በጐ ፈቃድ ለህሊና እርካታ ስንቅ መቋጠሪያ

20 Jul 2017

ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡባቸው መስኮች መካከል የትራፊክ ደንብ ማሳለጥ ይገኝበታል

 

ወጣትነት የአፍላነት ዕድሜ እንደመሆኑ ብዙ አዎንታዊና አሉታዊ ባህሪያት የሚታዩበት ነው፡፡ አንዳንዶች ዕድሜ የሚያመጣውን ተጋላጭነት በስልት ማለፍ ተስኗቸው ለአጓጉል ባሕሪያት ተዳርገው እስከ ዘለቄታው የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ሊዘፈቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ መነሻነት ሳያስተውሉ ተራምደው ራሳቸውን በከፍተኛ ሱሰኝነት ውስጥ ሰምጠው ያገኙታል፡፡ ይሄ ደግሞ ከራሳቸው ቀጣይ ሕይወት ባሻገር በቤተሰቦቻቸው፣ በማህበረሰቡ ብሎም በአገር ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ ነው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ይሄ ድርጊት ባለፈበት ያላለፉ አስተዋይ ወጣቶችም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህኛዎቹ ባላቸው ጠንካራ መንፈስና ብርታት ተደግፈው በሚያከናውኗቸው ተግባራት ለራሳቸው የህሊና እርካታ ከመሸመት አልፈው ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ ሲሆኑ ይታያል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወጣቶች የእረፍት ጊዜያቸውን እንኳን ሳይቀር የሚያሳልፉት ለሌሎች በጎ ተግባር በማከናወን ነው፡፡ ያለንበት ወርሃ ክረምትም እንዲህ ያሉትን ወጣቶች በየአካባቢው በተለያዩ መስኮች ተሳትፎ ሲያደርጉ ለመታዘብ ያስችላል፡፡

እኛም ከእግረ መንገድ ትዝብት አለፍ ብለን ለመሆኑ የዘንድሮው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ወጣቶቹስ ምን አስበው ይሆን? እስካሁንስ ምን ሲሰሩ ቆዩ? ስንል መጠየቅ ወደድን፡፡ ወጣት ወላንሳ ደሳለኝ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ውስጥ ደም ስትለግስ ነበር ያገኘኋት፡፡ ከዚህም በፊት በተለያዩ ጊዜያት ደም ለግሳለች፡፡ ወላንሳ እንደምትለው በእሷ ደም የሰውን ልጅ ሕይወት ማዳን መቻል ትልቅ የህሊና እርካታ ይሰጣታል፡፡ ለዚያውም በአንድ ሰው ደም የሁለትና ሦስት ሰው ሕይወት ማዳን መቻል ትልቅ ደስታና ኩራት እንደሚሰጣት ትገልጻለች፡፡ እርሷ የለገሰችው ደም እሷን ምንም የሚጎዳ ነገር አይደለም፡፡ በትንሽ ነገር ሊሞላ የሚችል ነው፡፡ እርሷ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እንዲህ ዓይነት የበጎ አድራጎት ሥራ እንዲሰሩ ጓደኞቿን ታስረዳለች፡፡ በዘንድሮው ክረምትም ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ የበጎ አድራጎት ሥራ ለመስራት ዓላማ አላት፡፡

ሌላኛው ወጣት ፉአድ ረዲ ይባላል፡፡ የትራፊክ የደንብ ልብስ ለብሶ የክረምቱን የበጎ አድራጎት ሥራ ተያይዞታል፡፡ ወጣቱ እንደሚለው በተለይ በክረምት ወራት የትራፊክ ፍሰት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ለእግረኞች በዝናብ የመሸፈን ችግር ስለሚኖር የትራፊክ ፖሊሶች ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ ለዚህም ፉአድና ጓደኞቹ እንዲህ ዓይነቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

«እኔ የትራፊክ አገልግሎት በመስጠት የሰውን ሕይወት ማዳን በመቻሌ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል፤ ይህን አገልግሎት ባልሰጥ ኖሮ ይሄን ደስታ አላገኘውም፤ ምናልባትም የእኔን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ቦታ ላይ እሄድ ነበር» የሚለው ፉአድ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተደረገለት ሰው ብቻ ሳይሆን ለአድራጊውም ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ አሽከርካሪዎችንም ሆነ እግረኞችን አቅጣጫ ያሳያል፤ ያስተምራል፡፡ ይህም በትራፊክ ሕግ ብቻ ሳይሆን ከሰው ጋር የመግባባትና ሰውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ልምድ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡

ወጣት ጀማል ደሳለኝ በተመሳሳይ በወጣቶች የክረምት የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ተሰማርቷል፡፡ እርሱ እንደሚለው የበጎ አድራጎት ሥራ መስራት ሌሎችንም በጎ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ አገልግሎቱን ከሚያገኙት ሰዎች በተጨማሪ ያየ ሁሉ ደስተኛ ይሆናል፡፡ ሰዎች በቅንነት እንዲህ ዓይነት ሥራ መሥራት እንዲችሉ አርአያ ይሆናል፡፡ በተለይ ልጆች ይህን ሲያዩ በበጎ ነገር እየተቀረፁ ያድጋሉ፡፡ ወጣቶችም በጎ ነገር የሚያደርጉት እርስ በእርስ ምሳሌ በመሆን ነው፡፡

