ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድሀኒቶች ቁጥጥርን ለማሳለጥ

15 May 2018

“ጤና” በዓለም ጤና ድርጅት ትርጓሜ መሰረት“ ከበሽታ ነፃ መሆን ” ብቻ ሳይሆን “አካላዊ ጤንነትን፣ ማህበራዊ ደህንነትን፣ ስነልቦናዊ እና ስነአእምሮአዊ ብቃትን” ሁሉ የሚያካትት ከመሆኑ አንፃር የጤና ጉዳይ ልዩ ትኩረትን መሻቱ መቸም የትም ቢሆን ተገቢ ነው። ችግር አለ ከተባለም ጤናን በመጠበቁ ላይ በታሰበውና በታቀደው ልክ አለመሠራቱ ላይ ይሆናል።
ኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ መጠነ ሰፊና ግዙፍ ችግርችን በመገንዘብ በመከላከል ላይ የተመሰረተ የጤና ፖሊሲ በ1986 ዓም አውጥታ ሥራ ላይ አውላለች፡፡በዚህም እንደ ወባ፣ ኤች አይቪ ኤድስና ቲቢ በመሳሰሉት በሽታዎች ላይ በመስራት ዜጎችን ታድጋለች፡፡
ዜጎች በበሽታ እንዳይጠቁ ሲታመሙም እንዲፈወሱ በሚል ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ መድሀኒቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በኩል መንግሥት ከፍተኛ ሀብት መድቦ ሢሰራ ቆይቷል፤እየሠራም ይገኛል።
መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ ለጋሾችም ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ነዋይ ለዘርፉ አውለዋል፡፡ ለአብነትም ከ2007 እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ኢትዮጵያ 36 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችንና የህክምና መሣሪያዎችን ከለጋሾች በመቀበል ጥቅም ላይ አውላለች።
ይህ ከፍተኛ ሀብት የሚመደብለት ዘርፍ በተለይ በመዳህኒት አቅርቦት በኩል ተግዳሮቶች እንደሚስተዋልበት ይጠቆማል፡፤ በድንበሮች አካባቢ በኮንትሮባንድ የሚገቡ የህክምና መሣሪያዎችና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድሀኒቶች ከፍተኛ ፈተናም ሆነው ቀጥለዋል። ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድሀኒቶች ኢትዮጵያን
በጣም ይፈትኑ እንጂ የብዙ አፍሪካ አገራት ችግር መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የዓለም ጤና ድርጀት ይሕን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ መሰረትም 10 በመቶ የሚሆኑትና ፈዋሽነት የሌላቸው መድሀኒቶች የሚሰራጩት በድሃና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ነው፡፡ይህ መሆኑ ደግሞ ህብረተሰቡ በአገሩ ህክምና ላይ እምነት እንዲያጣ፣ የአገራቱም ኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ እያደረገ ይገኛል፡፡
በአፍሪካ ብቻ በየዓመቱ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መድሀኒት 100 ሺ ሰዎች ለሞት ይዳረጋሉ።ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት የተቀናጀ ሥራ እንደሚጠይቅም ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚመክሩት።
የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በአገሪቱ የሚመረቱትም ሆኑ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድሀኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች የጤና መድን የመሆናቸውን ያህል ችግሮችም እንዳሉባቸው ጠቁመው፣የጤና እክል ከማድረሳቸው ባሻገር ሰዎችንም ለሞት እየዳረጉም ይገኛሉ ይላሉ። በዚህም ላይ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በትኩረት እንዲሠራ እየተደረገ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
