ወጣቶች ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት

12 Oct 2017

 

12ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ የዩኒቨርሲቲ ጥሪን በመጠባበቅ ላይ የሚገኝ አንድ አዲስ ተማሪ በውስጡ ከፍተኛ ጉጉት እንደሚታይበት እሙን ነው፡፡ ለዚህ ጉጉቱ በምክንያት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከየከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለእረፍት ወደአካባቢያቸው የሚመጡ ተማሪዎች ስላሉበት ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሙ መረጃዎች ናቸው። በክረምቱ የእረፍት ጊዜ ከዩኒቨርሲቲያቸው የሚመለሱ ተማሪዎች ሁሌም የሚናገሩት በቅጥር ግቢው ውስጥ ስላለው አስደሳችና ምቹ ግንኙነት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣት ነው፡፡ ወደዚያ የሚያመራ ወጣትም ቶሎ ለመግባባት፣ ብሎም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር፣ ለመከራከርና ሐሳብን በነጻነት ለመለዋወጥ እድል ያገኛል። በዚህም በግቢ ውስጥ ቆይታቸው አገራቸውን ማወቅ እንደጀመሩ የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡

ተማሪ ኤልያስ አወቀ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ ተማሪው የ12ኛ ክፍል ፈተናን ጨርሶ የተመደበበትን ዩኒቨርሲቲ ካወቀ ቀን ጀምሮ እንቅልፍ ሁሉ አጥቶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ ስለዩኒቨርሲቲ ይሰማው የነበረው ሁሉ በጣም እንዲጓጓ አድርጎታል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ግጭትና ብጥብጥ ስለመኖሩ ሳይሆን የእርስበርስ ፍቅር እንዳለ፣ ክረምት እንኳን ሲለያዩ እንደሚላቀሱ ነበር ለእረፍት ከሚመጡ የአካባቢው ተማሪዎች ይረዳ የነበረው፡፡ እንቅልፍ ነስቶትና አጓጉቶት የነበረው የግቢ ህይወት የጠበቀውን ያህል እውነት ሆኖ አግኝቶታል፡፡ በቅጥር ግቢው ውስጥ ያገኛቸውን የቅርብ ጓደኞቹን ልክ አብረው እንዳደጉ አይነት አብሮነታቸው ጎልብቶ ቆይቷል።

እንደ ተማሪው አባባል፤ «ትንቯ ኢትዮጵያ» እየተባለ የሚጠራውን ዩኒቨርሲቲ እውነት ሆኖ አግኝቶታል፡፡ በግቢ ውስጥ ከሚደረጉ የባህልና የስነ ጽሑፍ መድረኮች እንዲሁም የተለያዩ ውድድሮች የብሔር፣ ብሔረሰቦችን አለባበስና አጨፋፈርና ባህልም ለማወቅ ችሏል፡፡ በማደሪያው ከሚጋራቸው ጓደኞቹም ሆነ ከክፍል ጓደኞቹ የጠበቀ የጓደኝነት ትስስር መፍጠር በመቻሉ በአገሪቱ ውስጥ ብዙ ዓይነት ባህልና ቋንቋ እንዳለ ለማወቅ እድልን ፈጥሮለታል።

ይሁንና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከዋናው ትምህርት በተጨማሪ በርካታ መልካም ነገሮችን መገበያየት የመቻሉን ያህል አልፎ አልፎ ደግሞ ረብሻ እንዳለ ነው ተማሪ ኤሊያስ የሚናገረው፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች በብሄር እንዲሁም በኃይማኖት ጎራ በመለየት በሚደረግ ተራ ክርክር ነገሩ ተጋግሎ ወደ ትልቅ ግጭት ይደርሳል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሉ አቋም የሚመስላቸው ተማሪዎች እንደማይጠፉም ነው የሚያመለክተው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግጭት የሚፈጠረው በኃይማኖትና በብሔር ብቻ እንዳልሆነም ይናገራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተማሪ ከዩኒቨርሲቲው ጋርም አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ በአካዳሚክ ጉዳዮች እንዲሁም በካፍቴሪያና መሰል ጉዳዮች ላይም ግጭት ሊከሰት እንደሚችል ይገልጻል። በተማሪና በግቢው አስተዳደር አለመግባባት ተፈጥሮ ተማሪው ወደ ድንጋይ ውርወራ ሊገባ የሚችልበትም አጋጣሚ መኖሩን አልደበቀም፡፡ ይህ አይነቱ ችግር ግን ከዩኒቨርሲቲው በቂ የሆነ ግንዛቤና ሥልጠና ካለመስጠት የሚመጣ ነው ብሎ ያስባል፡፡

