የቤተሰብ ምጣኔን ማዘመን «በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ» Featured

26 Jul 2017

ወይዘሮ ፋጡማ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የአይሳኢታ አካባቢ ነዋሪ ናት። አራተኛ ልጇን ለመውለድ በዝግጅት ላይ እንዳለች  የዘገበው የዘ- አትላንቲክ ዴይሊ ፀሐፊ አሪየል ዚሩል ነው። ይህች እናት ትዳር ከያዘች ስድስት አመት ቢሆናትም በአጭር ጊዜ ውስጥ አራተኛ ልጅ ለመታቀፍ እቅዷ እንዳልነበር እንዲህ ስትል ነግረዋለች። «በአጭር ጊዜ ውስጥ አራት ልጆችን መውለድ አልፈልግም ነበር። በዚህ ምክንያት ከትዳር በፊት እሰራቸው ከነበሩ የተለያዩ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎች በመራቄ እኔም ሆንኩ ልጆቼ ለድህነት ተዳርገናል፤ ጤናችንም ተቃውሷል» ስትል አጫውተዋለች።

በእርግጥም በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እንደ ፋጡማ ያሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች እና እናቶች በወሊድ ምክንያት ከአምራችነት ርቀዋል፤ በዚህም የተነሳ በኢኮኖሚ ጥገኛ ለመሆን ተገደዋል። ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአገራቸው ማበርከት የሚገባቸውን ሳያከናውኑ እንደቀሩ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

እአአ በ2017 በለንደን በተደረገው የቤተሰብ ምጣኔ ጉባኤ ላይ፤  የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፕሪቲ ፓተን፤ «በዓለማችን በአሁኑ ወቅት 214 ሚሊዮን ሴቶች ማርገዝ አይፈልጉም። ይሁን እንጂ እነዚህ ሴቶች ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን ማግኘትና መጠቀም ባለመቻላቸው በድህነት እና በጤና መታወክ ይሰቃያሉ» ብለዋል።

እአአ በ2013 ገትማቸር የተሰኘው ኢንስቲትዩት ለሶስት አስርት ዓመታት ባስጠናቸው 66 ጥናቶች እንዳረጋገጠው የቤተሰብ ምጣኔን ተግባራዊ ያደረጉ ቤተሰቦች፤  በተለይ ደግሞ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን በቅርበት የሚያገኙ እናቶች እራሳቸውን ከጥገኝነት በማላቀቅ ጤነኛ እና አምራች ሆነዋል። በመሆኑም እንደ ፋጡማ ያሉ የዓለማችን ሴቶች ይህ እድል ቢመቻችላቸው ከራሳቸው አልፈው ለአገራቸው ኢኮኖሚ የማይናቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ጥናቶቹ ማረጋገጣቸውን ይፋ አድርጓል።

የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ የቤተሰብ ምጣኔ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ አስመልክተው እንደገለፁት፤  የቤተሰብ ምጣኔን ማሳካት የቻሉ አገራት የኢኮኖሚ እድገታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ ትልቅ አቅም ሆኗል። ሲሉ የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ በማንሳት ያስረዳሉ።

እንደ ቻይና፣ ህንድ፣ ማሊዥያ፣ ባንግላዲሽ፣ ኢንዶኒዥያና ብራዚል ያሉ አገራት ታሪክ ሲታይ የኢኮኖሚ እድገታቸውን በከፍተኛ ሁኔታና በፍጥነት ማሳደግ  የቻሉት አንድ እናት በአማካይ የምትወልደው ልጅ ቁጥር ተመጣጣኝ ማድረግ አሊያም መቀነስ በመቻላቸው ነው። ለአብነት ቻይና እና ህንድ በህዝብ ብዛታቸው ተቀራራቢ ናቸው። ይሁን እንጂ በኢኮኖሚ እድገታቸው ትልቅ ልዩነት ያመጡት የቤተሰብ ምጣኔያቸውን በሚገባ በማዘመናቸው እንደሆነ ፕሮፌሰር ይፍሩ ይገልፃሉ።

