የአንባቢን ፍላጎት የማርካት ጉዞ ጅማሮ

12 Mar 2018

ትምህርት ቤቶች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ ከሚያደርጓቸው መሰረተ ልማቶቻቸው አንዱና ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው ቤተ መጽሐፍት ነው፡፡ ቤተ መጽሐፍት ደግሞ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ በአግባቡ ሊደራጅና ተማሪዎች የሚፈልጉትን መጽሐፍት መያዝ ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በየትምህርት ቤቶች የሚገኙ ቤተ መጻሕፍት በዚህ መልኩ የተደራጁ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህ እውነት በታችኛው የትምህርት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የዘወትር አቤቱታ መሆኑ እውን ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ አንጻር ሲታይ ይህ አሰራር ሊቀየር እንደሚገባው እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም የቤተ መጽሐፍት ተጠቃሚው ፍላጎት በየጊዜው እያደገ እንደመሆኑ በተገቢው መጻሕፍት ያልተደራጁ ቤተ መጽሐፍት ይዞ ከመቀመጥ ባለፈ ተጠቃሚው በቀላሉ ሊያገኛቸው በሚችልበት ቴክኖሎጂ ታግዞ ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ይሄን የተረዳውም የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ብሔራዊ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እውን አድርጓል፡፡
“አሁን ላይ የተወሰነ መሻሻል ቢታይም፤ እኛ ድሮ ተማሪ እያለን አንድ መጽሐፍት ለአርባና ሃምሳ ተማሪ አገልግሎት ይሰጥ ስለነበር ወረፋ ይዘን ነበር የምንገለገለው”፣ የሚሉት የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ሳህለማርያም ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የዲጂታል ቤተመጽሐፍቱ እውን መሆን መረጃን በወረቀት ከማድረስ ይልቅ በሶፍት ኮፒ ለማድረስ፤ በወረቀት ያለን አንድ መጽሐፍ በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ይዞ ሲጠቀም ሌላው የማያገኝበትን አሰራር በማስቀረትም አንድን መጽሐፍ በአንድ ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች እንዲያነብቡት የሚያስችል ነው፡፡
እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፤ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱ በዋናነት ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለምርምር ተቋማት፣ ለኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ተቋማት ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን፤ እነዚህ ተቋማት የሚፈልጓቸውን መረጃዎች ከድረ ገጽ ላይ በማውረድ ወይም እዛው ላይ በማየት የሚያገኙበት አሰራር ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎችም የሚፈልጉትን መረጃ በሚፈልጉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ እንዲያገኙ፣ ቴክኖሎጂዎችን እንዲረዱና ለቴክኖሎጂ ሽግግሩ መፋጠንም የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የሚያስችል ነው፡፡ ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን መምህራንም የሚፈልጉትን ማጣቀሻ መጽሐፍት በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጣል፤ የመማር ማስተማር ሂደቱንም ፈጣንና ቀልጣፋ ያደርገዋል፡፡