ተማሪ አዳነ ጊቻን በበኩሉ እንደሚለው፤ ተማሪ ወደ ግቢ ሲገባ በቂ ሥልጠና መሰጠት አለበት፡፡ በተለይም ገና አዲስ የሚገባ ተማሪ በግቢ ውስጥ ያለ ነገር ሁሉ አዲስ ስለሚሆንበት መሰረታዊ የሆኑ ግንዛቤዎችን ቢያገኝ የተሻለ ነው። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ግን ይህ አይደረግም፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ ተማሪውን ሰብስቦ «እንኳን ደህና መጣችሁ» ብሎ መቀበሉ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ቢቻል እንኳን በግቢው ውስጥ ስለሚደረጉ አንዳንድ ጉዳዮች ቀርቶ ቢቻል የአካባቢውን ማህበረሰብ ማንነት ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ ተማሪው ዩኒቨርሲቲው ካለበት አካባቢ ማህበረሰብ ባህልና ወግ ጋር መተዋወቅ አለበት፡፡ ነገሮች ከፍተው በግቢ ውስጥ ግጭት እንኳን ቢከሰት ተማሪው በመጀመሪያ ሊያርፍ የሚችለው በአካባቢው ባሉ መንደሮች ነው፡፡ ስለዚህ ማህበረሰቡ ራሱ የዩኒቨርሲቲው አካል ነውና ተማሪዎችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ማስተዋወቅ ያልተለመደ ቢሆንም ቢሰራበት ውጤት ይኖረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እውቀት አስጨብጦ ከማስመረቅ ጎን ለጎን ልክ እንደወላጅ ሆኖ መቆጣጠር እንዳለበት የሚናገረው ተማሪ አዳነ፣ ግቢ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ወጣቶች በመሆናቸው ወዳልተፈለ ድርጊት እንዳይሄዱ ያስችላቸዋል ይላል። ይህ ቁጥጥር ከሌለ ግን ሊነሳ በሚችለው ቀላል ንትርክ እንኳ በቀላል መስታወት ወደ መሰባበር ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቅሰው አንዳንዴ በኃይማኖት እንዲሁም በብሄር አለመግባባት ሊኖር መቻሉን ነው፡፡ ስለዚህም ለተማሪው ወሳኝ የሆኑ ግንዛቤዎችን ማስጨበጥ መልካም መሆኑን ነው የተናገረው።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ ንጉሤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ እንደጠቀሱት፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ማስተዋወቅ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ነው ያለው፡፡ በግቢ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ከዚያ አካባቢ ሕዝብ ጋር መተዋወቅ አለባቸው፤ ባህሉንና የአኗኗር ዘይቤውን ሊረዱም ይገባል፤ ስለዚህም በተማሪዎች የተነሰዘረው አስተያየት ልክ መሆኑ ታምኖበት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡

ስለግቢው ግንዛቤና ሥልጠና በመስጠት በኩል ግን በየዓመቱ የሚደረግ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በየጊዜው ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የተማሪዎችን ጉዳይ በሚመለከት ደግሞ እርስ በእርሳቸው ችግራቸውን እንዲፈቱ እንዲችሉ የተማሪዎች ሕብረት ተቋቁሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ህብረት ተማሪዎች ችግሮቻቸውን አቅርበው መወያየትና መፍታት ካልተቻለም ወደሚመለከተው አካል መውሰድ የሚችሉበት ስርዓት መዘርጋቱን ያስረዳሉ፡፡ በአካዳሚክ ጉዳዮችም ሆነ በመመገቢያ እንዲሁም በማደሪያ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች የሚፈቱት በራሳቸው በተማሪ ተወካዮች ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ መመሪያዎችና ደንቦችን ሲያወጣ ደግሞ ከተማሪዎች ጋር በመወያየት ነው ይላሉ፡፡

