የገጸ ባህሪ አሳሳል በሀዲስ አለማየሁ መስታወት Featured

10 Jun 2018

የኪነጥበብ ስራዎች ልክ እንደ መስታወት በዘመናቸው ያለውን ገሃድ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። መስታወት ጉድፍንም ውበትንም በግልጽ ፊት ለፊት እንደሚያቀርብልን የሥነጽሁፍ ስራዎችም እንዲሁ ናቸው። እንደ ሐዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ያለው መጻህፍ ደግሞ በወቅቱ የነበረውን የንጉሳዊ ዘመን ኢትዮጵያ መስታወት ሆኖ አሳይቷል። ይህ መጻሃፍ በርካታ ጊዜ ብዙ የተባለለት ቢሆንም በየጊዜው ምስጢሩ ቢነገር የማይሰለች ነውና ዛሬም የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ምንዋጋው ተመስገን ስለፍቅር እስከመቃብር መስታወትነት ያነሱትን ጥናት መሰረት አድርጌ ሃሳቡን አቀብላችኋለሁ።

«የባለቅኔውን ሕይወትና ሥራዎች የምንመረምረው ራሳችንን፣ አገራችንን፣ ባህላችንንና ማንነታችንን ለመመርመር ነው። ባለቅኔው ወደእውነታችን የሚያደርስ መንገድ እንጂ በራሱ የመጨረሻ ግብ አይደለም» በሚለው ሃሳብ አቶ ምንዋጋው ይስማማሉ። በድርሰት ስራዎች ላይ የደራሲውን ፖለቲካዊ አቋም እናይበታለን፤ ርእዮተ ዓለማዊ ድምጹን እናደምጥበታለን። የኪነጥበብ ስራዎች በተለይ ከታላቅ ተመስጦና አንጽሮት የሚወለዱ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ትንቢታዊነት አያጣቸውም። ትናንትን ከመጥቀስ፣ ዛሬን ከመቅረጽ አልፈው ነገን በገሀድ ይተነብያሉ፤ ነገን በገሀድ ይገልጻሉ። ልቦለድም ይሁን ፍልስፍና የመሰሉ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ከማኅበረሰቡ ታሪክ፣ ባህልና ሕይወት ተቀድተው በአዲስ መልክ ተፈጥረው መልሰው ያንኑ የሚያሳዩን መስታወቶች ናቸው።
እንደ አቶ ምንዋጋው ማብራሪያ ከሆነ፤ ፍቅር እስከመቃብር የተጻፈበት ጊዜም ሆነ የአሁኑ ዘመን ማሳያ ይሆናል። ድርሰቱ የሰዎች የተጨናነቀ ማኅበራዊ ዓለም ማሳያ ነው። ገጸ ባሕርያቱ ከተለያዩ የሕይወት አቅጣጫዎች የተሳሉ እንደመሆናቸው በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውን ሰፊ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ይወክላል። ከገጸ ባሕርያቱ መካከል ባላባቶች (ፊታውራሪ መሸሻና ፊታውራሪ አሰጌ)፣ የቀሳውስት ቡድን (አባ ሞገሴና አለቃ ስርግው)፣ ገበሬዎች (ቦጋለ መብራቱና አበጀ በለው)፣ ባለቅኔዎችና መምህራን (በዛብህና አለቃ ክንፉ)፣ ባሮች (ሀብትሽና ልኩራ በሁሉ)፣ ንጉሠ ነገሥቱ (በስም ያልተጠቀሱ) ይገኙበታል።
ሐዲስ እንደሚነግሩን ለመማር ዓይነ ኅሊናን መክፈት ወሳኝ ነው። ብዙ ጊዜ አካላዊ ዐይኖች ሲዘጉ የማይታየው ይታያል፡፡ ለሰው ሁለት ዓይነት ዐይኖች አሉት። አንዱ ዓይነት አካላዊ ሁለተኛው ዐይነ ኅሊና ናቸው፡፡ ሁለቱ በአንድ ላይ አያዩም፤ ቢያዩም ደኅና አድርገው አያዩም። አካላዊ ዐይኖች ማየት የማይችሉትን ለማየት ዐይነ ኅሊናን መክፈት ያስፈልጋል። ከፍቅር እስከ መቃብርም እንዲሁ ምን እንማራለን? የሚል አጠይቆ አቅርበው ኅሊናችንን በመክፈት ስለ እያንዳንዱ ገጸባህሪ እና መልዕክቶቻቸው ያስረዱናል።
«ላግባሽ አሰጌ» (ፊታውራሪ አሰጌ)
ደራሲው በፊውታራሪ አሰጌ አሳበው ለዚያን ጊዜዎቹ ዋልጌ ባለሥልጣናት ሊነግሩን የፈለጉት ሥነ ምግባራዊ እሴት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው። በመጻሕፉ በቅጽል ስማቸው «ላግባሽ አሰጌ» ስለተባሉት ፊታውራሪ አሰጌ ሲገልጹ እንዲህ ይሉናል።
