በፍቅር ገመድ የተጎነጎኑት-ማንፍሬድ እና አፍሪካ Featured

11 Mar 2018
ሚስተር ማንፍሬድ ሴት ሚስተር ማንፍሬድ ሴት

ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ አንድ የቱሪስቶች ማረፊያ ሆቴል ቁጭ ብዬ ወዳጄን እየጠበኩ ነው። ከዚህ ጓደኛዬ ጋር በቀትር ለመገናኘት የተጣደፍነው በአፍሪካውያን በተለይም በኢትዮጵያውያን ፍቅር ከተለከፉ አንድ ጀርመናዊ የእድሜ ባለፀጋ ጋር ተገናኝተን በጋራ ለመጨዋወት ነበር። እኚህ ባለ ታሪክ ከእድሜያቸው ግማሽ በላይ በተካኑበት የሙያ መስክ እና በበጎ ፍቃደኝነት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጠይም ከጥቁር፤ ነጭ ከቀይ ዳማ ሳይለዩ፤ ያላቸውን ሳይሰስቱ እንካችሁ ብለዋል። እኛም ይህን ተገንዝበን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ግማሽ ምዕተ ዓመት በአፍሪካ አህጉር በመቆየት የቋጠሩትን ታሪክ አፍታተን ለናንተ ለአንባቢዎቻችን ለማካፈል የህይወት እንዲህ ናት ዓምዳችን እንግዳ አደረግናቸው። (ሁሉንም የዘመን አቆጣጠር በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር መሆኑን ልብ ይሏል)

ማንፍሬድ ማን ናቸው?
ከሠላሳ አገራት አንድ መቶ ሚሊዮን ሰዎችን ያሳተፈው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አብቅቶ ጥቁሩ ሰማይ በሰላም ብርሀን ለመተካት ዳርዳር የሚልበት ዘመን ነው። የጎርጎሮሳውያኑ 1944። በተለይ የዓለም ታላላቅ አገራት በጠንካራ ክንዱ እና በቁንጮ ጭራቅነቱ በሚታወቀው አዶልፍ ሂትለር የሚመራውን የናዚ ስርዓት ለመገርሰስ ያለ የሌለ ሀይላቸው እየተጠቀሙ ነው። ታዲያ እናት ልጇን አትውጠው ትደብቅበት አጥታ በምትቅበዘበዝበት ዘመን አንድ ተስፈኛ ህፃን በጀርመኗ በርሊን ከተማ ተወለደ። የ74 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ ሚስተር ማንፍሬድ ሴት።
የዓለሙን ጩሀት በቅጡ የማይረዳው ህፃን ኑሯቸውን በዝቅተኛ ገቢ ከሚደጉሙት ከአናፂ አባቱ እና ከቤት እመቤቷ እናቱ ጋር በጀርመን በርሊን የኑሮ ውጣ ውረድን «ሀ» ብሎ ጀመረ። በወቅቱ የጀርመኑ ናዚ የአገሩን ዜጎች «ዓለም ላይ ካሉ የሰው ዘሮች የተለዩ እና ምርጦች» እያለ ቢያሞካሻቸውም 8 ቤተሰብ ያቀፈውን ጎጆ ግን በችግር ከመቆራመድ፤ብሎም በድህነት ጠንካራ ክንድ ከመደቆስ አልዳነም ነበር። የዚህ ዳፋ በቀጥታ ለማንፍሬድ ደርሶታል። ማንፍሬድ የናዚ ጀርመን ተገርስሶ ሲወድቅ የ9 ወር ህፃን ነበር። ስርዓቱን በደንብ ማየት ባይችልም የአዶልፍ ሂትለር ጦስ ይዞት የመጣው የኢኮኖሚ ድቀት ግን በቀጥታ አርፎበታል። ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ባዶ እግሩን ነበር። ከትምህርት ቤት ውጪም የበርሊንን ጎዳናዎች በባዶ እግሩ ሊዳስሳቸው ይገደድ ነበር።
