የትምህርቱን ዘርፍ ተግዳሮት የነቀሰ መድረክ Featured

13 Feb 2017

በትምህርት ሰራዊት ግንባታ በአንዳንድ አካባቢዎች የተሻሉ ስራዎች ቢኖሩም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አልታየም፤

የአምባሰል፣የአንቺ ሆዬ፣የትዝታና ባቲ  የሙዚቃ ቅኝት መፍለቂያ በሆነችው ታሪካዊዋ ስፍራ ደሴ ከተማ የትምህርት ዘርፍ ማህበረሰብ  ተገናኝተዋል። ሰሞኑን አንድ ላይ በመገናኘት በሴቶች አመራር፣በትምህርትና  ሰራዊት ግንባታ፣ በአይሲቲ፣ በሰላማዊ መማር ማስተማር ፣ በትምህርት ጥራት፣ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ችግሮች ናቸው፣ለስራው እንቅፋት ሆነዋል ብለው ያሏቸውን  አንስተው በህጸጾቹ ዙሪያ ተወያይተዋል።

 ባለፉት ስድስት ወራት ጥሩ አፈፃፀም አሳይተዋል ከተባሉ ተቋማት የልምድ ልውውጥ ተካፍለዋል። የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥም በቀጣዩ ስድስት ወራት ትኩረት ሰጥተው በመስራት ዕቅዶቻቸውን ከግብ  ለማድረስም ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

ሴቶችን ወደ አመራር ለማብቃት የተደረገውን ጥረት በተመለከተ ከተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ   ሴቶች ወደ አመራርነት እንዳይመጡ የሚያግዳቸው  አንዱ ምክንያት  ያሉባቸው ተደራራቢ ኃላፊነት መሆኑን ነው የጠቆሙት። በአመራርነት ቦታ ያሉት  ወንዶች  ስለሆኑ ለሴቶች ሳይሆን ለወንዶች የማድላት ዝንባሌ ይታያል። ሴቶች አመራር ላይ ከወጡም በኋላ  የሚያጋጥማቸውን ችግር  አጉልቶ በማቅረብ ማሸማቀቅ እና ከቦታቸው እንዲነሱ  የማድረግ ሁኔታዎች  መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። «ለአሞራና ለድመት በአንድ ዕቃ ውሀ አይሰጥም» እስከማለት ደርሰዋል። በመሆኑም ሴቶችም ከወንዶች እኩል ተወዳደሩ ሊባሉ አይገባም። ከቤት ውስጥ  ስራ ጀምሮ በየደረጃው ኃላፊነታቸውን መጋራት፣ሴቶችን በትምህርት እንዲበቁና አመራርነቱን ከታች ጀምሮ እንዲለማመዱ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው ሀሳብም ተነስቷል።

 በትምህርት ሰራዊት ግንባታ በአንዳንድ አካባቢዎች የተሻሉ ስራዎች ቢኖሩም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳልተገኘ ነው የተነገረው። በተለይ ከተማሪዎች አንድ ለአምስት አደረጃጀት  ጋር ተያይዞ ጥሩ በሚባል ደረጃ ውጤት እየታየ ነው። ዝቅተኛ  ውጤት የነበራቸው ተማሪዎች በአንድ ለአምስት ተደራጅተው በመተጋገዝ ውጤታቸውን ለማሻሻል ችለዋል። ለዚህም በምሳሌነት የተጠቀሰው የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ነው። እንደአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲ መምህራን በኩል  የለውጥ መሳሪያን በመጠቀምና መተግበር በኩል ያለው እንቅስቃሴ  ደካማ  መሆኑ ተገምግሟል።

ከአይሲቲ ጋር ተያይዞም በነባር  ዩኒቨርሲቲዎች  የተሻለ አጠቃቀም መኖሩ ነው የተገለጸው። ለመማር ማስተማር፣ ለጥናትና ምርምር  እንዲሁም የተፋጠነ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት  አይሲቲን መጠቀሙ ተገቢ ነው። በዚህም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች  የአንድ ካርድ መታወቂያ ስርዓትን በማበጀት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎችን ከተቀላቀሉበት  ጊዜ ጀምሮ ጨርሰው እስኪወጡ ድረስ ለመከታተል፣ ለመቆጣጠርና እነርሱም ማንኛውንም አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ አስችሏል። ሆኖም ሁለተኛና ሶስተኛ  ትውልድ በሚካተቱት ዩኒቨርሲቲዎች በኩል  አይሲቲን  በውስጥ ማደራጀትና አጠቃቀም ወደ ኋላ  መቅረታቸው ነው የተገለጸው። 

