ክብር ለደግነት

06 Dec 2017

 

በዕድሜ ዘመናቸው ለአገራቸውና ለህዝባቸው የሚችሉትን ሁሉ አድርገውና አበርክተው የአረጋዊነት ዘመን ላይ ሲደርሱ ሁሉም ጧሪ ቀባሪ ያገኛሉ ማለት አይቻልም። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ጎዳና ላይ መውደቅ የሰው እጅ አይቶ መኖር እጣ ፋንታቸው ይሆናል። በኢኮኖሚ በበለጸጉ አገራት እነዚህን የአገር ባለውለታዎች መንግስት እስከ መጨረሻው የዚህ ምድር ቆይታቸው ድረስ ይጦራቸዋል። እንደ እኛ ባሉ አገራት ደግሞ የመንግስተ እጅ ሲያጥር ግለሰቦች ያንን ሃላፊነት ሲወጡ ይታያል። የአዲስ ዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም በመቄዶንያ እየተደረገ ያለውን እገዛና የአረጋዊያኑን ህይወት እንዲህ ትነግረናለች።

 

ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በትምህርት የጎለበተው ማንነታቸው አቅማቸውን ሳይሰስቱ ለወገን የሚተርፍ አኩሪ ተግባርን እንዲከውኑ አስችሏቸዋል።ጊዚያቸውን በሙሉ ለስራና ለትምህርት መስጠታቸውም የግል ህይወታቸውን ቦታ ማጣበቡን ያውቁታል። ይህ ሀሳብ ግን ከያዙት ዓላማ እንዲያዘናጋቸው አይሹም ነበር።

ዛሬ ላይ ሆነው የትላንቱን ማንነታቸውን ሲያስቡት ከማይረሳ ትዝታ ውስጥ ይገባሉ።ህይወት በብዙ ብትፈትናቸውም ያለፉበትን አስቸጋሪ መንገድ ግን አማረውት አያውቁም። ዕድሜያቸው ቢገፋም ዛሬም የተለየ ብርታትና ጥንካሬ አብሯቸው ነው። አሁንም ቢሆን ከሳቸው የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው። አቶ ተከስተ ብርሀን መንክር።

ከዛሬ 45 አመታት በፊት በመምህርነት ሙያ ከተቀጠሩ ብርቱና ጎበዝ ምሁራን መሀል አንዱ ናቸው። በቀለም ትምህርት ዘልቀዋል የተባሉ በጣት በሚቆጠሩበት ዘመንም እሳቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ ችለው ነበር። ሁሌም መስራትና መማርን ልምድ ያደረጉት ጠንካራው ምሁር በወቅቱ ሚስት ማግባትና ልጆች ማፍራት እንዳለባቸው አላጡትም። ይህ ሀሳብ ግን ከያዙት መንገድ የሚያደናቅፍ ቢመስላቸው ቅድሚያውን ሁሉ ለትምህርትና ለተቀጠሩበት ሙያ ሰጥተው ዕድሜያቸውን በብቸኝነት ሊገፉ ግድ ሆነ።

አቶ ተከስተ በጀርመን ሀገር ለትምህርት በቆዩበት ጊዜ የተሻለ ልምድና ዕውቀትን አትርፈዋል።ይህ እውነታም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት እንዲሰሩ አስችሏቸዋል። አመታትን በሚወዱት ስራ ላይ ቆይተው በጡረታ ሲገለሉም እንደአብዛኞቹ እረፍትን አልፈለጉም። በዕውቀት የዳበረው አዕምሯቸውን ሊጠቀሙበት በመሻት ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው የግል ኢንቨስትመንቱን ፈጥነው ተቀላቀሉ።

