«ስታንዳርድ በሌለበት በአይሲቲ መሰረተ ልማት ይሄ ነው ቀዳሚው ዩኒቨርሲቲ ማለት አይቻልም» -ዶክተር ማተቤ ታፈረ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት Featured

13 Feb 2017

የዓለም  የመረጃ ስርዓት  ህዝቦችን በአንድ ገበታ እስከማቋደስ ዘምኗል፡፡በሀገራችንም ከዚህ አኳያ በተለይ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ  የመጀመሪያው ትውልድ የሚባሉት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምንም ዓይነት  ርቀት ሳይገድባቸው  አንዲት መጽሐፍን  በጋራና  በአንድ ጊዜ እስከ መጠቀም በሚያስችላቸው የኢትዮጵያ ትምህርትና ምርምር ኔትወርክ ወይም  የተጠናከረ የአይሲቲ አገልግሎት  እስከ መተሳሰር   ዘልቀዋል፡፡

ቀዳሚው የቱ እንደሆነ ባይታወቅም ጅማና መቐለ   ዩኒቨርሲቲ  ከበር እስከ  መመገቢያ አዳራሽና ዶርምተሪ  ተማሪን  በቀላሉና  በፍጥነት የሚያስተናግዱበት የዘመነ  መረጃ አያያዝ ስርዓት  ያላቸው መሆኑን በተለያየ ጊዜ በዚሁ ጋዜጣ መዘገባችንም አይዘነጋ፡፡ጅማና  መቐለ   ዩኒቨርሲቲ  የተማሪን  መታወቅያ ካርድ   ኤሌክትሮኒክስ  እስከ ማድረግ ሄደዋል፡፡ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም የተማሪዎች የመረጃ ቋት በመገንባት በሥራ ላይ አውሏል፡፡የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምንጭ ሲሆን የሚታየውን  የግዢ ስርዓት  በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል ሶፍት ዌርም ሰርቷል፡፡በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማተቤ ታፈረን አነጋግረናቸዋል፦

አዲስ ዘመን፦ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያለው የመረጃ አያያዝና ያመጣው ለውጥ ምን ይመስላል?

 ዶክተር ማተቤ ፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሰራሮችን በተቻለ መጠን በሲስተምና በስርዓት የመምራት፣ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ የመጠቀም ፍላጎት አለ።ለአብነት ያህል ቀደም ሲልም«ስቱደንት ኢንፎርሜሽን  ማኔጅመንት ሲስተም»የተሰኘ የተማሪዎች የመረጃ ቋት ሰርተን በስራ ላይ አውለናል።የመረጃ ቋቱን ለበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ያበረከትነው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።  የመረጃ ቋቱ  ከተማሪ ምዝገባ ጀምሮ ተመርቆ እስከ ሚወጣ ድረስ የዘለቀ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።አጠቃላይ ገብቶ የሚወጣውም  በዚሁ ሲስተም ነው።በመሆኑም ቋቱ አያሌ ሥራዎችን አቅልሎልንና ችግሮችን ፈትቶልናል። የፀደቀ ግሬድ ጠፋብኝ የሚሉ ቅሬታዎችም መፈጠር ትተዋል።ማን እንደሚያስገባ፣ማን እንደሚያፀድቀው፣ መቀየር ሲያስፈልግ ማን እንደሚቀይረው የተቀመጠ ነገር ስለሆነ አሁን እንደ ዱሮው ግሬድ ጠፋብኝ፣ ተጭበረበረብኝ የሚባል ችግር የለም።

አዲስ ዘመን፦ከዚሁ የመረጃ አያያዝ ሳንወጣ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ የሆነውን የግዥ ስርዓት መስመር በማስያዝ በኩል ሶፍት ዌር ሰርታችኋል የሚለውንም ቢያብራሩልን?

