ገና እና ባህላዊ አከባበሩ Featured

13 Jan 2018

በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ የገናን በዓል ለማክበር ሽር ጉድ ይላሉ። ምናልባት እናንተም ይህን በዓል ለማክበር በጉጉት ከሚጠባበቁት ሰዎች መካከል አንዱ ልትሆኑ እንደምትችሉ እገምታለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ታዋቂ ኃይማኖታዊ በዓል የመካፈል ልማድን አይታችሁ ላይሆን ይችላል። በዚያም ሆነ በዚህ የገና በዓል በሚያሳድረው ተጽዕኖ መነካት ግን አይቀርም። ይህ በዓል ክርስቲያን ባልሆኑት አገሮች እንኳ ሳይቀር የንግዱንም ሆነ የመዝናኛውን ዓለም በመቆጣጠር ላይ እንደሚገኝ በብዙ መንገድ ማስቀመጥ ይቻላል። ስለዚህም ስለ ገና በዓል ሲነሳ በዕምነቱም ሆነ ከዕምነቱ ውጭ በዓሉን ልዩ አድርጎ መመልከት ግድ ይሆናል። እናም ከተለያዩ መረጃዎች የቃረምኳቸውን ሀሳቦች በማንሳት ጥቂት ልላችሁ ወደድሁ።
በየዓመቱ በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ የሚከበረው ይህ በዓል ከየት የመነጨ ነው? ከሚለው ልነሳ። ምክንያቱም በአዕምሯችሁ ውስጥ ጥያቄ የሚጭር ጉዳይ ነውና። ብዙዎች እንደሚያስረዱት አዝመራው ተሰብስቦ፣ ጤፍና የብርዕ እህል ሁሉ ታጭዶ በእርሻው ላይ ከብቶች ከተሰማሩ በኋላ ማሳው አውላላ መንደር ይሆናል። ይህ ደግሞ እረኞች እንዲቦርቁ ዕድሉን ያመቻችላቸዋል። ገበሬውም ቢሆን እህሉን በጎተራ ሞልቶ ከስራ ፋታ የሚያገኝበት ወቅት በመሆኑ ራሱን ፈታ ለማድረግ የሚሞክርበት ነው። ነጋዴውስ ከተባለ ደግሞ በእህል ጎተራውን የሞላውን ገበሬ የሚደሰትበትን ነገር በማቅረብ ያገለግልና ገንዘቡን ይሰበስባል።
ይህ ወቅት ለገበሬው ያስፈለገን ነገር መግዥያ ገንዘብ የሚሰበሰብበት ነው፤ ለነጋዴው ደግሞ ሸቀጡን በተገቢው ዋጋ ለገዢው የሚያስረክብበትና የኢኮኖሚ አቅሙን የሚገነባበት ሲሆን፤ ለእረኛው ደግሞ ያው ከላይ እንዳልኩት ክረምቱም ሆነ በጋው በእህል የተያዘው የእርሻ ቦታ መቦረቂያቸውን ሲያሳጣቸው ከርሟልና የሚለቀቅበት ነው። በመሆኑም ሁሉም የአገሪቱ ሰዎች በደስታ ይቦርቃሉ፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ነው ይህ ወር የፍስሃና የደስታ በዓል እንደሆነ የሚናገሩት፤ አመጣጡም ከዚህ ጋር ተያያዥናት እንዳለው የሚያስረዱት።
ገናን ስናነሳ ጨዋታውን ሳንጠቁም የማለፉ ዕድል አይገጥመንም። ምክንያቱም በአገራችን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ስላለውና የመደሰቻ አጋጣሚው በዚህ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ፣ ደስታ ከተባለ በውስጡ ጨዋታና ባህልን የሚያስተዋውቁ በርካታ ነገሮች ይኖራሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የገና ጨዋታ ዙሪያ የሚከወኑትና የጨዋታው ትዕይንት አንዱ ነው። ስለዚህም የጨዋታ ወግ ጥቂት ነገር ልበላችሁ።
ጨዋታው ከጥንት ጀምሮ የነበረ እንደሆነ መዛግብት ያስረዳሉ። ነገር ግን አመጣጡ ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች ሳቢያ መሆኑን ነው የሚያትቱት። እናም ይህ ጨዋታ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለ ዛሬ ላይ ሊደርስ ችሏል። በእርግጥ ይህ መጤ ባህል ጨዋታውን ነበር እንዲባል እያሰኘው ነው። ይሁንና መሰረቱ ምንድን ነበር? ማንስ ምን ያደርጋል? ባህላዊ እሴቱስ ምን ይመስላል? የሚለው ከኢትዮጵያኑ አዕምሮ ውስጥ አይፋቅምና መናገሩ መልካም በመሆኑ ነው ላነሳው የወደድኩት።
