‹‹የሪኮንስትራክቲቭ›› ቀዶ ህክምና በኢትዮጵያ አስፈላጊ ቢሆንም ከህዝቡ ፍላጎት እኩል አላደገም›› ዶክተር አታክልቲ ባራኪ - ዶክተር አታክልቲ ባራኪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ባለሞያ Featured

13 Mar 2018

ዶክተር አታክልቲ ባራኪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ባለሞያ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ሃኪምነት ተከታትለዋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውንም በዚሁ ተቋም በአጠቃላይ ቀዶ ሃኪምነት ስፔሻሊቲ ስልጠና አጠናቀዋል፡፡ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኖርዌ መንግስት ድጋፍ ለሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ፣ በኖርዌይ፣ በህንድና በእንግሊዝ አገር በፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ ተከታትለዋል፡፡ በአሜሪካንና በታይዋን አገራትም ከሙያው ጋር የተያያዙ አጫጭር ኮርሶችን ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ ሃኪምነትና በቀዶ ህክምና ባለሙያነት ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ሆስፒታሎች አገልግለዋል፡፡ በፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ከ16 አመት በላይ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በዚሁ ሙያቸው በአለርት ማዕክል እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና በኢትዮጵያ ስላለበት ደረጃ፣ አስፈላጊነቱና በተለይም ከስጋ ደዌ ህመም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የአካል ጉዳቶችን በቀዶ ህክምና እንዴት ማሻሻልና መመለስ እንደሚቻል አዲስ ዘመን አነጋግሯቸው እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ምንድን ነው?
ዶክተር አታክልቲ፡- የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ሁለት አበይት ዘርፎችን የያዘ ነው፡፡ አንደኛው የቁንጅና ቀዶ ህክምና (aesthetic or cosmetic surgery) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና (non aesthetic or reconstructive surgery) ነው፡፡ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምናን ከቁንጅና ቀዶ ህክምና በዋናነት የሚለየውም ይህንን አይነቱን ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎች በተለያየ ምክንያት አካላቸውን ያጡ፣ የአካላቸው የመስራት አቅም ያነሰ ወይም የአካልን ቅርፅ የሚያበላሽ ጉዳይ ያጋጠማቸው ናቸው፡፡ በብዙ አገራትም የሚሰራው ይህ አይነቱ የቀዶ ህክምና ነው፡፡ በቁንጅና ቀዶ ህክምና በአብዛኛው የሚስተናገዱት ግን ሙሉ አካል ኖሯቸው የነበራቸውን የፊት ገፅታ ወይም ሌላ የሰውነት አካል በአዲስ መልክ ለማሻሻል ወይም ለመለወጥ የሚደረግ የቀዶ ህክምና አይነት ሲሆን፣ ህክምናውም ውድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናው በኢትዮጵያ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ዶክተር አታክልቲ፡- የኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና በኢትዮጵያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ በአገሪቱ ያለውን የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ማወቅ የግድ ይላል፡፡ በቅርብ ጊዜ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ 17 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተለያዩ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ስምንት በመቶ የሚሆኑት አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህም ህክምናውን የሚፈልጉ አካል ጉዳተኞች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና ይህን ሊያስተናግድ የሚችል ተቋም እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም ነው፡፡ የህዝቡ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ በጊዜ ሂደት መለወጥ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲሁም የከተሞች መስፋፋትና እድገትን ተክትሎ የሚፈጠሩ የአካል ጉዳት ችግሮች ህክምናውን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምሩ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ የሚያበቁ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር አታክልቲ ባራኪ፡- ቀዶ ህክምናውን ለማድረግ ከሚያበቁ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በአካል ላይ አደጋ ሲደርስ ነው፡፡ ሰዎች በተለያየ መንገድ የተለያዩ አደጋዎች በብዛት ይደርስባቸዋል፡፡ ቀዶ ህክምና ከሚያስደርጉ ትልልቅ የህክምና ችግሮች ውስጥ ዋነኛ የሚባሉት የመኪና አደጋ፣ በፋብሪካ ውስጥ የሚገጥም አደጋ፣ ቃጠሎና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ እነዚህም በሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና የሚስተካከሉ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሰዎች በተፈጥሯቸው አብረዋቸው የሚወለዱ ችግሮች (በሽታዎች) ናቸው፡፡ በፊት ላይና በጭንቅላት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች፣ በእጅና በእግር ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ በፊት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ ኢንፌክሽኖችና በአንገት፣ በጭንቅላትና በሰውነት ቆዳ ላይ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶችም ቀዶ ህክምናው የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናው እንዴትና የት ይካሄዳል?
