«የሥራ ኤግዚቢሽን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሊስፋፋ ይገባል»-ዶክተር ሄርጶጤኖ ተሸቴ Featured

07 Aug 2017

በ2007ዓ.ም የተቋቋመው አርሲ ዩኒቨርሲቲ እንደማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሚኒስቴር የሰጠውን ተልኮ በመያዝ  ነው ወደ ሥራ የገባው። ዩኒቨርሲቲው በ2025ዓ.ም  ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚዎቹ እና በዓለም ታዊቂ ለመሆን ግብ አስቀምጦ እየሰራ ነው። የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ በሚመለከት ከዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንትና የትምህርት ጉዳዮች  ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሄርጶ ጤኖ ተሸቴ  ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

አርሲ ዩኒቨርሲቲ መንግሥት የሰጠውን ተልዕኮ ከማስፈፅም አንፃር  ምን ያህል ተጨባጭ ሥራዎችን እያከናወነ ነው?

ዶክተር ሄርጶጤኖ፦ ዩኒቨርሲቲያችን በሚኒስትሮች ምክርቤት በ2007ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ  እንደማንኛውም የትምህርት ተቋማት ትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠውን ተዕልኮ ይዞ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ጥኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በዚህም በመማር ማስተማር «እንደከዋከብት አትሌቶቻችን ሊቅ ባለሙያዎችን እናፈራለን» በሚል መሪ ቃል ነው ሥራውን የጀመረው፡፡ ይህንንም ሥራ በአምስት ኮሌጆችና በአንድ የሕግ ትምህርትቤቶች እያከናወነ ይገኛል፡፡

 ዩኒቨርሲቲያችንን በምሥራቅ አፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ለማሰለፍ እና በዓለም ታዋቂ ለመሆን በ2025ዓ.ም ራዕይ ይዘናል፡፡ ለራዕያችን መሳካት መሠረት ከአሁኑ ማሳያ የሚሆኑ ውጤቶች ተገኝተዋል ብዬ አምናለሁ። ይህም በህክምና  ተመርቀው አገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ 90ነጥብ2 በመቶ የሚሆኑት አልፈዋል። በሕግ ትምህርት ክፍል ደግሞ በ2008ዓ.ም ወደ99በመቶ እና በ2009ዓ.ም ከተፈተኑት የሕግ ተማሪዎች ውስጥ መቶ በመቶ አልፈዋል። እንዲሁም በሚድዋይፈሪ አገር አቀፍ የጥራት ፈተና ከተፈተኑት ውስጥ 88 ነጥብ 5አልፈዋል፡፡ በዚህም ከአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ሊቅ ባለሙያዎችን እናፈራለን ስንል በአመለካከት፣ በእውቀትና በክህሎቱ የታነፀ ዜጋን ለማፍራት  ለታቀደው አላማ  ጅምሩ ማሳያ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ሦስት መሠረታዊ ተልዕኮዎች አላቸው  የመማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር፣ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የተሰጡትን ተልዕኮዎች  በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት መንገድ የጀመረ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ የምርምር ሥራ ላይ በአርአያነቱ የሚጠቀስና ወደ ማህበረሰቡ የተሸጋገረ ሥራ ካለ  ቢገልጹልኝ?

ዶክተር ሂርጶጤኖ፦ በምርምር በኩል በ2009ዓ.ም ወደ 42ፕሮጀክቶች ቀርበው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ በተዘጋጀው የትኩረት አካባቢ (ቲማቲክ ኤርያ) መሠረት ችግር ፈቺ ናቸው ተብለው የተለዩ እና ወደ ሥራ የገቡት40 ናቸው፡፡ እነዚህ ምርምሮች ሸልፍ ላይ የሚቀመጡ ሳይሆን አካባቢውንና የማህበረሰቡን ሕይወት የሚቀይሩ መሆን አለባቸው ብለን ስለምናምን ውጤቱን እንዴት ነው ወደ ማህበረሰቡ የምንወስደው? በሚለው ደረጃ ላይ ነን፡፡ እነዚህ ምርምርና ጥናቶች የማህበረሰቡን ሕይወት ይቀይራሉ ብለን እየሰራን ነው፡፡ እንደሚቀይሩም እርግጠኛ ነኝ፡፡ 

አዲስ ዘመን፦ የማህበረሰብ አገልግሎትን በተመለከተ ዩኒቨርሲቲው በተጨባጭ ያከናወነው  ሥራ እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ሄርጶጤኖ፦ ማህበረሰብ አገልግሎትን በተመለከተ ዩኒቨርሲቲያችን በማህበረሰቡ ውስጥ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰቡ ውስጥ መገኘት አለበት ብለን እናምናለን። በዚህ አግባብ አንደኛ ከማህበረሰቡ የሚመጣውን ችግር መሠረት አድርገን፤ ሁለተኛ ከጥናትና ምርምራችን ውጤት ይዘን ወደ ማህበረሰቡ እንሄዳለን፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከማህበረሰቡ የሚመጡትን ጥያቄዎች መሠረት አድርገን ወደ ማህበረሰቡ የምንሄድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህም አንዱ የማህበረሰብ አገልግሎት ስንሰራ የነበረው ትልቁ  ሥራ ነፃ የሕግ አገልግሎት ነው፡፡

