« የተደሰትኩት በተማሪዎቼ ደስታ ነው» Featured

11 Feb 2018

ስለራሳቸው ብዙ መናገርን አይፈልጉም፤ የሠሩትን እንኳን ይህንን ብቻዬን ነው ያደረኩት ማለት አይወዱም። በተለይም «ይህ የሆነው ከእነርሱ ጋር በመሥራቴ ነው» የሚል ምላሽ ይቀናቸዋል። ወሬያቸው ሁሉ እኛ እንዳደረግነው፣ እኛ እንደሠራነው፣ እኛ ይህንን ፈጽመናል ነው። የመጨረሻውን የመምህርነት ማዕረግ እንዳገኙ ባውቅም የሰማሁት ግን እኛነትን በመሆኑ ተገርሜያለሁ። በእርግጥ ብዙ የሚያውቅና ብዙ የሚሠራ ሰው ስለ እራሱ ከሚያወራ ይልቅ ተግባሩ ቢናገርለት ይመርጣል። በተግባር የተደገፈው ሥራቸውም ቢመሰክርላቸው ያስደስታቸዋል።

እንግዳዬም ለዚህ ይሆናል ስለ ራሳቸው ብዙ መናገርን የማይፈልጉት። ይሁን እንጂ «ከእርስዎ ብዙ ነገር ሰዎች ይማራሉ፤ አስተማሪነት ከመደበኛው ትምህርት ውጪም አለ። ስለሆነም ልምድዎን ያስተምሩ፣ ያጋሩ» አልኳቸው። «እኔ ምንም የሚያስተምር ህይወት የለኝም። የሚጠቅምና የሚያስተምር ህይወት አለህ ካልሽ ለመናገር ዝግጁ ነኝ» በማለት ፈቃደኝነታቸውን ሰጡኝ። የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳዬ ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንግዳወርቅ።
ፕሮፌሰር ኤፍሬም ባለፈው ወር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ሰዎችን በሥራቸው መዝኖ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከሰጣቸው መካከል አንዱ ናቸው። ስለዚህም ጭውውታችንን የጀመርነው «እንኳን ደስ አለዎት» በማለት ነበር። በእርግጥ ብዙዎቹ ለእርሳቸው ይህ ማዕረግ መሰጠቱ «ዘግይቷል» የሚል እምነት አላቸው። ምክንያቱም በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል። ከአገር አልፈው በዓለም ላይ በሚሠሩ ተግባራት ተሳታፊ ናቸው። እውቅናውን ተከትሎ እንዳሉት «ይህ ማዕረግ ለእኔ ሁለት ነገሮችን ይዞ ብቅ ያለ ነው። የመጀመሪያው የበለጠ እንድሠራ የሚያበረታታኝ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኃላፊነት እየተጫነብኝ መሆኑን አሳይቶኛል። በተለይም ለአገሬ ከዚህ በላይ መሥራት እንዳለብኝ ትዕዛዝ የተላለፈልኝ መሆኑን ነው የምገነዘበው» ሲሉ አጫውተውኛል።
«በዩኒቨርሲቲ ህይወት ውስጥ አንድ ሰው መምህር ሆኖ ሲሠራ አገኘዋለሁ ብሎ የሚያስበው የመጨረሻው ነገር ስለሆነ በጣም ተደስቼበታለሁ። ከእራሴ ይልቅ የተደሰትኩት በተማሪዎቼ ደስታ ነው» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ መምህርነት ከምንም ነገር በላይ የሚወዱት ሙያ እንደሆነ፤ በተማሪዎቹና በእርሳቸው መካከል ያለው የእውቀት ልዩነት ጠቦ ማየታቸው፤ እንዲሁም አዲስ ነገር ለማግኘትና ሁልጊዜ ለመማር የሚያግዛቸው በመሆኑ እንደሚመርጡት ይናገራሉ። ለአገርም አንድ ነገር ማበርከት እንደቻሉ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው ነው ያጫወቱኝ። አገሪቱ ብዙ የተማረ ኃይል ያስፈልጋታል። ስለሆነም ያንን ኃይል በአግባቡ ቀርጾ በማውጣት ለአገር ማበርከት ሲቻል ደስተኛ ከመሆን ሌላ አማራጭ የለም ይላሉ።
«ዛሬ ላይ ሆኜ ድሮ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ያስተማሩኝን መምህራን ሳስባቸው እጅግ ደስታ ይሰማኛል። የእነዚህ ሰዎች ጥረት እኔን እዚህ አድርሶኛል። በመሆኑም እኔንም እንዲህ የሚያስቡኝ ልጆችን እያፈራሁ በመሆኔ ሁልጊዜም እደሰታለሁ» ሲሉ ይናገራሉ።
