«ከፈተና ጀርባ ድል መኖሩን ማንም ሳይዘነጋ ይሥራ፤ ሌሎችንም ያስብ»- ኢንጅነር በረከት ሰብስብ Featured

13 Jan 2018

ወዳጅ ከዘመድ የሚሰባሰብበት፣ የሩቁ ከቅርብ የሚገናኝበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ቂም የያዘ ቂሙን የሚረሳበት ቀን አውደ ዓመት ነው። ስለዚህም በዚህ ቀን በህይወት እንዲህ ናት አምዳችን ላይ አንድ እንግዳ ይዤላችሁ እቀርባለሁ። እንግዳዬ ደግሞ የገጠሩን የገና አከባበር ሁኔታ ያለፉበት ስለሆነ በሚገባ ያወጉናል። ይሁንና ዋናው ቁም ነገሩ ግን በህይወታቸው ያለው ምርጥ ተሞክሯቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
እንግዳዬን ሥራ ስለሚበዛባቸው ባሰብኩት ሰዓት ለማግኘት ከባድ ቢሆንም፤ ካላቸው ሰዓት ላይ ሸርፈው እንዲሰጡኝ ስጠይቃቸው ምንም አላቅማሙም ነበር። እናም በተባባልነው ሰዓት ወደ እኔ ቢሮ መጥተው የህይወት ተሞክሯቸውን አጫውተውኛል። እኔም ከዚህ ተሞክሯቸው ተቋደሱ ስል እንዲህ አቀረብኩላችሁ። መልካም ንባብ።
በፈተና የታጀበው ልጅነት
እንግዳዬ ኢንጅነር በረከት ሰብስብ ይባላሉ። የተወለዱት በጉራጌ ዞን ኧዥያ ወረዳ ቦነ ቀበሌ ውስጥ ነው። አባታቸው፣ እርሳቸው ከመወለዳቸው በፊት ከተለያዩ ሚስቶቻቸው 11 ልጆችን አፍርተው ሁሉም ይሞታሉ። ስለዚህም ተስፋ ቆርጠው ለብዙ ጊዜ ተቀመጡ። ይህ በእንዲህ እንዳለ አባታቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ተወዳጅና የሚከበሩ ስለነበሩ ብቻቸውን መሆን እንደሌለባቸው ታመነ። በዚህም የተሻለችና እርሳቸውን ታስከብራለች የሚሏትን ልጅ መርጠው ዳሩላቸው። የዛሬው እንግዳየየም ከዚህ ትዳርም የተገኙ ፍሬ ናቸው፡፡
አባትዬው ግን ዓይናቸውን ከልጃቸው ዓይን ላይ ሳይነቅሉም በውስጣቸው ከዛሬ ነገ ልጄ ይሞትብኛል ሲሉ በሰቀቀን ዓመት አሳለፉ፡፡ ያልታደሉት እንግዳዬ ግን ከዓመት የቁልምጫ ቆይታ በኋላ በእናት እጅ የማደግ እድሉን ተነፈጉ። በዓመታቸው እናታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ይህ ደግሞ ለአባታቸውም ሆነ ለእንግዳዬ ከባድ ፈተና ፈጠረባቸው። ለጨቅላው በረከት ጡት የሚያጠባና የሚንከባከብ እናት ጠፋ። አባትዬውም ቢሆኑ የልጅ አስተዳደግ ወጉን በቅጡ አያውቁም። ነገር ግን ምንም ቢሆን ቤተሰብ አይጥልምና እህታቸው ወስዳ እንድታሳድጋቸው ጠየቀቻቸው። እርሳቸው ግን ይሞትብኛል በሚል ስጋት ለጊዜውም ቢሆን በእንቢታቸው ጸኑ። ከዚያ ማሳደጉ ሲከብዳቸው መስጠቱን አማራጭ አደረጉ። እየተመላለሱ መጠየቃቸው ግን አልተቋረጠም። ነገሩ ሳይደግስ አይጣላ ሆነና የእንግዳዬ አክስት መሀን ስለነበሩ ልጅ የማይቦርቅበት ቤታቸው ልጅ አገኘ። እንግዳዬም የላም ወተት እየጠጡም አደጉ። እርሳቸውም ማንነታቸውን ሳይረዱ አክስታቸውን እማዬ የአክስታቸውን ባል ደግሞ አባዬ ማለት ጀመሩ።