የመረጃ ማዕከሉ ከተቋቋመ ገና አጭር ጊዜው ቢሆንም ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተሾመ፤ ለአብነትም በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወደ አንድ የመረጃ ቋት የሚገቡበት እድል እንዲፈጠር በማድረግ የጥናትና ምርምር ስራዎች በምን ርዕሰ ጉዳይ፣ በማን እና መቼ ተከናወኑ የሚለው እንዲታወቅ በማስቻል ተመሳሳይ ወይም ኮፒ ስራዎች እንዳይሰሩና አላስፈላጊ ድግግሞሽ እንዳይኖር ለማስቻል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በማዕከል ቴክኒካል አማካሪ የሆኑት አቶ ዮዳሄ ዓርአያ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የወረቀት መረጃዎችን ይዞ በሚገኝ ቤተ መጽሐፍት የመጽሐፍ እጥረት ሲኖር አንድ መጽሐፍ አንድ ተማሪ ከያዘ ሌሎች መጽሐፉን የሚፈልጉ ተማሪዎች ይሄን መጽሐፍ ማግኘት ስለማይችሉ የግድ እርሱ እስኪመልስ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት አንድን መጽሐፍ በቀላሉ 40 ተማሪ የሚፈልገው ቢሆን የሚፈጥረውን መጉላላትና የሚፈልጉትን መረጃ የማግኘት ችግር መገመት ይቻላል፡፡ አሁን ግን ዓለም ካለበት የቴክኖሎጂ ደረጃ አኳያ አንድ ተማሪ የትም ቦታ ሆኖ መጽሐፍ በሞባይል ስልኩ ወይም በላፕቶፕ ኮምፒዩተሩ ላይ ማንበብ ሊፈልግ ይችላል፡፡ የዲጂታል ላይብረሪ እውን መሆን ደግሞ ተማሪዎች በወረቀት ላይ ያለን መረጃ ለማግኘት ከሚደርስባቸው መጉላላት እንዲላቀቁና በድረ ገጹ አማካኝነት የሚፈልጉትን መጽሐፍ ወይም ሌላ ሰነድ በሶፍት ኮፒ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ አንድን መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ይዞ የመቀመጥን አሰራር፤ በዲጂታል ላይብረሪው የተለቀቀን አንድ መጽሐፍ አንድ ሚሊዮን ተማሪም ቢሆን በአንድ ጊዜ እንዲገለገልበት እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ይሄን በመገንዘብም ዩኒቨርሲቲዎች የተለመደውን ቤተ መጽሕፍት ቀስ እያሉ ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራ ጀምረዋል፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከልም ባለፉት ሶስት አመታት በዚህ ዙሪያ እየሰራ ሲሆን፤ አሁን ላይ ተጠናቅቆ ወደስራ የገባው ዲጂታል ቤተ መጽሐፍትም በዋናነት ተደራሽነቱ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንዲሁም ማንኛውም ጥናትና ምርምር ለሚያደርግ ሰው የሚያገለግል ነው፡፡ በዚህ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ወደ 57ሺ የሚጠጉ መጻሕፍት፣ ከ600ሺ በላይ የፓተንት መረጃዎች፣ ከሰባት ሺ በላይ የሕግ ሰነዶች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ሲሰሩ የነበሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የዲዛይኖች እና ሌሎች የተለያዩ ሰነዶች አሉ፡፡ በቀጣይም የዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱ ተደራሽነት በማሳደግ ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ለሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ ለመጀመሪያ ደረጃ እንዲሁም ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የሚሆኑ መጽሐፍትን፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንና ስዕሎችን የያዙ ሰነዶችን በማካተት በተተኪው ትውልድ ላይ የመስራት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
እንደ አቶ ዮዳሄ ገለጻ፤ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱ ኢንተርኔት ባለበት አካባቢ ሁሉ የሚሰራ ሲሆን፤ የኢንተርኔት መቋረጥ ቢያጋጥም ግን በሞባይል አፕሊኬሽን ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት በሁለት መልኩ አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል፡፡ ይሄም የሞባይል አፕሊኬሽኑ ኢንተርኔት ባለበት ወቅት የሚፈልገውን የትምህርት መስክ መሰረታዊ ፓኬጅ በማውረድ ኢንተርኔት በሚጠፋበት ወቅት በፓኬጁ ውስጥ ያሉ በርካታ መጽሐፍትን መጠቀም የሚያስችለው ነው፡፡ ሁለተኛው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በኢንተርኔት (ኢትዮጵያን ኢዱኬሽናል ሪሰርች ኔትዎርክ) አማካኝነት ዲጂታል ቤተ መጽሐፍቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁንም በ33 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ግን ከእነዚህ ሁለቱ መንገዶች ባለፈ ሌሎች የመድረሻ መንገዶች እየታሰቡ ሲሆን፤ መጽሐፍቱም በአግባቡ ተደራጅተው ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ከሰው