ህልም
ተወልደው ያደጉት ሐረር ከተማ 1957ዓ.ም ሲሆን፤ በወቅቱ የተማረና መምህር የሆነ ወይም በሌላ የመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚሠራ ትልቅ ቦታ ደርሷል ተብሎ ይታመናል። ይህንን ግብ መምታት ብቻ ነበር ህልማቸው። ይሁንና ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ነገሩ ተቀየረ፤ ሌላ መሆንንም ተመኙ፤ሌላ ማድረግም ታሰባቸው። ትልቅ የሚባለውን ደረጃ ለመያዝም ይጣጣሩ ጀመር። በተለይም በወቅቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዘርፍ ምንድነው? የሚለው ነገር አሳስቧቸው ነበር። እናም የዩኒቨርሲቲ መምህር መሆኑን ተገንዝበው ገቡበት፤ አደረጉትም።
ፕሮፌሰር ኤፍሬም በእያንዳንዱ ሥራቸው ውስጥ «ይህንን እሆናለሁ» ብለው ሠርተው አያውቁም። ያሰቡት ነገር ላይ ለመድረስ ግን ወደኋላ አይሉም። ሥራው በራሱ ደግሞ መሻሻሎችን ይዞላቸው ብቅ ስለሚል ለያዙት ተግባር የበለጠ ይታትራሉ። ይህ ደግሞ የመጨረሻውን የመምህርነት ማዕረግ አቀዳጅቷቸዋል። ከዚህ በኋላም ቢሆን የበለጠ ለመሥራት ጉልበት እንደሆናቸው ይናገራሉ።
ከቄስ ትምህርት...
ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንደዛሬው የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በሌለበት ወቅት ፊደል ለመቁጠር ልዩ ስሙ አደሬ ቲኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቄስ ትምህርት ለመማር ሄደዋል። በዚህም እስከ ዳዊት ድረስ ዘልቀዋል፤ ከዚያም ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመዝገብ ሄዱ። ይሁን እንጂ ብዙ ተማሪ በአካባቢው ስላለ ፈተና መውሰድ ግድ ሆነ። የቀረበላቸውን የመግቢያ ፈተና ወሰዱ። ፈተናው ንባብ በመሆኑ ብዙ ተማሪዎች ማለፍ ስለቻሉ ዕድሉ ወደ ዕጣ ተቀየረ።
ይህ በመሆኑ ዕድል ሳይቀናቸው ቀረ። ወደ ቤት ከሄዱ በኋላ ግን ለብዙ ቀናት መቆየት አልቻሉም፤ ቤተሰቡን ካላስገባችሁኝ ሲሉ አስቸገሩ። እነርሱም እፎይታን የሚያገኙት ትምህርት ቤት ሲያስገቧቸው መሆኑን ተገነዘቡና ከቤታቸው በቅርብ ርቀት በሚገኘው ልዑል ራስ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገቡ አደረጓቸው። እዚህም ቢሆን እንደዚያው ፈተናና ዕጣ ነበር። ሆኖም ተሳካላቸውና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ሐረር መድሐኒዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ 12ኛ ክፍል ተማሩ።
እዚህ ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ በትምህርታቸው ታታሪ ከሚባሉት መካከል አንዱ ናቸው። ሁልጊዜም ከሽልማት ርቀው አያውቁም። ከትምህርት ቤቱ አልፎ ከቤተሰቦቻቸው ሽልማት ይበረከትላቸዋል። ዩኒቨርሲቲ ከገቡም በኋላም ቢሆን ይኸው ሁኔታ ነው የቀጠለው። በዚህ ሥራቸው ዛሬ ላይ የመጨረሻውን የመምህርነት ማዕረግ ማለትም በመድሀኒትና የአካል መስተጋብር የትምህርት መስክ የፕሮፌሰርነትን ማዕረግ አግኝተዋል።