እየተመላለሰ የሚጠይቃቸውም አባታቸው ሳይሆን አጎታቸው ይመስላቸው ነበር። በኋላ ግን ይህ አባታቸው መምጣት አቆመ። ምክንያቱ ደግሞ የባለቤታቸውን ሞትና የልጃቸውን ከዓይናቸው መራቅ በማሰላሰል በሀዘን ተጎድተው ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በመሞታቸው ነው። አንድ ቀን ግን ያሳደጓቸው አክስታቸውን እንጂ እናታቸው እንዳልሆኑ በመስማታቸው ወደቤት ሲገቡ የማንነት ጥያቄ አነሱ፡፡ በወቅቱ አክስቲቱ እጅግ ከፋቸው፤ ምን አጎደልኩብህ በሚልም አዘኑ። ነገር ግን መጠጊያ የሌላቸው እንግዳዬ በይቅርታ ከማለፍ በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ሲገነዘቡ ይቅርታ ጠየቁና አለፉት፤ ድግስ ተደግሶም ጸቡ እንዲበርድ ተደረገ።
«እኔ እድለኛ አይደለሁም፤ በመጀመሪያ እናቴን ቀጥሎ ደግሞ አባቴን አጣሁ። ከዚያ ደስተኛ ሆኜ መማርና ተሞላቅቄ መኖር ስጀምር አክስቴን ሞት በሚባለው ጉድ በማይታወቅ ምክንያት አጠኋት» ሲሉ እንባ በተቀላቀለበት ስሜት የሚናገሩት እንግዳችን፤ አክስታቸው የጓደኛዋ ሰርግ ላይ ለመታደም ወንዝ አቋርጣ ለመሄድ ስትነሳ እርሳቸው አብረው መሄድ እንደሚፈልጉ ቢናገሩም የሚሰማቸው አጡ። ከዚያም አደራውን ለሌላኛዋ እህታቸው ሰጥተው ልጄን ጠብቂ በማለት ጉዟቸውን ቀጠሉ። ከዚያ በኋላ ግን አልተመለሱም።
እንግዳዬ ማታ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚናፍቋት እናታቸው(ያሳደገቻቸውን አክስት ማለት ነው) መምጣቷን ይጠይቃሉ፤ አልመጣችም የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። ሁለት ቀን ሦስት ቀን ሆነ፤ አክስትዬዋ ግን የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ። ግራ ተጋቡ። ከዚህ በኋላ ግን እርሷን ማጣት እንደሌለባቸው ስላመኑ ፍለጋ ጀመሩ፤ ሊያገኟት ግን አልቻሉም። ስለዚህም ተስፋ ቆረጡ፤ አሁን ድረስም በምን ምክንያትና የት እንደደረሰች፤ ምን እንደሆነች አያውቁም። ግምታቸው ግን በወቅቱ ወንዙ ሞልቶ ስለነበር ወስዷት ይሆናል የሚል ነው። በዚህ ምክንያትም ያለቻቸውን እናት አጥተው ተቀመጡ።
አሁን የሌላኛው ቤት ምዕራፍ ተጀመረ። ሰውን መቅረብ ፈሩ፤ ሁሉንም ሰው በእርሳቸው እድለቢስነት የሚያጡት መሰላቸው። ነገር ግን አደራውን የተቀበለችው ሌላኛዋ አክስታቸው የእርሳቸው ነገር ያሳስባታልና ትንከባከባቸዋለች። ባልዬው ደግሞ የእርሳቸው እዚህ መሆን ሥራውን ስለሚያቀልለት ተመችተውታል። ከአቅማቸው በላይም ያሰራቸዋል፤ ሆኖም አልተከፉም። ምክንያቱም ሥራ ይለምዱበታል፤ ከሰውም ጋር የሚተዋወቁበት አማራጭን ይፈጥርላቸዋል። በዚያ ላይ ትምህርታቸውን በሚገባ እየተከታተሉ ናቸው። ስለዚህ አንድ ቀን በራሳቸው እንደሚቆሙና የራሳቸው አላማን እንደሚያሳኩ ስለሚረዱ የተባሉትን ያደርጋሉ።
የትምህርት ጅማሮ