ዶክተር ማተቤ፦ ከሶፍት ዌር ጋር ተያይዞ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዢ ስርዓቱን የሚያሳልጥ የግዢ ሶፍት ዌር አዘጋጅቷል። በዚህ ሶፍት ዌር አማካኝነት በተለይ የንብረት ምዝገባን አስመልክቶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በእያንዳንዱ ስታፍ ምን ንብረት እንደወጣ፣ስቶር ውስጥ ምን ዓይነት ዕቃ እንዳለ በቀላሉ ማወቅ ተችሏል።የግዢ  ስፔስፊክሽንም በአይሲቲ መሰረተ ልማት ሆነ ማንኛውም ጉዳይ በሲስተም ነው የሚያልቀው።ይሄን ማድረግ የሚያስችለውን ሶፍት ዌር ሌሎች ቢሮዎች ሳይቀር እየወሰዱት ነው። በአገር አቀፍ ደረጃም የመሸጥ ፍላጎቱ አለን። በዚህ በኩል ሶፍት ዌሩን መጠቀም እንፈልጋለን ከሚሉ ተቋማት ጋርም  ግንኙነት ጀምረናል። በተጨማሪም ስንት ሰው ነው ያለው፣በምን ያህል የትምህርት ደረጃ፣በምን ያህል ስብጥር የሚሉና ከሰው ሀብት አያያዝ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲያችን  ሁልጊዜ በትምህርት ሚኒስቴር ሲጠየቅ የሚቸገርባቸውና ግልፅ ያልነበሩ የሰው ሀብት ጉዳዮችን  በሶፍት ዌር ለማድረግም  እየሰራን ነው ያለነው። በዚህ በኩል ያለው በአይሲቲ መሰረተ ልማትም  ሶፍት ዌር እየተጠናቀቀ ነው። ሶፍት ዌሩ ሲጠናቀቅና ወደ ሥራ ሲገባ የሰው ሀብት አመራር ጉዳይ  ግልጽ ይሆናል። የሰው ሀብት ብቻ ሳይሆን የተማሪዎች ካፍቴሪያም በካርድ ሲስተም  ሶፍት ዌር የመስራት ፍላጎት አለ።ይሄን ጅምር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በይፋ እናወጣዋለን። በተጨማሪም የመምህራን የሥራ ግምገማም በሶፍት ዌር እንዲሆንና ተማሪዎች በዚህ እየገቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ፍላጎት አለ።ይሄም እየተጠናቀቀ ነው።በአጠቃላይ  ዘመናዊ የመረጃ አያያዝን አስመልክቶ በተቋማችን በአይሲቲ መሰረተ ልማት ጥሩ ጥሩ ጅማሬዎች አሉ።

አዲስ ዘመን፦ ጅማሬዎች በአይሲቲ መሰረተ ልማቱ በቂናቸውና ምንም ተግዳራቶች የሉባቸውም ማለት ይቻላል?

ዶክተር ማተቤ፦ ጥሩ ጥሩ ጅማሬዎች ቢኖሩም እነዚህ ጅማሬዎች በራሳቸው በቂ ናቸውና ተግዳሮቶች የሉባቸውም  ማለት አይቻልም፡፡ለምሳሌ፦ የኔትወርክ መቆራረጥን ማንሳት ይቻላል።የሰለጠነ ባለሙያ፣ ስታንዳርድ አለመኖርና ሌሎች በርካታ አወዛጋቢ ችግሮች ቢኖሩም  ዞሮ ዞሮ በራሳችን በመሞከር እየሄድንበት ነው ያለው። 

አዲስ ዘመን፦ ዩኒቨርሲቲያችሁ በአይሲቲ መሰረተ ልማት በኩል አርዓያ ወይም ደግሞ ሞዴል ነኝ ብሎ ያስባል?

ዶክተር ማተቤ፦  በአይሲቲ መሰረተ ልማት በኩል አርዓያ ወይም ደግሞ ሞዴል ማነው ለሚለው  ምላሽ ትምህርት ሚኒስቴር የሚመልሰው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ስታንዳርድ በሌለበትና እንደ አዲስ እየመጣንበት ባለው ሁኔታ ይሄ ተቋም  ነው ቀዳሚው ማለት ያስቸግራል። በግዢ፣በንብረት አያያዝ፣በተማሪ ውጤት  አያያዝ የትኛውና ማነው የሚሻለው የሚለውን ለይቶ ለማወቅ ቁጭ ብሎ መገምገም ያስፈል ጋልም።የመቐለ፣ የጅማ ፣የባህር ዳር ነው የሚሻለው ለማለት የሚቻለውም ከገመገምን በኋላ ነው።ሆኖም ለጊዜው እንደእኔ፣እንደኔ ዩኒቨሪሲቲዎች አሁን በየራሳችን እየሄድን ያለንበት ሁኔታ በፊት ያልነበረ ከመሆኑና ባለሙያዎች ከመነቃቃታቸው ጋር  ተያይዞ ጥሩና ወደ  ስታንዳርድ የሚያመጣ ነው።

አዲስ ዘመን፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥና ለማስቀጠል ምን ስልት አለ?

ዶክተር ማተቤ፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ የምንጠቀምባቸው በርካታ ስልቶች አሉ።አንዱና ዋናው አደረጃጀት መፍጠር ነው በተማሪም፣ በመምህሩም፣ በአመራሩም፣በአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪው ሰራተኛም የተለያየ አደረጃጀት ተፈጥሯል።ይሄ ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ ሰላማዊ መማር ማስተማሩን ስንጀምር ከሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር አሁን ያለንበት ሁኔታ ምንድነው፣ምን ችግሮች አሉ፣ለወደፊቱ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን    እናድርግ፣    እንዴት  እንፍታ ቸው? በሚል ቁጭ ብለን ገምግመን ነው ወደ ስራ የገባነውም። ይሄ በብዙ መልኩ ተሳክቶልናል።የተሳካበትን መንገድ መግለፅ ካስፈለገ  በየጊቢው ሚኒ ኮማንድ ፖስት አለ።የእያንዳንዱ ጊቢ ኮማንድ ፖስት በምክትል ፕሬዚዳንቶች ነው የሚመሩት። የተማሪዎችን ሕብረትና የሴኔት መሪዎችን ጨምሮ በየሳምንቱ ነው የምንገመግመው።የመስተንግዶ፣ዶርምተሪ አካባቢ ያሉና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች   በየሳምንቱ በመገምገም ይፈታሉ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩን ጭምር የሚሰበስበው ኮማንድ ፖስት አለ። በአጠቃላይ ችግሮች ሲከሰቱ ወድያው፣ወድያው ነው የምንፈታቸው።ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከችግሮች ባሻገር አብዛኛው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያስኬደው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተፈጠረው የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት ነው።ከዚህ በኋላም ቢሆን ከተማሪዎችና ከሰራተኞች ጋር ጥሩ መስተጋብር አለን።አመራሩም በተገቢው መንገድ ተናቦ ነው የሚሰራው።በመሆኑም ቀጣዮቹን ወራቶች ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ሂደት  በዚህ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ይቀጥላል የሚል ዕምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፦ እንደ ተቋም በዩኒቨርሲቲው ከነበሩና  በኮማንድ ፖስቱ ከፈታችኋቸው ችግሮች ለአብነት ቢጠቅሱልን? 