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በተነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የአምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሀ ግብርን ለማሳካት ከተቀመጠው ግብ አኳያ በርካታ ጉዳዮች ተጨማሪ  ርብርብ የሚጠይቁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። በተለይም የለውጥ ሰራዊት ግንባታ  ከመጀመሪያው ደረጃ ሰራዊት ግንባታ  አልፎ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ላለመደረጉ  ዋናው ችግር  የመንግስት ስልጣን አተያይና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ በበቂ ሁኔታ ያለመላበስ  መሆኑን  ይናገራሉ።

 ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግስትና ህዝብ  ባደረጉት ጥረት የሴቶች ትምህርትና ስልጠና ተሳትፎ ውጤታማነትና ተጠቃሚነት እየተሻሻለ መጥቷል። ሆኖም ግን አሁንም የሴት አመራሮችን በየደረጃው  ከማብቃት አንፃር ክፍተቶች መኖራቸውን  ይገልጻሉ። በተለይም በተቀናጀ  ተግባር ተኮር ትምህርትና ፕሮግራም  የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መረባረብ  ያስፈልጋል ይላሉ።

በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍም ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውን  ነው  የገለፁት። የትምህርትና ስልጠና ተሳትፎን  ከማረጋገጥ አንፃር ሰፊ ለውጥ እየተመዘገበ መጥቷል። ሆኖም  በቅደመ መደበኛና ልዩ ፍላጎት የሚታዩ ክፍተቶችን በመዝጋት እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ተደራሽነት፣የሴት ተማሪዎች እና የትምህርት ዕድል ያላገኙ ጎልማሶችን በሙሉ ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር  ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤  ትምህርት ተግባራዊ መደረግ ያለበት ከተደረሰበት ልማትና ዕድገት አኳያ የስርዓቱ  ጠንካራና ደካማ ጎን  እየተገመገመ ነው። በመሆኑም  የትምህርት ሚኒስቴር  ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት የሚያገለግሉ  የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ጀምሯል። ይህም በአንድ  በኩል የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመውሰድ  በሌላ በኩል  መካከለኛው ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ  የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል ጥንቅር በጥራት፣ በብቃት፣ በብዛትና በተገቢነት  እያዘጋጁ ለመሄድ ነው።

የትምህርት ጥራት በሚመለከት  ሰፋፊ እይታዎች ይኖራሉ። አንዱ በትምህርት ማህበረሰብ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን መለየት ነው። የትምህርት ጥራት እምብርት  የሚባሉት መምህራን ናቸው። በመሆኑም   መምህሩ የሰራውን ስራ አመራሩ ሊደግፈው ይገባል። ስለዚህ የመምህሩ ስራ የተሳካ የሚሆነው የአመራር ስርዓቱ የተሳካ ሲሆን ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአጠቃላይ ትምህርት እንዲሁም  በቴክኒክ ሙያና ትምህርት ስልጠና  ኮሌጆችም የአመራር ስርዓቱ አጋዥ እንዲሆን ነው የሚሰራው።

አመራሩ  ቁርጠኝነቱን ካረጋገጠ  መምህራንና ሌሎች አካላትን የመደገፍና የማነሳሳት ሚናውን መወጣት ይችላል። ሁለቱ ተደጋግፈው ጥራት ያለው አገልግሎትና የመማር ማስተማር ስራ ይሰራሉ። የሁለቱ ድምር ውጤት  በተማሪ  ውጤትና  በትምህርት ጥራት ላይ ትልቅ ለውጥ  ማምጣት ይቻላል።

የትምህርት ጥራት ጉዳይ ፈተና ማለፍ ያለማለፍ ጉዳይ አይደለም። እያንዳንዱ  ተማሪ በትምህርት ቆይታው ወቅት የሚፈለገውን  እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት  ይዟል? ሙሉ ሰብዕና የተላበሰ  ብቁ ዜጋ ሆኖ  ወጥቷል ወይ  የሚል መሆን እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

ሁለተኛው የትምህርት ጥራት ማሳኪያው  በትምህርና ቴክኖሎጂ ሰራዊት ግንባታ  ላይ ትኩረት ማድረግ መሆኑን ይናገራሉ። ሁሉም ሰው በጥንካሬና በጉድለት የሚገለፅ ጎን ይኖረዋል። በመሆኑም  በልማት ሰራዊቱ ዙሪያ ተሰባስበው  የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚያስችላቸው ቁመና ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። በመሆኑም የትምህርት ጥራትን የማሳካት አንዱ ስራ  በትምህርትና ቴክኖሎጂ  ሰራዊት ተደግፎ መሄድ መሆኑንም አስገንዝበዋል። ይህንኑ የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች  ላቦራቶሪ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ቤተ ሙከራ ለማደራጀት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