የዩኒቨርሲቲ ቆይታ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፋርማሲ ትምህርት ቤት የፋርማሲ ተማሪ ሲሆኑ ነበር ከቤተሰብ መለየት የጀመሩት። በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲቀጥሉ ስዊዲን ከሚገኘው ካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት ጋራ በጥምረት ስለሚሠራ ስዊዲን በመሄድ ጭምር ትምህርቱን ተከታትለው ውጤታማ ሆነዋል። የፋርማሲ ትምህርት ክፍል የተለያዩ ክፍሎች አሉት። ስለሆነም አንዱን በመምረጥ ስፔሻላይዝድ ማድረግ ስለሚጠበቅባቸው «ፋርማኮሎጂ»ን መርጠው መከታተል ሲጀምሩም በፍላጎታቸው ላይ የተመሰረተ ስለነበር ግባቸው ተሳክቷል። የትምህርት ዓይነቱ የአንድን አካል ውጤታማ ጤንነት ለመጠበቅ መድሐኒቶችንና አካልን መስተጋብራዊ ግንኙነት በሚገባ ማወቅ ነው። ስለዚህም ህመሙን አጥፍቶ በደህናው ጊዜ የነበረን ሰውነት ማምጣት መቻል ስለነበር በሚገባ ተወጥተውታል።
የመድሐኒትና የአካል መስተጋበር ሳይንስን የሚያጠና የትምህርት መስክን ወይም ስነ መድሐኒትና የአካል መስተጋብር ሊባል የሚችለውን ትምህርት በሚገባ በማጥናት ዓለም አቀፍ የምርምር መጽሄቶች ላይ አሳትመዋል። መስኩን የመረጡበት ዋነኛ ምክንያት መድሐኒት ሲሰጥ ወስዶ መጠቀም ብቻ ሳይሆን መድሐኒቶቹ እንዴት አድርገው ይፈውሳሉ? የሚለውን ለማወቅ ስለሚፈልጉ ነው። በመጨረሻ ዓመት ላይ የሚሠራውን የመመረቂያ ጽሑፋቸውንም በዚህ ዙሪያ ያደረጉት ግባቸው መሳካቱን ለማረጋገጥ እንደሆነ አጫውተውኛል።
«መድሐኒት ማግኘት በጣም ደስ ይላል። ሰዎች ድነው ማየት ከምንም በላይ ይማርካል። ድሮ እንኳን ልጆች ሆነን የአገር ባህል መድሐኒት አዋቂ ተብሎ የሚጠራው ሰው ፊታችንን ሲያባብሰንና ስንድን የሚሰማን ስሜት ቀላል አይደለም። እናም እኔም ህመምተኞች ይህ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ስል ይህንን ሙያ መርጫለሁ» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ አገሪቱ በተፈጥሮ የታደለች ስለሆነች ብዙዎችን የምንፈውስበት መድሐኒት በቀላሉ ማግኘት የምንችልበት አማራጭ እንዳለ ይናገራሉ።
የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ኦስትሪያ ከሚገኘው ከቬይና ዩኒቨርሲቲ እና የድህረ-ዶክትሬት ዲግሪያቸውን እዚያው ኦስትሪያ በሚገኘው ቬይና ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ዶክትሬታቸውን ሲማሩ በፋርማኮሎጂ የሠሩት የመመረቂያ ጽሑፍ ይበልጥ እንዲነቁ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። ከዚያም የትምህርት መስኩ ይበተናልና አንድ ነገር እንዲመርጡ ተገደው ስለነበር «ኒሮ ሳይንስ» የሚባለውን በመምረጥ ትምህርቱን መከታተል ጀመሩ። ትምህርቱ በአዕምሮ ዙሪያ የሚያጠና ሲሆን፤ አጠቃላይ አካላችንን በመምራት የሚያስተዳድረው እርሱ ስለሆነ በዚህ ላይ እየተማሩና እየተመራመሩ ቆዩ። በተለይም ከዘር ጋር የተያያዘ በሽታ፣ የመርሳትና ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጡ በሽታዎች ላይ በስፋት አተኩረው ይሠሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ለሌሎች የተሻገረ እውቀት