ዶክተር አታክልቲ፡- ህክምናው በተለይም ስጋደዌን በሚመለከት በአብዛኛው በመንግስት ጤና ማዕከላት የሚሰጥ በመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በአነስተኛ የገንዘብ ወጪ የሚስተናገድ ይሆናል፡፡ ትልቁ የቀዶ ህክምና ክፍያም ከ350 ብር የማይበልጥ ነው፡፡ ይህም በመንግስትና በረጂ ድርጅቶች ድጋፍ የሚደረግለት የህክምና ዘርፍ መሆኑን ያሳያል፡፡ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምናን በሚመለከት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጠኑም ቢሆን በግል ተቋማት ላይ አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፤ ነገር ግን ህክምናው በበቂ ሁኔታ አልተስፋፋም፡፡ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና አቅም ኖሯቸው በግል ህክምና ማድረግ የማይችሉ ከመሆናቸው አኳያ አገልግሎቱን በመንግስት ተቋማት ያገኛሉ፡፡
ህክምናው ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ሌሎቹ ቀዶ ህክምናዎች ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማከም አይቻልም፡፡ ሌሎች ተጓዳኝ የህክምና ባለሙያዎችንም በማካተት የሚካሄድ በመሆኑ ከሌሎች ቀዶ ህክምናዎች የተለየ ያደርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በስጋ ደዌ ህመም ምክንያት የአካል ጉዳት የሚያጋጥማቸው ሰዎች በቀዶ ህክምናው እንዴት ይስተናገዳሉ?
ዶክተር አታክልቲ፡- የስጋ ደዌ ህመም በዋናነት የነርቭ ችግር ነው፡፡ አንድ ሰው የመጀመሪያውን የህመም ምልክት በሚያይበት ጊዜ ህክምናውን በማግኘት ባክቴሪያውን ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ የነርቭ መቆጣት ሊያጋጥም ስለሚችል አሁንም ወደ ህክምና ቦታ በመሄድ የተቆጣውን ነርቭ ማርገብ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ጡንቻዎች ይላላሉ፤ ስሜት አይኖርም፤ የነርቭ ስርአት የሚቆጣጠረው አካል አይኖርም፡፡ በመሆኑም እንደ አካል ጉዳቱ መጠንና አይነት ታይቶ የቀዶ ህክምናው ይከናወናል፡፡ የእጅና እግር የመስራት ብቃት እንዲሻሻል የተለያዩ ቀዶ ህክምናዎች ይካሄዳሉ፡፡ ጡንቻዎችን የማዟዟር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ የተወጠሩ ነርቮች እንዲላሉና እንዲላቀቁ ይደረጋል፡፡ በጡንቻ መላላት ምክንያት የእግር ጣቶችና የእግር ቅርፅ እየተበላሸ ስለሚሄድና ቁስል ስለሚያመጣ በቶሎ የመጡትን ያለ ቀዶ ህክምና እግሮቻቸውን በምን መልኩ መንከባከብ እንዳለባቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ከዛ የከፋ የአካል ጉዳት የገጠማቸውን ደግሞ ልዩ ጫማዎች እንዲዘጋጅላቸው ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ሂደቶችን ካለፈ የተለያዩ አይነት የቀዶ ህክምናዎች ይደረጋሉ፡፡ እነዚህ ቀዶ ህክምናዎች በዋናነት የሚሰሩትም አለርት ማዕከል ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቀዶ ህክምናው የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣትና ታካሚውን ማርካት ይቻላል?