ምንም እንኳን የማንፍሬድ ቤተሰቦች ኑሯቸውን የሚመሩት የቤቱ አባወራ በአናፂነት ሥራ ተሰማርቶ በሚያገኛት አነስተኛ ገቢ እየተደጎሙ ቢሆንም ሁሉም ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ከመግባት እና ዘመናዊ ትምህርትን ከመከታተል አላገዳቸውም ነበር። ማንፍሬድም እድሜው ለመኖር እውቀትን የሚጠይቅበት ወቅት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በበርሊን በሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት ገብቶ መከታተል ጀመረ። ጎበዝ ተማሪ ካልሆነ የአባቱን የአናፂነት መዶሻ መረከቡ ስለማይቀር የግዴታ በትምህርቱ ጠንካራ መሆን እንዳለበትም በልጅነት አዕምሮው ጠንቅቆ ተረድቶ ነበር።
ህይወት ፈተና የበዛባት የተወሳሰበ የዳንቴል ክር መሆኗንም ገና በጨቅላ እድሜው ነበር የተገነዘበው። እነዚህ የልጅነት ፈተናዎች ደግሞ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ እንዲከታተል የኋላ ደጀን ሆኑት። በኋላም መክሊቱ ወደሆነው የግብርና ሙያ ላይ እንዲሰማራ ብሎም የህይወት ጉዞው ፈር እንዲይዝ መንገዱን ወለል አድርገው ከፈቱለት። ማንፍሬድ ዘመናዊ ገበሬ ለመሆን ሳይንሱን ለማጥናት ፍላጎት አደረበት። በትሮፒካል አግሪካልቸር የትምህርት ክፍል የግብርና ሙያን አጠና። ሙያውን የበለጠ ለማዳበርም ሲዊዘርላንድ እና አሜሪካን አገር ተጉዟል።
እውቀት በተግባር ሊፈተን
እኔና ወዳጄ ከጀርመናዊው አዛውንት ጋር ተቀምጠን እየተጨዋወትን ነው። ያሳለፋቸውን የህይወት የከፍታ እና የዝቅታ ወቅቶች ሲያወጉን ረጋ ካለ አንደበታቸው ጋር ተደምሮ የልጅነት ህይወታቸውን በችግር አሀዱ ብለው ቢጀምሩም በነበራቸው ጥንካሬ እና ብሩህ ተስፋ ታግዘው ህይወትን ድል እንደነሷት ያሳብቅባቸዋል። ማንፍሬድ ወጋቸውን ቀጥለዋል። ከኛ የሚጠበቀው አንዳንድ ጥያቄዎች እያነሱ ፈር ማስያዘ ነበር። የልጅነታቸውን ዘመን ለመግለፅ አክብሮታችን አንደተጠበቀ ሆኖ «አንቱታው» ስለከበደን ትረካችንን አንተ እያልን እንቀጥል።
ማንፍሬድ አሁን የልጅነት ዘመኑን ጨርሶ ብዙ ትግል እና ጥንካሬን ወደሚጠይቀው የወጣትነት ህይወት ገብቷል። የከፍተኛ ትምህርቱን በሚፈልገው የሙያ መስክ አጠናቋል። ሥራ መግባት ይኖርበታል። ሆኖም ቀጥታ በጀርመን የግብርና ሥራ ውስጥ መሰማራት አልፈለገም። ይልቁንም ወገኖቹን ጥሎ ወደማያውቃት የአፍሪካ ምድር ለመጓዝ ልቡ ተነሳሳ። ምክንያቱ ደግሞ አንድ እና አንድ ነበር። ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ የተፈጥሮ ፍላጎቱ መሆኑ ነው። እርሱ በልጅነቱ ማጣትን እና ችግርን በሚገባ አይቶታል። ስለዚህ አሁን ላይ ያለውን እውቀት ተጠቅሞ እራሱን ማዳን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መድረስ እንዳለበት የወጣትነት እድሜው አስገንዝቦታል። ለዚህ ደግሞ አንድ አማራጭ መጠቀም ይኖርበታል። በጎ ፍቃደኛ መሆን።
ወቅቱ 1966 ነው። የአፍሪካ አገራት በጊዜው በተለይም በግብርና ላይ ሙያዊ ድጋፍን ከምንጊዜውም በላይ ይፈልጉ ነበር። እርሱ ደግሞ ሁለት ነገሮች ነበሩት። አንድ እውቀት፤ ሁለትም ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን ለመርዳት የሚሻ ቅን ፍላጎት። ስለዚህ የምዕራብ ጀርመን መንግሥት ጋር ቀርቦ በበጎ ፍቃደኝነት ማገልገል እንደሚፈልግ አሳወቀ። ፍላጎቱን የተረዱ አካላትም ማንፍሬድ ልቡ ወደሻተው የሙያ መስክ እንዲሰማራ መንገዱን ጠረጉለት። ንፁህ ልብ ያለው ማንፍሬድ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አፍሪካ ምድር ለመጓዝ ተነሳ። በወቅቱ የጀርመን መንግሥት በአንዳንድ አገራት ውስጥ በግብርናው ዘርፍ ላይ ድጋፍ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ያስተዳድር ነበር። ማንፍሬድም በነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ባለሙያ ሆኖ ነበር የተመደበው።
