መጥረጊያ ያላጸዳው አመለካከት Featured

16 May 2018

ተደጋግሞ እንደሚባለው ማንኛውም ሰውና የተሰማራበት  የስራ  ዘርፍ  ክቡር  ነው። የትኛውም ባለሙያ በተሰማራበት  ሙያ  ራሱንንና ቤተሰቡን ከመምራት ባለፈ ለሙያው ስነምግባር ተገዢ መሆኑም ማንነቱን እንዲያስከብር ያደርገዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን የስራን ክቡርነት አቅልለው የሚያዩ በርካቶች በስራ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ያነሰ ክብርና ግምት እንዳላቸው ይስተዋላል።ለእንዲህ አይነቱ እውነታ ቅሬታቸውን የሚገልጹት  የጽዳት ሰራተኞችም በሙያቸው ዙሪያ የአንዳንድ ተጠቃሚዎችን በጎ ያልሆነ ድርጊት እንደማሳያ ይጠቅሳሉ።የአዲስዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም በጽዳት ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ህይወትና የስራ ላይ ፈተናዎችን በተመለከተ ከጉዳዩ ባለቤቶች ያገኘቸውን ተሞክሮ «እነሆ» ብላናለች። 

 

ሌቱ አልፎ ንጋቱ ሲቃረብ፣ በዕንቅልፍ የደከሙ ዓይኖቿ ይነቃሉ። በነጋ አልነጋ ጭንቀት ሲባትት ያደረው አካሏም ለጉዞ ፈጥኖ ይዘጋጃል። ከቤት ርቃ መንገድ ለመጀመር ግን እግሮቿ በኩራት አይራመዱም። ከሞቀ መኝታዋ ወጥታ ከጎዳናው ስትገባ አይኖቿ ሌሎች መንገደኞችን ያማትራሉ። ሁሌም ቢሆን ለብቻዋ መጓዝን አትደፍርም። እሷ ድንገቴ ኮሽታ ያስደነግጣታል። የጨለማውም ግዝፈት ያስፈራታል። እናም አብሯት የሚራመድ እስክታገኝ ድረስ የእግር ኮቴ ስታዳምጥ ትቆያለች።
አንድ ቀን ወይዘሪት የሺ መኩሪያ ከቀበና አካባቢ ወደ ውስጥ አልፎ ከሚገኘው መኖርያ ቤቷ ማልዳ ወጣች። የዚያን ዕለት ጨለማው በወጉ አልገፈፈም። መንገዱም ገና አልተጋመሰም። ይሄኔ ልቧ በድንጋጤ መምታት ጀመረ። ፍርሀት ይወራት፣ ያንቀጠቅጣት ያዘ። ፊትና ኋላዋን እየቃኘች መንገዷን ቀጠለች። በዚህ መንገድ ብዙ ክፉ አጋጣሚዎች እንዳሉ ታውቃለች። ሌቦች ወጪ ወራጁን ጠብቀው ይዘርፋሉ፣ ይደበድባሉ። የነጋባቸው ጅቦችም ወደ ጫካቸው ሲገሰግሱ ሰዎችን ይተናኮላሉ። የሺ እነዚህንና ሌሎች ወሬዎችን ሰምታለች።
ወጣቷ በአዕምሮዋ ብዙ ሃሳብ ይመላለሳል። መስሪያ ቤቷ ከሌሎቹ ሠራተኞች ቀድማ መድረስ አለባት። ሥራ ቦታዋ አይቀሬው ግዴታ ይቆያታል። ብርድና ዝናብ፣ ጨለማና ጭጋግ ለእሷ መሰሉ ሠራተኛ ሰበብ አይሆንም። በሰዓቱ ተገኝታ ግዴታዋን መወጣት አለባት። እሱን ከውና ስታጠናቅቅ ደግሞ ጤና አጥተው አልጋ ላይ ለዋሉት እናቷ መድረስ ይኖርባታል።
