የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በወጣቶች አንደበት

07 Dec 2017

 

ዩኒቨርሲቲ ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› እየተባለ የሚጠራበት ዋነኛ ምክንያት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ የለተያየ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህል ያላቸው ወጣቶች በአንድ ቦታ ላይ ስለሚገናኙበት ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለያየ ጊዜ እንዳሉትም ኢትዮጵያን ማየት የሚጀምሩት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው፡፡ የአገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ወግ ማወቅ የሚጀምሩት ዩኒቨርሲቲ እዚያ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያላቸው ቆይታ በሙሉ ከተለያዩ ብሄርብሄረሰቦች ጋር ቢሆንም ከዚህ በበለጠ ደግሞ ህዳር 29 ሲመጣ አንድ ልዩ ትዕይንት ይፈጥራል፡፡ በግቢው ውስጥ የብሄርብሄረሰቦች ቀን ይከበራል፡፡ ይህን የብሄርብሄረሰቦች ቀን የሚያከብሩት ራሳቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ የየራሳቸውን ባህና ወግ የሚያሳይ አልባሳት የለበሱ ወጣቶች የተለያየ ትርዒት ያሳያሉ፡፡ ይህ ነው ወጣቶችን አገራቸውን እንዲያውቁ የሚያ ደርጋቸው፡፡

ወጣት ተመስገን አሰፋ ይባላል፡፡ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ አሁን በሥራ ላይ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በነበረው የሦስት ዓመት ቆይታ ይከበር የነበረው የብሄርብሄረሰቦች ቀን ብዙ ነገር እንዲያውቅ አድርጎታል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት የተለያዩ የአጨፋፈርና የአለባበስ ባህሎችን በተለያየ አጋጣሚ ቢያይም የትኛው የየትኛው እንደሆነ አያውቅም ነበር፡፡ የብሄርብሄረሰቦች ቀን በሚከበርበት ጊዜ ግን ከነማብራሪያው የትኛው የየትኛው ብሄር እንደሆነ ማወቅ አስችሎታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ጭራሽ እስከመኖ ራቸውም የማያውቃቸው ባህሎችን ማወቅ ችሏል፡፡ በታሪክ መጻሕፍት ላይ ብቻ ስማቸውን ተጽፎ የሚያውቃቸውን ብሄር ብሄረሰቦች በአካል ማየት አስችሎታል፡፡ የክፍልና የማደሪያ ክፍል ጓደኞቹም ከተለያየ ብሄር የመጡ ስለሆነ በግቢው ውስጥ የማያውቀው ነገር ሲመለከት እነርሱን ይጠይቅ ነበር፡፡

ቋንቋን በተመለከተም ተመስገን አንድ ነገር ያስታውሳል፡፡ ከአንድ ቋንቋ ውስጥ እንኳን የተለያየ ዘዬ አለ፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆነው ግን የተለያየ ዘዬ ያላቸው አሉ፡፡ ይህ የዚህ አካባቢ ነው ይህኛው የዚህ ነው የሚለውንም ለማወቅ አስችሎታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች ቋንቋዎችን ማወቅ ችሏል፡፡ ቋንቋውን መናገር ባይችል እንኳን ቢያንስ ያ ቋንቋ የማን እንደሆነ ማወቅ ይችላል፡፡

ከግቢ ተመርቆ ከወጣ በኋላ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ሲያይ ዩኒቨርሲቲን ነው የሚያስ ታውሰው፡፡ ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት የቻለው ግቢ ውስጥ ስለሆነ፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ በመገናኛ ብዙኃን እንጂ እንደያኔው የተለያዩ ብሄርብሄረሰቦችን በአንድ ጊዜ አንድ ቦታ ማግኘት አይችልም፡፡ መሪ ቃሉንና ህብረ ዝማሬውን በሰማ ቁጥር ግቢ ውስጥ የነበረው ትዝ ይለዋል፡፡ አሁን ላይ የትኛው አለባበስ፣ አጨፋፈርና ቋንቋ የየትኛው እንደሆነ ማወቅ የቻለው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በነበረው ቆይታ ነው፡፡