ቀዳሚ ማረፊያ ኢትዮጵያ
ጊዜው 1966 ። የጀርመን መንግሥት ማንፍሬድን «የሚኒስትሪ ኦፍ ኮሚኒቲ ዴቨሎፕመንት» የጀመረው ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ እንዲሆን መደበው። «የተቀደሰች እና ኩሩ ህዝብ ያላት አገር» እያለ ወደሚጠራት ኢትዮጵያ ገባ። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ አገር ሲመጣ የመጀመሪያ ስራውን በዚህቺው አገር ጀመረ። ኢትዮጵያ እንደገባም በሰሜን ሸዋ ክፍለ አገር ማጀቴ በሚባል ቦታ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ላይ ተመደበ።
ማንፍሬድ ወቅቱን ልክ ዛሬ ላይ እንደሆነ ሁሉ ሁሉንም ነገር ያስታውሳል። «በእስራኤል አገር የሚገኙ የምርጥ ዘር ዶሮዎችን በቀበሌዋ እያመጣን ከአራት የሥራ አጋሮቼ ጋር በኢንኩቤተር እናባዛ ነበር» ይላል። በአካባቢው በሚገኙ ስምንት መንደሮች ውስጥ እነዚህን የዶሮ ዝርያዎች በማሰራጨት አርሶአደሩ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ነበር የበጎ ፍቃደኛው ወጣት ባልደረቦች የሚሰሩት። በቀበሌው የሚረቡ ዶሮዎችን እና የሚገኘውን እንቁላልም አዲስ አበባ ድረስ በማምጣት ለገበያ ያቀርቡ ነበር። አርሶአደሮችን በሙያ ማገዝ እና ዘመናዊ የግብርና ሳይንስን ማስተማር በጎ ፍቃደኛ ሆነው የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢን አቋርጠው ለመጡት የነ ማንፍሬድ ቡድን አባላት የመንፈስ እርካታን የሚያጎናፅፍ ሀይል ነበረው።
ለዚህ ወጣት ደግሞ ከሁሉም በበለጠ አገሩ ውስጥ ያልተመለከተውን ወግ፣ ባሀል እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንዲመለከት እረዳው። ዓለምን በጀርመን ዓይን ሲመለከት ማደጉ ሌላ ውበ እሴቶች ያሏቸው አገሮች መኖራቸውን እንዳይገነዘብ አድርጎት ነበር። አሁን በእድሜ መግፋቱ አስረሱት እንጂ አማረኛ ቋንቋንም አቀላጥፎ መናገር ችሎ ነበር። አሁንም ቢሆን ሰላምታ ለመለዋወጥ የሚረዱ ጥቂት መግባቢያዎች ያውቃል።
ማንፍሬድ የኢትዮጵያን ምድር በረገጠበት የአገሪቷ ዜጎቸ ቁጥር 17 ሚሊዮን ይደርሱ ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ አፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ስር ትተዳደር ነበር። በጊዜው የነበረው ማህበረሰብ ፈሪሃ አግዚአብሄር ያለው እና እጅግ ሰው አክባሪ መሆኑን ከሚመሰክሩ የውጪ አገር ዜጎች መካከል ቀዳሚው ማንፍሬድ እና ጓደኞቻቸው ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም።