የፅዳት ሠራተኛዋ ይህን ሁሉ እያሰበች ወደ ፊት ተጉዛለች። በመንገዷ አጋማሽ አብሯት የሚዘልቅ መንገደኛ እንደሚገጥማት ገምታለች። አሁን ገና ከዋናው መንገድ አልደረሰችም። የመንደሩን እጥፋት ጨርሳ ከአስፓልቱ እስክትገባ ሰፈሩ ሁሌም እንዳስፈራት ነው። የሺ ድንገት ኮሽታ ቢጤ የሰማች መሰላት። ከጀርባዋ የሚከተላት እንዳለም ገመተች። አጠገቧ እስኪደርስ ማንነቱን አላወቀችም። ከኋላዋ የደረሱ ስፖርተኞች ግን ፈጥነው ለዩትና ወደእሷ ሳይቀርብ እያዋከቡ መለሱት። ቆይታ የሺ የሆነውን ሁሉ ተረዳች። እሷን ሲከተላት የቆየው መንገደኛ ሰው ሳይሆን አያ ጅቦ መሆኑን አወቀች።
ይህ ካጋጠማት በኋላ የሺ ለብቻዋ ከቤት መውጣት አትደፍርም። ሰዎች ሲበራከቱና መንገዱ በእግረኞች ሲያዝ ጠብቃ አብራ ትጓዛለች፡፡ የሰፈሯን ስጋት በዚህ ዘዴ አዋዝታ ከመስሪያ ቤቷ ስትገባ እሷን የሚጠብቀው የፅዳት ሥራ ከነብዙ ችግሮቹ ይቀበላታል። የሥራ ልብሷን ቀይራ መጥረጊያና መወልወያዋን በመያዝ ለዕለት ሥራዋ ትሰለፋለች፡፡ የምታየውን እንዳለየች ሆናም ኃላፊነቷን በጥንካሬ መወጣት ትጀምራለች።
ወጣቷ ከሦስት ዓመታት በላይ በዘለቀችበት የፅዳት ሥራ ብዙ ተፈትናለች። ሙያዋን አክባሪ ብትሆንም የሥራዋ ባህርይና የአንዳንድ ሰዎች ድርጊት ያሳደረባት አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። የሺ የማለዳውን ውጣ ውረድ አልፋ ወደ ሥራ ስትገባ የመጀመሪያ ተግባሯ መፀዳጃ ቤቶችን መጎብኘት ነው። በዚህ ቦታ ለዓይን የሚከብዱ ለመናገርም የሚቸግሩ ድርጊቶች ያጋጥሟታል።
የሺ ሁሌም ለሥራ ወደ ውስጥ ስትዘልቅ የአንዳንድ ሰዎች የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ልምድ ያስገርማታል። አብዛኛዎቹ ከተጠቀሙ በኋላ ውሃ የመልቀቅ ፍላጎቱ የላቸውም። ከተገቢው ቦታ ይልቅ በወለል ላይ የመጠቀምና አካባቢውን የመበከል ልምድ ተክነዋል። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በግርግዳዎች ላይ ቆሻሻን በማኖር አስጸያፊ ድርጊት ይፈጽማሉ።
ይህን ያልተገባ ልምድ ለመጠቆም ደግሞ እሷና ባልደረቦቿ «እባካችሁ» ሲሉ በማስታወቂያ መልክ ለማሳሰብ ሞክረዋል። አብዛኛዎቹ ለማሳሰቢያው «ጆሮ ዳባ ልበስ» ማለታቸው አሁንም ድረስ የቢሮ አካባቢዎች በመጥፎ ሽታና በቆሻሻዎች እንዲበከሉ እያደረገ ነው። ከዚህ ባለፈ ‹‹ሰዎች ስለሰዎች ማንነት ሊጨነቁ ይገባል›› የምትለው የሺ ይህን የሚያደርጉት ሰዎች ድርጊቱ በእነሱ ላይ ቢደርስ ምን እንደሚሰማቸው በማሰብ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡
በፅዳት ሥራ ቆይታዋ የበርካቶችን ያልተገባ ልማድ አስተውላለች። ሁሌም ለፅዳት ስትሰማራ ከሚያጋጥማት በእጅ ከቆሸሸ አካባቢ ሌላ በፊት መታጠቢያ ሳህኖች (ሲንኮች) ላይ የምታገኘው የጫማ ጭቃና የጸጉር እጣቢም ዘወትር እንድታዝን ያደርጋታል። እንደውም አንዳንዴ በመፀዳጃ ሳህኖች ላይ ከነጫማቸው ወጥተው የሚጠቀሙ ሰዎች ያጋጥሟታል። እነዚህም ቢሆኑ ትተውት ለሚሄዱት የጫማቸው ጭቃና አቧራ የማይጨነቁና ለሌሎች ሰዎች ደንታ የሌላቸው ናቸው።