የዛሬው ኢንጅነር በረከት፣ ትምህርትን መማር የጀመሩት የመጀመሪያዋ እናት (አክስታቸው) ዘንድ ሲሆን፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ያለምንም ውጣ ውረድና ችግር ተምረዋል። ይህ ግን ሌላ ችግር ፈጥሮባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የተሻለና ጎበዝ ተማሪ በመሆናቸው በወራት ውስጥ ከአንዱ ክፍል ወደ አንዱ ክፍል መዘዋወራቸው ብዙዎችን አስቆጥቷል። ለእንግዳዬ የትምህርቱ ሁኔታ ከእርሳቸው እውቀት በላይ አልነበረም። ስለዚህም መምህሮቹ እንዲዛወሩ ሲያደርጓቸው በየክፍሉ እንቅፋት የሚሆን አንድ መምህር ይቃወማቸዋል።
በአንድ ዓመት ዝውውር አራተኛ ክፍል ሲገቡ አንድ የሚያስተምራቸው መምህር አትችልም ብሎ ወደ ሦስተኛ ክፍል ይመልሳቸዋል። ምክንያቱ ግን የእርሳቸው አለመቻል ሳይሆን የሰውየው ልዩ ባህሪ ነው። ይሁንና በመብታቸው ላይ ለሚመጣው ነገር የማይደራደሩ ስለነበሩ ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ ርዕሰ መምህሩ ይጓዛሉ። ርዕሰ መምህሩም ይህንን ያደረገውን መምህር ሲጠይቁ አይችልም ተባሉ። ከዚያ የወሰዱት አማራጭ አራተኛ ክፍል ያሉትን ተማሪዎች በሙሉና እርሳቸውን ጨምሮ ፈተና እንዲወስዱ አደረጉ። በዚህ ደግሞ እንግዳዬ ሁሉንም መቶ አመጡ። ይህ ደግሞ በአራተኛ ክፍል ተማሪነታቸው እንዲቀጥሉ አስቻላቸው።
በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ተደጋጋሚ ፈተና የገጠማቸው ኢንጅነር በረከት፤ ሁሉንም ወደ ጎን በመተው ትምህርታቸው ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር። ይህ ደግሞ እስከመጨረሻው በትምህርታቸው ታታሪና ውጤታማ እንዲሆኑ አግዟቸዋል። በተለይም የአክስታቸው ሞት ከተሰማ በኋላ የሚፈትናቸው ነገር ቢበራከትም ተስፋ አለመቁረጣቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዴት እንደሚሆኑ አስተምሯቸው ያለፈ መሆኑን ያስረዳሉ።
ስድስተኛ ክፍል እያሉ ታታሪ ነጋዴና ታታሪ ተማሪ ሆነው እንደነበር የሚያወሱት ባለታሪኩ፤ ከሰኞ እስከ አርብ ትምህርታቸውን በአግባቡ ከተከታተሉ በኋላ አርብ ከዘጠኝ ሰዓት ተኩል በኋላ እስከ እሁድ ማታ ድረስ ዶሮ በጀርባቸው እየተሸከሙ ስድስት ሰዓት በእግራቸው በመሄድ ይነግዱ እንደነበርም አጫውተውኛል። በሂደትም ስለሳባቸውና ትርፋማም ስላደረጋቸው ትምህርታቸውን ወደ ጎን ተውት። በዚህ ደግሞ የመጀመሪያ ሴሚስተር ላይ ከ44 ልጅ 44ኛ ወጡ። ይህ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ትምህርታቸው ላይ የሚያጠላው ነገር ኃይለኛ መሆኑን ስለተረዱ ቶሎ ብለው ማንበብ ላይ ትኩረታቸውን አደረጉና ሰራቸውን በከተማ ብቻ ማከናወን ጀመሩ። በእርግጥ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ የራሳቸውን ህይወት ራሳቸው ለመምራት ከአክስታቸው ቤት ለቀው ነበር። እናም ትኩረታቸው ለትምህርት በመሆኑ ሁለተኛ ሴሚስተር ላይ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ወደሚቀጥለው ክፍል ተዘዋወሩ።