ምሁሩ ተከስተ መምህርነትን ተሰናብተው ወደ ግል ስራ ሲገቡ አብረዋቸው ካሉ አጋሮቻቸው ጋር ግዴታቸውን ሊወጡ ግድ ነበር። ይህ ጥረትና ልፋት ግን እንዳሰቡት ሆኖ ፍሬ አላስገኘላቸውም። ሩቅ አሳቢው ተከስተ ይህ መሆኑ ሰላም ቢነሳቸው ብስጭትና እልህ አብሯቸው ውሎ አደረ። የዚህ ውጤት ደግሞ ጤና ነስቶ ከቤት ያውላቸው ጀመር። 31 አመታትን ከስኳር ህመም ጋር አብረው ቆይተዋል። እነዚህን ጊዚያት በጥንቃቄ ማሳለፋቸው ግን በሽታው ለከፋ ጉዳት ሳያጋልጣቸው እንዲቆይ አድርጓል።

አንድ ቀን ግን ሲመላለስባቸው የነበረው ህመም ክፉኛ ጸናባቸው። ውስጣቸው የቆየው ንዴትና ብስጭትም በሽታቸውን አባብሶ ከሆስፒታል ደጃፍ አደረሳቸው። ሁኔታቸውን የተረዱ ሀኪሞች ተሯሩጠው ሊረዷቸው ፈጠኑ። በዕለቱ የተደረገላቸው እርዳታ ነፍሳቸውን ከሞት ታደገው። የስኳር ህመሙ ከአቅም በላይ መጨመር ግን አንድ እግራቸውን ከመቆረጥ አላዳነውም።

ይህ ከሆነ በኋላ ጠንካራው ተከስተ ቤት ሊውሉ ግድ ሆነ። ከሁሉም በላይ ግን ብቸኝነት ችግራቸውን አባሰው። በቅርብ ተገኝቶ ህመማቸውን የሚጋራ የቅርብ ቤተሰብ ያለመኖሩም ሌላ መከራ ይሆናቸው ጀመር። ጠያቂ ዘመድ፣ አስታማሚ ሚስትና ልጆች የላቸውምና ጧት ማታ የጠያቂዎችን እጅ ናፈቁ። ባዶ ቤት ውሎ ማደርና የሰዎችን እጅ ማየቱም ብርቱውን ምሁር ሆድ አስባሳቸው።

ከጊዚያት በኋላ ከማዘር ትሬዛ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ለእንክብካቤ መግባታቸው መፍትሄ ሆኖ አገዛቸው። ይህ መሆኑ ለአንዳንዶች ቢያስገርምም ለብቸኛው ታማሚ ግን ትልቅ እፎይታ ሆነ። ተከስተ ያለፉበትን የህይወት መንገድ ቢያውቁትም ሁሉንም እንደ አመጣጡ ተቀብሎ «ተመስገን» ማለትን አልዘነጉም። እዛም ቢሆን ያላቸውን ዕውቀትና ችሎታ ለመለገስ ወደ ኋላ አላሉም። ድርጅቱን ሊጎበኙ የሚመጡ የውጭ ዜጎችን ከሰራተኞች ጋር በማግባባትና የትርጉም አገልግሎትን በመስጠት የአቅማቸውን ሲያበረክቱ ቆዩ።

በወቅቱ ስለማንነታቸው የሰሙ አንዳንድ ሰዎች ወደሳቸው ቀርበው ከልምዳቸው ይካፈላሉ። ሁሌም ዕውቀታቸውን ለማጋራት የማይሰስቱት መምህርም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሌሎችን ለመርዳት ይበረታሉ። ከቀናት በአንዱ ቀን ደግሞ ስለሳቸው የሰሙ ሰዎች ቀርበው አነጋገሯቸው። ካሉበት ስፍራ ወጥተው እነሱ ወዳሰቡላቸው ቦታ ቢሄዱም የተሻለ መሆኑን አማከሯችው። ተከስተ ይህን ሲሰሙ የተባሉትን ለማድረግ ፈቀዱ። ከጊዚያት በኋላም የሜቄዶኒያን የበጎ አድራጎት ድርጅትን ተቀላቀሉ።