አቶ ሄኖክ እንደሚሉት፤ በተለይም በዚህ ዓመት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሰፋ ያለ ሥልጠና ለማዘጋጀት አስቧል፡፡ ሥልጠናውም በዋናነት የሚያተኩረው በስነ ምግባር ላይ ሲሆን፣ ተማሪዎች ከግቢው አስተዳደርና መምህራን ጋር እንዴት መስራት እንዳለባቸው፣ ምን አይነት ደንብና ሥርዓት መከተል እንደሚጠበቅባቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሥልጠናው ለአንድ ሳምንት ያህል የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ኃይማኖትን በተመለከተ አቶ ሄኖክ ሲናገሩ፤ በግቢ ውስጥ ምንም አይነት ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴ መደረግ የለበትም ይላሉ፡፡ አገሪቱ የምትመራበት ሕገ መንግሥት ኃይማኖት ከትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት እንደሌለው የሚያመለክት መሆኑን ያስታውሳሉ፤ ተማሪዎችም መተዳደር ያለባቸው በሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የኃይማኖት ነጻነት ስላለም የትኛውም ተማሪ የሚፈልግበት የእምነት ተቋም ሄዶ የራሱን ሃይማኖታዊ ሥርዓት መፈጸም ይችላል፡፡ በግቢ ውስጥ ግን የሁሉም እምነት ተከታይ ስላለ አንዱ የአንዱን ማንኳሰስም ሆነ ኃይማኖታዊ ስርዓትን መፈጸም ከአንድ ጨዋ ተማሪ የማይጠበቅ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ «ይሁንና በዚህ በኩል ምንም ችግር አጋጥሞን አያውቅም፡፡ አልፎ አልፎ ችግሮች ቢፈጠሩም በሌሎች አለመግባባቶች እንጂ በኃይማኖት የተነሳ ግጭት ተፈጥሮ አያውቅም፤ ተማሪው በዚህ ላይ እርስ በእርሱ የተከባበረ ነው» በማለት ይገልጻሉ፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማተቤ ታፈረ እንደሚሉት፤ ገና ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ አዳዲስ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለነባር ተማሪዎችም ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ከተማሪዎች ጋር ውይይት ያደርጋል፡፡ ተማሪዎችም ያላቸውን ሀሳብ በማቅረብ ከተማሪዎች ሕብረት ጋር በመሆን ይወያያሉ፡፡

ተማሪዎች የአገራቸውንም ሆነ የአካባቢን ማህበረሰብ ለማወቅ በግቢ ውስጥ የእርስበእርስ መማማሪያ መድረኮች አሏቸው፡፡ የባህል ማዕከልና ሌሎች የስነ ጽሑፍ መድረኮች ላይ ልምድና ተሞክሯቸውን ይለዋወጣሉ፡፡ በኃይማኖትም ሆነ በብሄር በኩል የሚታይ ግጭት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አጋጥሞ አያውቅም። ተማሪዎች እርስበእርስ የመከባበር ባህሪም አላቸው፡፡ በአካዳሚያዊ ጉዳይም ይሁን በሌሎች አገልግሎቶች ተማሪዎች ቅሬታ ካላቸው ከራሳቸው በተመረጡ ተወካዮች አማካይነት ወደሚመለከተው አካል ደርሶ መፍትሔ ያገኛል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ከተማሪዎች ማስተዋል እንደሚቻለው የእርስበእርስ መከባበርና መፈቃቀር መኖሩን ነው፡፡ ለዚህም ነው የብዙ ሰዎች ትዝታ የዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቆይታ የሚሆነው፡፡ ይህ የሚሆን ግን በጥንቃቄ ሲያዝ ነው፡፡ የአገራቸውን ታሪክ፣ ወግና ባህል አውቀው የሚከባበሩና የሚፈቃቀሩ እንዳሉ ሁሉ በብሄርና በኃይማኖት የሚናቆሩም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ተምሬ አገሬን እጠቅማለሁ ከሚል አንድ ወጣት ግን የሚጠበቀው የአገሩን ዋና ህግ የሆነውን ህገ መንግስት ማወቅና መተግበር ሲችል ሲሆን፣ ለግጭት መነሻ ሆነው የሚነሱ ሐሳቦች ሁሉ በአግባቡ በእኩል ሁኔታ የተመለሰበት ሰነድ ነውና ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው።

 

ዋለልኝ አየለ

 

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።