ድንገተኛ የሕክምና ወጪንና ጉዳቱን የማስቀረት ቁልፍ መላ

13 Feb 2018

የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ በአመዛኙ የአርሶ አደርና አርብቶ አደር የሕብረተሰብ ክፍሎች የጤና ተጠቃሚነትን ለማበረታታት እንዲያስችል ከ2003 ወዲህ በሃገሪቱ የገጠር ክፍሎች ስለተተገበረው ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት በቅርቡ ለጋዜጠኞች እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ በማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ትግበራ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በመድኑ ተጨማሪ ወረዳዎችን ለማካተት እየተደረገ ስለሚገኘው ዝግጅት የቀረቡትን ማብራሪያዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።
የማሕበረሰብ አቀፍ መድን አገልግሎት አስፈላጊነት
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከሠሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት 11 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የጤና ወጪውን መክፈል ባለመቻሉ የተነሣ ብቻ በጤና ተቋማት አይገለገልም፡፡በዓለም ላይ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለህክምና በሚያወጡት ወጪ ብቻ በቀጥታ ወደ ድህነት ይገፋሉ፡፡አገራት ከህመም በፊት በሚደረግ አነስተኛና ተከታታይ መዋጮ ሰዎች ህመም ሲያጋጥማቸው የህክምና አገልግሎት ያለክፍያ የሚያገኙበትን የጤና መድን ስርዓት በመዘርጋት ከዚህ ችግር መውጣት ችለዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት አንድ ሰው በዓመት ሶስት ጊዜ የጤና ተቋማትን መጎብኘት እንደሚኖርበት ያስቀምጣል፡፡ በኢትዮጵያ ግን በአማካይ አንድ ሰው ወደ ጤና ተቋማት የሚሄደው በሦስት ዓመት ሁለት ጊዜ ነው፡፡ይህም ከስታንዳርዱ አምስት እጥፍ በታች ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሕክምና ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣት፣ የግንዛቤ ችግሮች እና በህክምና ወቅት የሚጠየቀው ያልተጠበቀ የህክምና ወጪ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም ህብረተሰቡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ባለማግኘት ሳቢያ ሊደርስበት የሚችለውን ችግር በዘለቄታዊ ለመፍታት መንግስት የጤና መድን ኤጀንሲን በአዋጅ ቁጥር 191/2003 በማቋቋም የማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ስርዓትን ተግባራዊ አድርጓል።
ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ከህብረተሰቡ፣ ከመንግስት እና ከሌሎች ምንጮች ሀብትን በማሰባሰብ እና በህብረተሰቡ መካከል የእርስ በእርስ መደጋገፍ ስርዓትን በመፍጠር ተጠቃሚው የጤና አገልግሎት በሚሻበት ወቅት አብዛኛውን ከኪስ የሚከፈል ወጪ በማስቀረት ፍትሐዊ፣ጥራት ያለው እና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያገኝበት ስርዓት ነው።በገጠርና በከተሞች አካባቢ መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣በተናጠል ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ የጤና ወጪ ጫና ማስቀረት እና በከፍተኛ የጤና ወጪ ምክንያት ቤተሰቦች ወደ ከፋ ድህነት እንዳይገቡ ለማድረግም ተመራጭ መፍትሔ ነው።
የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሙከራ ትግበራና የደረሰበት ሽፋን
በ2003 ዓ.ም የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የሙከራ ትግበራ መመሪያ ከወጣ በኋላ 2004 ዓ.ም ላይ በኦሮሚያ፣ትግራይ፣አማራና ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተመረጡ አስራ ሶስት ወረዳዎች የሙከራ ትግበራ ተካሂዷል።በ13ቱ ወረዳዎች የሙከራ ትግበራ የግምገማ ጥናት ከተካሄደ በኋላ ፥በ2008ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና መድን አገልግሎቱ እንዲስፋፋ ተደርጎ በ201 ወረዳዎች እንዲጀመር ተደርጓል።ይህ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በ289 ወረዳዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
አገልግሎቱ በከተሞችም መደበኛ ባልሆነ ክፍለ-ኢኮኖሚ ህይወታቸውን የሚመሩና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተሞች ነዋሪዎችን ጭምር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተስፋፋ ነው ።ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ለሙከራ በተመረጡ 10 ወረዳዎች ባለፈው ህዳር ወር አገልግሎቱ በይፋ ተጀምሯል።
አመታዊ የአባልነት መዋጮ መጠንና የሚሸፈኑ አገልግሎቶች
