አርሂቡ…ኑ ቡና ጠጡ

11 Oct 2017

 

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ብቻም ሳትሆን የቡና ወዳጅ አገር ናት ቢባል ቅጥፈት አይሆንም።ለዚህም ይመስላል በመዲናይቷም ሆነ በሌሎች የአገሪቷ ክፍል የጀበና ቡና ጠጡ ቤቶች በርክተው መታየታቸው። የቡና ጠጡ ስራም ከትላልቅ ሆቴሎች እስከ መንገድ ዳር እስከሚገኙ ደሳሳ ቤቶች ድረስ የሚታይ ትዕይንት ሆኗል። በዚህም በርካቶች ኑሯቸውን የመደጎሚያ አንድ የስራ መስክ አድረገውታል። የአዲስ ዘመኗ መልካም ስራ አፈወርቅም በቡና ጠጡ ስራ በመሰማራት ኑሯቸውን እየገፉ የሚገኙ ሰዎችን በማነጋገር የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲህ አቅርበዋለች።

 

ግርግር ከበዛበት ጎዳና ከአንዱ ጥግ ተቀምጣ ወጪ ወራጁን በአትኩሮት ትቃኛለች። በየማህሉ አቧራ እያስነሳ አካባቢውን የሚረብሸው ንፋስም እምብዛም እንዳላወካት ያስታውቃል። የፀሐዩን ግለት የለመደችው ይመስላል። እንደነገሩ በላስቲክ የተቀየሰችው ጠባብ ጎጆ ያልያዘችው የለም። በጎጆዋ ውስጥ እዚህም እዚያም ቋጠሮዎች ይታያሉ። አንባሻ፣ ትኩስ ፓስቲ፣ ጥራጥሬ… ሌሎች ነገሮችን ይዘዋል።

መሀል ለመሀል የተዘረጋው አግዳሚ ጠረጴዛ ላይ የሻይ ብርጭቆዎች ተደርድሮ በእግሮቹ ስር ፔርሙሶችንና ማንቆርቆሪዎችን አዳብሏል። የሚነፍሰው ንፋስ አሁንም አሁንም የመንገዱን አቧራ እያፈሰ ወደ ቤት ያስገባል። ይህ ሁሉ ሲሆን በወይዘሮዋ ፊት ላይ የተለየ ገጽታ አይነበብም። የፈዘዙ አይኖችዋ ወደ ውጭ ማየታቸውን እንደቀጠሉ ነው።

ድንገት ከወደውጭ «ቤቶች» የሚል ድምጽ ተሰማ። በርከት ያሉ ሰዎች ናቸው። ጎንበስ እያሉም ወደውስጥ ዘለቁ። ቤቱን አስቀድመው የሚያውቁት ይመስላል። ይሄኔ በትካዜ ቆዝማ የነበረችው ሴት በፍጥነት ከመቀመጫዋ ተነሳች። እንግዶችዋን ቦታ አስይዛም በረከቦት የተደረደሩ ሲኒዎችን መልክ ማስያዝ ጀመረች። ዝምታ ውጦት የነበረው ስፍራ በእንግዶቹ ጨዋታ ደመቀ። የተዳፈነ የሚመስለው ከሰል ተያይዞ ቤቱ በእጣን ሽታ ታወደ። ትካዜ የለበሰው የወይዘሮዋ ገጽታ በአንዴ በደስታ ሲፈካ ታየ።

ዕድሜ ጠገቡ የቡና እረከቦት መልከ ብዙ ስኒዎችን አጠጋግቶ ደርድሯል። ቀድሞ ቡና የተቀዳበቸው ስኒዎች መድረቅ የጀመረው ጭላጭ አተላ በሴትዬዋ ሸካራ እጆች ተለቃልቀው ለሥራ ተዘጋጁ። ባለቡናዋ ደስ እንዳላት ያስታውቃል። ወይዘሮ ዘሪቱ አረቦ በዙሪያዋ ከበው የእሷን እጅ የሚጠብቁ ደንበኞችዋን በወጉ ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለች ነው።