በጀርመን መንግሥት ድጎማ የሚደረግለት ፕሮጀክትም በተደጋጋሚ ጊዜ በንጉሱ ምስጋና በማግኘቱም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተደጋጋሚ ሽፋን አግኝቷል። በማንፍሬድ እይታ የፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረር በሁሉም ዘርፍ ላይ አገራዊ ቅኝት ባለው መልኩ ብልፅግና እንዳይመጣ እንቅፋት ቢሆንም አንፃራዊ በሆነ መንገድ የንጉሱ ስርዓት የፈራረሰውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት ጥረት የሚያደርጉበት ጊዜ ነበር።
አገሩን የኔ ሙያዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በማለት ወደ ማጀቴ ያቀናው ማንፍሬድ እስከ 1969 ድረስ በግብርና በተለይም በዶሮ እርባታ ሥራ ላይ ቆየ። ከላይ እንደጠቀስነውም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ከማረግ ባለፈ አርሶአደሮች ፕሮጀክቱ ደግፏቸው ምርቶቻቸውን በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንዲያቀርቡ አስቻላቸው። ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ነገሮች እየተቀያየሩ በመምጣታቸው ፕሮጀክቱ ተቋርጦ ወደሌላኛው የአገሪቷ ክፍል እንዲዘዋወር ተደረገ።
በሌላኛው የአገሪቷ ክፍል በሆለታ ከተማ የጀርመን መንግሥት በሚደግፈው ቮኬሽናል ሴንተር እና የጤና ጉዳዮች ላይ መስራት ጀመረ። ሙያው ግብርና ቢሆንም በጎ ፍቃደኛ በመሆኑ የመጀመሪያው ፕሮጀክት ሲቋረጥ ወደ አገራቸው አልተመለሰም። ይልቁንም የጀርመን መንግሥት በመደባቸው ሆለታ ላይ ከኢትዮጵያውያን ባህል ጋር ተዛምዶ ሲያገለግል ቆየ። አሁን የያኔው ወጣቱ ማንፍሬድ በዛሬው አዛውንት ማንፍሬድ ተተክቷል። ትረካችንም በአክብሮት ተለውጧል።
መለያየት ሞት ነው
ከ1966 ጀምሮ በኢትዮጵያ ለአራት ዓመታት የቆዩት ማንፍሬድ በአገሪቷ ጀርመኖች የጀመሩት ፕሮጀክት በመጠናቀቁ ወደሌላ አፍሪካ አገር ለመዘዋወር ተገደዱ። በቶሎ ከአገሪቷ ወግ እና ባህል ጋር ለተላመዱት የያኔው ጠንካራ ወጣት ውሳኔው እጅግ አስቸጋሪ ነበር። ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት ምንም አይነት አማራጭ ስላልነበር ውሳኔውን ማክበር ነበረባቸው። በዚህም ጋና እና ቡርኪናፋሶ ወደሚያዋስኗት የምዕራብ አፍሪካዋ ቶጎ አቀኑ። በዚያ ለአራት ዓመታት በተመሳሳይ ፕሮጀከት ላይ ከጂቲ ዜድ ጋር ሰሩ።
ማንፍሬድ ኢትዮጵያን ከረገጡ በኋላ አፍሪካ ልትለቃቸው አልቻለችም። ለእረፍት እና ቤተሰብ ጥየቃ አንዳንዴ ወደ ጀርመን ቢጓዙም የእድሜያቸውን እኩሌታ ግን በዚህችው አህጉር ውስጥ እንዲያሳልፉ ተገደዱ። ከቶጎ በኋላ ወደሌላኛዋ አፍሪካዊት አገር አይቮሪኮስት በተመሳሳይ ፕሮጀክት ተጉዘው ለተወሰኑ ዓመታት አሳለፉ። ረጅሙን የሥራ ጊዜያቸውን የተሻማችው ግን ኮንጎ ነበረች። ለ17 ዓመታት በአገሪቷ ጂቲ ዜድ በሚሰራው «የኮሚውኒቲ ዴቨሎፕመንት» ሥራዎች ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ቅንነት በተሞላበት መንገድ አገለገሉ። እአአ ከ1992 እስከ 94 ባለው ጊዜ ደግሞ ማንፍሬድ ሱዳን እና ሩዋንዳ ነበሩ። በሁለቱ አገራት በነበሩ የእርስ በርስ ጦርነቶች ላይ የአደጋ ጊዜ እርዳታን ከመንግስታቸው ጋር በመሆን ያቀርቡ ነበር። በተለይ ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተው የዘር ጭፍጨፋ መንስኤ እና ያስከተለውን አሰቃቂ ገዳት በቅርበት ተከታትለዋል።