በአሁኑ ወቅት የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አባል መሆን የሚቻለው በቤተሰብ ደረጃ ነው፡፡ መዋጮ የከፈለ ወይም የተከፈለለት አባወራና እማወራ እንዲሁም መክፈል የማይችሉ እማ/አባወራ ሙሉ በሙሉ አባል ይሆናሉ። አገልግሎቱ ከሙከራ ትግበራ በኋላ ዓመታዊ ክፍያው ከነበረበት 132 ብር በገጠር የሚገኙ አባላት 240 ብር በዓመት ከፍለው እንዲገለገሉ ተደርጓል። በገጠር ከተሞች የሚኖሩ ተጠቃሚዎች ደግሞ 350 ብር በመክፈል አባል መሆን ይጠበቅባቸዋል። አገልግሎቱ በቀጣይ በትልልቅ ከተሞች ሲስፋፋ አመታዊው የአባልነት ክፍያ 500ብር እንዲሆን ተወስኗል።በሂደትም የገቢ መጠንን ያገናዘበ የመዋጮ መጠን እንደሚተገበር 2008 ዓ.ም በወጣው የማስፋፊያ መመሪያ ላይ ሰፍሯል።
የጤና መድኑ ስራ በጀመረባቸው ወረዳዎች ላይ የሚገኙ ተገልጋዮች የመድን አገልግሎት እንዲሰጡ ውል ባሰሩ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የተመላላሽ ሕክምና፤የተኝቶ ሕክምና፤የቀዶ ህክምና፤በሕክምና ባለሙያዎች የታዘዙ የምርመራ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የተገኙ ውጤቶች
በአገልግሎቱ በታቀፉ ወረዳዎች ከ15ሚሊዮን በላይ ህዝብ የጤና መድን ሽፋን አግኝቷል።የቤተሰቦች የጤና ወጪ ጫናን በመቀነስ ከከፍተኛ የጤና ወጪ መታደግ እየተቻለ ነው።የጤና መድኑ በተተገበረባ ቸው አካባቢዎች የሚገኝ ሕብረተሰብ የጤና አገልግሎት አጠቃቀም መጠኑ ጨምሯል። በቤተሰብ ደረጃ የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት በማጠናከር እናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት ባስፈለጋቸው ጊዜ እንዲያገኙ አስችሏል።
የጤና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል ጭምር የራሱን ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣መክፈል የማይችሉ የድሃ ድሃ አባላት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ የጤና አገልግሎት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን እገዛ እያደረገ ይገኛል።በተጨማሪም የዜጎች ተሳትፎም እንዲያድግ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
የጤና መድኑን የሚመጥን የጤና አገልግሎት ጥራት የማረጋገጥ ኃላፊነት
የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ወረዳዎች ጤና ተቋማትን ዝግጁ ማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ኤጀንሲው፣ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ጤና ቢሮዎች በጋራ ተቋማቱን ለማጠናከር እየሠሩ ናቸው።የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት ጥራት ኮሚቴ ማቋቋም ጀምረዋል።በመላ ሀገሪቱ ጤና ተቋማት ከተደራሽነታቸው ባሻገር ተገልጋዮች የተሟላ አገልግሎት የሚያገኙባቸው ለማድረግ የማሻሻያ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።የሚያጋጥመውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ወደ ስራው እንዲገቡ እየተደረገ ነው፥መጋዘኖችም እየተስፋፉ ይገኛሉ።ከዚህ በተጨማሪ የመድሀኒት ስርጭት ስርዓቱን መለወጥ ያስፈልጋል።
ለዚህም የመድሀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጄንሲ በድጋሚ ይዋቀራል።በእስካሁኑም የመድሃኒት አቅርቦቱ መሻሻሎች አሳይቷል።ከጊዜ ወደ ጊዜ የሃኪሞች ቁጥር እየጨመረ ነው።አሁን በየወረዳው የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ጠቅላላ ሀኪሞች አሉዋቸው።ጤና ባለሙያዎችን ብቃት ማሳደግ አንዱ የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጀንዳ ሲሆን ርህሩህ፣ተንከባካቢና አክባሪ ሐኪሞችን ለመፍጠር አምባሳደሮች በመምረጥ እየተሰራ ይገኛል።
የጤና መድኑን ሽፋን የማሳደግ ውጥን
የጤና መድን አገልግሎቱ ባልተጀመረባቸው ክልሎች አገልግሎቱን ለማስጀመር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ሀረሪ እና ድሬዳዋ መመሪያ ጸድቆ የአባላት ቅስቀሳ እና የምዝገባ ስራ እየተከናወነ ነው።በኢትዮ ሶማሌ ክልል እና ጋም ቤላ ክልል የትግበራ መመሪያ ወጥቷል፣በአፋር ክልል መመሪያ ለማጽደቅ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ይገኛል።
አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ክልሎች በተያዘው ዓመት በ197ወረዳዎች የአባላት ቅስቀሳና የምዝገባ ስራ እየተሰራ ነው።የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን አካል የሆነው የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ሲሆን አንድን ወረዳ ትራንስፎርም ለማድረግ በወረዳው በዚህ የጤና መድን መታቀፍ ያለባቸው ነዋሪዎችን የመድኑ አባል ማድረግ ሲቻል በመሆኑ ማሕበረሰብ አቀፍ የጤና መድኑ በ2012ዓ.ም መደበኛ ባልሆነ ክፍለ-ኢኮኖሚ የተሰማሩ ከ80-85 በመቶ ዜጎች እንዲያቅፍ ይጠበቃል።
በመድኑ የትግበራ ሂደት ያጋጠሙ ዋና ዋና መሰናክሎች
በየአስተዳደር እርከን ያለው አመራር አገልግሎቱን በተመሳሳይ የባለቤትነት ኃላፊነት በሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ አለመሆኑ አንዱ መሰናክል ነው።ስርዓቱ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ሌላኛው ፈተና ነበር።በሌላ በኩል የጤና ተቋማት ዝግጁነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት በትግበራ ሂደት ከታዩ ችግሮች አንዱ ነበር።

 በሪሁ ብርሃነ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።