ዛሬ አቶ ተከስተ ብርሀን በሜቄዶኒያን አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ አመታትን አስቆጥረዋል። በስኳር ህመም ጉዳት የደረሰበት አንድ እግራቸውም ሰው ሰራሽ አካል ተገጥሞለት እንደበፊቱ ይራመዳሉ። በድርጅቱ ውስጥም የአረጋውያን ጉዳይ አስፈጻሚና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ያገለግላሉ። አሁን እንደቀድሞው ጥንካሬና የተለየ ብርታት ከፊታቸው ይነበባል።

ዛሬ የትላንቱን ማንነታቸውን እያስታወሱ ማዘንና መቆዘም ልምዳቸው አይደለም። እንደሳቸው ዕምነት በህይወት አጋጣሚ መፈተን መልካም የሚባል ነው። ሁሉን አልፎ ለለአሸናፊነት መብቃት ደግሞ ለሌሎች ጭምር ታላቅ ተስፋ ይሆናል። ከምንም በላይ ግን በዕድሜ የገፉና የአዕምሮ ሀሙማንን በአቅማቸው መርዳታቸው ያስደስታቸዋል። ይህ አጋጣሚም ቀሪውን ህይወታቸውን ለበጎነት እንዲያውሉት ምክንያት ሆኗልና ለውስጣቸው የተረፈው ሀሴት የተለየ መሆኑን አዛውንቱ ተከስተ በኩራት ይናገራሉ።

አቶ ተሾመ ወርቁ በሜቄዶንያ መርጃ ማዕከል የመገኘታቸው ምክንያት ያጋጠሟቸው ተደራራቢ የህይወት ፈተናዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ከአመታት በፊት ለእስር የተዳረጉበት አጋጣሚ ቆይቶ ነጻ ቢያወጣቸውም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመለያየት ግን ሰበብ ነበር። ይህ እውነታም ቀሪውን ጊዚያቸውን በብቸኝነት እንዲገፉ ማስገደዱ አይቀሬ ሆኗል።

አቶ ተሾመ ለረጅም አመታት ያገለገሉበት መስሪያቤት ሲፈርስ ለራሴ የሚሉት ጥሪት አልነበራቸውም። ከእስር ከተፈቱ በኋላም የቤተሰቦቻቸው መበታተን ለከፋ ችግር ዳርጎ ሲያንገላታቸው ቆይቷል። ጤና በነበሩ ጊዜ ራቅ ወዳለ አካባቢ ተጉዘው ለመስራት ሞክረዋል። ውሎ አድሮ በአይናቸው ላይ የደረሰው ህመም ግን እንዳሻቸው እንዳይሆኑ እንቅፋት ፈጠረባቸው።

አስቀድሞ በአንደኛው አይናቸው ላይ የነበረ ጉዳት ቆይቶ ወደ ሌላው አይናቸው ተዛመተ። ይህም የጤንነታቸው ጉዳይ አሳሳቢ አደረገው። ይባስ ብሎ ብርሀናቸው ጨለመና አይኖቻቸው ታወሩ። ይሄኔ ተሾመ እጅግ ግራ ገባቸው። የሚመራ ልጅ የሚሰበስብ ቤተሰብ የላቸውምና በጭንቀት ተዋጡ። የዛኔ ተለይተዋቸው በነበረ ጊዜ ሚስት ለስደት ልጆችም ለመበታተን ተዳርገዋል። በመሀላቸው የነበረው የአመታት ክፍተትም ከልጆቻቸው ጋር ዳግም ሊያግባባቸው አልቻለም።