ተማሪዎች በአጠቃላይ ትምህርት፣በቴክኒክና ሙያና ስልጠና ትምህርት በትምህርት ቤት  ቆይታ የሚያደርጉት ለተወሰነ ሰዓት ነው።ሌላውን ጊዜ የሚያሳልፉት ከወላጆች ጋር በመሆኑ ተማሪው የትነው  የዋለው? የሚለውን  የመከታተል ስርዓት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ  የተማሪ  ወላጅ  መምህር ህብረት የራሳቸውን ሚና  ይጫወታሉ። በእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ተማሪው በአስተሳሰብ ፣ ክህሎትና እውቀት ላይ የተሻለ  ውጤት ይዞ መውጣት  አለበት። በዚህ ላይ ትኩረት በማድረግና  ጥሩ ልምድ ካላቸው ተቋማት ተሞክሮ  መውሰድ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

 በጥሩ ምሳሌነት የተጠቀሰው  የወሎ ዩኒቨርሲቲ  ነው። ዩኒቨርሲቲው በዙሪያው ያሉ መምህራንን ከየትምህርት  አይነቱ ጋር በማጣመርና የተሟላ  መማማር በመፍጠር  በአካባቢው  ያሉ የትምህርት ተቋማት በመጠነ  ማቋረጥና በመጠነ መድገም ዜሮ  ደረጃ አድርሷል። መጠነ መዝለቅና ማጠናቀቅን በከፍተኛ  ደረጃ ያሻሻለበትም  ሁኔታ ታይቷል። ይሄ ውጤታማነት በአመራሩና በመምህሩ እጅ ላይ ያለ  መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ነው ያስረዱት።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ ሰላማዊ መማር ማስተማር  በሌለበት ቦታ  የትኛውንም የልማት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና  የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ማሳካት አይቻልም። በመሆኑም በአንድ በኩል  ሰላምን በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ  መስራት፤ በሌላ በኩል  ለሰላም መደፈረስ ምክንያት የሚሆኑ አጀንዳዎችን ለማጥፋት መስራት ያስፈልጋል። አደናቃፊ የሆኑ አስተሳሰቦችን መጠቀሚያ ለማድረግ  የሚነሱትን በጋራ መታገል፤ በተለይም በስነምግባርና ስነ ዜጋ  ላይ የሚሰሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።

ለሰላማዊ መማር ማስተማር  መምህራን፣ተማሪዎችና በዙሪያው ያሉ  ማህበረሰቦች   በትምህርት ላይም ሆነ ከውጪ ርብርብ ማድረግ አለባቸው። ትኩረት መስጠት ያለባቸው የስነዜጋና ስነምግባር  መምህራን  ብቻ ሳይሆን  ሁሉም  መምህራን ከሚሰጧቸው ትምህርት ጋር  የስነምግባርና ስነ ዜጋ ትምህርትን  አካተው  መስራት ያስፈልጋል። ሙሉ ሰብዕና ያለው ፣በእውቀት፣ በክህሎትና በአስተሳሰብ የተገነባ  ትውልድ  በመቅረፅ ስራ ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ሚኒስትሩ ያሳሰቡት።   

 በቀጣዩ ስድስት ወራት ትኩረት የሚሰጠው ሌላው ጉዳይ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎችን  በተቀናጀ ሁኔታ የማስፈጸም አቅም መገንባት የሚመለከት ነው። በታሪካዊና ስነ ምህዳራዊ ምክንያቶች ተመሳሳይ የማስፈጸም አቅም ላይ ያልደረሱ ክልሎችን በተቀመጠው የድጋፍ አግባብ  ዙሪያ  ሰፊ ተገቢውን ደጋፍ  ማድረግ ይጠበቃል። በተለይም የትምህርትና ስልጠና ተደራሽነትና ጥራትን በማረጋገጥ በኩል  ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች የሚሰራ ስራ በልዩ እቅድ ተይዞ ከፌደራል እስከ ክልል በተቀናጀና በተደራጀ  ሁኔታ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል።

ለትምህርት ጥራት፣ለሰላማዊ መማር ማስተማር፣ ለአገር ልማትና እድገት፤ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሁሉም ርብርብ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በዚህ ዙሪያም መግባባት ላይ ተደርሷል። በየክልሎችም በእቅዶች ተካቶ የሚተገበር ይሆናል።

አልማዝ አያሌው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።