‹‹ይህ ትውልድ የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ሞገስ የሚያዋርዱትን የመታገል ግዴታ አለበት›› - ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

ይህ ትውልድ ትናንት በድህነት የሚታወቀውን የአገሪቱን ገጽታ የመለወጥና የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ሞገስ የሚያዋርዱትን የመታገል ግዴታ እንዳለበት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አመለከቱ፡፡

‹‹ሰንደቅ ዓላማችን የሉዓላዊነት መገለጫ፤ በብዙሃነት ላይ የተመሰረተው አንድነታችን ዓርማ ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ ለ9ኛ ጊዜ በነገው ዕለት በመላ አገሪቱ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ በብሄራዊ ቤተ መንግስት በሰጡት መግለጫ፤የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ የነጻነት ትግልና ድል፣ የዘላቂ ሰላም፣ የብሔራዊ እኩልነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና በራስ ትጋትና ጥረት ወደ ስልጣኔ ለመውጣት የሚደረገውን ትግልና የውጤቱም አርማ ነው፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፣ የዚህ ዘመን ትውልድ ሰንደቅ ኣላማዋ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ፣ በጽኑ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ መሰረት ላይ እንድትቆም ያላሰለሰ ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እንዲሁም የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ሞገስ የሚያዋርዱትን የመታገል፣ የማስቆምና የመኮነን ኃላፊነትና ግዴታም አለበት፡፡

‹‹ሰንደቅ ዓላማ የሀገሮች መለያ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ቢችልም ለኢትዮጵያውያን ግን ከዚህ በላይ የጠለቀና የረቀቀ ትርጉም አለው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከታሪክ አንጻር የነጻነት ጉልህ አርማ፤ ከብዝሃነት አኳያ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ አንድነት መገለጫ ምልክት በመሆኑ ይህ ትውልድ ትናንት በድህነት የሚታወቀውን የአገሪቱን ገጽታ የመለወጥ፣ ክብሯን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የማድረግ ግዴታ አለበት። በዚህ ሂደት የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ሞገስ የሚያዋርዱትን ሊታገላቸው እንደሚገባ በአፅንኦት አሳስበዋል።

የሰንደቅ ዓላማ ትርጉም ጥልቀት የሚኖረው በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ፍላጎቶችን በፍትሃዊነት ማርካት ሲቻል በመሆኑ፤ ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ እውቀትና ጉልበቱን በማስተባበር ስኬታማ ሆኖ መገኘትና ከፊት የሚያጋጥመውን ፀረ ልማት አደጋ በተባበረ መንፈስ መመከት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፤ የበለጸገችና ጠንካራ አገር ለመገንባት የአመለካከት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው መላው ህዝብ የተጀመረውን ልማት የማስቀጠል አገራዊ ኃላፊነትና ግዴታም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

«ዛሬ የሰንደቅ ዓላማዋ ከፍታ በዓለም መድረክ እየጨመረ ሲሆን ይህም መላው የአገሪቱ ህዝቦች በእልህና በቁጭት መንፈስ በድህነት ላይ የከፈቱት ዘመቻ ብሔራዊ ክብርን ከፍ እያደረገው በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም እየተመዘገበ ያለውን ልማት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለመቀልበስ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በአገሪቱ ጥቅም ላይ አፍራሽ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት እውን ሆኖ ሳለ፤ ልዩነትን በኃይል ለመጨፍለቅ መሞከር ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በመሆኑ መላው ህዝብ ሊታገለው የሚገባ ጉዳይ ነው» ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በልማት በሚገለጸው ብሔራዊ አርበኝነት አማካኝነት ብሔራዊ ክብርና ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ እንድትል መላው ህዝብ ላደረገው አስተዋፅኦ ፕሬዚዳንቱ አመስግነው፤ በአሁኑ ወቅት ለሥርዓቱ አደጋ የሆኑትን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ የተጀመረው ልማት እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አቅር በዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እንደ ሽፋን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ማፍረስና ለግል ፍላጎትና ጥቅም ለማዋል የሚጥሩ ፀረ ሰላም ኃይሎችን መላው ህዝብ ነጥሎ ማውጣትና ብሔራዊ ጥቅምን ለጠላት አሳልፈው በመስጠት የተሳተፉትን ማጋለጥና መታገል ይጠበቅ በታል፡፡ የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የአገር መከላከያ ሰራዊትና የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ከህዝቦች ጋር በመሆን ባካሄዱት አኩሪ ተጋድሎ የአገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ አልፎ ለአፍሪካ ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት ተችሏል፡፡

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የሚከበረው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በስኬት ተጠናቆ የሁለተኛው በተጀመረበትና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማስፋፋት ተግባሮች እየተሰሩ በሆኑበት ወቅት መሆኑን አመልክተው፤ ፓርኮቹ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ከማምጣት ባሻገር ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡ እንዲሁም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ዋና ዋና አገራዊ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

 

ፀሐፊ ዑመር እንድሪስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።