ሩዋንዳን በማንፍሬድ ዓይን
በእ.አ.አ 1994 በሩዋንዳ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ጎሳዎች ላይ የተካሄደውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ማስታወስ ለማንፍሬድ «የደረቀ ቁስልን» እንደመነካካት ነው የሚሰማቸው። ጉዳዩን ወደኋላ መለስ ብለው ሲያስተውሉት የሰው ልጅ መጥፎ ጎኑ ቁልጭ ብሎ የታየበት እንደነበር ይናገራሉ። በዚያን ወቅት በክቡር የሰው ልጆች ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ዘርን መሰረት አድርጎ በህዝቦች መካከል ተነስቷል የሚል አመለካከትም የላቸውም። በዋናነት ፖለቲካና የቋንቋ ልዩነት ተደራርበው የፈጠሩት ልዩነት እልቂት ነው የሚል እምነት አላቸው። «francophone» በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዲሁም «anglophone» በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት እንጂ ለብዙ ዘመናት በጥብቅ ቁርኝት ሲኖሩ በነበሩት ሁቱና ቱትሲ የቂም በቀል ተነሳሽነት አለመሆኑን ይናገራሉ
ማንፍሬድ ሩዋንዳ በነበሩበት ጊዜ የአውሮፓውያንን ጣልቃ ገብነት በአፍሪካ አገራት በተለይም በሩዋንዳ መኖሩን ታዝበዋል። የፈረንሳይ ጣልቃ ገብነትም በሁለቱ የሩዋንዳ ጎሳዎች መካከል ቂም እና ጥላቻ እንዲኖር ጉልህ ድርሻ መጫወቱን ተመልክተዋል። በቆይታቸውም ሁለት ጊዜ ለሞት ከሚያበቃ አደጋ ተርፈዋል። ለ51 ዓመታት በአፍሪካ ምድር ላይ በበጎ ፍቃደኝነት በተለያዩ አገራት ሲሰሩ እንደ ሩዋንዳ ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭት አጋጥሟቸው አያውቅም ነበር።
ኢትዮጵያን መናፈቅ
ከጀርመናዊው አዛውንት ጋር የምናደርገው ጨዋታ ቀጥሏል። ካኪ ቁምጣ፣ ቲሸርት እና እጅጌ የሌለው ጃኬት የደረቡት የእድሜ ባለፀጋ በራሳቸው ላይ የኃይለስላሴ ምስልና ባንዲራ ያለበት ኮፍያ አድርገዋል። የቀድሞውን ንጉስ አፄ ኃይለስላሴ ምስልን ለማድረግ ለምን መረጡ? ጃማይካዊ አሊያም ጥቁር አፍሪካዊ ቢሆኑ ብዙም የሚያስገርም አይመስልም ነበር። ነገር ግን እሳቸው ለኢትዮጵያ ከሌሎች አፍሪካ አገራት በተለየ ፍቅር አላቸው።
በአገሪቷ ጥቂት ዓመታትን የቆዩ ቢሆንም ህብረተሰቡ ባለው ልዩ ስብእና፣ ሃይማኖተኝነት እና ጠንካራ አገራዊ ስሜት የተለየ ፍቅር እንዲያድርባቸው አድርጓል። ኢትዮጵያ ውስጥ በቆዩበት አራት ዓመታት ከንጉስ አፄ ኃይለስላሴ ጋር የመገናኘት አጋጣሚው ተፈጥሮላቸዋል። «ወቅቱ 1967 ነበር። ባዘጋጀነው የግብርና ኤግዚቢሽን ላይ ንጉሱ ተገኝተው ነበር። እጅግ ማራኪ ስብእና ያላቸው እና ግርማ ሞገሳቸውም የሚያስፈራ ነበር። ትሁት እና ለአገራቸው ዜጎች አሳቢ እንደነበሩም በቆይታዬ ተግንዝቤያለሁ» ይላሉ። ስለ አጼ ኃይለስላሴ አንስተው አይጠግቡም።