ዶክተር ማተቤ፦ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ከፍተኛ የመብራት ችግር ነበረብን።ይሄን ችግር ለሁሉም ጊቢዎች ጀነሬተር እንዲገዛና በሁሉም ጊቢዎች አውቶማቲክ እንዲሆን በማድረግ ፈተነዋል።ሌላው የነበረብን ችግር ውሀ ሲሆን በራሳችን ጉድጓድ በመቆፈርና ከከተማው አስተዳደር ጋር በመነጋገር ለዩኒቨርሲቲው በተለየ መንገድ  ሳይቋረጥ  ውሃ እንዲላክ አድርገናል።አንድ ጊዜ መንገድ በመዘጋጋቱና የትራንስፖርት እጦት በመኖሩ ከገጠመን ችግር በመነሳትም ሱቅ ቢዘጋና አቅርቦት ባይኖር ተማሪዎቻችንን ቢያንስ  ለአንድ ወር መመገብ የምንችልበት ክምችት እንዲኖር በማድረግም ከምግብ አቅርቦት ጋር ሊከሰት የሚችልን ችግር ፈትተናልም።ይሄን ለአንድ ወር የሚሆን ክምችት በየአንዳንዱ ጊቢም ያሟላንበት ሁኔታ አለ።

አዲስ ዘመን፦ ይሄ ማለት ከግዥ ስርዓት ጋር በተለይም ከተማሪ ቀለብ ጋር በተያያዘ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የገጠመው ወይም ሊገጥመው የሚችል ተግዳሮት የለም ማለት ነው?

ዶክተር ማተቤ፦ የግዢ  ስርዓቱ ከፍተኛ ማነቆዎች ያሉት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሩን  በዝምታ ማለፍ ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ግዢ የሚፈፀመው በዕቅድ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ግዢ ከዕቅድ ውጭ ሊፈፀም ይችላል፡፡ለምሳሌ፦ ለተማሪዎች   ቀለብ የሚውል ጤፍ ያቀርቡ የነበሩ በግርግሩ ሰሞን ትራንስፖርት ስለተቋረጠ አናቀርብም ያሉበት ሁኔታ ነበር፡፡በዚህ ጊዜ ደግሞ የግድ እንጀራ ወደ መግዛት ነው የተሄደው፡፡ነገር ግን የእንጀራ ግዢ የሚፈፀመው ደግሞ በግዢ ስርዓት ነው፡፡በመሆኑም  የግዢ  ስርዓቱ  ይሄን የተቋማቱን ተጨባጭ ሁኔታ ማገናዘብ አለበት የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ለአንድ ወር የሚበቃ የቀለብ ግዢ ብንፈጽምም ግዢው የዩኒቨርሲቲዎቹን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ባለመሆኑ ከመስመር ውጭም የገዛናቸው ነገሮች የሉም አይባልም፡፡

አዲስ ዘመን፦  ሴቶችን ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት በማምጣት በኩል በተቋማችሁ  ያለው ምንድነው?

ዶክተር ማተቤ፦ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዝቅተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ  ሴቶችን ወደ አመራር የማምጣት ፍላጎት አለ፡፡ይሄን ፍላጎት መሰረት አድርገን በሁሉም ደረጃ ወደ ውሳኔ ሰጪነትና ወደ አመራርነት ያመጣናቸው ሴቶች አሉ፡፡በተለይ በከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ዝግጅታቸው ዶክተሬትና ማስትሬት የሆኑ ሁለት የዩኒቨርሲቲ  ምክትል ፕሬዚዳንቶች ወደ አመራርነት  አምጥተናል፡፡ይሄ የሆነው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ቁርጠኝነትና በተቋማቱ ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነትና አመራርነት ለማምጣት ቀደም ሲል ትምህርት ሚኒስቴር አስቀምጦት በነበረ አቅጣጫ ነው።ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሴት በመመራትም በአገሪቱ ቀዳሚ ተሞክሮ የነበረው ከፍተኛ ትምህርት ተቋምም ነው።

አዲስ ዘመን፦በዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን።

ዶክተር ማተቤ፦እኔም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስም አመሰግናለሁ።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።