ርህራሄ እና አክብሮት ከጤና ባለሙያዎች

14 Feb 2017

የጤና ባለሙያዎች ለእናቶች ርህራሄና አክብሮት በማሳየት የአመለካከት ለውጥ ሊያመጡ ይገባል፤

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ፤ በ1980ዎቹ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተገናኙ ችግሮች ምክንያት ከ100 ሺ እናቶች 708ቱ ለህልፈት ይዳረጉ ነበር። ይህንን ችግር በመሠረታዊነት ለመፍታት የጤና ተቋማት ማስፋፋት፣ የጤና ባለሙያዎችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ የማስገባት፣ በጤና ተቋማት ግብአቶችን የማሟልት ተግባራት ተከናውነዋል።

ይህን ተከትሎም የእናቶችን የሞት ምጣኔ በመቀነስ ረገድ አገሪቱ ይበል የሚያሰኝ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ይሁንና አሁንም በወሊድ እና ከወሊድ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ችግሮች ምክንያት ለህልፈት የሚዳረጉ እናቶች በርካታ ናቸው።

ከኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በአሁኑ ወቅትም  ከ100 ሺ እናቶች መካከል  412  እናቶች በወሊድ ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ። ይህ አሃዝ አሁንም በአገሪቱ ያለው የእናቶች የሞት ምጣኔ አገሪቱ ብዙ የቤት ሥራ እንዳለባት አመላካች ነው።

በሁለተኛው የዕድገትና ሽግግር ዘመን የእናቶችን የሞት ምጣኔ ወደ 199 ለማውረድ ግብ ተጥሎ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፤ ለግቡ ስኬት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ወሳኝ መሆኑ የማያጠያይቅ ነው። በዚህ ረገድ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የጤና ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በየዓመቱ በወርሃ ጥር የሚከበረው የጤናማ እናትነት ቀን ባለፈው ወር «ርህራሄና አክብሮት የተሞላበት የጤና አገልግሎት ለጤናማ እናትነት!» በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ጊዜ በአዳማ ሜዲካል ኮሌጅ በተከበረበት ወቅት  የኮሌጁ ፕሮቮስት ዶክተር አለማየሁ ግርማ  እንዳሉት ፤ ሁሉም ህብረተሰብ ለእናቶች መስጠት ያለበትን አክብሮት እና ርህራሄ ሊያሳይ ይገባል፡፡  በተለይም በየጤና ተቋማቱ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ለእናቶች ተገቢውን ክብር እና ርህራሄ ማሳየት ይኖርባቸዋል።

የጤና ባለሙያዎች ለነፍሰ ጡር እናቶች  ክብር እና ርህራሄ የሚያሳዩ ከሆነ እናቶች በጤና ተቋማት ላይ ያላቸው መተማመን ከፍ ይላል ያሉት ዶክተር አለማየሁ፣ ይህም በጤና ተቋማት የእርግዝና ክትትል የሚያደርጉ እና የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ነው  ያስረዱት፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕፃናት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አሸናፊ ግርማ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በእናቶች ሞት ቅነሳ ላይ የተሠሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶችን ቢያስገኙም አሁንም ተግዳሮቶች ይስተዋላሉ፡፡

ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል በጤና ተቋማት ተገቢውን የህክምና ክትትል የሚያደርጉ  እናቶች ቁጥር ከተያዘው ግብ አንጻር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን አቶ አሸናፊ ይገልጻሉ፡፡ በጤና ተቋማት ውስጥ አንድ ጊዜ የህክምና ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር የጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ አንድ እናት በእርግዝና ወቅት ቢያንስ አራት ጊዜ ክትትል ማድረግ እንደሚኖርባት ነው ያመለከቱት።     

«የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚደረገው ርብርብ የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የእርግዝና ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር ከፍ ሲል ነው» የሚሉት አቶ አሸናፊ፣ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ የእናቶች የህክምና ክትትል ከታሰበው ግብ አንጻር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

እንደ አቶ አሸናፊ ማብራሪያ ፤ የነፍሰ ጡር እናቶችን የህክምና ክትትል ከፍ በማድረግ የእናቶችን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጤና ባለሙያዎች ርህራሄ እና አክብሮት የተሞላበት አገልግሎት በተለይም ለእናቶች  እንዲሰጡ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው።

የህክምና ባለሙያዎች ለእናቶች ርሁሩ መሆን እናቶች ያለምንም መሸማቀቅ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎቶችን ስለሚያገኙ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ለሚሠረው ሥራ እገዛ ያደርጋል።