እንግዳዬ ኢንጅነር በረከት እስከ ስምንተኛ ክፍል በዚህ ሁኔታ ነበር ትምህርታቸውን የተከታተሉት። የሚኒስትሪ ፈተናም ከፍተኛ ውጤት ካመጡት መካከል አንዱ ሆነዋል። በወቅቱ እንደሚደረገው መምህር ለመሆን እንዲሰለጥኑ ወደ ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተወሰዱ። በዚያም ለስድስት ወር ትምህርታቸውን ተከታተሉ። በዚህ ወቅትም ቢሆን እንግዳዬ ጎበዝ ተማሪ ነበሩና ጠመንጃ እስከመስራት ደርሰው ነበር። ተሞክሮም ውጤታማ በመሆኑ ከጃንሆይ የትምህርት እድል ተበርክቶላቸዋል። ሆኖም ችግር ተከትሏቸው እየተጓዘ ስለነበር ሳይሳካላቸው ቀረ።
ትምህርት እድሉ ይሰጠኛል በሚል አንድ ዓመት አሳለፉ። ወይ መምህር ወይ ተማሪ ሳይሆኑ መሀል ላይ ችግር ገጠማቸው። ከዚያ ግን መስራትና መብላት ስላለባቸው ወደ ተመደቡበት ሊሙ ገነት ተጓዙ። በዚያ ሲደርሱ ግን ምንም አይነት የትምህርት መሳሪያም ሆነ ትምህርት ቤት አልነበረም። ምን ውስጥ እንደሚያስተምሩ ግራ ተጋቡ። በራስህ ተወጣው ነውና ነገሩ ቤት ተከራይተው በዚያ ማስተማራቸውን ቀጠሉ። በዚህ ሁኔታ ግን መዝለቅን አይፈልጉም ነበረና አማራጭ ቀየሱ።
ማህበረሰቡን በመሰብሰብም «እናንተ ዘርታችሁ፤ አጭዳችሁ ሳይሆን እግዚያብሔር በሰጣችሁ በረከት የምትኖሩ ናችሁ፤ በዚያ ላይ ሀብታችሁ ቢዛቅ የማያልቅ ነው። ታዲያ ለምን ይሆን ልጆቻችሁ በኪራይ ቤት እንዲማሩ የምታደርጉት» በማለት ጥያቄ አቀረቡላቸው። በወቅቱ የአገሩ ገዢ አልነበሩምና ይህንን ንግግራቸውን ሲሰሙ ውስጣቸው ተነካና አስጠሯቸው። እርሳቸውም አክባሪዬን አልንቅም በማለት ወደ ቦታው አመሩ። አገረ ገዢውም «ሰደብከን አሉ» ይሏቸዋል። እርሳቸውም ስድብ ሳይሆን በረከታችሁን ለሌሎች አካፍሉ ነው ያልኩት በማለት ይመልሱና ከመስተንግዶው በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።
«ይህ ጊዜ እቤቴ እንደምደርስ እርግጠኛ ያልሆንኩበት ነበር። ምክንያቱም ሰደብከኝ ተብያለሁ፤ ስለዚህ ይገሉኛል ብዬ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ አገሬ ለመመለስ ተነስቼ ነበር። ሆኖም አገረ ገዢው ቀድመው ጅማ በመሄድ ታሪኬን አውግተው ኖሮ እዚያ ስደርስ ተአምር መስራቴ ተነገረኝ» የሚሉት እንግዳዬ፤ የቢሮው ኃላፊ በደስታ ትመለሳለህ? ሲሏቸውና ትምህርት ቤቱ ሊሰራ እንደሆነ ሲሰሙ በጣም እንደተደሰቱ አጫውተውኛል። ይህ የመምህርነት ህይወታቸው ያበቃበት ሰዓት ነበር። ምክንያቱም ቀጥታ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ትምህርት በመጀመራቸው ነው።
በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊ የነበሩት ከበደ ሚካኤል ነበሩና፣ ጃንሆይ የሰጧቸውን የትምህርት እድል ለምን ተግባራዊ አይደረግልኝም ሲሉ ይጠይቃሉ። እርሳቸው ግን ሊያደርጉላቸው ቢፈልጉም በተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት ሳይሳካ ቀረ። ደርግም ገባ። ስለዚህ ይህንን ማሰብ ዋጋ የለውም። በኋላ ግን እንዳልካቸው መኮንን በተሾሙበት ሰዓት ዝናቸው ተሰምቶ ኖሮ ተግባረዕድ እንዲማሩ እድሉ ተመቻቸላቸው። እስከ 12ኛ ክፍልም በዚሁ ትምህርት ቤት ተማሩ። ከዚያ አምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ግቢ ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ መማር እንደጀመሩ የአሜሪካ የውጭ ትምህርት እድል አገኙ። ሆኖም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ይሰሩ ስለነበር መልቀቂያ አምጣ ተባሉ።
ድርጅቱ ደግሞ ተምረህ እኛን የምታገለግለን ከሆነ እንፈቅዳለን በሚል ደብዳቤ ይጽፋል። ትምህርት ሚኒስቴር ለዚህ ድርጅት እንድታገለግል አይደለም መማር ያለብህ በሚል ይሰርዘዋል። በዚህ ተናደው ሳሉ ሌላኛው እድል ከተፍ ይላል፤ የአውሮፓ የትምህርት እድል፡፡ በዚህ ግን ብዙ መሰናክል ሳይገጥማቸው ጀርመን ቬና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለመማር ጓዛቸውን ጠቅልለው ሄዱ። ዲግሪያቸውንም በኢንጅነሪንግ ዘርፍ ያዙና ወደ አገራቸው ተመለሱ። ከዚህ በኋላ ግን ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ በአዕምሯቸው ላይ አደጋ ደረሰ።
የሥራ ሀሁ
እንግዳዬ ከላይ እንደጠቆምኩት ያልሞከሩት የሥራ ዘርፍ አለ ብሎ ለመገመት ያዳግታል። በንግዱ ዘርፍ ገና በልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ የተዋጣላቸው ነበሩ። በተለይ ወቅቱን የዋጀ የነጋዴ ሥራ በመስራት የሚያክላቸው አልነበረም። ከዶሮ ተነስቶ የቀንድ ከብት ነጋዴ እስከመሆን ሰርተዋል። ከዚያም አልፈው ወቅቱ ምን ይፈልጋል የሚለውን በማየትም ይሰራሉ። እንደውም በአንድ ወቅት ያደረጉትን ሲያጫውቱኝ፤ «በአካባቢው ዘንድ የገና በዓልን አስመልክቶ የዘይት አቅርቦት ይጠፋል። ስለዚህም በምን መልኩ በዓሉን ማሳለፍ እንዳለባቸው ግራ መጋባታቸውን ስመለከት በአይሱዙ መኪና ከላይ እንደ እህል ተጭኜ አዲስ አበባ ገባሁ። ጠዋትም ከሌሎች የንግድ ሥራዎቼ ያተረፍኩትና ከግምጃ ቤት በመበደር ስድስት የሚደርስ በርሜል ዘይት በመግዛት ወደ ቦታው ተመልሼ ምሽት ድረስ በመሸጥ 400 ብር አትርፌያለሁ። ይህ ደግሞ ለቀጣዩ ንግዴ የተሻለ አቅም ፈጥሮልኛል» ነበር ያሉት።