ከተስተናጋጆቹ አብዛኞቹ በአካባቢው የቀን ሥራ ላይ የሚውሉ የጉልበት ሠራተኞች ናቸው። ብዙ ጊዜ የምሳ ቋጠሯቸውን ፈተው እህል ውሃን የሚቃመሱት በእሷ ጎጆ ነው። ይህ ባይሆን እንኳን አንባሻና ፓስቲ በልተው ትኩስ ቡናዋን ፉት ለማለት ከስፍራው አይታጡም። ቡና መኖሩን የሚያውቁ አንዳንድ መንገደኞችም አምሮታቸውን ለመወጣት ከጎጆዋ ጎራ ማለታቸው ተለምዷል። በአካባቢው በጉልት ንግድ ላይ የሚውሉ ሴቶችም የዘሪቱ የዘወትር ደንበኞች ናቸው። ለአንድ ስኒ ቡና አራት ብር እየከፈሉ በተወዳጁ ቡናዋ ይስተናገዳሉ።

ወይዘሮ ዘሪቱ አረቦ ሦስት ልጆችዋን ያለ አባት ስታሳድግ ብርታት ተለይቷት አያውቅም። ባለቤቷን በሞት ካጣች ወዲህ ልጆችዋን የማስተዳደር ኃላፊነት በትከሻዋ መውደቁ ግድ ነበር። ኑሮን ለማሸነፍ ያልሞከረችው የለም። እንጨትና ቅጠል ለቅማ ሸጣለች። በየሰው ቤት እየዞረችም ጉልበቷ የሚፈቅደውን ሁሉ ሰርታለች። ሁሌም ከፊቷ የማይለየው ደማቅ ፈገግታ ጨዋታዋን በሳቅ እያጀበ ከብዙዎች ጋር ያግባባታል።

"የእኔ" የምትለው ቤት የላትም። ለእሷ ዘመዷ ጉልበቷ ነውና ሌት ተቀን ብትለፋና ብትሮጥ ደከመኝን አታውቅም። የሚረዳትና አይዞሽ በሚላት ወዳጅ ዘመድ ላይም መመካት አትችልም። እሷ ሁሌም ቢሆን በልጆችዋ ላይ ተስፋ እንደጣለች ነው። አንድ ቀን ለቁምነገር ደርሰው፤ ለወግ ማዕረግ እንደሚበቁ ስታስብ ውስጧ ሀሴት ይሞላል። ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ በአዕምሮ ህመም ሳቢያ ቤት መዋል የጀመረችው ሴት ልጇ ጤንነት ሁሌም ያሳስባታል። "አደራ" ብላ የምትሰጠው የቅርብ ሰው የላትም። እሷን ከቤት ትታ ሥራ ስትሄድ ልቧ በሥጋት እንደተሞላ ይውላል። ከዚህ ጭንቀት ለመዳን ያላት አማራጭ ከመንደር ቤቶች ይልቅ ኮንደሚኒየም መከራየት ነበር። ይህን ስትወስን ግን ክፍያውና የዕለት ገቢዋ አልጣጣም ብሎ ፈትኗታል። በየቀኑ ቡና እያፈላች የምታገኘውን ለኪራይ ስትከፍል ለጓዳዋና ለቀለብ እጅ እያጠራት በሀሳብ የምትብሰለሰልበት ጊዜ የበዛ ነው።

ሳቂታዋና ተጫዋችዋ ዘሪቱ ግን ሁሌም በፈገግታ ተሞልታ የነገን መልካም ተስፋ በጉጉት ትጠብቃለች። የጀበና ቡናዋን ከዘወትር ደንበኞችዋ ጋር ያኑርላት እንጂ በኑሮዋ መቼውንም ቢሆን አትከፋም። ሁሌም ከእሷ ይልቅ የተሻለ ስፍራን መርጠው የሚሄዱ ቡና ወዳዶች እንዳሉ ታውቃለች። ገበያ ዕድል ነው ብላ የምታምነው ወይዘሮ ግን በዚህ ሆድ ብሷት አያውቅም። አልፈው የሚሄዱትን በአይኖችዋ ሸኝታ ወደእሷ የሚመጡት «አርሂቡ»ለማለት ሁሌም ዝግጁ ነች።