የሺ አሁን ያለችበት መስሪያ ቤት ተቀጥራ ከመግባቷ በፊት በሌሎች ቦታዎችም ግቢ በማስዋብና በአትክልተኝነት ሥራ ላይ ቆይታለች። በቋሚነት መደብ ለፅዳት ሥራው ተወዳድራ ስትገባና የወር ደመወዝተኛ ስትሆንም በእጅጉ ተደስታ ነበር። አሁንም ቢሆን በሥራው ክቡርነት ታምናለች። ስለነገ ማንነቷም መሰረት ለመጣል ያቋረጠችውን ትምህርት የመቀጠል ዓላማዋን ሰንቃለች።
ወይዘሮ ማህሌት በቀለም በመስሪያ ቤት የፅዳት ሙያ ላይ ከሦስት ዓመታት በላይ ቆይታለች። ተቀጥራ ለምትሠራበት ሙያ ኃላፊነቷን የምትጀምረው ገና ከማለዳው አንስቶ ነው። ወይዘሮ ማህሌት ልክ እንደየሺ ሁሉ አራት ኪሎ በሚገኘው መስርያ ቤቷ በሠዓቱ ለመገኘት በጠዋቱ መነሳት ግድ ይላታል። እንጦጦ ኪዳነምህረት አካባቢ ከሚገኘው መኖርያ ቤቷ ወደ መስርያ ቤት ለመሄድ ሁሌም በጠዋት ጉዞ ትጀምራለች፡፡ ባሰበችው ሰዓት ተነስታ ለመጓዝ ግን አካባቢው በጫካ የተከበበ መሆኑ ስጋት እንደፈጠረባት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ማልዶ የሚገሰግስ የቀማኞችና የአውሬዎች ሲሳይ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች፡፡
ወፍ ሲንጫጫ አንስቶ እግሮቿን ለጉዞ የምታሰላው ወይዘሮ ብዙዎች ጉዞ መጀመራቸውን ስታረጋግጥ ከቤቷ ትወጣለች። ይህን ከማድረጓ በፊት ግን የእናትነት ግዴታዋ ወደ ኋላ ይመልሳታል። ገና አንድ ዓመት የሞላትን ልጇን በወጉ አጥብታና አለባብሳ ለጎረቤት አደራ መስጠት አለባት። ደርሳ እስክትመለስና የሰጠችውን እስክትቀበልም ልቧ ለሁለት ይከፈላል።
ወይዘሮ ማህሌት በፍጥነት ገስግሳ የምትሄድበት ቢሮ ስትደርስ ሥራዋን የምትጀምረው መፀዳጃ ቤቶችን በማፅዳት ነው። ብዙ ጊዜ ገና ከበሩ የሚቀበላት መጥፎ ሽታ ወደ ውስጥ ስትዘልቅ ለዓይን ከማይመች እይታ ጋር ያገናኛታል። እሷ ለሙያዋ የተለየ ክብር ያላት መሆኑ ሥራዋን በአግባቡ እንድትወጣ አላገዳትም። ይሁን እንጂ በየቀኑ የምታየው ያልተጋባ ድርጊት አንዳንዶችን እንድትታዘብና በተግባራቸው እንድታፍር አድርጓታል።
ከአንድ ዓመት በፊት ነፍሰጡር በነበረችበት ጊዜ ደግሞ የምትመለከተው ቆሻሻና ለአፍንጫዋ የሚደርሰው መጥፎ ሽታ ለእሷ እንደማይስማማ ታስታውሳለች፡፡ ይሁን እንጂ እንደምንም ከራሷ ጋር ታግላና የውስጧን ስሜት አሸንፋ ቀኗን በድል ስትወጣ ቆይታለች። ለእሷ ይህ አጋጣሚ ፈታኝ የሚባል ቢሆንም ከማንነቷ ይልቅ የሙያ ግዴታዋን በማስቀደሟ ሥራዋን በብቃት ተወጥታለች።
ዛሬም ይሁን ትናንት ግን ለፅዳት ባለሙያዋ ወይዘሮ ማህሌት እጅግ የሚያሳዝናት አንድ እውነት አለ። ሁሌም የአንዳንድ ሰዎች ያልተገባ ልማድ እንደባህል ሆኖ መቀጠሉ በእጅጉ ያስገርማታል፡፡ በየቀኑ በየመፀዳጃ ቤቶቹ የሚታየው የአጠቃቀም ችግር አለመሻሻሉ ያሳስባታል። ከቢሮ እስከ መፀዳጃ ቤቶች በምታደርገው የፅዳት ሥራ ፈታኝ ነገሮች ገጥመዋታል። አንዳንዶች በመፀዳጃ ቤቶች አካባቢ የሚተገብሩት አሳፋሪ ድርጊት ሁሌም ይዘገንናታል፡፡