ሌላኛዋ ወጣት መድኅን አብርሃለይ ትባላለች፡፡ በ2005 .7ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በባህርዳር ሲከበር የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ነበረች፡፡ በግቢው ውስጥ ባለው የባህል ማዕከልም ተሳታፊ ነበረች፡፡ እንዲህ የብሄርብሄረሰቦች ቀን በሚከበርበት ጊዜ ደግሞ ልዩ ዝግጅት በማድረግ የተለያየ ትርዒት ያሳያሉ፡፡

የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ እዚያ ነበር የተመለከተችው፡፡ የያኔው አከባበር ለመድኅን በብዙ ምክንያት ልዩ ትውስታ ነበረው፡፡ የብሄርብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ያየችው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ ቀኑ የተከበረውም እሷ በምትማርበት ባህርዳር ነው፡፡ የበዓሉ ታዳሚ ሳይሆን ተሳታፊ ነበረች፡፡ በምትሳተፍበት የባህል ማዕከል ውስጥ የብሄርብሄረሰቦች ቀን ሲደርስ አባላቱ የየራሳቸውን ብሄር ወክለው እንዲያሳዩ ሲደረግ እሷ የትግራይን ወክላ ተሳትፋ ነበር፡፡

እሷ የትግራይን ባህል ወክላ ስትሳተፍ ጓደኞቿም የየራሳቸውን ወክለው ሲሳተፉ፤ በዚህ ውስጥ በሚደረገው የረጅም ጊዜ ዝግጅት ውስጥ ብዙ ነገር እንድታውቅ አስችሏታል፡፡ ወደግቢ ከመግባቷ በፊት እንኳን የሌሎችን ብሄሮች የራሷ የሆነውን የትግራይን እንኳን ብዙ የማታውቀው ነገር ነበረው፡፡ በሚደረገው ዝግጅት ውስጥ ግን ብዙውን ነገር አጠናች፡፡ በዚህም ብዙ ነገሮችን ማወቅ ቻለች፡፡

በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች እንዲያከብሩት መደረጉ አገሪቱ ‹‹የበርካታ ብሄርብሄረሰቦች አገር ናት›› የሚለውን በተግባር እንድታይ አድርጓታል፡፡ በግቢ ውስጥ የምታያቸው ተማሪዎች በበዓሉ ላይ ሲሳተፉ የትኛው ብሄር እንደሆኑ ለማወቅ አስችሏታል፡፡ የባህል ልብስ ለብሰውና ተውበው ይታያሉ፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የብሄርብሄረሰቦች ቀን መከበሩ አንድ ሌላ አስተዋፅዖ እንዳለውም ታምናለች፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘው አብዛኛው ወጣት ነው፡፡ ለተለያየ ዘመናዊ ባህል ተጋላጭ ነው፡፡ ለምሳሌ በአለባበስ ብዙ ከአገር ወግና ባህል ጋር የማይሄዱ የአለባበስ አይነቶች ይታያሉ፡፡ ይህ የሆነው ወጣቶች ብዙም የአገራቸውን አኩሪ ባህሎች ስለማያዩና ስለማያውቋቸው ነው፡፡

እንዲህ የብሄርብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ግን ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ ማየት ይችላሉ፡፡ ከውጭ ተኮርጆ ከሚለበሰው በላይ ውበት እንዳለው ያምናሉ፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ያሉ የአለባበስ፣ የአጨፋፈርም ሆነ የቋንቋ ውበቶችን ሲያዩ አገራቸው ምን ያህል የታደለች እንደሆነች ማየት ያስችላል፡፡