በወቅቱ የህዝብ ቁጥሩ አነስተኛ ነበር። የንጉሱ ስርዓት ከጣሊያን የቅኝ ግዛት ሙከራ እና አስከፊ ጦርነት ውስጥ ዜጎቹን በመሰረተ ልማት፣በትምህርት እና በስልጣኔ አንድ እርምጃ ወደፊት ለመውሰድ ሲያደርጉት የነበረውን ትጋት አዛውንቱ ጀርመናዊ በስፍራው ተገኝተው መታዘባቸውን ይመሰክራሉ። «እርሳቸው ታላቅ ንጉሥ ነበሩ። ከንግስት ኤልሳቤጥ ቀጥሎ ጀርመንን ሲጎበኙ ከፍተኛ አቀባበል አግኝተዋል» በማለት ንጉስ ለአገራቸው እና ለዓለም ሰላም ጠበቃ የቆሙ ብሎም ኢትዮጵያን እንድትበለፅግ በፍፁም ልባቸው የታገሉ መሆኑን ያምናሉ። በወቅቱ የነበረውን የውጪ ተፅኖ በመገንዘብም «እግርህን የምትዘረጋው በአልጋህ እርዝማኔ ልክ ነው» በማለት አፄ ኃይለ ስላሴ የሰሩትን ሥራ ያሞካሻሉ።
በአዛውንቱ ጀርመናዊ ሚስተር ማንፍሬድ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን ከሌሎች አገራት ባህል፣ ሀይማኖት እና ታሪክ ጋር ማነፃፀር ፍፁም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም የአገሪቷ ባህል፣ ወግ እና ታሪክ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ስርዓቱ ጥንታዊነቱን የጠበቀ ነው። በተለይ በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለራሳቸውም ሆነ ለሰው ልጅ ሁሉ ክብር ያላቸው ናቸው። በተለያየ ዓለማት የሚኖሩ አገራት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያላቸው ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ የሚመሳሰል እሴቶች አሏቸው።
ማንፍሬድ ከ47 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን በድጋሚ ለማየት እድሉን አግኝተዋል። አሁን አገሪቷ እርሳቸው ከሚያውቋትም በላይ በብዙ መንገድ ተለውጣለች። የህዝብ ቁጥሩ ጨምሯል። ስልጣኔ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ተስፏፍቷል። እርሳቸው የሚያውቋት አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ቀድሞ ከነበራቸው ገፅታ ፍፁም ተቀይረዋል። ነገር ግን ይሄ ሁሉ በቂ አይደለም ባይ ናቸው። ኢትዮጵያ እንዲሁም ሁሉም የአፍሪካ አገራት በተሻለ ፍጥነት ወደ እድገት እና ስልጣኔ ለመጓዝ ከፈለጉ ከዚህም በላይ በትብብር መስራት ይኖርባቸዋል።
ዓለም ላይ ነገሮች በፍጥነት ይቀያየራሉ። አንድን ባህል እና ማንነት ሳይበረዝ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው። ሚስተር ማንፍሬድ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያንም ቀድሞ በሚያውቋት ቦታ አላገኟትም። በተለይ በአዳዲስ የውጪ ተፅኖ እና የተበረዘ ማንነትን ተመልክተዋል። ነገር ግን ሁሉም ትክክል አይደለም የሚል እምነት የላቸውም። ለዚህ ደግሞ እንደምሳሌ የምትሆናቸው የትውልድ አገራቸው ጀርመን ነች። በጀርመን ከዚህ ቀደም በተለይ በእምነት በኩል የሙስሊም ማህበረሰብ አልነበረም። አሁን ግን ከአገሪቷ አጠቃላይ ዜጎች 8ነጥብ 2በመቶ የሚሆኑቱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው።