ኢትዮጵያያዊያን የማይጠፉና የማይለወጡ ባህሎች አሏቸው፤ ግን በየጊዜው ከማስታወስ አኳያ ብዙም ትኩረት አልተቸራቸውም። ሆኖም ባህላቸውን ለቀው ለሌሎች አገራት ባህል ማራመጃ እየሆኑ ነው። ይህንኑ የገናን ነገር ስናነሳ የምንመለከተው ከፈረንጆች አዲስ ዓመት መግቢያ ጋር በማያያዝ ብዙ የእኛ ያልሆኑ ነገሮች ገብተው ማህበረሰቡን የሌላ ባህል ተከታይ አድርገውታል። በተለይ ደግሞ ህፃናቱ እንዲለብሱትና እንዲጫወቱት የሚደረጉበት ሙሉ ጌጡ የገና አባት ተብሎ በሚጠራው የውጭ ባህል ነው። እንደው ዕውነቱን እናውራ ከተባለ ይህንን የሚያስጌጥና ልጆችን የሚስብ ነገር አጥተን ይሆን ይህ እየተደረገ ያለው? መልሱን ለአንባቢዬ ልተውና ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስ።
ጭውውታችን የገና ጨዋታን በተመለከተ ነውና በየዓመቱ በታህሣሥ ወር በተለይ በኢትዮጵያ የገጠሩ ክፍል እረኞች በድምቀት የሚጫወቱት ሲሆን፤ በአብዛኛው ጨዋታው ወሩ እንደገባ የሚጀመር ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከታህሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ ይጧጧፋል። የገና ጨዋታ ሁለት ቡድኖች ጎራ ለይተው የሚጋጠሙበት ልዩ ባህላዊ ትዕይንት ነው። በአብዛኛው የሰሜኑ አካባቢ የሚከወን ሲሆን፤ “ጥንጓን” ወይም “ሩሯን” የሚመቱበትን የዱላው ራስ ወይም “ገና” የሚሉትን ይዘው ይጫወታሉ። ገና የተባለውን ስያሜም ከዚሁ ጋር አያይዘው እንደሚያከብሩት ይነገራል።
ዱላው ከወደ ራሱ እንደ ከዘራ ቆልመም ያለ ሲሆን፤ አሁን በዘመናዊ መልኩ በከተሞች ከምናየው የተለየ ጨዋታ የሚከናወንበት ነው። በስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በገባው ዘመናዊ የገና ጨዋታ ህግ መሰረት፤ ዱላውን (ገናውን) ወደ ላይ ማንሳት አይቻልም። በጥንታዊው ወይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚደረገው የገና ጨዋታ ግን ይህ ጉዳይ አይከለከልም፤ ይልቁንም እንደተፈለገው በማንሳት፣ ሩሯን (ጥንጓን) አክርሮ መለጋት ይቻላል። እናም በዚህ መመሪያ መሰረት እረኞች ጊዜያቸውን በደስታ ያሳልፋሉ።
በገና ጨዋታ ላይ የሚሰነዘሩ ተረቦች በርካታ ናቸው። በተለይ በተሸናፊው ላይ የሚወርደው የስድብ ናዛ ቁጥር ስፍር የለውም። በእርግጥ በዚህ ጊዜ መቀየም የሚባል ነገር የለም። ይልቁንም እንደ መዝናኛና እንደ ማድመቂያ ተደርጎ ይወሰዳል። የሚተርበው ቡድን እንኳን በተረቡ ይዝናናል፣ ይስቃል እንጂ ቂም መያዝ ብሎ ነገር አያስብም፤ ምክንያቱም ጨዋታው የገና ነዋ። ተሸናፊውም በእልህ ለማሸነፍ ይነሳሳል እንጂ በጨዋታ አድማቂው ተረብ አይቆጣም። በጨዋታው ላይ የሚሰነዘሩ ወይም የሚወረወሩ ተረቦች በአብዛኛው በአካላዊ ገፅታ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ለምሳሌ ቁመት፣ እርዝመትና እጥረት፣ ውፍረትና ቅጥነት ወዘተ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም “አሲና በል አሲና ገናዬ
እያሃ … አሲና በል አሲና ገናዬ” እያሉ ተጋጣሚዎች ጨዋታውን ያደሩታል። ክብ እየሰሩም ይጨፍራሉ፤ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ተረቡ ይቀጥላል። ለምሳሌ አጫጭሮቹን የቡድን አባላት ለመተረብ አሸናፊዎቹ እንዲህ ይላሉ።
‹‹ይህን ወዳጅ ብላ ታስከትለዋለች
አንድ ቀን ጩልሌ ታስወስደዋለች፡፡›› አጭሮቹ በተራቸው ደግሞ
‹‹ረጅም ነህና ሞኝነት አታጣም
እቆርጥልሃለሁ አሳጥሬ በጣም
ይኸን ረጅሙን ጎምዶ ጎማምዶ
ግማሹን በርጩማ ግማሹን ማገዶ›› እያሉ የአፀፋ ምላሹን ያዥጎደጉዱታል፡፡ ወፍራሞች ደግሞ ቀጭኖችን እንዲህ ይሏቸዋል።
‹‹ሲሄድ ቅትር ቅትር ሲበላ እንዳንበጣ
ወዘና የሌለው የጨጓራ ቋንጣ›› በተረቡ በትር ያረፈባቸው ቀጭኖችም በአፀፋው ምላሻቸውን ሲሰጡ እንዲህ ይላሉ።
‹‹እየው አካሄዱን አረማመዱን