በሌላ በኩል የብሄርብሄረሰቦች ቀን ህገመንግ ስታዊ ስርዓቱንም እንድታውቅ አድርጓታል፡፡ በራስ ቋንቋ መናገር፣ የራስን ሃይማኖት መከተል፣ የራስን ባህል ማዳበር የሚያስችል ሥርዓት እንደሆነ ያሳያል፡፡ በርካታ ብሄርብሄረሰቦች ተፋቅረውና ተቻችለው ሲኖሩ ያሳያል፤ ህብረብሄራዊ አንድነት ምን እንደሆነ በተግባር ያመላክታል፡፡ ወጣቶች በንድፈ ሀሳብ የሚማሩትን የታሪክ እና የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በተጨባጭ የሚያዩበት ሆኖ አግኝታዋለች፡፡

ወጣት መድኅን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የብሄርብሄረሰቦች ቀን ልዩ ትውስታ ይፈጥርባታል፡፡ በ2005 .ም ባህርዳር ላይ በተከበረው ተሳታፊ ስለነበረች ቀጥሎ ባሉት ዓመታትም በግቢው ውስጥ ሲከበር የድርሻዋን ታበረክት ነበር፡፡ በተለይም በሚደረገው ዝግጅት ውስጥ የአካባቢውን ባህል እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡ በአካባቢው ካሉ ሰዎች የአልባሳትና የተለያዩ ቁሳቁስ መዋዋስ ነበር፡፡ ማህበረሰቡም የተለያዩ አልባሳት ለብሰው ሲያይ ‹‹ይህ የማነው›› እያለ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ውስጥ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማሳወቅም ይኖራል፡፡

መድኅን ከግቢ ውስጥ ከወጣች በኋላ ህዳር 29 በመጣ ቁጥር ብዙ ነገር ያስታውሳታል፡፡ በየዓመቱ ሲከበር የሚኖረውን መሪ ቃል፣ በዓሉ ሲከበር የታዩ ነገሮችን፤ ለምሳሌ በመቀሌ ሲከበር እንደነበረው ጀበና እና በባህርዳር ሲከበር እንደነበረው መሶብ አይነት ነገሮችን በጉጉት ትጠባበቃለች፡፡ በሚከበርበት ከተማ ውስጥ የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ያችን ከተማ እንድታውቃት ያደርጋታል፡፡ ከተማዋን ከዚህ በፊት በስም ብታውቃትም እንዲህ የብሄርብሄረሰቦች ቀን የሚከበርባት ሲሆን ደግሞ ብዙ ነገር ስለሚባልላት ስለከተማዋ ብዙ ታሪካዊ ዳራ ይወራል፡፡

ተማሪ ደምሰው አበራ ባለፈው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባ ሲሆን ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በሚማርበት ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች ያከበሩትን የብሄርብሄረሰቦች ቀን ያስታውሳል፡፡ እንደሌሎች ወጣቶች ሁሉ እሱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ያሉ ብሄርብሄረሰቦችን ታሪክ፣ ባህልና ወግ ማወቅ ያስቻለው እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው፡፡

ተማሪ ደምሰው በዚህ ዓመት የሚከበረውን የብሄር በሄረሰቦች ቀንም ለማየት እየጠበቀ ነው፡፡ የባህል ማዕከል ተማሪዎች ከሚያደርጉት ዝግጅት ጀምሮ በህዳር 29 ሰሞን ባሉት ቀናት ሁሉ የአገሩን ባህልና ወግ የሚያሳዩ ነገሮችን ያስተውላል፡፡

እንዲህ አይነቱ አከባበር በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ትምህርት ቤቶችም መከበር እንዳለበትና ተማሪዎች የየአካባቢያቸውን ባህል ማወቅ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲሆን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡት ስለሚበዙ ልዩ ትኩረት ቢስብም በአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ተማሪዎችም የየአካባቢያቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡

የአገራቸውን ታሪክ ወግና ባህል ማወቅ የጀመሩት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደሆነ ብዙ ወጣቶች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ይህ አይነት አከባበር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ለዚህ የሚያግዙ አስፈላጊ ነገሮችን መሟላት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ የባህል አልባሳትና የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎች እጥረት እንዳያጋጥም መስተካከል አለበት፡፡ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ አገራቸውን አውቀው መውጣት አለባቸው፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።