«የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት አሁንም ብዙ ሥራዎችን ይሻል» -ዶክተር አክሊሉ አዛዥ የኢትዮጵያ ድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት

10 Oct 2017

የኢትዮጵያ ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ሥርዓት ገና ያልዳበረ እና ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ እንደሆነ የሕክምና መስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአገራችን በድንገተኛ ሕክምና ልዩ መስክ ወይም ስፔሻሊቲ የሰለጠኑ ሐኪሞች ሃያ አንድ ብቻ መሆናቸው የኢትዮጵያ ድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር መረጃ ያስረዳል። ይህም አገልግሎቱ ገና በማደግ ላይ ያለ መሆኑን አመላካች ነው። የኢትዮጵያ ድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር መስራቾች አንዱና በፕሬዚዳንትነት እየሰሩ ያሉት ዶክተር አክሊሉ አዛዥ በሕክምናው ምንነት፣ በዕድገቱና መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን ፡- ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ምን ማለት ነው?

ዶክተር አክሊሉ፡- ድንገተኛ ሕክምና በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች አስቸኳይ ሕመም ወይም አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሰጥ የነፍስ አድን ሕክምና ሲሆን፣ ይህም የሰው ህይወትን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከማለፍ መታደግና ተጎጂ ዘለቄታዊ ሕክምና የሚያገኝበትን ዕድል የማመቻቸት አገልግሎት ነው። የሕክምና አገልግሎቱም ታካሚው ከቤቱ ወይም አደጋ ከተከሰበት ቦታ ጀምሮ የሕክምና ተቋም እስኪደርስ የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ የሚያገኝበት ከመሆንም አልፎ ከመደበኛ ሕክምና ሰጪ ባለሙያዎች ጋር በተግባቦት ሥርዓት በመደጋገፍ የታካሚውን ህይወት ለማቆየት የሚደረግ ጥረትም ነው። ይህም በቅድመ ሆስፒታል ወይም በአንቡላንስ ቡድን ድጋፍ ይከናወናል። ሕብረተሰቡ ጭምር ይሳተፍበታል።

አዲስ ዘመን፡- የአገራችን የአደጋ ተጋላጭነት ደረጃ ምን ይመስላል ?

ዶክተር አክሊሉ፡- የትኛውም አገር ከአደጋ ተጋላጭነት ነፃ አይደለም። በአገራችን የትራፊክ አደጋ በርካታ ሞትና አካል ጉዳት እያስከተለ ከጊዜ ወደ ጊዜም የአደጋው መጠን እየጨመረ ይገኛል። በሌላ በኩል የኮንስትራክሽን ዘርፉ መስፋፋት የሰራተኞች የመውደቅ አደጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም በአገራችን የተሽከርካዎች መብዛት፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የግንባታና ኢንቨስትመንት ማደግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ ድንገተኛ አደጋዎች እየጨመሩ ይሄዳሉ። ሌላው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዓለም ላይ እንደ ኢቦላ፣ ሳርስንና መርስን የመሳሰሉ ፈታኝ የበሽታ ወረርሽኝና ተላላፊ በሽታዎች ሊፈጠሩ ችለዋል። ሌሎች ከፍተኛ ድንገተኛ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ የሽብር ጥቃት የመሳሰሉት ችግሮችም አሉ። ከነዚህ ሁሉ እኛ ነፃ ነን ማለት አንችልም፤ ስለሆነም ዝግጁነት ያስፈልጋል። ለተጠቀሱት ጅምላ ድንገተኛና መደበኛ ድንገተኛ አደጋዎች ሁሉ በተገቢ አኳኋን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ አለብን።

አዲስ ዘመን፡- በአገራችን የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት በየትኞቹ የህክምና ተቋማት ይሰጣል?

ዶክተር አክሊሉ፡- የሕክምና አገልግሎቱ በሁሉም ሆስፒታሎች ይሰጣል። ነገር ግን በልዩና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ የአለርት የአደጋ ማእከል እንዲሁም በጎንደር፣ ሃዋሳ፣ አዳማና ዓይደር መቀሌ ሆስፒታሎች ልዩ የድንገተኛ ሕክምና ማእከላት ተቋቁመዋል።

አዲስ ዘመን፡- የአገራችን የድንገተኛ ሕክምና ዘመናዊነትና ተደራሽነት እንዴት ይመለከቱታል?

ዶክተር አክሊሉ፡- አሁን ጥሩ ጅማሮ ላይ እንገኛለን። በአፍሪካም ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ኢትዮጵያ በሁለተኝነት ትቀመጣለች። ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በላይ አሁን ላይ ለድንገተኛ ሕክምና የትምህርት መስክ ላቅ ያለ ትኩረት ሰጥታለች። የአምቡላንስ አገልግሎቱ እያደገ ነው። ከአስር ዓመት በፊት በወረዳዎች የነበረው የአንቡላንስ ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። አሁን በመላ አገሪቱ 1600 አምቡላንሶች አሉ። ይህ ማለት በእያንዳንዱ ወረዳ አንድ ወይም ሁለት አምቡላንስ አለ። ነገር ግን በነዚህ አምቡላንሶች በድንገተኛ ሕክምና የሰለጠነ ባለሙያ አለ ማለት ግን አይደለም። በቂ ባለሙያዎች ማፍራት ይጠበቅብናል። የአደጋ ማዕከላትንም እያቋቋምን ነው። ነገር ግን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያላቸው ቅንጅት ግን ብዙ የሚቀረው ነው። በዚህም የብዙ ዜጎች ህይወት ያልፋል። እኛም ይሄን ክፍተት ለይተን በመስራት ላይ ነን። አገልግሎቱ የተዋጣለት አስተዳደር እንዲሁም የቁጥጥርና ግምገማ ያስፈልገዋል። የግብዓት እጥረት በየጊዜው ማሟላት ያስፈልጋል። የሰው ኃይልም በበቂ መጠን ለማፍራት ማህበሩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ጥረት እያደረግን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- የአገራችን የድንገተኛ ሕክምና ሥርዓት ክፍተቶችን ቢጠቅሱልኝ?