«ዓለም ላይ ብዙ ነገር ይቀየራል። ይሄን ማስቆም አይቻልም። ባህል ከባህል ጋር ይበረዛል። ሀይማኖቶች ይስፋፋሉ። ይሄ ጤናማ ለውጥ ነው» የሚሉት ሚስተር ማንፍሬድ እንደ እሳቸው አስተውሎት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገራት የእድገት እና ለስልጣኔ እንቅፋት፤ ለባህል መበረዝ እና ለማንነት ግጭት መጋለጥ ዋንኛው ምክንያት «ኒዮ ኮሎኒያሊዝም» ወይም ደግሞ በኢንቨስትመንት እና በንግድ ትስስር የቀድሞው ቅኝ ገዥ አገራት ከአህጉሪቱ ጋር በሚፈጥሩት ጣልቃ ገብነት ነው። ስለዚህ ሳይወለዱባት ሁሌም የሚናፍቋት ኢትዮጵያ ከዚህ ማነቆ አምልጣ ሉአላዊነቷ ሳይደፈር የስልጣኔ ጫፍ ላይ ለመውጣት መታገል አለባት የሚል ቀና ተግሳፅ ይሰጣሉ።
በተለይ ከአጼ ምኒልክ ብዙ ነገር መረዳት ይቻላል። ማንፍሬድ አጼ ምኒልክ ለዓለም ህዝብ «ኢትዮጵያዊነት» ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ያስመሰከሩ መሆናቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ማንም አገር በቀላሉ መጥቶ ኢትዮጵያ ላይ ልሰልጥንም ሆነ ሀያል ልሁን ማለት እንደማይችል አሳይተዋል። ይሄ ደግሞ አጼ ምኒልክ በወቅቱ ፋሽስት ጣሊያንን ሲገረስሱ የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን ለሦስት ሺ ዘመን የቆየ ነው። በጀርመናዊው አዛውንት እይታ አሁን እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታትም በዚሁ ቆራጥ የራስ ማንነት መታገል ያስፈልጋል።
ጡረታ የፈጠረው እፎይታ
ሚስተር ማንፍሬድ 51 ዓመታት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በበጎ ፍቃደኝነት ተዘዋውረው ሰርተዋል። አሁን እረፍት አስፈልጓቸዋል። በዘመናቸው ተግተው በመስራታቸው እዚህ ፀጋ ላይ ደርሰዋል። ጡረታ በመውጣታቸው የሚወዱትን የኢትዮጵያ አየር በእርጋታ እንዲኮመኩሙ እድሉን ከፍቶላቸዋል። አሁን መጣሁ መጣሁ እያለ የሚያስፈራራቸው እርጅና ባይጫጫናቸው ኖሮ መላው ኢትዮጵያን በድጋሚ ዞረው መመልከት ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን የአዲስ አበባ እምብርት የሆነችው ፒያሳ ላይ ከትመው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የጉዞ መቆጣጠሪያ መሳሪያቸውን አንገታቸው ላይ አጥልቀው በእግራቸው ዞር ዞር ማለታቸው አልቀረም።
በቀን 6 ኪሎ ሜትር በእግር ይጓዛሉ። በመንገድ ላይ «ሰዎችን ማውራት ያስደስተኛል» ይላሉ። በተለይ የኢትዮጵያውያን ልዩ ፈገግታና ትህትና የተሞላበት ሰላምታ ሚስተር ማንፍሬድ ልብ ውስጥ ተሰንቅሮ ቀርቷል። ታዲያ ከስኬታማ የሥራ ዘመን በኋላ አዕምሮን ዘና ለማድረግ ሁለተኛ አገራቸውን ቢመርጡ ማን ይፈርድባቸዋል።
የማንፍሬድ 5 ወንድም እና እህቶች አሁን በህይወት የሉም። እርሳቸው የሁሉም ታናሽ ነበሩ። ነገር ግን የፊታቸው ገፅታ ላይ የብቸኝነት ስሜት አይነበብም። አፍሪካ ውስጥ በሰሩባቸው ዓመታት ብዙ ቤተሰብ አፍርተዋል። በሄዱበት የሚቀበላቸው አያጡም። ተግባቢ እና ተጫዋች መሆናቸው ደግሞ በሰዎች እንዲከበቡ ያደርጋቸዋል። ቀሪ ዘመናቸውን ያለፏቸውን ፈተናዎች እና የስኬቶች መንገዶች ከወዳጆቻቸው ጋር እያወጉ ይኖራሉ። ከዚህ በላይ ሀሴት ከየት ይገኛል?
