ተፈጥሮን ለመታደግ የተቀናጀ ጥምረት

 

ዜና ሐተታ

ተፈጥሮ ላይ ያነጣጠረ አሉታዊ ተጽእኖ የአገር ብሎም የዓለም ስጋት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች ተከስቶ የነበረው የአየር መዛባት በተለይም በግብርናው ምርታማነት ላይ ያስከተለው ቀውስ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ድርቁን ተከትሎ የተፈጠረው የሰብል ምርት መቀነስም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደ አንድ መድረክ በዚሁ ጉዳይ ላይ አተኩሮ መክሯል፡፡ ውይይቱ በኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እና በፖፕሌሽን ሄልዝ ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም ትብብር የተዘጋጀ ነው፡፡ ውይይቱም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሥነ- ሕዝብ እና የተዋልዶ ጤና እንዲሁም በቤተሰብ ዕቅድ የተቀናጀ ጥምረት፣ በወንዞች ተፋሰስ ልማት፣ በደን ሀብት፣ በጥብቅ ቦታዎች አያያዝ እና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች አገራዊ ገፅታ ቢኖራቸውም መድረኩ በዋናነት ትኩረቱን በኦሮሚያ ክልል ላይ አድርጎ ነበር፡፡

የፖፕሌሽን ሄልዝ ኤንድ ኢንቫይሮመንት ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም ዋና ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ተክሉ፤ በቤተሰብ እቅድና በጤና አገልግሎቶች በተከናወኑ ተግባራት የውልደት መጠን እና ሞት መቀነሱን ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና በክልሉ እነዚህ ለውጦች እየተመዘገቡ ቢሆንም በአንዳንድ የደን እና ጥብቅ ቦታዎች እንዲሁም የአርብቶ አደር አካባቢዎች የአገልግሎት እጥረቶች በስፋት ስለሚስተዋል ለወደፊት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ይናገራሉ፡፡ የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማም ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጠጋግተው በሚኖሩባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተቀናጀ የልማት አገልግሎቶችን ማዳረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መፍትሔዎችን ማመላከት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ብዛት ባላቸው ደኖችና ተፋሰሶች አካባቢ የሕዝብ ቁጥር ማሻቀብ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያስከትለው ችግር በርካታ ነው፡፡ በመሆኑም በሥነ ተዋልዶ ጤና እና የቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር እስካሁን ዘርፎች በተናጠል መፍትሔ ሲፈልጉ ነበር፡፡ የአካባቢዎቹ ችግሮች ግን ውስብስብና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም አገሪቱ በዘርፉ የያዘቻቸውን የዘላቂ ልማት ግቦችና ዕቅዶች ለማሳካት በጤና እና በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም አካባቢ ጥበቃ ላይ የተሰማሩ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

«የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ቀዳሚ ችግር ድህነት ነው» የሚሉት አቶ ነጋሽ፤ «በዚህ ምክንያት ኑሯቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተፈጥሮ ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ተፈጥሮ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖ ከፍተኛ ነው» ይላሉ፡፡ በተቀናጀ መልኩ ለነዋሪዎቹ አማራጭ የኑሮ መንገዶችና የልማት አቅጣጫዎች ማመላከት ካልተቻለ የጉዳዩ አሳሳቢነት እየጨመረ እንደሚመጣ ያስገነዝባሉ፡፡

የአካባቢ፣ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ሽፈራው ነጋሽ፤ የድንበር ተሸጋሪ ወንዞችን መነሻና ብዙ አገር በቀል እፅዋትን በዘላቂነት ለመጠበቅ የተቀናጀ አሠራር ወሳኝ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ አገር የተቀናጀ ልማትን እውን ከማድረግ አንጻር አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ተግዳሮቶችና ውስንነቶች መኖራቸውን ያነሳሉ፡፡ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና የልማት ፍላጎቶችን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ ከተለመደው የተናጠል አሠራር መውጣት እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጆች ጤና እና አኗኗር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሥነ ሕዝብን ተለዋዋጭ ባሕሪ፣ የሰው ልጆች ጤና እና የመኖሪያ አካባቢ ቁርኝት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ትኩረት እንደሚፈልግ የገለጹት ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ ናቸው፡፡ ጫናው በተለይም በሴቶችና በወጣቶች ላይ የሚበረታ በመሆኑ ጉዳዩ የላቀ ትኩረትን ይጠይቃል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ኃላፊ ዶክተር ሀሰን የሱፍ በበኩላቸው፤ ክልሉ ወደ አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ የሚኖርባቸው ሰባት ብሔራዊ ፓርኮች አሉት፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው የያዩ ደንን ጨምሮ 15 ጥብቅ ደኖች በዋናነት ሰው ሰራሽ የሆኑ ችግሮች ተጋርጠውባቸዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ውድ ሀብቶች ሁሉን አቀፍ የሆነና ዘላቂነታቸውን የሚያረጋግጥ መፍትሔ እንደሚሹ ጠቁመዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት በ2003 .11 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የደን ሽፋን በ2007 .ም ወደ 15 በመቶ ማደጉን ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ብሩክ በርሄ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።