ወጣት ጀማል እንደሚናገረው ግን፤ የበጎ አድራጎት አገልግሎቱ ለልጆች ብቻ ሳይሆን ለአዋቂዎችም አርአያ መሆን ያስችላል፡፡ ብዙ ትላልቅ ሰዎች እንኳን ይህን የበጎ አድራጎት ሥራ እንደቀላል የሚያዩት አሉ፤ ግን ወጣቶች ሲሰሩ ሲያዩ ይደሰታሉ፡፡ የታላላቅ ሰዎች ምክርና ምርቃት ትልቅ ደስታ ይሰጣል፡፡ በተለይም በክረምት ወራት መንገዶች በጎርፍ ስለሚሞሉ ለአዛውንቶችና አካል ጉዳተኞች አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ማሻገርና መንገድ ማስያዝ የምስጋና ጸጋን ያስገኛል ይላል፡፡

በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች እንዳሉም ይገለጻል፡፡ ከአሽከርካሪዎችም ከእግረኞችም የሚገላምጡና የሚሳደቡ ሰዎች አሉ፡፡ ለምን ተናገረን? እያሉ ይቆጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ባለማወቅ ሲሆን አንዳንዶችም ሆን ብለው የሚያደርጉት ነው፡፡ አንዳንድ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች በተመስጦ ሀሳብ ውስጥ ገብተው ለአደጋ ሲጋለጡ መታዘቡንም ይናገራል፡፡ የዚህን ጊዜ ሰዎችን ማስታወስና ከአደጋ ማዳን ለእነሱም ለበጎ አድራጊውም ትልቅ ደስታ ነው፡፡

ምንም እንኳን አንዳንድ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች ሲመክሯቸው ገላምጠው የሚያልፉ ቢኖሩም መናገሩ ግን አስፈላጊ መሆኑን ነው ጀማል የሚናገረው፡፡ ምናልባትም አንድ ቀን ችግሩ ይገባቸውና ያመሰግኑ ይሆናል በሚል ተስፋ፡፡ የትራፊክ አደጋ በደረሰ ቁጥር ልክ መሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ወጣቱ በዋናነት በትራፊክ ላይ ይሰማራ እንጂ በሌሎች ዘርፎችም ይሳተፋል፡፡ ጽዳትና ችግኝ መትከልም ይገኝበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና የከተማዋ ወጣቶች ፌዴሬሽን ለዘንድሮው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የፌዴሬሽኑ ምክትል ሰብሳቢ እና የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አባይነህ አስማረ፤ እንደገለጸው ከዛሬ 15 ዓመት በፊት በጥቂት ወጣቶች የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሁን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን ፈጥሯል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እንዲዳብርም አድርጓል፡፡

በመንግሥትም ይሁን በግለሰብ ደረጃ ሊወጣ የነበረን ወጪም አድኗል፡፡ ባለፈው ዓመት በተደረገው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንኳን በመንግሥት ይወጣ የነበረውን 48 ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለራሳቸው ለወጣቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ነው ወጣት አባይነህ የሚገልጸው፡፡ ወጣቶቹ ገና በወጣትነታቸው ኃላፊነትን የመሸከም፤ የሕዝብን አደራ የመወጣትና በቅንነት የማገልገል ልምድ አዳብረዋል፡፡ አንዱ ለአንዱ አርአያ በመሆን አዎንታዊ ግንዛቤ መፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይም አሁን አሁን እያዳበረ ከመጣ ወዲህ ወጣቶች በጉጉት የሚጠብቁት ተግባር ሆኗል፡፡ ወጣቶችን እርስበርስ በማስተዋወቅና በማስተሳሰር ብዙ ልምዶችን እንዲለዋወጡ አድርጓቸዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምት ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነም ወጣት አባይነህ ይናገራል፡፡ አገልግሎቱ በበጋ ወራትም የሚሰጥ ነው፤ ዳሩ ግን በክረምት የተለየ ትኩረት የሚሰጠው ብዙ የከፍተኛ ትምህርትም ሆነ የሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በእረፍት ላይ ስለሚሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በክረምት ወቅት የበጎ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡

ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ውጪ ስለሚሆኑ አስጠኚ ይፈልጋሉ፣ መንገዶች በክረምት ስለሚበላሹ መጠገን ያስፈልጋቸዋል፣ አዛውንቶችና የአካል ጉዳተኞች በክረምት በሚበለሻሹ መንገዶች የባሰ ስለሚቸገሩ አጋዥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምት የበለጠ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ትራፊክ አገልግሎት፣ የደም ልገሳና የመሳሰሉት በበጋም እንደሚደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጣቶችን የማብቃት ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ አሻግሬ፤ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች ማዕከላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡ በክረምት ብዙ ወጣቶች በማዕከላቱ ውስጥ ስለሚገለገሉ ማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ትኩረት ይደረግበታል፡፡ የክረምቱን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከወጣቶች ፌዴሬሽንና ከሌሎች የሚመለከታቸው መሰል መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳና በሌሎችም አገልግሎቶች በጋራ ይሰራል፡፡

ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዘጠኝ መቶ ሺ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ፡፡ በዚህም 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሥራ ለመስራት ታስቧል፡፡ የሚሰጡ አገልግሎቶችም፤ የጤናና ሰብዓዊ አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል፣ የአካባቢ ልማትና ጽዳት፣ የትራፊክ ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የኪነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ንቅናቄ እንዲሁም የንባብ ሳምንት ፌስቲቫል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።