የትላንቱ ታታሪ የአሁኑ አይነስውር ጎልማሳ አሁን የሰዎችን እጅ ሊያዩ ግድ ሆነ ። በየቀኑ የሌሎችን እገዛ መናፈቃቸውም ከተረጂነት ላይ ጣላቸው። ተከራይተው ለሚኖሩበት ጠባብ ቤት ኪራይና የዕለት ቀለብ ከሚያውቋቸው እየለመኑ ማሟላት ግድ ሆነባቸው። ይህ ብቻውን ግን መፍትሄ ሆኖ አላዘለቃቸውም። ርቆ ለመሄድና ተንቀሳቅሶ ለመስራት ችግር ቢሆንባቸው አንድ ቀን ሲያስቡት የከረሙትን ሊፈጽሙ ከቤት ርቀው ዋሉ።

ወደ ሜቄዶኒያ የአዕምሮና የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ሲደርሱ ማንነታቸውን ያዩ በጎ ሰዎች አቅፈው ተቀበሏቸው። ችግራቸውን ከስር መሰረቱ ሲያስረዱም መስሚያ ጆሮዎችን አላጡም። በዕለቱ ተቀባዮቻቸው በቀጠሮ ሲሸኟቸውና ወደመጡበት ሲመለሱ ግን አሉበት ደርሰው ይጎበኙኛል የሚል ዕምነት አልነበራቸውም።

አሁን አቶ ተሾመ በማዕከሉ አምስት አመታትን በኑሮ አሳልፈዋል። ምንም እንኳን አይኖቻቸው ከብርሀን ጋር ቢራራቁም በተለያዩ ሙያዎች ቆይተዋልና የአቅማቸውን ለማበርከት አልተቸገሩም። ህይወት በተለያየ አጋጣሚ ፈትና እዚህ ብታደርሳቸውም በማዕከሉ የሚገኙና በአዕምሮ ህመም ያሉ ሌሎችን ሲመለከቱ ከእሳቸው የሚጠበቀውን ለማድረግ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም።

ምንግዜም ሰዎች መልካም ለመስራት ካሰቡ ሁኔታዎች ምክንያት እንደማይሆኗቸው ያምናሉ። ለዚህም ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው የሚለው አባባል ይገዛቸዋል። በማዕከሉ ያለው እውነታም ይሄው ነው። ሰዎችን ከወደቁበትና ከተረሱበት አውጥቶ ዳግም ህይወት የሚዘራበት አለም። እሳቸውንም ለዚህ ላበቃቸው የድርጅቱ መስራች ወጣት ክቡር ዶክተር ቢኒያም.. ያላቸው ምስጋና ከልብ የመነጨ ነው።

ሁለቱን የሀገር ባለውታዎች ያገኘኋቸው በቅርቡ በዋቢሸበሌ ሆቴል ጋርደን አዳራሽ ተከፍቶ በነበረውና «ክብር ለደግነት» በሚል በተሰየመው የኤን ጂኦ እና ቻሪቲ ኤክስፖ መክፈቻ ላይ ነበር።የሜቄዶኒያ መርጃ ማዕከልን ጨምሮ በርካቶች የተሳተፉበት ይህ የሶስት ቀናት ኤክስፖ የበጎ አድራጎት ተቋማት ለአገራችን፣ለአህጉራችንና ለዓለማችን እያደረጉ ያለውን በጎነት ለማመልከት ሲባል የተዘጋጀ ነው።

የኤክስፖው አዘጋጅ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ወልደገሪማ እንደሚሉትም የኤክስፖው መዘጋጀት ዋንኛ ዓላማ በጎ የሚሰሩ ድርጅቶችን መልካምነት ለማሳየትና የእነሱን መርህ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚቻልበትን አቅጣጫ ጭምር ለማመላከት ነው። ለወገን ደራሽነታቸውን በተግባር ያሳዩ ወገኖችን ምግባር ለማስመስከር የኤክስፖው ገጽታ አንድ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስም በክብር ለደግነት ኤክስፖ ላይ ከስልሳ ያላነሱ ተቋማት ተሳትፈዋል ብለዋል።

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።