ከንግዱ በኋላ ደግሞ ውጤታማ ተማሪ በመሆናቸው ብዙ ተቋማት ቴክኒካዊ ስራዎችን እንዲያከናውኑላቸው ይፈልጓቸው ነበር። መኪና መገጣጠም፤ ማሽኖችና ሳይክሎች በአጠቃላይ ቴክኒካዊ ነገሮችን በተመለከተ በግላቸው በየተቋማቱ እየተዘዋወሩ ይሰራሉ። ይህ ተግባራቸው ደግሞ በቋሚነት ብርሀንና ሰላም የህትመት ድርጅት እንዲቀጥሯቸው አድርጓቸዋል። በብርሃንና ሰላም ከተራ መካኒክነት እስከ ምሽት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ማናጀርነት የሚያደርስ ሥራ ሰርተዋል። በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ተቀጥሮ የቴክኒኩን ዘርፍ የሚመራው ሰው ከሌለ ከእርሳቸው ውጭ መፍትሄ የሚሰጥ አልነበረም።
በብርሃንና ሰላም የመጀመሪያው ማሽን ተከላ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊ እርሳቸው ናቸው። በዚህ ቤት ብዙ ውጣውረዶችን እንዳሳለፉ የሚገልጹት እንግዳዬ፤ ምንም ከባድ ፈተና በላዬ ላይ አመራሩ ቢጥልም የምሰራው ለአገሬ ነው ብዬ ስለማምን ችግሩን ችላ እለዋለሁ። እንደውም እኔን የሚተኩ ኢትዮጵያዊ ኢንጅነሮች እንዲኖሩም በማሰብ 11 ሰዎች እንዲቀጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሬያለሁ፤ ሲሉ አውግተውኛል።
እንግዳዬ ከአውሮፓ ከተመለሱ በኋላም በዚህ ቤት ብዙ ዓመታትን ሰርተዋል። ሆኖም ችግሮ ሲሰፋባቸውና የሚሰጣቸው ትኩረት አናሳ ሲሆን ትተው ወጡ። ነገር ግን እርሳቸውን ለሚሹ ጉዳዮች ሁሉ እጃቸውን ይዘረጉ ነበር። አይደለም ላደጉበት ቤት ሌሎችም ቢሆኑ ይህንን እይልን ካሏቸው እንቢ የሚል ነገር ከአንደበታቸው እንደማይወጣ ይናገራሉ። ከዚያ መውጣታቸው ለሥራቸው እንቅፋት ሳይሆን ጥንካሬን እንደሰጣቸው የሚገልጹት ኢንጅነር በረከት፤ የራሳቸው የሆነውንና ጄኔቭ በማለት ስያሜ የሰጡትን ሆቴል ለማስተዳደርና ሌሎች አጋርነት ያላቸውን ተግባራት ለመከወን እንዳገዛቸውም አውስተውኛል።
ዛሬም ቢሆን ጄኔቭን ከመምራት በዘለለ የተለያዩ ሸሮች ውስጥ በመግባት ትርፋማነታቸውን ሳይለቁ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያስረዳሉ። በተለይ ደግሞ በሥራ የሚያግዟቸው ልጆች ስላላቸው ተደስተው እየኖሩ እንደሆነም ነው ያወጉኝ።
ገና እና ልጅነት
የገና ጨዋታ በአካባቢያቸው የተለየ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። በተለይም ደግሞ ገና የወንዶች ስለሆነ ወንድ ልጆች የተለየ የመጫወትና የመዝናናት እድሎችን ያገኙ ነበር። ገና ሲከበር እንደሌሎቹ በዓላት ብዙም ትኩረት ተሰጥቶት ምግብና መጠጥ አይዘጋጅለትም። ሆኖም በጨዋታውና የአካባቢው ሰው ችግረኛን በመርዳት የማክበር ልምዱ ስላለው ገና ሲመጣ ሁሉም በደስታ ይቀበለዋል፤ ተደስቶበት እንዲያልፍም ይፈልጋል። በተለይ ደግሞ ገና በሚባለው ዱላ በቡድን ሆነን ከተጫወትን በኋላ የሚደረገው የትግል ፍልሚያ እጅጉን የሚናፍቅ ነው። ስለዚህም ሁሉም የአካባቢው ወንድ ልጆች ይህንን ለማሳለፍ በጉጉት ይጠብቀዋል።
