ኪነጥበብ - ለአካባቢም ውበት

13 Jan 2018

ኪነጥበብ የትኛውን ማህበረሰብ የሚያነቃና ወደ ተግባር እንዲገባ የሚያደርግ መሆኑን መናገር ለቀባሪው አረዱት ይሆናል። እናም ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽዳትና ውበት ባዘጋጀው መድረክ ላይ በመገኘት በአካባቢያቸው እየተከሰተ ያለውን ችግር ለማስወገድና ሲያሳስባቸው የቆየውን ጉዳይ የኪነ ጥበብ ሰዎች በምን መልኩ ተሳትፈው የድርሻቸውን ለመወጣት የሚያስችል ውይይት በካፒታል ሆቴል ተካሂዷል። በውይይቱም ላይ በርካታ ሀሳቦችንም አንሸራሽረዋል። ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበዋል።
በወቅቱ አንድም ሰው ከቦታው ሳይንቀሳቀስና የሻይ ዕረፍት እንኳን ሳይኖር ነበር መሳጭ ውይይቱን ሲሳተፉ የቆዩት። ይህ ደግሞ ይህ የጽዳት ጉዳይ ምን ያህል እንዳሳሰባቸው የሚያመላክት ነው። በተለይ አንዳንዶቹማ እንባ በተናነቀው ስሜት ሲናገሩ ችግሩ ምን ያህል ግዝፈት ያለውና የባለሙያዎቹን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ አይፈጅም። መቼም ምን ተባለ ማለታችሁ እንደማይቀር እገምታለሁ። ያው ጉዳያችን ኪነ ጥበብ ነውና ከራስ የጀመረ ሥራ ይሰራ የሚል ነው። ምክንያቱም ታዋቂ ሰዎችንና የኪነጥበብ ባለሙያዎችን የሚከተለው ማህበረሰብ እጅግ በርካታ መሆኑ ይታወቃል። ስለሆነም ተረፈ ምርቶች በአካባቢና በሰው ልጆች ላይ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት እንረዳለን። ለዚህም በቆሻሻ አወጋገድ ላይ ህብረተሰቡን ለማስተማር ይህን እናድርግ ብሎ መነሳት ያስፈልጋልና ምክረ ሀሳቡን በሚገባ ለመተግበርም ተነስተዋል።
በወቅቱ ከተሳተፉት መካከል አርቲስት ችሮታው ከልካይ እንዳለው፤ የቆሻሻ አያያዝ፣ አጓጓዝና አወጋገድ ሥርዓት ደካማ በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ የሚፍጠሩት ቆሻሻዎች በሰው ልጆች፣ በአካባቢና በእንስሳት ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋን እንደሚያስከትሉ ማንም አያጣውም። በዚህም በመዲናችን አዲስ አበባም የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሂደት ላይ የሚታየው ደካማ ሥርዓት በከተማዋ ነዋሪዎችና እንስሳት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖን ፈጥሯል። ይህ ደግሞ መሻሻልም ሆነ መቃለል የሚችለው አዕምሮ ላይ በሚሰራ ሥራ ነው። ለዚህም ቅርቡ አርቲስቱ ነውና በተለያየ መንገድ ማህበረሰቡን ማስተማር ይገባዋል።
የከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የከተማዋን ጽዳት ለመጠበቅ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም የማህበረሰቡ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ልማድ ደካማ በመሆኑ ከተማችን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ እንዳልተቻለ ማሳያዎች አሉ የሚለው አርቲስት ችሮታው በተለይ በትምህርት ቤት አካባቢዎች ኪነታዊ በሆነ መልክ ማስተማሩ ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ ያስረዳል። ይህ ደግሞ የሚጀምረው ከእራሱ ከአርቲስቱ መሆኑንም ይገልጻል። አርቲስት የማይገኝበትና የማያየው ነገር የለም። እናም ባገኘው አጋጣሚ በአካባቢ ጥበቃም ሆነ በጽዳቱ ዙሪያ ማስተማር ላይ መስራት እንዳለበትም ይናገራል።
የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነ ማንም ይረዳል የምትለው ደግሞ ኮመዲዋ ቤቲ ዋኖስ ነች። እርሷ እንደምታነሳው፤ የአካባቢ ብክለትን እንዲቀርፍ ለማስተማር በጥበብ ሙያቸው አንድ ተግባር በመፍጸም እንዳለባቸው ታምናለች። ይህ ደግሞ የራሴን ልጅ ከማስተማር መጀመር አለብኝም ነው ያለችው። ከወዳደቁ ላሰቲኮች፣ አጥንቶችና የብረት ቁርጥራጮች የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርፃ-ቅርፆችን ሰርቶ የሚጣል ነገር ዋጋ እንዳለው የሚያሳየው የጥበብ ባለሙያው ነው።