ዶክተር አታክልቲ፡- በሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና በጣም ትንሽ የሚባሉ ነገሮች በታካሚው ላይ ትልቅ ለውጥ ሲያመጡ ይታያሉ፡፡ በተለይም የስጋ ደዌ ታማሚዎች የእጅ ነርቫቸው ሲቃጠል በእጃቸው እቃ መያዝ አይችሉም፡፡ ይሁን እንጂ ቀዶ ህክምናው ጡንቻዎችን በማስተካከልና በማዟዟር እቃዎችን በእጆቻቸው እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ በቀዶ ህክምናው ለውጥ ቢመጣም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ስራው የሚቆም አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ታማሚ ለቀዶ ህክምና አምስትና ስድስት ጊዜ ያህል ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህም የጎደለው አካሉ የበለጠ እንዲስተካከል ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህክምናውን ለመስጠት አስቸጋሪ የሚያደርጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር አታክልቲ፡- በዘርፉ የሰለጠኑ ሙያተኞች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ በቀዶ ህክምና ቡድኑ ውስጥ መካተት የሚገባቸው ተጓዳኝ የህክምና ሙያተኞች ቁጥር አናሳ መሆን፣ የተቋማት ጠንካራ ያለመሆን እንዲሁም ህክምናው በጥቂት ተቋማት ውስጥ መሰጠቱ የህክምናው ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ታማሚዎች ጉዳቱ ሲደርስባቸው በቶሎ ወደ ህክምና ቦታ አለመምጣትም ሌላኛው የህክምናው አስቸጋሪ ገፅታ ነው፡፡ የመጀመሪያ የአካል ጉዳተኝነት ምልክት ደረጃ ላይ የሚደረገው ቀዶ ህክምና የከፋ የአካል ጉዳት ከመድረሱ በፊት ለማቆም ያስችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ደረጃ ካለፈ የዚያኑ ያህል የቀዶ ህክምናውን አስቸጋሪና ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ በተቋም ደረጃ በአለርት ማዕከል የስጋ ደዌ የቀዶ ህክምናን ለማካሄድ በቂ መሳሪያ ያለ ቢሆንም፤ በሌሎች አገልግሎቱ በሚሰጥባቸው ተቋማት ግን በበቂ ሁኔታ አይገኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀዶ ህክምናውን በበቂ ሁኔታና በሚፈለገው መጠን ለመስጠት መፍትሄው ምንድን ነው?
ዶክተር አታክልቲ፡- በማዕከሉ ህክምናውን ፈልገው የሚመጡ ሰዎች አንድም ችግሩ ኖሮባቸው የሚመጡ አሊያም አዳዲስ ታማሚዎች ናቸው፡፡ አዳዲስ ታማሚዎች በተቻለ መጠን ምንም አይነት የአካል ጉዳት እንዳይደርስባቸው ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የቀዶ ህክምናውን የሚሰጠው ተቋምና ባለሙያዎች ቁጥር ውስን በመሆኑ የቀዶ ህክምናውን በበቂ ሁኔታና መስጠት አልተቻልም፡፡ በጊዜው ለማስተናገድም አልተቻለም፡፡ ይህንንም ለማሻሻል በርካታ ስራዎች መስራት አለባቸው፡፡ ተቋማትም መስፋፋት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግስት በተለይም የስጋ ደዌ የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ቢያደርግም፤ በየቦታው ያሉ ተቋማትና የህክምና ባለሙያዎች ህክምናውን እንደሚሰጡ ማረጋገጥ ላይ ሰፊ ክፍተት ይታያል፡፡ ይህን ክፍተት ማሟላት የሚቻል ከሆነ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ከመደረሱ በፊት መከላከል ይቻላል፡፡ የጤና ባለሙያዎችን የስጋ ደዌ ህክምናን ማሰልጠን የሚቻል ከሆነም ትንንሽ ቁስሎችን እዛው ማከም ይቻላል፡፡ በሌሎች ቦታ ላይ የሚገኙ ተቋማት ህክምናውን እየሰጡ ቢሆኑም፤ ያላቸው አቅም ደካማ በመሆኑ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እዛ ቦታ ላይ ያሉ ባለሙያዎችንም ማብቃት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህክምናውን አስመልክቶ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ይኖር ይሆን?
ዶክተር አታክልቲ፡- ፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህከምናን አስመልክቶ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ እንዳይኖር ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ ህክምናው አስፈላጊ በመሆኑም በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲሰጥ ሊሰራበት ይገባል፡፡ በጊዜያዊነት በርካታ ችግሮች ያሉበት የህክምና ዘርፍ ቢሆንም በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር የሚሰጡ ስልጠናዎች እየተስፋፉ ሲሄዱ ህክምናውን በተሻለ መልኩ መስጠት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፍቃደኛ ሆነው ለሰጡኝ ሙያዊ ማብራሪያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር አታክልቲ፡- እኔም አመሰግናለሁ

አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።