ሚኒስትሩ ‹‹መዳኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች ዘርፍ ከፍተኛ ችግር አለበት፤ጉዞውም ከአንድ አገር ተነስቶ ወደተለያዩ አገራት እንደመሆኑ ኢትዮጵያም ብቻዋን ምንም ዓይነት ሥራ ብትሠራ ችግሩ ይቀረፋል ማለት አይቻልም፡፡ በመላው አፍሪካ ይህንን ሀሳብ በማቀንቀንና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ትልቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ይላሉ።
እንደ ዶክተር አሚር ማብራሪያ፤ መድኃኒቶች የትኛውም አገር ላይ ቢመረቱ ኢትዮጵያም የምታመርታቸውን ወደ የትኛውም አገር ስትልክ የግብይት ሰንሰለቱን ተከትለው እንዲያልፉና ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ተግባር ለማከናወን በመላው ዓለም ከሚገኙ አምራቾች፣ አቅራቢዎች እንደዚሁም በአፍሪካ ከሚገኙ የቁጥጥር ባለሰልጣናትና የጤና ሚኒስትሮች ጋር ከፍተኛ ግንኙነት በመፍጠር እየተሠራ ነው።
ይህ ሂደት ከተሳካ በአፍሪካ አንድ ገበያ በመመስረትና መድኃኒቶችም ሆኑ የህክምና መሣሪያዎች በየትኛውም አካባቢ ላይ ሲንቀሳቀሱ የት ተመረቱ ፣ ለኅብረተሰቡስ ሲቀርቡም ፈዋሽነታቸው ምን ያሀል ነው፣ የሚለውን በቀላሉ ለመለየት ያስችላል።
እያንዳንዱ አገር የራሱ የቁጥጥር ስርዓትና ባለሰልጣን መሥሪያ ቤት አለው የሚሉት ሚኒስትሩ ፣ ወደ አፍሪካ የሚገቡትንም ሆነ በየአገራቱ የሚመረቱት መድኃኒቶች ችግር አለባቸው የለባቸውም የሚለውን ለመቆጣጠር የጋራ የመለያ ቁጥር (ኮድ) ስለሌላቸው በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህንን ማሸነፍ የሚቻለው እንደ አፍሪካ አንድ በመሆንና የሚመረቱበት ቦታ እንዲታወቅ፣ ችግር ኖሮባቸው ሲገኝም አስመጪው አልያም አምራቹ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ይህ እውን እንዲሆን ኢትዮጵያ ቁርጠኛ ሆና እየሠራች ትገኛለች።
« ኢትዮጵያ ብቻዬን ይህንን ሥራ እሠራዋለሁ ብትል የማይሆን ነገር ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱ በራሷ አመርታ የምትሸፍነው የመድኃኒት ፍላጎት በጣም ጥቂት ከመሆኑም በላይ አብዛኛው ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚገባ ነው፤ በመሆኑም አስገዳጅ ህግ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ ውጤታማ አያደርግም » ብለዋል።
ይህ ተግባር በተናጠል የሚሠራ እንዳልሆነም በመጠቆም፣ በአሁኑ ወቅት ሥራውን ያሳልጣሉ የተባሉ ሁለት ተቋማት አየተቋቋሙ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ይጠቁማሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ከተቋማቱ አንዱ « አፍሪካን ሲዲሲ» የሚባልና ድንገተኛ ችግር ሲፈጠር ለአፍሪካ የሚቆም በአፍሪካ ኅብረት ስር የሚቋቋም ኅብረት ነው፡፡ የቁጥጥር ሥራውም በአፍሪካ ደረጃ እንዲቋቋም ሀሳብ ቀርቦ እየታየ ነው። ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባም አጠቃላይ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያ ስርጭትን በአፍሪካ ለመቆጣጣር ያስችላል ። ይህም ከማህበራዊ ችግር ፈቺነቱ በላይ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙም ከፍተኛ ነው።
ይህ ሥራ በግንኙነት መረብ (ኔትዎርክ ) የሚከናወን በመሆኑ በመጀመሪያ ደረጃ ( ፌዝ ዋን) ላይ በቁጥጥር ባለስልጣኑና በጤና ተቋማት ብቻ እንዲታወቅ ለማድረግ ይሠራል ። ይህ ሲሆን ደግሞ የየክልሉ የቁጥጥር ባለሥልጣናት ፣የጤና ቢሮዎች፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የጤና ተቋማት እንዲያውቁት ይደረጋል።