መድሐኒት የሚገኘው በሁለት ዓይነት መልኩ ነው። የመጀመሪያው በአጋጣሚ የሚገኝ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሽታውን ማዕከል ያደረገ ሥራ ማከናወን ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሚያስረዱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ አሁን እየተሠራ ያለው በሁለተኛው አማራጭ ነው። በአገር ባህል መድሐኒቶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እየሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በዚህ ዘርፍ በርካታ ምርምሮችን አድርገዋል። በምርምር የታገዙ ሥራዎችንም ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከ104 በላይ ጽሑፎችን በዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ አሳትመው እውቀታቸውን አሰራጭተዋል።
በተለይም «ኒሮ ሳይንስ» ላይ ያተኮሩት ሥራዎች የገነኑ ሲሆን፤ በሽታዎች እንዴት ይመጣሉ? መፍትሄያቸው ምን መሆን አለበት? ለመቋቋምስ እንዴት ይቻላል? የሚለውን ይዘት ያካተተ ሥራ በመሥራት ይታወቃሉ። የአገር ባህል መድሐኒቶችን የያዙ፤ በተመሳሳይ ጫት ላይ እየተከናወነ ያለውን ጥናት በሚመለከትም ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ አሳትመዋል። የታተሙት ደግሞ በኒሮ ሳይንስ መጽሔቶች ላይ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ የአገር ባህል መድሐኒቶች ላይ በሚሠሩ ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ ነው።
«የሚፈሰው ጉልበት መጠንና የሚፈጀው ጊዜ የውጤታማነት መሰረት ይሆናል። ምክንያቱም ውጤቱ ትልቅና ትንሽ ይሆናል» ብለው የሚያምኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ከ20 ዓመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር፣ በመመራመር፣ እና ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ቆይተዋል። ከ100 በላይ የማስትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን፣ ሦስት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን አማክረውአስመርቀዋል። በአሁኑ ጊዜ ከ20 በላይ የማስትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን፤ 10 ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን በማማከር ላይ ይገኛሉ። በርካታ በአገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት ስብሰባዎች ላይ ተሳትፈዋል፤ ጥናቶችን አቅርበዋል። የበርካታ ማህበራት የቦርድ አባልና የበርካታ ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ገምጋሚ ሆነው አገልግለዋል።
ዩኒቨርሲቲውን በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ ሆነው መርተዋል፤ አገልግሎትም ሰጠተዋል። ለአብነት በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የድህረ ምረቃ ዳይሬክተር፣ የጤናሳይንስ ኮሌጁ ቺፍ አካዳሚ ኦፊሰር ነበሩ። በአሁኑ ጊዜም የፋርማሲ ትምህርት ቤት ዲን ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ። በብዙ ዓለም አቀፍ የምርምር ህትመቶች ላይ የአድቫይዘር ቦርድ አባል በመሆንና ሳይንሳዊ ህትመቶች ላይ ይሠራሉ። ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የምርምር ሥራዎችን በመገምገምም ይታወቃሉ።