እአአ ከ1980 በፊት  ለረጅም ዓመታት የህንድ አጠቃላይ የምርት እድገት የቻይናን ይበልጥ ነበር።  በመሆኑም በእነዚህ ወቅቶች የቻይና ኢኮኖሚ ከህንድ ያነሰ ነበር። እአአ በ1980 በተለይ ቻይና «የአንድ ልጅ» ፖሊሲዋን ይፋ ባደረገችበት ወቅት  እንኳ የህንድ ኢኮኖሚ የቻይናን ይበልጠው ነበር። ይህን ፖሊሲ በሚገባ ተግባራዊ ካደረገች ጀምሮ ግን  የቻይና አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የህንድን በሁለት እጥፍ እንደሚበልጠው የዓለም አቀፍ ተቋማትን መረጃ አስደግፈው ፕሮፌሰር  ይፍሩ ለማሳያነት ጠቅሰዋል። በዚህም ቻይና የዓለማችን ግዙፍ የኢኮኖሚ እድገት ባለቤት አድርጓታል ብለዋል።

አሁን ይፋ የተደረጉት የዓለም አቀፍ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እአአ  እስከ 2030 ድረስ የቻይና ኢኮኖሚ የዓለማችን ግዙፍና ቀዳሚው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ህንድም የቤተሰብ ምጣኔዋን በማዘመኗ ኢኮኖሚዋ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

ተጨማሪ ምሳሌ እንመልከት። የናይጄሪያ ህዝብ ብዛት 192 ሚሊዮን ነው። ኢንዶኒዥያ 200 ሚሊዮን አካባቢ ነው። በመሆኑም ኢንዶኒዥያ እና ናይጄሪያ ተቀራራቢ የህዝብ ብዛት ያላቸው አገራት ቢሆኑም  የኢንዶኒዥያ ኢኮኖሚ እአአ ከ1980ዎቹ በፊት ከናይጄሪያ ኢኮኖሚ ያነሰ ነበር። ኢንዶኒዥያ በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ያላት ፖሊሲና የተከተለችው ስትራቴጂ ውጤታማ ስላደረጋት የናይጄሪያን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው መልኩ ለመብለጥ ችላለች። አሁን ኢንዶኒዥያ የናይጄሪያን ኢኮኖሚ እጥፍ በሚባል ደረጃ አልፋ ሄዳለች።

ትንበያዎች እንደሚያመለክቱት የዓለምን ኢኮኖሚ ይቆጣጠሩታል ተብለው የሚገመቱት አገራት በዋናነት የቤተሰብ ምጣኔያቸውን ማሳካት የቻሉት ናቸው። ይህ ማለት አንድ እናት በአማካይ የምትወልደው ልጅ ቁጥር መቀነስ ወይም ማመጣጠን ችለዋል ማለት ነው። ይህ ሲባል በሌላ አነጋገር «በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የህፃናት ቁጥርን ከማብዛት ይልቅ መካከለኛ እድሜ ያለው ትውልድን ማብዛት  አምራችን ህዝብ ማብዛት ማለት ነው» ሲሉ የህብረተሰብ ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ።

እናቶች የሚወልዷቸውን ልጆች መጠን ማመጣጠን መቻል ማለት ደግሞ በርካታ ትርጉሞችን ይይዛል። እናቶች ወይም ሴቶች የአገሪቱ ግማሽ አካል ናቸው። የሚወልዷቸው ልጆች የተመጣጠኑ መሆኑ ብዙዎቹ ሴቶች ጤነኛ ይሆናሉ፤ በተጨማሪም  ለብዙዎቹ  መልካም አጋጣሚ ስለሚሆን ወደ ተለያዩ ስራዎች ይሰማራሉ የሚል ሙሉ እምነት አለ።

እንደ ፕሮፌሰር ይፍሩ፤  የቤተሰብ ምጣኔን ማሳካት ሲቻል ብዙ ህፃናትን ከሞት ወይም ከተለያዩ ችግሮች ለመታደግ ይቻላል። በዚህም ህፃናቱ ጤነኛ ሆነው ያድጋሉ። ጤነኛ ሆነው ሲያድጉ ይማራሉ፤ አምራችም ይሆናሉ። በመሆኑም ከጥገኝነት በመላቀቅ ነፃና ራሳቸውን ችለው አምራች ወደ መሆን ይሸጋገራሉ። በዚህም ከራስ አልፎ ለአገር የሚተርፍ እድገት ለማስመዝገብ ይበቃሉ ሲሉ የእነ ቻይና እና ኢንዶኒዥያ የኢኮኖሚ እድገት ምስጢር የገለፁት።