ዘሪቱን ተሰናብቼ ከቤቷ ወጣሁና መደዳውን የጀበና ቡና ያለባቸውን ቤቶች በወፍ በረር መቃኘት ጀመርኩ። አብዛኞቹ የተሻለ እይታን ለመሳብ የሚወዳደሩ ይመስላሉ። የቡና አፈላልን የሚያሳዩ በርካታ ስዕሎችን ጨምሮ ባህላዊ መጋረጃና አልባሳቱ፣ መቀመጫውና የስኒ መደርደሪያው አንዱ ከሌላው ለመላቅ የተዘጋጁ መሆናቸውን መገመት ይቻላል። በጀበና ቡናው አካባቢ ያሉ ደንበኞች ተግባረ ብዙ ናቸው። በእጃቸው ጫት የያዙትን ጨምሮ ለጨዋታ የሚገናኙት ሁሉ በዕጣኑ መአዛ እየታወዱ የልብ የልባቸውን ያወጋሉ።

መልከ ብዙዎቹን የጀበና ቡና አካባቢዎች አልፌ ከአንድ ዘመናዊ ህንፃ ውስጥ ተገኝቻለሁ። ይህ ህንፃ ከከተማዋ መሀል የሚገኝ ሰፊ የንግድ ማዕከል ነው። የመጀመሪያው ፎቅ ላይ ስደርስ በርከት ያሉ ሰዎች በኮሪደሩ ላይ ከሚገኝና የጀበና ቡና ከሚፈላበት ስፍራ ተሰባስበው ተመለከትኩ። በተመሳሳይ ሁኔታ ሁለተኛው ፎቅ ላይ ስደርስም የገጠመኝ ይሄው ነበር። አሁን በሦስተኛው ፎቅ ላይ ላይ ነኝ ።

በዚህ ቦታ ላይ ደግሞ ቀድሞ ካየኋቸው ቡና ጠጪዎች በቁጥር የላቁ ሰዎች ተሰባስበው የቡናውን መድረስ ሲጠባበቁ አስተዋልኩ። ለቡና ቁርስ የተዘጋጀው ፈንዲሻ ለእንግዶቹ እየታደለ ነው። በመልካም መአዛ የታወደው ስፍራ በደንበኞቹ ሞቅ ያለ ጨዋታ ታጅቦ ቀጥሏል። የቀደሙት ቦታ ሲለቁ አዲስ የሚገቡት ደግሞ በስፍራቸው ይተካሉ።

በዚህ መሀል እንግዶቹን በደማቅ ፈገግታ እየተቀበለ በትህትና የሚያስተናግደውን ወጣት አስተዋልኩ። በህንፃው ላይ የጀበና ቡናን ከጀመሩት መሀል አንዱ ነው። ይህን ወጣት ብዙዎቹ በሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኝነቱ ያውቁታል። ከስምንት ዓመታት ላላነሰ ጊዜም የስፖርት አፍቃሪ አድማጮቹ በሚያቀርበው ዘገባ ጆሯቸውን ሲሰጡት ቆይተዋል።ጋዜጠኛ ዘርአይ እያሱን።

ጋዜጠኛው ኢትዮጵያ ሬዲዮን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲሠራ ቆይቷል። የእሱ የሙያ ድር የተወጠነው በደቡብ ክልል ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት ቢሆንም የሬዲዮ ፋና የስፖርት ጋዜጠኝነቱ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በእግር ኳስ ላይ ተመርኩዞ የፃፈው «ከሜዳ ውጭ የተሰኘው መጽሐፉም ተነባቢነትን አትርፎለታል። እነዚህን የሙያ አመታት በፍቅር ያሳለፈው ጋዜጠኛ ዘርአይ በውስጡ ሲብሰለሰልበት የቆየውን ዕቅድ ለመፈፀም ጊዜው ስለመድረሱ ያወቀው አንድ ቀን ነበር።

ዘርአይ በቆየባቸው የጋዜጠኝነት አመታት በሙያው ደስተኛ ነበር። ይሁን እንጂ እሱን ጨምሮ አብዛኞቹ በሚያበረክቱት ልክ የሚሰጣቸው ክፍያ በቂ ያለመሆኑን ያምናል። ይህ መሆኑ ደግሞ ኑሮን አሸንፎ ለመቀጠል ያለውን ህይወት አዳጋች ሲያደርገው አስተውሏል። አንዳንዴ ለተጨማሪ ጥቅማ ጥቅም ሲባል የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶች ደግሞ እሱ አበክሮ የሚፀየፋቸው ናቸው። የሙያው ስነ ምግባር ከሚፈቅደው ውጭ ባልተገባ ምግባር የሚሳተፉ አጋሮቹንም ልማድ ያውቀል። ስለዚህ ዘርአይ እራሱን በተሻለ አቅም ለማጠናከር መንገዱን መቀየር እንዳለበት አመነ።