ሁለተኛውና ትንሽ ከበድ የሚለው ደረጃ (ፌዝ 2) ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ በቀላሉ ያንን እያስገባ ባለበት ቦታና በሚያገኘው የመረጃ መለዋወጫ መሣሪያ (ቴክኖሎጂ) የሚያይበት ሂደት ነው ። ይህ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችም ሊያስፈልጉት ይችላሉ ተብሎ ታሳቢ ይደረጋል።
አንዳንድ ጊዜ የኢንተርኔት መቆራረጥ በሚኖርበት ወቅት ሥራው እንዳይቋረጥ በማንዋልም ዲጅታልም በሆነ አሠራር መጠቀም የሚያስችል ሁኔታ እንዳለም ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣የጤና ባለሙያዎች ቴክኖሎጂውን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ዘመናዊ አሠራርን በመከተል የአመለካከት ለውጥ ጭምር እንዲያመጡ እየተሰራ ነው።
‹‹መጀመሪያ በሀሳቡና በሥራው ላይ እንደ አፍሪካ፣ እንደ ኢትዮጵያ መስማማት ያለብን ብዙ ጉዳዮች ከመኖራቸውም በላይ ከአምራች ጀምሮ በችርቻሮ አገልግሎት እስከሚሰጠው ክፍል ድረስ ስምምነት የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፤ለዚህም ውይይቶች ይደረጋል››ብለዋል፡፡
ይህንን ሥራ ከሚያሳልጡት መካከል «ኦርቢት ሄልዝ» የተሰኘው ኩባንያ አንዱ ነው። የኩባንያው
ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓዚዮን ቸርነት ‹‹ኩባንያው ጤናን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ አልሞ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ የጤና ጉዳይ ታካሚን በማከም ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ሰዎች እንዳይታመሙ፣ ሲታመሙም ከቴክኖሎጂ ጋር እጅና ጓንት በሆኑ የጤና ባለሙያዎች እርዳታ እንዲያገኙ እየሠራ ነው›› ይላሉ።
አሁን ባለው የአገራችን ልምድ አንድ ሰው ታሞ ሆስፒታል ሄዶ ወረፋ ከመጠበቅ ጀምሮ በርካታ እንግልቶችን በማለፍ ህክምና እንደሚገኝ ጠቅሰው፣በዚህ የተነሳም ብዙ ሰዎች መዳን እየቻሉ በተንዛዛ አሠራር ምክንያት እንደሚሞቱ ይናጋራሉ። በሌሎች የዓለም ክፍሎች ይህ አሠራር በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ምንም አይነት መጉላላት ሳይደርስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትክክለኛውን ህክምና ማግኘት እንደሚቻል ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ፓዚዮን ማብራሪያ፤ ይህንን አሠራር ሆስፒታሎች ክሊኒኮች እንዲሁም መድኃኒት ቤቶች ከተጠቀሙ በቀን ምን ያህል አገልግሎት ፈላጊ እንደመጣ፣ ስንት ሰው እንደታከመ ፣ ስንቶቹስ እንደተፈወሱ እና እንዳልተፈወሱ ለምን እንዳልተፈወሱ ለመረዳት ይችላሉ፡፡ይህንን ማድረግ ተቻለ ማለት የአገሪቱ የጤና ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ይለወጣል ማለት ነው፡፡
ቴክኖሎጂው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የጤና ሰርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ የሚገኙትን ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድኃኒቶች ሰርጭትና እያደረሱ ያለውን ጉዳት ለመዋጋት እንደሚያስችልም አቶ ፓዚዮን ጠቁመው፣በየሆስፒታሎቹና መድኃኒት ቤቶቹ የሚከሰተውን ስርቆትም ለማስቆም ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ።