በመጸዳጃ ቤቶች ውስጥ በአግባቡ መወገድ የሚገባቸው ቆሻሻዎች እንደነውር ሳይቆጠሩ በየሜዳው ይጣላሉ። በተለይ አንዳንድ ሴቶች በንጽሕና መጠበቂያ ቁሶች ላይ ያላቸው የአወጋገድ ልማድ እጅግ ደካማ ነው። ብዙ ጊዜም በእጅ መታጠቢያዎችና በመመላለሻ ወለሎች ላይ ለዓይን የሚከብዱ ድርጊቶች ተፈጽመው ማስተዋሏ ከሰው ልጆች የማይጠበቅ ነውና አሁንም ያሳዝናታል። እንዲህ ዓይነቱን ያልተገባ ድርጊት ከሚፈፅሙ ሰዎች የሚሰነዘረው አስተያየት ደግሞ ያስገርማታል፡፡ እነሱ በየቀኑ ለእንዲህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት ሳይታክቱ አንድ ቀን እንከን ሲያገኙ የፅዳት ባለሙያዎችን ለመውቀስና ለመክሰስ ይሯሯጣሉ፡፡
አንዳንዴ ደግሞ በቢሮ ያሉ ሠራተኞች በጠረጴዛቸው ላይ የሚያፈሱት ሻይና የሚያንጠባጥቡት ምግብ ለፅዳት የሚያዳግትበት ጊዜ ይኖራል። ይህን በተመለከተም ብዙዎች ምክርና አስተያየት ለመቀበል ቀና አይደሉም። ሁሉንም ሠራተኛ እንደባህርይው አቻችሎ የማደር ልማዱ እንዳላት የምትናገረው ወይዘሮ ማህሌት የሥራ ግዴታዋ ጥንቃቄን ከታላቅ ኃላፊነት ጋር እንድትለምድ አድርጓታልና በዚህ ትደሰታለች።
ማንም ሰው የሚጠቀምበትን ንብረት እንደራሱ በመቁጠር ሊጠነቀቅለት እንደሚገባ ወይዘሮ ማህሌት ታምናለች። የፅዳት ሙያን ሥራዬ ብለው ለያዙ ሠራተኞች ደህንነትም ማሰብ ታላቅነትን ያሳያል ባይ ነች። ‹‹ማንም ቢሆን በሰውነቱ ክቡር ነው›› የምትለው ወይዘሮዋ ማሰብና መተሳሰብ ካለ ችግሮችን እየፈቱ ለመጓዝ መንገዱ ቀና እንደሚሆን በእርግጠኝነት ትናገራለች። ማህሌት ዛሬ ባለችበት ሙያ ላይ የመቀጠል ሃሳብ የላትም። ለዚህ ውጥኗ ደግሞ ራሷን በትምህርት አሳድጋና ማንነቷን ለውጣ በተሻለ ዕድገት መጓዝ ትፈልጋለች፡፡
እንደ የሺና ወይዘሮ ማህሌት ሁሉ በርካቶች በተሰማሩበት የፅዳት ሙያ ላይ በሚያጋጥማቸው የተጠቃሚዎች እንከን ሳቢያ ሁሌም ቅሬታቸውን ያሰማሉ። እውነት ነው! በቀላሉ መጠቀምና ለሌሎች ማሰብ እየተቻለ በአጉል መዘናጋት የሚመጣው ልማድ ጉዳቱ ለሁሉም መሆኑ አይካድም። የፅዳት ሠራተኞቹ መጥረጊያና መወልወያ ቆሻሻውን ለማፅዳት ቢያግዛቸውም፤ የሰዎችን ያልተገባ ድርጊት ለማስተካከል ግን አላስቻላቸውም፡፡ አንዳንዶች የቆሸሸውን ልማዳቸውን በመልካም አመለካከትና ሥርዓት ሊያፀዱት እንደሚገባ አጥብቀው ያሳስባሉ፡፡ እስቲ ሁላችንም ወደ ራሳችን በመመልከት ልምዳችንን እንቃኝ። በተለይም የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀምና ቆሻሻን የማስወገድ ልምዳችንን በመፈተሽ ራሳችንን መገምገም ይገባል፡፡

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።