ኃይል ጀምሮ እስከ ቴክኖሎጂ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላትም ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በተለያየ መልኩ ያገኟቸውንና የራሳቸው ብቻ የሆኑ መጽሐፍትን ጭምር የጋራ ላለማድረግና በሌሎች ምክንያቶች የዩኒቨርሲቲዎች በሚፈለገው ልክ ተባባሪ ያለመሆን አዝማሚያ አለ፡፡ ሆኖም ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው የመጽሐፍት ሀብት በማካፈል በጋራ የመስራትን ባህል ማዳበር ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህን በጋራ መጠቀም የሚያስችል አሰራርም ቢዘረጋ መልካም ነው፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ሰብስቦ፣ አደራጅቶ፣ ተንትኖና እሴት አክሎ ለመረጃ ተጠቃሚዎች የማሰራጨት ዓላማን ይዞ በ2004 በሕግ የተቋቋመው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል፤ በ2006 በይፋ ስራ መጀመሩን የሚገልጹት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ ይታገሱ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ መረጃን መሰረት ያደረገ የፖሊሲ አወጣጥና ማርቀቅ ሂደት እንዲኖር ለፖሊሲ አውጪዎች መረጃዎች እንዲደርሱ ማድረግ፤ ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዙና እሴት የታከለባቸው መረጃዎችን ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለምርምር ተቋማት፣ ለተማሪዎችና ተመራማሪዎች የማሰራጨት ሥራን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለተግባሩ መሳካት ዕውን የሆነው የብሔራዊ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍትም ከየትኛውም ምንጭ የሚገኙ መረጃዎችን በማደራጀትና በማከማቸት በኢንተርኔት አማካኝነት ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች ተደራሽ የሚደረግበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ፍስሃ እንደሚናገሩት፤ በእስካሁኑ ሂደት የድረ ገጽና የአሰራር ማበልጸግ እንዲሁም የይዘት ማደራጀትና ማከማቸት ተግባራት ተከናው ነዋል፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ መመዘኛ በትምህርት ዘርፍነት የተጠቀሱ በማህበራዊም ሆነ በተፈጥሮ ሳይንስ መስኮች ከ25 በላይ በሚሆኑ መስኮች መጽሐፍቶች ያሉት ሲሆን፤ በጠቅላላው ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ (መጽሐፍት፣ ጆርናሎች፣ የምርምር ውጤቶች) ይዘቶች በዲጂታል ላይብረሪ ውስጥ በኦን ላይን ተለቅቀዋል፡፡ ተጠቃሚው አንድም በድረ ገጹ ኦንላይን በማንበብ፤ በሌላም በኩል የሚፈልገውን መረጃ በነጻ አውርዶ መጠቀም ይችላል፡፡
ማንኛውም ሰው ኢንተርኔት ባለበት የኢትዮጵያ ክልል ሁሉ stic.gov.et ብሎ ቢገባ ሊያገኘው እንደሚችልም ታውቋል፡፡ በኢንተርኔት ኔትዎርክ የታቀፉ ዩኒቨርሲቲዎች ይሄንን ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ከኢንተርኔት ውጪ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ እውቀትና መጽሐፍት የሁሉምና ለሁሉም እንደመሆናቸውም ይህ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ከመጽሐፍት፣ ከጆርናል አርቲክሎችና ከምርምር ውጤቶች ባለፈ ዝርዝር ዓለማአቀፍ የፈጠራ ዲዛይኖች ያሉበት በመሆኑ ለፈጠራ ባለሙያዎች እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ በመሆኑም በታዳጊ አገሮች ከትምህርት ጥራት ጀምሮ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ያለው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በትምህርቱ ዘርፍ በዚህ መልኩ በዲጂታል ቤተመጻሕፍት በስፋት ለመጠቀም ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ሌሎች በቤተ መጻሕፍት ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ለመስራት ማዕከሉ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በትብብር ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።