የማንፍሬድ የህይወት መንገድ
ባለፉት ዓመታት የሥራን ክቡርነት ተገንዝበው በጥንካሬ እና በቅን ፍላጎት ሰርተዋል። ሁሉም ሰው ሊደርስበት የሚገባው ግብ በህይወቱ ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ከምንም ነገር በላይ ግን ላለፉት 51 ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ሲቆዩ የተገነዘቡት የሰላም እና የአንድነትን ጥቅምን ነው። አፍሪካ እስካሁንም ድረስ በስልጣኔ ወደኋላ ልትቀር የቻለችው ይህን መገንዘብ የሚችሉ መሪዎች እና ተከታዮች በማጣቷ ነው። የውጪ ተፅእኖን አስወግዶ አንድነትን ማጠንከር ከተቻለ ኃያላን የደረሱበት ስፍራ ላይ መድረስ ቀላል ነው።
ማንፍሬድ ለጊዜው በሩዋንዳ በሚገኝ አነስተኛ መንደር ውስጥ መቀመጫቸውን አድርገዋል። የአካባቢውን ማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ሊጨምር ይችላል ብለው ያመኑበትን ድጋፍ በአቅማቸው ያደርጋሉ። ከጡረታ በኋላ ግን ቋሚ የግል ሥራ ላይ የመሰማራት ፍላጎት የላቸውም። በጉብዝናቸው ዘመን ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ሰርተውበታል። ሁሉም ሰው ህይወቱን በዚህ መልክ መምራት አለበት የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። ሌላኛው ጠንካራ የህይወት ፍልስፍናቸው «ለመስራት አልኖርም እምሰራው ግን ለመኖር ነው» ይላሉ። ይህም ደግሞ በዘመናቸው ሁሉ ጠንካራና ሥራ ወዳድ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በጥሩ ሁኔታ ለመኖር ከተፈለገ ሥራን መናቅ የለብንም ይላሉ።
ማንፍሬድ ቀለል ባለ መንገድ ህይወትን ማጣጣም ችለዋል። «ለመኖር ጠንክሬ ብሰራም ግን በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ እምብዛም ተማርኬ አላውቅም» ይላሉ። አሰስ ገሰስ ሳያበዙ በቀላሉ መንገድ ህይወትን መኖር ይቻላል የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። አሁን ተጨማሪ 10 እና 15 ዓመታትን በህይወት መኖር ይመኛሉ። «ዕድሜዬ ገፍቷል። አምላክ ወደኔ ና እስኪለኝ የጡረታ ጊዜዬን በደስታ ማሳለፍ እፈልጋለሁ» ያሉት ማንፍሬድ በተለይ ከግማሽ በላይ የሆነውን ዕድሜያቸውን ከምንም በላይ እንደ ቤተሰቤ አየዋለሁ ያሉትን የአፍሪካ ህዝብ በበጎ ፍቃደኝነት እያገለገሉ በፍቅር ማሳለፋቸው የስኬት ማማ ላይ አስቀምጧቸዋል።

ዳግም ከበደ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።