ምንም እንኳን እጅግ ከሚወደው የጋዜጠኝነት ሙያ ለመለየት ፈታኝ ቢሆንበትም ፍፁም መቁረጥ ነበረበት። እናም ለአመታት ከራሱ ሲመክርበት ለቆየው የንግድ ሥራ የቱ እንደሚሻለው ሲያማርጥ ቆየ። በመጨረሻ በውስጡ ሲብሰለሰልበት ለኖረው ዕቅድ ሀሳብ ነድፎ ከውሳኔ ደረሰ። ውሳኔውም ከጀበና ቡና ንግድ ላይ አሳረፈው።

አሁን ዘርአይ ሙሉ ጊዜውን ለጀበና ቡና ንግድ ሰጥቷል። ሥራውን ሲጀምረው በጥቂት የገንዘብ መነሻ ነበር። የሙያ ለውጥ ሲያደርግም ቀላል የማይባሉ ፈተናዎችን ተጋፍጧል። በሥራው ሂደት ኪሣራ ቢያጋጥምና እንደታሰበው ሆኖ ባይገኝ የሚመጣውን ሁሉ አምኖ ለመቀበልም ዝግጁ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ በገቢውም ሆነ በውሎው እርካታ የሚያገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ዘርአይ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንደመገናኘቱ የተለያዩ ልምዶችን አዳብሯል። ከሁሉም ግን በተሰማራበት የሙያ መስክ ደንበኞችን እንዴት መያዝ እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል።

አንድ ቀን በዘርአይ ቤት እንዲህ ሆነ። በየጊዜው ቤቱን ከሚጎበኙ ደንበኞች መሀል አይቷቸው የማያውቅ እንግዶች ቡና ሊጠጡ ወደ እሱ ቤት ጎራ ይላሉ። እንግዶቹ በዛው ህንፃ ላይ ከሚገኝ አንድ ጸጉር ቤት ለመዋብ የመጡ ሁለት ሴቶች ነበሩ። እንደተለመደው አስተናጋጇ ቡናውን ከቁርስ ጋር አዘጋጅታ ለመቅዳት ተዘጋጀች። ትኩሱ ቡና ከመንቆርቆሩ በፊት ግን የሁለቱም እጆች ፈጥነው በስኒዎቹ ላይ አረፉ። ወዲያውኑም ቀጭኑን ትዕዛዝ አስተላለፉ።

ሴቶቹ እሷ በያዘችው ሳይሆን ቀይ ቀለም ባለው ስኒ ብቻ መጠጣት እንደሚፈልጉ ኮስተር ብለው ተናገሩ። ይህን ዕውነታ የሰማችው አስተናገጅ በሁኔታቸው ግራ ተጋባች። የደንበኞቹን ፍላጎት የተረዳው ዘርአይ ግን ምርጫቸውን በማክበር የፈለጉት እንዲሆን የፈቀደላቸው ወዲያውኑ ነበር። እንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች በንግድ ዓለም ለሚገኝ ሰው የደንበኞችን አያያዝ ለማወቅ እንደሚረዳ ወጣቱ ይናገራል። ዘርአይ የቀድሞ ማንነቱን የሚያውቁ በርካታ ሰዎች በቤቱ ሲስተናገዱ ይውላሉ። ስለማንቱ ያላቸው አክብሮትም ላቅ ያለ ነው። እሱም ቢሆን እንግዶቹን በመልካም ምግባር ተቀብሎ በፈገግታ ሲያስተናግድ መዋሉን ተክኖበታል። ብዙ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በአካባቢው ሴቶች ቡና ይልቅ የእሱ ገበያ መድራት ያስገርማቸዋል። በአድናቆትም ምክንያቱን ጭምር የሚጠይቁት አይጠፉም። የዘርአይ ምላሽ ግን ሁሌም ቢሆን የተለመደ ነው። «መልካም አቀባበልና ደማቅ ፈገግታ»

