምና ዶክትሬት የተመረቁት ተማሪዎች በራሳቸው ከፍለው የተማሩ ቢሆንም በመንግስት ስር ተመድበው ለሁለት አመት ለማገልገል ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ ዶክተር መስፍን አርአያ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ያለውን የሰለጠነ የጤና ባለሙያ ክፍተት ለመሙላት የሚደረገው ጥረት በመንግስት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ከግሉ ዘርፍ ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

ቤቴል ሜዲካል ኮሌጅ ያስመረቃቸው ተማሪዎችም በጤናው ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ለተጀመረው ጥረት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ የገለጹት ዶክተር አርአያ፤ በግል ጤና ኮሌጅ ደረጃ 16 ዶክተሮችን ማፍራት የባለሙያዎች እጥረት ላለባት ሀገር እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። በተለይም ከተመራቂዎቹ ዘጠኙ ሴቶች መሆናቸው በህክምናው ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም ላሉ ሴቶች አርአያ የሚሆን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

 

 

ፀሐፊ መርድ ክፍሉና ራስወርቅ ሙሉጌታ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።