ሰዎች ቆሻሻን በአግባቡ እንዲያስወግዱ ለማስተማር ጥረት ማድረግ ላይ በራስ በመሳቅና ራስን በማስተማርም ለውጦች እንዲመጡ የጥበብ ባለሙያው ማድረግ ይችላል። ስለሆነም የኪነጥበብ ባለሙያዎች በተለያዩ መርሃ ግብሮቻቸው ላይ እነዚህንና እነዚህ መሰል ተግባራትን በመከወን ማህበረሰቡን ካለበት ችግር ውስጥ ማላቀቅ ይጠበቅበታል። በተለይም ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ማህበረሰብ ከቆሻሻ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ምክንያቶች ለሞትና ለበሽታ መዳረጉ ማሳሰብ ያለበት ሁሉንም ቢሆንም የኪነጥበብ ባለሙያው ግን በይበልጥ ተሰሚነትና ተቀባይነቱ በእጁ ነውና ሊሰራበት ይገባልም ትላለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያሳየው በቆሻሻ ምክንያት የሚከሰተው ብክለት ለአካባቢ ደህንነት አንዱና ዋነኛው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አርጋግጧል፡፡
ከወዳደቁ ላስቲኮችና የብስኩት ማሸጊያዎች የሚሰሩ ስራዎች ህብረተሰቡ ለአጭር ጊዜ ተጠቅሞ የሚጥላቸው ላሰቲኮች ናቸው። ሆኖም የዕድሜ ልክ ችግር ሊሆኑ እንደማይሉ ለማስገንዘብ ባለሙያው ጥቂት መሰዋዕትነት ቢከፍል ነው የሚሉት ደግሞ አርቲስት ደባሽ ተመስገን ነው። በቆሻሻ ምክንያት የሚመጣ የአካባቢ ብክለት ስለሚያሳስበንና ጥቅም የላቸውም ተብለው የሚጣሉ ቁሶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል በማሰብ ብዙ ተግባር ይከወናል። ታዳጊ ልጆች ደግሞ ይህንን ተግባር መመልከት ከቻሉ ተተኪ ይሆኑና ከጽዳቱ ባለፈ እንደ ቢዝነስ ማግኛነት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም ያስረዳል።
በእርግጥ ይህንን በመስራትና ቆሻሻን በመለቃቀም ለሥራ ስናውል በሥራቸው ላይ የሚሰጡት አስተያየቶች አበረታች ላይሆኑ ይችላሉ፤ እንዴት ይህንን ያደርጋል እርሱ የተከበረ አይደል የሚልም አይጠፋም። ነገር ግን ያ የሚሰራው ሰው ማሰብ ያለበት ያለውን ጥቅም እንጂ ስድቡን መሆን የለበትም ይላልም። ይህን ሥራ ስንሰራ መልካም አስተያየት የምናገኝ ይመስላል፤ የሚያሳዝነው ግን ብዙ ውጣ ውርዶችን እያለፍን ልናደርገው የምንችለው ነው። ስለዚህ ጥሩ ነገር ጠብቆ ሁሉንም ተግባር መከወን አይቻልም። ለውጡም በአንድ ጀንበር ይመጣል ብሎ ማሰብ አይገባም። እናም በየጊዜው አዳዲስ ትዕይንቶችን በመፍጠር ጊዜያዊ ሳይሆን ቋሚ ነገር መስራት ይገባል ይላል።
አይረቡም ከተባሉ ነገሮች ብዙ ጠቃሚ ነገር መስራት እንደሚቻል ማሳየትና ሰዎች ተገፋፍተው ወደዚያ ሙያ እንዲገቡ የማድረግ ኃይል ያለው የኪነጥበብ ባለሙያ ብቻ ነው። እናም ይህ ባለሙያ ባለው አቅምና ጊዜ ይህንን ዘርፍ ሊደግፍ ይገባዋል። ሆኖም እንጀራው ይህ ስለሆነም በመንግሥት ልዩ እገዛ ሊደረግለት ይገባል፤ ማበረታቻዎችና ማቴሪያሎችም ያስፈልጉታል። እርሱ ሙያውን ተጠቅሞ ለመስራት ሲሞክር ከኪሱ አውጥቶ መሆን የለበትምና በታዋቂነቱና ደስተኛ ሆኖ እንዲሰራ ልዩ እገዛ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ገቢ የሚያገኝበትን ሥራ ትቶ መስኩን ለመደገፍ ይጥራል። ነገር ግን ኪሳራ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ለሌሎችም መነቃቃት አይፈጥርም። በተጨማሪም ዘላቂነቱ ላይም ጥላ ያጠላልና ዘርፉ ላይ የሚሰሩ አካላት ይህንንም አበክረው ሊመለከቱት እንደሚገባ ይናገራል።
በውይይቱ ላይ ከንፈሩን ሳይመጥና ውስጡ እየተፈጠረ ባለው የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ክፍተት ያልተነካ አልነበረም። ስለዚህ ሁሉም በአንድ ድምጽ ምቹ ሁኔታ ይፈጠር እንጂ እቅዱን እናሳካዋለን፤ በልማቱም ሆነ በማህበራዊ አገልግሎቱ ውስጥ ጥበብ የማትገባበት ነገር የለምና እርሷን ተመርኩዘን የበኩላችንን እናደርጋለን በለው ነው የተሰናበቱት። እኔም ያላችሁትን ለመፈጸም ያብቃችሁ በማለት ለዛሬ የያዝኩትን ሃሳብ ልቋጭ። መልካም በዓል!

ጽጌረዳ ጫንያለው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።