ዶክተር አክሊሉ፡- የአገልግሎቱ ሥርዓት አለመጠናከር ትልቁ ክፍተት ነው። ኀብረተሰቡ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ እንዲሁም አምቡላንስ ማግኘት የሚችልበት የተግባቦት መስመር ወይም አርተሪ በበቂ መጠን መዘርጋት አለበት። ይህን የትብብርና የግንኙነት አሰራር ማጠናከር ያስፈልጋል። የግብዓት እጥረትና በሆስፒታሎች ለድንገተኛ ሕክምና ክፍል የሚመደበው ቦታ በጣም ትንሽ መሆኑ ሌላው ችግር ሲሆን የጤና ተቋማትም ዝግጁነት ይጎድላቸዋል። ይህም ራሱን የቻለ ማነቆ ነው። የኀብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ መቀረፍ ያለበት ጉዳይ ነው። የመጀመሪያ እርዳታ ግንዛቤ ማሳደግ ኀብረተሰቡ ራሱ ቀድሞ እንዲከላከል ያስችለዋል። ይህም የድንገተኛ ሕመሞችን ምንጭን የምናደርቅበት ሁኔታ ይፈጥራል። አደጋ በሚደርስበት ወቅትም ማስቀረት የሚቻሉ ሞቶችን ይቀንሳል። በድንገተኛ አደጋ ምክንያት ከሚከሰቱ ሞቶች የሚበዙት በመጀመሪያው ሰዓት የሚከሰቱ በመሆናቸው ግንዛቤ ያለው ሰው የአየር ትቦ እንዲከፈት በማድረግ፣ የደም መፍሰስን ማስቆም፣ አተነፋፈስን ለማስተካከል መርዳት፣ ጉዳቱን የሚያባብሱ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን መከላከል ይቻላል። በዚህም የሚደርሱ ሞቶችን እና የአካል ጉዳቶችን መቀነስ ያስፈልጋል። የጤናን ጉዳይ በትምህርት ውስጥ አካቶ ልጆችን እያስገነዘብን ስንሄድ ችግሩ ይቀረፋል። ዘለቄታዊ መፍትሔም ማምጣት ይቻላል። አሁን ችግሩን ለመቀነስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ለ1 መቶ ሺ የኀብረተሰብ ክፍሎች አጫጭር ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል። ስልጠናው እውቀትና ክህሎትን የሚያስጨብጥ በመሆኑ በድንገተኛ አደጋ ወቅት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ከማን ጋር መገናኘት እንደሚጠበቅና አደጋና ሕመሞችን ለመለየት ይረዳል። ይህም አገልግሎቱን ያቀላጥፈዋል።

አዲስ ዘመን፡- በአገራችን የድንገተኛ ሕክምና ትምህርትና ስልጠና ምን ይመስላል?

ዶክተር አክሊሉ፡- በአዲስ አበባ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር በጠቅላላ ሕክምና የተመረቁ ሐኪሞች በስፔሻሊቲ ደረጃ ሦስት ዓመት የሚሰለጥኑበት መርሐ -ግብር አለ። ሌላ በድህረ-ምረቃ የድንገተኛና ፅኑ ሕሙማን ሕክምና የሁለተኛ ዲግሪ እያሰለጠነ ይገኛል። አሁን በቅርቡ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ-ግብር በአስር የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችና ከፍተኛ ሆስፒታሎች መሰጠት ጀምሯል። በዩኒቨርሲቲው አንድ የድንገተኛ ሕክምና ማሰልጠኛ ማእከል ይገኛል። በዚህ የስልጠና ማእከል አንድ ሺ ሁለት መቶ ሐኪሞች የሰባት ሳምንት የድንገተኛ ሕክምና ስልጠና ወስደዋል። የሕክምና መስኩ የስፔሻሊቲ ትምህርት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም እየተሰጠ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለማዘመን ያበረከተው አስተዋፅኦ ምን ይመስላል?

ዶክተር አክሊሉ፡- እንደ ማህበር ወሳኝ አቅጣጫዎች አሉን። በመጀመሪያ ደረጃ የአባል ሐኪሞች ብቃት ማሳደግና ወቅቱን የጠበቀ ክህሎት እንዲይዙ ማድረግ ነው። ይህም ለተገልጋዮች የምንሰጠው አገልግሎት ጥራት ያለው እንዲሆን ይረዳል። በሌላ በኩል የድንገኛ ሕክምና ለማስፋፋት ማህበሩ ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር ተቀራርቦ ይሰራል። ማህበራችን በጤና ጥበቃ ስር የተቋቋመው የድንገተኛና ፅኑ ሕሙማን ግብረ- ሐይል መስራችና ግንባር ቀደም ተሳታፊም ነው። የድንገተኛ ሕክምና የአራት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ሲቀረፅ የበኩላችንን አበርክተናል። ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር በሐኪሞች አቅም ግንባታ የበኩላችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን። ማህበራችን ከተለያዩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተመሳሳይ የሙያ ማህበራት ዝምድናና ቁርኝት ፈጥረናል። የአፍሪካና የዓለም አቀፉ የድንገተኛ ሕክምና ፌዴሬሽኖች አባል ነን። ይህም ወቅታዊ የሕክምና መስኩ ሳይንስና እውቀት ወደ አገራችን ለማምጣት ተቆራኝተን እንሰራለን።

 

በሪሁ ብርሃነ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።