የተሸነፈው ቡድንም ወቅቱ የእህል ጊዜ ስለሆነ በቁና አፍሶ እህል እንዲገብር ይደረጋል። በዚህ ደግሞ ቤተሰብ መቃወም አይችልም። በተሸናፊውም በአሸናፊውም ተደስቶ የተባለውን ያደርጋል። ይህ ግብር ግን የሚሰጠው ለሁለት አይነት ሰዎች ነው። አንደኛው ግቡልኝ ቤተሰቤን አጥቻለሁ የሚለው ጋር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አራስ ጋር ነው። ስለዚህ ገናን ስናከብር ሁለት አይነት መንገዶችን ተከትለው እንደሆነም አጫውተውኛል። ዛሬ ግን ይህ የለም፤ በገጠሩም ሆነ በከተማው የአውሮፓው ባህል ተንሰራፍቷል። ገናን ለእነዚህ ጉዳዮች ማድመቂያነት መጠቀሙም እንዲሁ ተዳክሟል። ይህ ትዝታ ከሆነ ሰነባብቷልና ወደ ማንነታችን እንመለስ ሲሉም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ገጠመኝ
እንግዳዬ በበርካታ ውጥንቅጥ ህይወት ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው የተነሳ ሊናገሯቸው የሚችሉት ገጠመኞችም እንዲሁ ብዙ ናቸው። ነገር ግን ለአምዱ የሚሆኑና በጣም አይረሱኝም ያሏቸውን ሁለቱን ነገሮች ላውጋችሁ። የመጀመሪያው ጀርመን ውስጥ እያሉ ያጋጠማቸው ሲሆን፤ ለመዝናናት ወደ አንድ ምሽት ቤት ያመራሉ። በዚያም የሚፈልጉትን መጠጥ አዘው እየተዝናኑ ቆዩና ወደ ዶርማቸው ለመመለስ ሲነሱ ነጮችና ጥቁሮች በፍጹም የማይስማሙበት ቦታ ውስጥ ገብተው ኖሮ አንዱ ነጭ በጀርመንኛ «አንት ንፍጣም» ይላቸዋል።
ያ የኢትዮጵያዊነት ወኔ ውስጣቸውን ይፈታተነውና ማንን ነው እንዲህ የምትናገረው ብለው በቦክስ ይነርቱታል። በወቅቱ ብዙ ነጮች በአካባቢው ነበሩ፤ ወዲያውም አንድ ጊዜ ቢያሳርፉባቸው ከምድረገጽ የሚያጠፏቸው የሚመስሉ ግዙፍ ሰውነት ያላቸው ነጮች ከፊታቸው ይደቀናሉ። ልምታው አልምታው በሚል ስሜት ውስጥ እንዳሉም ብልጣብልጡ እንግዳዬ በእግራቸው መሀል ሾልከው እግሬ አውጭኝ ብለው ይፈረጥጣሉ። በዚያ ሩጫቸው መካከልም የጥቁሮችን ደህንነት የሚጠብቁ ሰዎች መኪና ይዘው ሲጓዙ ተመለከቷቸውና እጃቸውን ይዘው መኪና ውስጥ እንዲፈናጠጡ አድርገዋቸው አተረፏቸው። ከዚያም ሳምንት ሙሉ ከዶርም ሳይወጡ በፍራቻ ያሳለፉት ጊዜን እንደማይረሱት ነግረውኛል።
ሌላው በብርሃንና ሰላም እየሰሩ ሳለ የገጠማቸው ነው። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ የገነባውን ህንጻ የሚያስመርቅበት ወቅትና የጃንሆይ የዘውድ በዓል ነበር። በዚህ ቀን ደግሞ ጋዜጦች የሚታተሙት ልዩ እትም ሆነው ነው። በወቅቱ የቴክኒክ ሙያውን የሚመራው ሰው ለእረፍት ወደ አገሩ ተጉዟል። በተቋሙ ኢትዮጵያዊ የቴክኒክ ባለሟል ደግሞ እርሳቸው ብቻ ናቸው። እናም ማሽኑ እንቢ በማለቱ የተነሳ 48 ሰዓት ሊሞላቸው ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ተሳካላቸውና ጋዜጣው ታተመ። ይህም ቢሆን እንደ ላይኛው የማይረሱት ገጠመኛቸው መሆኑን ነበር ያጫወቱኝ።