አንዳንዴ እንደ ስኒው የቀለም ምርጫ ሁሉ ቡናው ቀጠነ፣ አልያም ወፈረ ሲሉ የሚነጫነጩ ደንበኞች አይታጡም። የሙዚቃ ምርጫም በእነሱ ፍላጎት ብቻ እንዲሆን የሚሹ ጥቂቶች አይደሉም። ይህ ሲሆን ግን ሁሉንም እንደባህርይውና ፍላጎቱ ተቀብሎ ማስተናግድ ግድ ይላል። ዘርአይ ይህ ሥራ የገንዘብ ትርፍ ብቻ ሳይሆን የሰው ሀብትም አስገኝቶለታል። በውሎው የተለያየ ሙያ ካላቸው ሰዎች ጋር ይገናኛል። ክእነሱ የሚያገኘው ዕውቀትና ልምድም የበረከተ ነው።

ገና በአስራ ሁለት አመቱ እናቱን በሞት ያጣው ዘርአይ የቤተሰብ ፍቅር ሳስቶበት እንዳደገ ይሰማዋል። ያለፈበት አዳጋች የህይወት መስመርም በሌሎች እንዳይደገም የሚጨነቀው ከልቡ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ በስሩ ቀጥሮ ለሚያሠራቸው ሠራተኞች ስሜት እንዲጠነቀቅ ምክንያት ሆኖታል። ከእነሱ ጋር ያለው ግንኙነት የአሠሪና ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን ፍቅርና መከባበር የተመላበት ጭምር ነው።

ወጣቱ ዘርአይ ትላንት በጋዜጠኝነት ዓለም፤ ዛሬ ደግሞ በጀበና ቡና ንግድ ላይ ተሰማርቶ ህይወትን መምራት ቀጥሏል። በእሱ ዕምነት ግን አሁን ያለበት ሥራ የመጨረሻ ግቡ አይደለም። ወደፊት ደግሞ ካለበት ከፍ ብሎ ንግዱን ማስፋፋት ይሻል። ዘርአይ በጋዜጠኝነት ሙያ ከመሰማራቱ አስቀድሞ ከነበረው ልምድ በመነሳት የእግር ኳስ ተጨዋች እንደሚሆን የሚገምቱ በርካቶች ነበሩ።

ወደ ሚዲያው ከገባ በኋላም በሙያው ልቆ እንደሚገፋ ታምኖበት ነበር። ዛሬ ባለበት ሥራ ላይ እንዲህ ቢገኝም የነገ ዕቅዱ ወዴት እንደሚያደርሰው የሚወስነው ደግሞ በውሰጡ ያለው ጥንካሬ ብቻ ይሆናል። ሁሌም የሥራ ክቡርነትን የሚያምነው ዘርአይ ለሥራው ተገዢ ሆኖ ማገልገልን ለምዶታል። ማፅዳትና መጥረግ ካለበት ሌሎችን አይጠብቅም። ትላንት ብዕር የጨበጡ ጣቶቹ ዛሬ ለጉልበት ሥራም ሰንፈው አይታዩም።

ዘርአይን ተሰናብቼ ከዘመናዊው ህንፃ ወጣሁ። አይኖቼ መልሶ የጀበና ቡና ከደረደሩ ሴቶች ላይ አረፈ። ይህም ብቻ አይደለም። ከአንዱ ጥግ ተቀምጠው በቡታጋዝ ጭስ እየታወዱ ሻይቡናን አፍልተው በፔርሙስ ይዘው የሚዞሩትን ጭምር ተመለከትኩ። እንደ ወይዘሮ ዘሪቱ በላስቲክ ጎጆ እንደሚገኙትና እንደወጣቱ ዘርአይ ጽዱ በሚባል ሥፍራ እንዳሉት ሁሉ ከጎዳና የማይጠፉት እነዚህ ባለቡናዎች በሥራ ክቡርነት የሚያምኑ ናቸው። በተለይ የተመቻቸ የገበያ ቦታን ቢያገኙ የተሻለ ህይወትን ይመሩ እንደነበር ተሰማኝ። እነሱም በመልካም ፈገግታ ደንበኞቻቸውን «አርሂቡ» ማለትን ያወቁበታልና።

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።