የጤና ባለሙያዎች የባህሪ ለውጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው በመጠቆም ነፍሰ ጡር እናት የህክምና ክትትል ካልተደረገላት ለችግር ልትጋለጥ እንደምትችል በመገንዘብ እያንዳንዱ ዜጋ እናቶች ወደ ህክምና ተቋማት እንዲሄዱ በማስገንዘብ፣ ርህራሄ እና አክብሮት በማሳየት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕፃናት ጉዳዮች ባለሙያ አቶ ስንታየሁ አበበ እንደሚናገሩት፤ በጤና  ተቋማት መካከል የእናቶች ቅብብሎሽ መጠናከሩ ፣ በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የእናቶችንና  የሕፃናትን ጤና አገልግሎት በነፃ እንዲሰጥ መደረጉ፣ የድንገተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት በየአካባቢው መስፋፋት፣ ለእናቶች ጤና መሻሻል እና ለእናቶች ሞት ቅነሳ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በጤና ተቋማት ለእናቶች የወሊድ አገልግሎት የሚሆኑ የግብዓት ግዢና ስርጭትን ማጠናከር፡ በጤና ተቋም የድህረ ወሊድ ቆይታን ከ24-48 ስዓት እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ስንታየሁ ገለጻ ፣ከዚህ ጎን ለጎን እናቶች አገልግሎት ያገኙ ዘንድ የማቆያ ስፍራና ግብአቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን በጤና ተቋማት ውስጥ በማሟላት ለእናቶች ሞት ቅነሳ ሠፊ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም በእርግዝና ወቅት አደጋ ሲያጋጥምና በምጥ ጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አገልግሎት ለማግኘት ሲኬድ የውሳኔ መዘግየት፤ ከቤት እስከ ጤና ተቋም ለመድረስ መዘግየት፤ ጤና ተቋም ከተደረሰ በኋላ የሚያጋጥሙ መዘግየቶች አሁንም በኢትዮጵያ ለእናቶች ሞት መከሰት ምክንያት እየሆኑ እንደሚገኙ ነው አቶ ስንታየሁ ያብራሩት።

ዶክተር አለማየሁ ግርማ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ጊዜያት የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ለእናቶች የህክምና አገልግሎት በመስጠት ረገድ በርካታ ውስንነቶች እንደነበር አንስተዋል፡፡ በተለይም ለእናቶች ርህራሄ እና ክብካቤ የተሞላበት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንደነበር አውስተዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ከባለሙያዎች ጋር ከስምምነት በመድረስ ለሁሉም እናቶች ጥራት ያለው እና ነጻ የወሊድ ክትትል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ሰው አክባሪ እና ተንከባካቢ እንዲሆኑ እና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት የመስጠት ልምድ አጠናክሮ ለማስቀጠል በቀጣይነት እንደሚሰራም ነው ያብራሩት ፡፡

ወይዘሮ ኮከቤ ጌታቸው በአዳማ ከተማ የ04 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን  በጤና ተቋም ነው የተገላገሉት ፡፡ በጤና ተቋም የእርግዝና ክትትል በማድረጋቸው እና ለወሊድም ወደ ጤና ተቋም በማምራታቸው ያለምንም እንከን የመጀመሪያ ልጃቸውን ለመገላገል መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በጤና ተቋማት የወሊድ ክትትል የሚሰጡ ባለሙያዎች ክብካቤ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ኮከቤ፣ አሁንም ነፍሰ ጡር መሆናቸወንና በአዳማ ሜዲካል ኮሌጅ የእርግዝና ክትትል እያደረጉ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ሌሎች ነፍሰ ጡሮች ወደ ህክምና ተቋማት ሲሄዱ አልፎ አልፎ የሚያመናጭቁ እና ርህራሄ የሌላቸው ባለሙያዎች እንደ ሚያጋጥማቸው እናቶች ሲያወሩ መስማታቸውን ነው የሚያነሱት፡፡ ‘‘ የጤና ባለሙያዎች ክብካቤ እና ርህራሄ ለእናቶች ከምንም የሚበልጥ ማበረታቻ ነው‘‘ የሚሉት ወይዘሮ ኮከቤ፣ ሁሉም ባለሙያዎች ይህን በመረዳት በተቻላቸው አቅም ለእናቶች የተለየ ክብካቤ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።