ቴክኖሎጂው በተለይም አንዱ ዘንድ ያለውን መድኃኒቶች ሌላው ማግኘት እንዲችል እንዲሁም ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መዳኃኒቶች ለይቶ ከገበያ ለማስወጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ክብካቤ አስተዳደርና
ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደነቀው እንደሚሉት፤ ዓለም አቀፍ የመድኃኒቶችና የህክምና መሣሪያዎች ክትትልና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፤ኢትዮጵያም ይህንን ስርዓት ለመገንባት ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በተለይም አዳዲስ ልምዶችን ለመቀመር ከኢጋድ አገራት ጋር አዲስ አበባ ላይ ውይይት በማድረግ የተወሰነ ልምዶች መቀመራቸውን ጠቅሰው፣ይህንን ወደ አገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ቀይሮ በተግባር ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ወደ አገሪቱ የሚገቡ መድኃኒቶች ከ 80 በመቶ በላይ ሌሎች አገራት ላይ የሚመረቱ ናቸው ፤ደህንነትና ጥራታቸውን ለማረጋገጥም የተለያዩ ስልቶች አሉ›› የሚሉት አቶ የሁሉ፣ ስልቶቹ ግን ሲመረቱ ጀምሮ ያለውን ሂደት የሚያሳዩ እንዳልሆኑ ያብራራሉ፡፡
ወደ ዓለም አቀፉ የመድኃኒቶች ቁጥጥርና ክትትል ስርዓት መግባት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ስርዓት የመድኃኒቶቹን አመራረት ፣ ከየትኛው አገር እንደመጡ፣ ፋብሪካቸው የት እንደሚገኝ፣ እንዴት እንደተጓጓዙ፣ ማን እንዳስመጣቸው፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው መቼ እንደሚያበቃ፣ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላም ወደየትኛው የጤና ተቋም እንደተሰራጩ ክትትል ለማድረግ የሚያስችል የመረጃ ስርዓት ለመዘርጋት ይረዳል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ የሁሉ ገለጻ ፤አሠራሩ ከተዘረጋ በዚህ መልክ ያልገቡትንና ሲገቡም ችግር የተገኘባቸውን ለመሰብሰብ ቀላል ከመሆኑም በላይ ኅብረተሰቡ በአገሪቱ የህከምና አገለግሎት ላይ እምነት እንዲያሳድርም ይረዳል።
የአገር ውስጥ መድኃኒትና የህከምና መሣሪያ አምራቾች ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ ከፍተኛ ፍላጎት አለ የሚሉት አቶ የሁሉ፣ ዓላማውም መሠረታዊ መድኃኒቶች ላይ የሚታየውን የጥራት ጉድለት በአገር ውስጥ ምርት መፍታት እንዲሁም ለወጭ ገበያ ለማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱ ተረጋግጦ ማለፉ ከታካሚዎች ከጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ከጤና ተቋምና ከተቆጣጣሪዎች ከአከፋፋዮችና አምራቾች አንጻርም ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ የሁሉ ገለጻ፤ኢትዮጵያ ይህንን አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ከቻለችና ሂደቱም ከተሳካ በጣም ተጠቃሚ ትሆናለች። ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ መድኃኒቶች ጥራትና ደህንነት ላይም ምንም ጥርጣሬ አይኖርም ።
«አትመመኝ አይባልም፤ ማረኝ ነው እንጂ » እንደሚባለው ሰዎች ታመው ወደ ህክምና ተቋማት ሊሄዱ ይችላሉ፤ ወደ ጤናቸው አንዲመለሱ ደግሞ ጥሩ የህክምና ባለሙያ ፣ ፈዋሽ መድኃኒትና የህክምና መሣሪያ ያስፈልጋል። በመድኃኒት ጥራትና ደረጃ ላይ ሊሠራ የታሰበው ግቡን ይመታ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

እፀገነት አክሊሉ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።