ለነፃ የሕግ አገልግሎት የሚሆኑ 20 ማዕከላትን በዙሪያችን ከፍተናል። እነዚህም በኤች.አይቪ የተጠቁ  ሕፃናትን እና  አቅመ ደካሞችን የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችና መምህራን ጥብቅና እንዲቆሙላቸው በማድረግ ደረጃ በአካባቢው ሊመሰገን ያስቻለ ሥራ ነው የሰራነው፡፡ ሌላው በፌስቱላ የተጎዱ ሰዎችን አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ለምሳሌ በወሊድ ጊዜ የተጎዱ እናቶችን በቀጥታ ሆስፒታሉ መጥተው ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ፤ በየጤና ጣቢያው በመሄድ እየሰበሰብን የነፃ ህክምና እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ በተጨማሪም ነፃ የዓይን ሕክምና እየሰጠን ነው፡፡ እኔም በሙያዬ  የዓይን ሕክምና እስፒሻሊስት በመሆኔ  ሕክምናውን የምንሰጠው በነፃ ነው።

አዲስ ዘመን፦ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የቅብብሎሽ ሥራ እንደሆነ ይታወቃል፤ በመሆኑም  ዩኒቨርሲቲው በግቢው ውስጥና ከግቢ ውጪ ጥራትን ለማስጠበቅ ምን እየሰራ ነው?

 ዶክተር ሄርጶጤኖ፦ ትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን። ለዚህም የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሁለት ሞዴል ትምህርት ቤቶች ከዞንና ከከተማው አስተዳደር መርጠን የአቅም ግንባታ ሥራ እየሰራን ነው። አስተማሪዎችንና ፈፃሚዎችን ከማብቃት በተጨማሪም የትምህርት ግብአቶችን፤  ለምሳሌ ኮምፒውተሮችን፣ ፎቶ ኮፒ ማሽኖችን፣ መጽሐፍቶችን ወዘተ በማቅረብ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎችን ወደ ጥናት የሚያነሳሳና የትምህርት ግብዓት የሚሆኑ፣ መምህራንን ብቁ የሚያደርግ ሥራ በተመረጡት ትምህርት ቤቶች  እየሰራን ነው፡፡ የሴት ተማሪዎችን እገዛ በተመለከተ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ ለምሳሌ ልዩ ፕሮግራም በማዘጋጀት መምህራን ችግሮቻቸውን በመለየት እገዛ እያደረጉ ነው፡፡ በተለይ ሴት ተማሪዎቻችን በራሳቸው እንዲተማመኑ የማድረግ ሥራ በስፋት እየሰራንበት ያለ ተግባር ነው፡፡ በዚህም በዩኒቨርሲቲያችን ያሉ ሴት ተማሪዎች በራሳቸው እንዲተማመኑ አድርገናል፡፡ አብዛኛው የማዕረግ ተመራቂዎች ሴቶች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ብሎ የተገኘ ውጤት አይደለም፡፡  

በሌላ በኩል ከአረብ አገር ለተመለሱት ዜጎቻችን ሥልጠና እንሰጣለን። የሥራ አማራጮችን አይተው ሥራ እንዴት መፍጠር እንደሚችሉ፤ እንዴት መቆጠብ እንደሚችሉ የማስተማር ሥራን እንደ አንድ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰራንበት ነው፡፡ 

አዲስ ዘመን፦ አሰላ  የገብስና የስንዴ አገር ነው፤ ማህበረሰቡ ይህንን ምርት በዘመናዊ አመራረት ተጠቅሞ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ  ከማድረግ አንፃር ምን እየሰራችሁ ነው?

 ዶክተር ሄርጶጤኖ፦  እንደ የልህቀት  ማዕከል አድርገን  ከለየናቸው  መካከል  የስንዴና የገብስ አካባቢ በመሆኑ የተለየ የስንዴና የገብስ ዝርያን  በመለየት ሞዴል ለሆኑ አርሶአደሮች እያደልን  ነው። እነዚህ ሞዴል አርሶአደሮች ውጤታማ ሲሆኑ ለሌሎቹ አርሶአደሮች እንዲያስፋፉ ነው የምናደርገው፡፡ በዚህም በተለያዩ ወረዳዎች ላይ በማህበር ከደራጁት ውስጥ የተመረጡት  ከዩኒቨርሲቲያችን ጋር እንዲሰሩ እያደረግን ነው፡፡ በተጨማሪም መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጥናት ያገኙት የስንዴ ዝርያ አለ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትብብር ፈጥረናል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተመሳሳይ በትብብር እየሰራን ነው፡፡