በአገር ውስጥ ደግሞ ፋርማሲ የምርምር ህትመት ላይ የቦርድ አባል በመሆን በተባባሪ ኤዲተርነት ያገለግላሉ። ብዙ ጊዜያቸውን የሚወስደውም ይህ የግምገማ ስርዓቱ ነው። ምክንያቱም አገር አምኖና አዋቂ ነው ብሎ ስለሚልከው እንዲሁም በተለያዩ በጉዳዮች ዙሪያ ጥልቅ ምርምር ያደረገ ሰው ስለሚመለከተው በውሳኔው ጠንቃቃ መሆን፣ በጥልቀት ማየትና አስተያየቱ ጉዳዩን የሚያጎለብት መሆን ይጠበቅበታል። ስለዚህም እርሳቸውም ይህንን ከማሟላት አኳያ ስለሚተጉ ብዙ ጊዜ ይሰጣሉ። ይህንን ሲያደርጉ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ምርምር ህትመቶች ግምገማ ያደርጋሉ።
ወረቀቶቹ በብዛት የሚመጡት ከአፍሪካና ኤዥያ እንዲሁም ከአውሮፓ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ከቻይና የሚመጣው እየሰፋ ነው። ተጠናቆ የሚሰጠው በ15 ቀን ውስጥ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮም ሆነ የአፍሪካ ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ በሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ላይ ጽሑፎችን ያቀርባሉ። የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ የሀገረሰብ መድሐኒት ከየት ወዴት የሚለውን መጽሐፍ በሚያዘጋጁበት ወቅት ገምጋሚ ሆነው ሠርተዋል። በኤች.አይ.ቪና መሰል በሽታዎች ዙሪያ በሚዘጋጁ መጣጥፎችና መጽሔቶች ላይ ይሳተፋሉ።
መጀመሪያ ሥራቸውን የጀመሩት ከትውልድ ቀያቸው ብዙም ሳይርቁ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ አሰበ ተፈሪ ሆስፒታል በፋርማሲስትነት ነው። ከዚያም ሐረር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ተቀይረው ከቤተሰባቸው ጎን ሆነው ሠርተዋል። ቀጥለውም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር በአዲስ አበባ ስለመጡ በዚሁ ቀርተው የተማሩበትን ዩኒቨርሲቲ ወደ ማገልገል ገብተዋል።
በልጅነት «ሼፍነት»
በቤት ውስጥ እያሉ እናታቸውን በተለያየ መልኩ ያግዙ የነበሩት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ እናታቸው ወደ ገበያ ሲሄዱም ሆነ ከቤት ሲወጡ ይህንን አድርግና ጠብቀኝ ይባላሉ፤ የምትሄዱበት ቦታ አይታወቅምና ሁሉን ነገር መሞከር አለባችሁ ይሏቸዋል። እናም እንግዳዬም ቤት ውስጥ ምግብ አብስለው ቤተሰቡን ይመግባሉ። በዚህ ደግሞ ጥሩ ሼፍ እንደሆኑ በቤተሰቡ ተመስክሮላቸዋል። በእርግጥ ልክ እንደእናታቸው እጅ የሚያስቆረጥም ወጥና ሌሎች ምግቦችን አያበስሉም፤ ዓይነቱም ቢሆን የሚከብድና የበዛ አልነበረም። ሆኖም በየጊዜው በሚያደርጉት የመሥራት ጉጉት ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን እንዳይራቡ የማድረግ አቅም ነበራቸው። ይህ ደግሞ አብሮ ተከትሏቸው ተጉዟልና ባህር ማዶ ሲሄዱ ምንም ሳይቸገሩ ምግብ አብስለው እንዲመገቡ ረድቷቸዋል። ሌሎች የአያት ልጅ ቅምጥሎችን እንኳን ሳይቀር ሽንኩርት አከታተፍና ምግብ ማብሰል ያስተምሩ ነበር። ዛሬም ቢሆን ባለቤታቸውን ቀድመው እቤት ከተገኙ ምግብ በማብሰል ያግዛሉ። ይህ የሴት ሥራ ነው የሚል አስተሳሰብ በእርሳቸው ዘንድ የለም። ገበያም ቢሆን ሄደው ለምግብም ሆነ ለሌላ አገልግሎት የሚውለውን አስቤዛ የሚሸምቱት እርሳቸው ናቸው።