ቤተሰባዊ ህይወት
በአካባቢያችን ምንም የጤና ኬላም ሆነ ሀኪም የለም፤ ትምህርት ቤትም፣ ውሃም ሆነ መንገድም የለም። ስለዚህ ከቤተሰቤ በፊት ቅድሚያ የሰጠሁት የአካባቢውን ሰዎች በማሰባሰብ እነዚህ ነገሮች እንዲሟሉ ማድረግ ላይ ነው። ከዚያም መጀመሪያ ላይ መንገድ እንዲሰራ አደረግሁ፤ ቀጥዬም ትምህርት ቤት ማህበረሰቡ እንዲጨምርበት በማድረግ እስከ ስምንተኛ ክፍል እንዲያድግ አደረግሁ ሲሉ አጫውተውኛል፡፡ ይህንን ተከትሎም የስምንተኛ ክፍል ውጤት ሲታይ ከአገሪቱ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ያ ትምህርት ቤት ሆነ። ከዚያ ሌሎቹ ነገሮች በትምህርት ሚኒስቴርና መንግሥት በሚያደርገው እገዛ ሊሳካ እንደቻለ ይገልጻሉ።
ይህንን አድርገው ከጨረሱ በኋላ አገቡና ልጆችን ወለዱ። አሁን የአራት ልጆች አባት ናቸው። የልጅ ልጅም ለማየት በቅተዋል። አንዱ ልጃቸው ትምህርቱን በቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርት መስክ አጠናቆ ከእርሳቸው ጋር እየሰራ ይገኛል። ሴቷ ልጃቸው ደግሞ በኢንጅነሪንግ ዘርፍ እየተማረች ሳለ አንድ ኮርስ ሲቀራት በመውለዷ ምክንያት አቋርጣ ስለነበር እየተማረች ነው። ሦስተኛ ልጃቸው ደግሞ ማርኬቲንግ የትምህርት ዘርፍ እየተማረች የምትገኝ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ትመረቃለች። ሌላው ወንዱ ልጃቸው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው። እናም በዚህ ሁሉ ትግል ውስጥ አልፈው ለዚህ በመብቃታቸው ደስታቸው ወሰን የለውም።
መልዕክት
«ከፈተና ጀርባ ድል መኖሩን ማንም ሳይዘነጋ ይሥራ፤ ሌሎችንም ያስብ» የሚሉት እንግዳዬ፤ ምርጥ ዜጋ ማለት ድሃው ህዝብ ነው። ምክንያቱም ተሞላቆና ሁሉ ነገር ተሟልቶለት የሚማረው ልጅ የቤተሰቡን ሀብትና ንብረት መከታ ስለሚያደርግ ለትምህርቱ ትኩረት አይሰጥም። ወላጅም ቢሆን መብቱን እንጂ ግዴታውን ስለማያሳውቀውም፤ የተበላሸ ትውልድ ለመሆኑ ተጠያቂው አሳዳጊው እንደሆነ ይናገራሉ። ጉዳዩም ሊታሰብበት እንደሚገባ ይናገራሉ። በተጨማሪም እያንዳንዱ ትውልድ ውጤታማነቱን የተቀዳጀው በህብረተሰቡ እገዛ መሆኑን ሳይዘነጋ ለእነርሱ መኖርንም ጎን ለጎን ማሰብ እንዳለበትም ያሳስባሉ።
እንግዳዬ ኢንጅነር በረከት ሰብስብ በርካታ ቁምነገሮችን በጭውውታችን ሲያወጉኝ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ የነገሩኝን ሁሉ ለእናንተ አንባቢዎቼ ለማውጋት ጊዜና ቦታ ገድቦኛልና ከብዙ በጥቂቱ ከእርሳቸው ተሞክሮ እንደተቋደሳችሁ በማሰብ ለዛሬ የያዝኩትን ሀሳብ በዚህ ልቋጭ። ሠላም!

ጽጌረዳ ጫንያለው 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።