እንደ ቃሪያ ሎሚ ወጥሮ ሆዱን›› እንዲህ እንዲህ እየተባለ ጨዋታው ለዛውን ይዞ ይከናውናል። በዙሪያውም ትዕይንቱን የሚከታተሉት አካላት ደስታቸውን ያጣጥማሉ። የተረቡን አሸናፊዎችም በራሳቸው ቡድን ሞራል እየሰጡ ይስቃሉ። በለው እያሉም ያበረታታሉ። የገና ጨዋታ በሁለቱ ቡድኖች የሚደረገውን ግጥሚያ ብቻ አይደለም። በተጨማሪም ሴቶችን የሚያሳትፍ ትዕይንታዊ ተግባር ይከወንበታል። በጥንቱ የገና ጨዋታና አሁንም በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ሴቶች ባይጫወቱም በሜዳው ወይም በግጥሚያ ማሳው ዙሪያ ሆነው የሚደግፉትን ቡድን ያበረታታሉ፤ የሚነቅፉትን ደግሞ በተረብ ይሸነቁጡታል። በመሆኑም እነርሱም የጨዋታው አድማቂና መዝናኛ ናቸው።
‹‹ወንድ ነው ብዬ … ብሰጠው ጋሻ
ለናቱ ሰጣት ላመድ ማፈሻ
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጦር ላባቱ ሰጠው ለቤት ማገር›› የመሳሰሉትን እያሉ ተወዳጁን የገና ጨዋታ ያደመቀውን አካል ይደግፋሉ። በጥንቱም ሆነ በአሁኑ ገጠር አካባቢ ይህ ተግባር ሲከወን “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እንደሚባለው ሴቶችን በዚህ ጨዋታ ለምን ተሳተፋችሁ ተብሎ የሚገስጻቸው አይኖርም። እናም በነጻነት ይጨፍራሉ፤ ይጫወታሉም። ከጨዋታው በኋላ መብል መጠጡ ተሰናድቶ፣ ድግሥ ላይ ጌታውም ሎሌውም እኩል ይቀመጣሉ። አብረው ይበላሉ። አብረው ይጠጣሉ።
በገና ጨዋታ አሽከርና ጌታው እኩል ይጫወታሉ፤ ይራገጣሉ። በዚህ ወቅት ነው በእርሻ ሥራም ሆነ በዝናብ ምክንያት ጨቅይቶ የቆየውን ሜዳ ነፃ ለመቦረቅና ለጨዋታ ምቹ የሚደረገው። እንደየአካባቢው ባህልና ወግ መሰረት ለባህላዊ ጨዋታዎች ያመቻል። አርሶአደሩም የእረፍት ጊዜው ነውና በተለያዩ ጨዋታዎች ዘና ይላል።
የገና ጨዋታ የህዝቡን የአብሮ የመኖርና እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህል ያጠናክራል። ይሄው በዓመት አንዴ ብቻ ተጠብቆ የሚካሄድ ጨዋታ በህዝቡ እጅግ ተናፋቂ ነው። እናም ይህንን ባህል ማንኛውም ዜጋ በሌሎች ባህል ነጣቂዎች ሳይወረስበት ነባሩን ማቆየት አለበትና በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ የባህል ተቆርቋሪዎች ባህሉን እያሳዩ ይገኛሉ። እንዳይበረዝም መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። ያው ተቀብሎ የመተግበሩ ጉዳይ የባህል ወዳዱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ። ስለዚህም ስለገና ጨዋታ ካነበብኩት አንድ የመጨረሻ ነገር ልበልና ላብቃ። ግን ከሁሉም በፊት ሰው ባህሉን ይጠብቅ፤ ኢትዮጵያዊነትን ላለመልቀቅ ይታትር መልዕክቴ ነው።
ልጃገረዶችም ፍቅረኛቸውን የሚያስቡበት በናፍቆት የሚጠባበቁበት፣ ስንኝ ቋጥረው የሚመላለሱበትም ናፋቂ ጊዜ መሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ግጥሞችና ንግግሮችም አሉ። ለዚህ አብነት የሚሆን አንዱን እነሆ ይህ ግጥም ያገኘሁት ደግሞ ኢዜአ «አንዴ ብቻ አሲና በል! ለምን? በሚል ጽሁፉ ከአስቀመጠው ግጥም ሲሆን ልጃገረዶችም ሆኑ ገናን የሚናፍቁ ሰዎች ምን ያህል በግጥም ራሳቸውን እንደሚመለከቱ ለማሳየት ነው።
የወጣውን በመመልከት ነው፤
"ታህሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣
እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡
ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና፣
ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና፡፡
ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣
ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታህሣሥ፡፡
በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣
እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ፡፡"

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።