«አሁን ኢትዮጵያም በዚህ አይነት ለውጥ ወይም ሽግግር ላይ ትገኛለች» የሚሉት ፕሮፌሰር ይፍሩ አገሪቱ በ2000 ዓ.ም ከነበራት አምስት በመቶ የቤተሰብ ምጣኔ ወደ  35 በመቶ ያደገበት ፍጥነት ከየትኛውም አገር ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ያስረዳሉ። አሁንም ከዚህ በላይ ማሳደግ በተቻለ ቁጥር የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በተጓዳኝ ማሳደግ ይቻላል ባይ ናቸው። በመሆኑም  የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የጤና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፈጣን ኢኮኖሚ እድገት መሰረት ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት የቤተሰብ ምጣኔያቸውን ተመጣጣኝ በማድረግ የቤተሰብ ጤንነትንም ሆነ አምራች ዜጋን በማፍራት ረገድ ድጋፍ ይሻሉ። በዚህም የተነሳ የተለያዩ የበለፀጉ አገራትን ድጋፍ ለማግኘት የተዘጋጀን እቅድ ይዞ የአገራቱን ድጋፍ ለማግኘት ብርቱ ስራን  ይጠይቃል።

«ጤነኛ ህብረተሰብ ባፈራን ቁጥር የኢኮኖሚ እድገታችን እጅግ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ያደርገዋል። በዚህም ሁኔታ ኢትዮጵያ የቤተሰብ ምጣኔዋን ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት እንድትደግፍ የእንግሊዝ መንግስትን ከአምስት ወራት በፊት በእቅድ ላይ የተመሰረተ ጥያቄ አቅርበን ነበር። በመሆኑም በእነዚህ ወራቶች በተደረገ ውይይትና ድርድር እንግሊዝ የኢትዮጵያን እቅድ ተቀብላዋለች።  በዚህም የተነሳ አገሪቱ የሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር እርዳታ አድርጋልናለች» ብለዋል ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን።

እርዳታው የእንግሊዝ መንግስት ኢትዮጵያ በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ለምትሰራው ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። የቤተሰብ ምጣኔ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ግልፅ መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ። በዚህም የተነሳ የቤተሰብ ምጣኔ የእድገት መሰላል አንዱ ምሰሶ ይሆናል።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጆ ሞየር በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቤተሰብ ምጣኔን በማዘመን የኢኮኖሚ እድገቷን ማሳደግ እንደሚቻል የነደፈችው ስትራቴጂ ስኬታማ በመሆኑ የእንግሊዝ መንግስት በዘርፉ የሚያደርገውን ትልቁን እርዳታ መስጠቱን አስረድተዋል።

በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የቤተሰብ ምጣኔን ለማዘመን የተሰጠው እርዳታ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረግ ዳይሬክተሯ አመልክተዋል። በዚህም ድጋፍ ከ13 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለው ከ15 ሚሊዮን በላይ አላስፈላጊ እርግዝናን በመከላከል የሶስት መቶ ሺ ህፃናትን ሞት ለማስቀረት እንደሚቻል ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

እርዳታው ኢትዮጵያ ከነባሮቹ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች በተጨማሪ እናቶች በራሳቸው በቀላሉ ቆዳ ስር የሚወጉት «ሳያ ፕረስ» የተሰኘ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ እንደምታስገባ ፕሮፌሰር ይፍሩ ጠቁመዋል። ቴክኖሎጂው እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሳይመጡ በራሳቸው ወይም በቤተሰብ አባል በቀላሉ ሊተገበር የሚችል መሆኑ የተለየ ያደርገዋል።

ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያስገነዝበው የበለፀጉ አገራት አምራች ዜጎችን ቁጥር ያበዙት የቤተሰብ ምጣኔያቸውን በማዘመናቸው ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያም ይህን ተሞክሮ በመቀመር የቤተሰብ ምጣኔዋን በማዘመን ፈጣን ኢኮኖሚ እየገነባች ያለችው ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቷ ነው።

ሀብታሙ ስጦታው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።