አብሮነት
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ህብረተሰብ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጣቸው ነበር። እናም ይህንን ተከትሎ «አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ»የሚባልም ተካቶ ይሰጣል። ይህ ደግሞ አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዝ ስለነበር ብዙው ተግባር በድራማ መልክ ይከወናል። ገጸባህሪያቱን ወክለው እንዲተውኑ ይደረጋሉ። በዚህም ማንኛውንም ባህሪ ተላብሰው ቢጫወቱ የተዋጣላቸው ነበሩ። በወቅቱም ምርጥ ተዋናይ የመሆን ህልም እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚለወጡት ነገሮች ሳቢያ እየተውትና ሌሎችን ነገሮች እየተኩበት ሄደዋል።
የህብረተሰብ ትምህርት ማህበራዊ ግንኙነታቸው እንዲዳብር ሁነኛ ሚናን ተጫውቷል። ከሰዎች ጋር የመግባባትና ነገሮችን በህብረት የማድረጉ ጉጉት እንዲያድርባቸውም አስችሏቸዋል። አንድ ነገር የማወቅ ጉጉታቸውም እንዲጨምርና ሁሉንም ነገር መሞከር ለበለጠ ውጤታማነት እንደሚያበቃ የተማሩትም በዚህ ዓይነት ተሳትፎ ውስጥ በማለፋቸው ነው። በባህሪ በጣም አስቸጋሪ ከሚባሉት ተርታ እንዳይመደቡ፤ ዝምተኛና ነገሮችን አገናዝቦ መወሰንን እንዲጀምሩ ያደረጋቸው ይህ ተሳትፏቸው ነው።
«ልጅነትን ዳግመኛ ባስባትና ዕድሉን ባገኝ ማየት የምፈልገው ነፃ የሆነ ሃሳብን ማራመድን፣ አለመጨነቅና አለማዳላትን እንዲሁም ንጹህ ልብን ይዞ መጓዝን ነው። ስለ እኔ የሚያስበውም ብዙ ስለሆነ ችግሮችን በቀላሉ ማለፍ እችልበታለሁና ይናፍቀኛል» በማለት የልጅነት ዘመናቸውን የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ በልጅነት ዕድሜያቸው የእግር፣ የእጅና የቅርጫት ኳስ በመጫወት የሚያክላቸው አልነበረም። በብይ ጨዋታም ቢሆን የተካኑ ነበሩ። ቼዝ መጫወትም በጣም ያስደስታቸዋል። በውድድር ባይደገፍም ጥሩ ተጫዋች መሆናቸውን ለማመላከት ለትምህርት በሄዱባቸው ቦታዎች፣ እንዲሁም ኮንፍረንሶች ላይ ሲሳተፉ ተጫውተው ያሸንፋሉ። እሁድ እሁድ ሥራ ካልበዛባቸው ጓደኞቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን በመያዝ እንጦጦ ላይ መናፈስን ይመርጣሉ።
ፍቅር በአጋጣሚ
ለሥራ ጅጅጋ በተመደቡበት ወቅት ነበር የዛሬዋን ባለቤታቸውን ያገኟት። አብሯቸው የተመረቀ የልብ ጓደኛቸው ጋር ሲመላለሱ ዓይናቸው አረፈባት፤ ልባቸውም ተመኛት። ግን ደግሞ የጓደኛቸው ሚስት እህት ነችና እንዴት ይህንን ማድረግ ይቻላቸው፤ ግራ ተጋቡ። ነገር ግን ወደዋት ነበርና ያሰቡትን ከማድረግ ለመቆጠብ አልቻሉም። እናም ቅድሚያ ለሚወዱት ጓደኛቸው ጉዳዩን አጫወቱት። እርሱም ተስማማና ቅርርቡ ተጠናከረ። ጎልብቶም ለትዳር በቃ። በዚህ ደግሞ ዛሬ ድረስ የማይቆጩበትን ተግባር እንዳከናወኑ ይሰማቸዋል። ምክንያቱም ባለቤታቸው ለስኬት እንዲበቁ ሁልጊዜም ትተጋለች።
ለባሏም ሆነ ለልጆቿ ትልቅ ክብር አላት። ይህ ደግሞ በቤት ውስጥ ምንም ዓይነት መቃረን ሳይፈጠር 21 ዓመታትን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል። ሦስት ልጆች አፍርተዋል።