በአጠቃላይ ትብብሩ ከመንግሥት ድርጅቶች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር አብርን ለመስራት አስችሎናል፡፡ በከብት ማድለብና ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር  በቅንጅት እየሰራን ነው፡፡

 በሌላ በኩል የልህቀት ቦታ ብለን የያዝነው አካባቢው የአትሌቶች መፍለቂያ እንደመሆኑ መጠን ስፖርትና ስፖርት ሳይንስ ከዚህም ውስጥ በስፖርት ሜድሲንን  የተሻለ ደረጃ ላይ እናደርሳለን ብለን እየሰራን ነው። በዚህ አግባብ የልህቀት ማዕከል አድርገን እየሰራን እንደ ከዋክብት አትሌቶቻችን ሊቅ ባለሙያ እናፈራለን ስንል በትምህርቱ ጎን ለጎን አትሌት የማፍራትና  ከዘርፉ ክልሉ ብሎም አገራችን ተጠቃሚ እንድትሆን ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም አላማችን ይሳካ ዘንድ እስከታች ድረስ ወርደን እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ  እንደመሆኑ  መንግሥት ያስቀመጠውን የሰው ኃይል በመሟላት ረገድ  ምን ያህል ስኬታማ ነው?

ዶክተር ሄርጶጤኖ፦ በነገራችን ላይ አርሲ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም አዲስ የሚባል  አይደለም። አዳማ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ተከፍሎ ነው፤ አዳማ ሳይንስ ቴክኖሎጂና አርሲ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠሩት። ስለዚህ የእኛ ኮሌጆች የመጡትም ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ስለሆነ የግንባታ ሥራውን ነው እንጂ እንደ አዲስ የምናየው በሰው ኃይል አዲስ አይደሉም፡፡

 ለምሳሌ የግብርናና የጤናን ኮሌጆች40ዓመት አካባቢ የቆዩ እና መማር ማስተማር ከጀመሩ ከአስር ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ ነው አይባልም፡፡ መንግሥት ያስቀመጠውን  ቀመር አስቀድመን ለማሳካት ጥረት እያደረግን ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በተሻለ አፈፃፀም ላይ እንገኛለን። ክፍተቱን ለመሙላትም ከአገር ውጪ ትምህርት እየተከታተሉ ያሉ ብዙ አስተማሪዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሥራ ላይ ያሉት ወደ454መምህራን እና ትምህርት ላይ ያሉት ደግሞ 242ናቸው፡፡ ስለዚህ ወደ እቅዱ እየተጠጋን ነው።

አዲስ ዘመን፦ ማህበረሰቡ ወደ ዘመናዊ ንግድ አሠራር እንዲገባ እና በተለይም አሁን ካለው  ኋላቀር የንግድ ሥርዓት እንዲወጣ ዩኒቨርሲቲው ምን እየሰራ  ነው? 

ዶክተር ሄርጶጤኖ፦ ትላልቅ ሥራ ፈጥረው የሚሰሩ ሰዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲው እየጋበዝን የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን። ዘመናዊ ንግድ ያለውን ጠቀሜታ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት እያስተማርን ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን በቅርቡ ሊመረቁ የደረሱ ተማሪዎች የሥራ ኤግዚቢሽን አዘጋጅተን ተማሪዎቹ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር እንዲገናኙና ጥሩ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች እንዲመረጡ አድርገናል፡፡

በዚህም ተማሪዎቻችን  ከአሰሪዎች ያገኙት ልምድ አለ፤ አሰሪ ድርጅቶችም ከተማሪዎቻችን ያገኙት ልምድ ይኖራል። በተጨማሪም ማህበረሰቡም ሥራ ፈጠራ ላይ የሚማረው ነገር እንደሚኖር እናምናለን፡፡ በዘ ልማድ በንግድ ውጤታማ የሆኑ ሰዎችን ሳይቀር ከሳይንሱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህም መሠረት የሥራ ኤግዚቢሽን ብዙ ተማሪዎችን እንዲቀጠሩልን አድርጓል። ስለዚህ እንደ ጥሩ ተሞክሮ የሥራ ኤግዚቢሽን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሊስፋፋ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስት ኮሌጆች ያስተማራቸውን 1996ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ፤ እንዲሁም በዲፕሎማ ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሲያስመርቅ «እንደከዋክብት አትሌቶቻችን ሊቅ ባለሙያዎችን እናፈራለን» ብለን የያዝነውን ግብ ለማሳካት የመሠረት ድንጋይ የጣልንበት ነው ብሎ ለመናገር ይቻላል፡፡ 

አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር  ሄርጶጤኖ፦ እኔም አመሰግናለሁ ፡፡  

አብርሃም አባዲ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።