«ልጆቼን በራስ የመተማመን ባህላቸውን ነጥቄ ማሳደግ አልፈልግም። ምክንያቱም የቀደምነው ልጆች ያጣነው ብዙ ነገር አለ። እንደፈለገን እንድንናገር አይፈቀድልንም፤ ጎረቤት ወይም ትልቅ ሰው በአካባቢው ካለ ተደብቀን እንድንቀመጥ ወይም ወደውጪ እንድንወጣ ይደረጋል። ይባስ ብሎ መናገር ባለብን ጉዳይ እንኳን ዕድሉ አይሰጠንም። አንተ ልጅ ነህ፣ ልጅ ፊት... እያሉ ያርቁናል» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ከቤተሰብ መማር የሚገባቸውን ባለማግኘታቸው ስለሚቆጫቸው ልጆቻቸው በራሳቸው እንዲወስኑ አድርገው እንዳሳደጓቸው ይናገራሉ።
በእርግጥ ይህንን ባህል ሙሉ ለሙሉ መቃወም ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም በእያንዳንዱ ነገር ላይ ቁጥብነትን ያስተምራል፤ ለሰዎች አክብሮት እንዲኖረንም ያደርጋል እንዲሁም ቅድሚያ ለራስ የሚለውን ነገር አስቀርቶ አንተ ትብስ የሚለውን ባህሪ እንድንላበስም ዕድል ይሰጣልም ሲሉ አጫውተውኛል። የአንድ ሴት ልጅና የሁለት ወንድ ልጆች አባት የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ሁለቱ ልጆቻቸው ዩኒቨርሲቲ የገቡ ሲሆን፤ እንደቀደመው ዛሬ ላይ የልጆችን ውሳኔ በቤተሰብ ጫና ማስቀየር አይቻልምና ፍላጎታቸውን ያማከለ ምርጫ እንዲኖራቸው አድርገዋቸው እንደነበር ይናገራሉ።
የመጨረሻው ልጅም ቢሆን የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ «የዛሬ ልጅ ከእኛ ጊዜ ልጅ የተለየ ነው። ድሮ ተምሮ ራሱን ማውጣት ከቻለ ብቻ ነው ኑሮን በራሱ የመምራት አቅም ይኖረዋል የሚባለው። ዛሬ ግን ባይማርም የራሱን መስመር ይዞ በተለያየ መልኩ ተሰማርቶ ራሱን ማሸነፍ ይችላልና ሥራውን በትምህርት እንዲያግዝ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ አደርጋለሁ» ብለውኛልም።
«የቤት አባወራነትን በሁለት መልኩ ማየት ያስፈልጋል። የመጀመሪያው በቤት ውስጥ ጊዜ ሰጥቶ ማሳለፍ ልኬታው ምንድነው? የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ቤተሰብ በሚገባውና በሚረዳው ልክ ቤቱ ላይ ምሰሶ የሚሆን ተግባር መከወን ነው። ስለዚህም ከዚህ አኳያ ሲታይ በሚፈለገው ልክ ነኝ ባይባልም አይደለሁም ማለት ግን አይቻልም። ቤተሰቦቼ ባማሳልፈው ተግባር እጅግ ደስተኞች ናቸው። ውሎዬንም በሚገባ ይደግፉታል። በተለይ ባለቤቴ ሥራን ለኑሮዬ በሚመች መልኩ ስለማውለው ታግዘኛለች እንጂ አትከፋብኝም፤ ጊዜ አትሰጠኝም የሚል ነገር አታነሳም። ልጆቼም ቢሆኑ እንዲሁ ናቸው» የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ጊዜ ሲያስፈል ጋቸውም ፈቃድ እንዲጠይቁ ግልጽ የሆነ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ ዘና ማለት ሲፈልጉም አብረዋቸው እንደሚሄዱና ብዙም ባይሆን ደስተኛ እንደሚያደርጓቸው ይናገራሉ። ሥራው በሰዓት የተገደበ ባለመሆኑ ግን የሚፈለገውን ጊዜ ሰጥቻለሁ ብለው እንደማያምኑም ነው ያጫወቱኝ።
ሽልማትና የቀጣይ እቅድ
በኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር አንድ ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ተመራማሪ በሚል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በተለያዩ የምርምር ሥራዎቻቸውና በተሳተፉባቸው መድረኮች ሁሉ እንዲሁም ባማከሩበት ዘርፍ በርካታ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል። ዛሬ ደግሞ የመጨረሻው የመምህርነት ማዕረግ ፕሮፌሰርነትን ከዩኒቨርሲቲው አግኝተዋል። «ሽልማቴ ተማሪዎቼ ናቸው። ሁልጊዜ በአዲስ መርህ ተራምደው ለአገራቸው አዲስ ነገር ሲያበረክቱ ማየት ለእኔ ትልቁ ሽልማቴ ነው» የሚል እምነት አላቸው። ይህንን አስቀጥሎ ለመሄድ ደግሞ የቀጣይ በርካታ እቅዶችን ይዘዋል። በጥምረት የሚሠሩ ሥራዎቹን ማስቀጠል አንዱ ሲሆን፤ በሀገረሰብ መድሐኒቶች ዙሪያ በርካታ የምርምር ሥራዎች ተከናውነዋልና እነዚህን ሥራዎች ወደ ፋብሪካ ሄደው አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።
መልዕክት
የፋርማሲ ሙያ የተለየ ተሰጥኦን የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም በአመለካከት ብቃት የሚወሰን ነው። ስለዚህም ንግድንና ሙያን አቀናጅቶ መጓዝ አስቸጋሪ ነው። መድሐኒት ከመሳሪያ ቀጥሎ ለደህንነት አጋዥ የሆነ መሳሪያ ነው። እናም የሰውን ህይወት ለመታደግ ተብሎ የማይተገበር ከሆነ እንደሌሎች ሸቀጦች እንጂ እንደ መድሐኒት አይሆንም። ትርፍ የሚገኝበት ሰዎችን በማትረፍ እንጂ ገንዘባቸውን እንዲያፈሱና እንዲገኙ በማድረግ መሆን የለበትም።
የፋርማሲ ትምህርት የተለየ ሸቀጥ የሚከናወንበት ነው። ስለሆነም የተለየ ትምህርትና የተለየ ስነ-ምግባር ያስፈልገዋል። ይህንን የተማረም ሰው ልዩ መሆን ይጠበቅበታል። ነገር ግን ባለሙያ ያልሆነ ሰው የመድሐኒት እደላ ያደርጋል፣ ህጋዊ ያልሆኑ መድሐኒቶች በስርጭት ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል። ብዙ በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ትክክል ያልሆኑ ተግባራት አሉ። እናም እነዚህን ለመፍታት በማህበሩ ደረጃ ሦስት ነገሮች ላይ ጥናት ለማድረግ እየታሰበ ነው። እነርሱም የባለሙያው ጥንካሬ ላይ፣ ትምህርት ጥራቱና ስነምግባር ላይ ሲሆኑ፤ ከጥናቱ በኋላ የሚገኘውን ውጤት ማዕከል በማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀመጥ ይሆናል። ነገር ግን አሁን ላይ ከመስማት ባለፈ ይህን አድርጉ ማለት ይከብዳል። የእያንዳንዱ ሰው አመለካከት በጉዳዩ ዙሪያ መቀየር እንዳለበት ይታመናል። ለሰዎች እንጂ ለገንዘብ ትኩረት መስጠት ቅድሚያ መሰጠት የለበትም፤ የሚለውን ሁሉም መውሰድ ይኖርበታል። ሃሳብን ወደ ተግባር ለመቀየር እጅግ ፈታኝ የሚሆነው የአቅርቦት ችግር ስለሆነም በአገሪቱ ያለው ተመራማሪ የሃሳብ ችግር ስለሌለበት በዚህ ዙሪያ አገሪቱ መሥራት ይጠበቅባታል ይላሉ።
«ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ መሠራት እንዳለበት አምናለሁ። እዚህ ደረጃ ላይ የሚሠራው ያልተማረና ሥራ የሌለው ነው። ከመሰረቱ ያልተያዘ ነገርን ከቆመ በኋላ ማቃናት እጅግ ከባድ ነው። አሁን ላይ እገሌ እንዲህ ሆነ ቢባል ብዙ አይጠቅምም። ለዚያ ሰው መበላሸትም ሆነ ደህንነት መሰረቱ መነሻው የሚሆነው። አገሪቱ ትኩረት አድርጋ ልትሠራበት የሚገባው በተማረ ኃይልና ጠባቂ ባልሆነው ሰው ታች ላይ የሚማሩትን ልጆች ማቅናት መሆን ይኖርበታል። ዛሬ ላይ እኔና መሰሎቼ ለዚህ የበቃነው በራሳችን ጥረት በመሆኑ ይህ ትውልድ ይህንን ያህል መስዋዕትነት መክፈል የለበትም»ይላሉ። ከእንግዳዬ ጋር ብዙ ቁም ነገሮችን ተጨዋውተናል። ይሁንና ጊዜና ቦታ ገደበኝና ከህይወት ተሞክሯቸው ጥቂቱን አካፈልኳችሁ። መልካም ዕለተሰንበት!

 

ጽጌረዳ ጫንያለው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።