«ላግባሽ አሰጌ ከማናቸውም የበለጠ ሴትና ዘፈን አጥብቀው ይወዱ ነበር። ከጀግና ወይም ከሽማግሌ አዝማሪ የሚያከብሩ፣ ከንጉሥ ቀጠሮ ለሴት ቀጠሮ ቅድሚያ የሚሰጡ ነበሩ። ቆንጆ ሴት ከመጠን በላይ ከመውደዳቸው የተነሣ ቆንጆ ሴት ባዩ ጊዜ አእምሮ የሚሰውር በሽታ እንዳለባቸው ሰዎች ራሳቸውን መግዛት ያቅታቸው ነበር። ሴት ከመጠን ያለፈ መውደዳቸውን የሚያውቁ ሰዎቻቸው አንዳንድ ጥቅም ሲፈልጉ ሴት ይዘው በመቅረብ ወይም ሴት ለማቅረብ ተስፋ ይሰጧቸው ነበር። የእርሳቸውን ክብርና ጥቅም የሚጎዳ ወይም ስለአስተዳደርና ስለፍርድ የነበራቸውን ኃላፊነት የሚጎዳ መሆኑን ለጊዜው ማየት አይችሉም ነበር» ተብሎላቸዋል። ሐዲስ በዚህ በኩል የዘቀጠ ማንነት ለፍርድ ሰው እና ለአስተዳደርነት እንደማያበቃ በአግባቡ ነግረውናል።
መንግሥቱ ፊታውራሪ መሸሻ (የመንግሥታዊ ሥነ ምግባር ማሳያ)
ፊታውራሪ መሸሻን ህዝብ ያልወደደው ስራ ለማንም እንደማይጠቅም የታየበት ገጸ ባህሪ ሆኖ እናገኘዋለን። «በጎልማሳነትዎ በፈረስ፣ በጉግስ፣ በተኩስ ተወዳዳሪዎችዎን በማሸነፍዎ፣ በጦር ሜዳ ሄደው ጠላቶችዎን ድል መተው በመመለስዎ ሰዉ ሁሉ ሲያደንቅዎ፣ ሲያከብርዎ፣ ሲፈራዎ ጊዜ፣ ለምነው ሳይሆን ተለምነው፣ የጠየቁትን ብቻ ሳይሆን ያልጠየቁትን ጭምር ሲያገኙ ጊዜ እግዚአብሔር በሰፊ መሬቱ ከእርስዎ በቀር ሌላ ክብሩንና ጥቅሙን የሚወድ ሰው እንዳልፈጠረ፣ ሰዉ ሁሉ የእርስዎን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ የራሱ ፈቃድ የሌለው ሆኖ እንደተፈጠረ በሙሉ ልብዎ አምነው በዚሁ ልመራ ብለው ተነሡ። በዳኝነት መንበር ቢያስቀ ምጥዎ በሕግ ፈንታ ፈቃድዎን ሕግ አድር ገው ልፍረድ አሉ። ሀገር ቢሰጥዎ በሕግ እንዲያስ ተዳድሩትና እንዲጠ ብቁት የተሾሙበትን ሕዝብ እንደቀማኛ ይዘርፉት ጀመር። እንዲ ያው በአጭሩ ሕዝብ የጠላው እግዚአብሔር የጠላው መሆኑን ማወቅ አቃተዎ። ስለዚህ ያደን ቅዎ፣ ያከብርዎ የነበረው ሰው ሁሉ ይጠላዎ ጀመር። ሁሉም ሞትዎን ያለዚያም ሽረትዎን አጥብቆ ፈለገ» በሚል ሐዲስ በመጻህፋቸው በገጽ 266 ላይ በአግባቡ አስተችተዋቸዋል።
የጉድ ማኅበር ምንነት
አብዛኛውን ጊዜ በርካቶች የተሳሳቱበት ነገር እንደ ትክክለኛ ነገር ይቆጠራል ይባላል። ጉዱ ካሳም ዕውነትን ይዞ ቢጓዝም በዙሪያው ከበውት የሚገኙ ሰዎች ጋር ለየቅል የሆነ አካሄድ ስላለው የእርሱ መንገድ የጥፋት ተደርጎ ተቆ ጠረ። ባለንበት ዘመንም አገርና ወገን የሚጠቅም ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች በአብዛኛው ህዝብ የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት እብድ ሊያስብላ ቸው ይችላል።
ጉዱ ካሣ እንደሚነግረን «ጉድ» የሚባለው መጠሪያ ለእርሱ የተሰጠ አላግባብ ሆኖ እንጂ ደገኛው ወይም ትክክለኛው ጉድስ የምንኖርበት ማኅበር ነው። በከበበው ዓለም ውስጥ የግሉን ዓለም ፈጥሮ በሰው መካከል ብቻውን ሆኖ ይኖር የነበረው ጉዱ ካሣ የሚኖርበትን (የምንኖርበትን) ማኅበር «ዐይን እያለው ፍሬውን ከገለባ ለይቶ ማየት የማይችል፣ አእምሮ እያለው የሚጠቅመውን ከሚጎዳው ለይቶ ማስተዋል የማይችል፣ እንደበግ መንጋ በፊቱ የሚሄደውን ተከትሎ የሚንጋጋ፣ እንደጭነት ከብት የጫኑትን ተሸክሞ የሚጎተት የጉድ ማኅበር» ይለው ነበር።
የንጉሥ ግብርንም ሲተች «ከሀብቱ ሀብት ከፍሎ እንደሚገብር ከሰውነቱ ከፍሎ ለንጉሥ የሚገብረው የመንፈስ ግብር ነው!» እያለም እምቢተኛነት መለመድ እንዳለበት ካሳ ያስተምራል። ነገር ግን ምንም ቢሆን በግዕዙ እንደሚባለው «ብዙኃን ይመውዑ» ብዙኃን ያሸንፋል ነውና ብዙኃኑ አሸንፈው ጉዱ የሚለው ቅጥያ የካሣ ዳምጤ ስም ማዳመቂያ ሆነ።
ጉዱ ካሳም ይህንንኑ በእራሱ ላይ የደረሰውን ግፍ ያብራራል። «የእኛስ ዘመን ማኅበራዊ ሥሪት በምን ይለያል? … ባሪያው እንዲሸጥ እንዲለወጥ፣ እጀ ሠሪው እንዲናቅ እንዲጓጠጥ፣ ደሀው በጌታ እንዲገዛ እንዲረገጥ ተመድቧል። የድሀ ሽማግሌ ‘አንተ’ እየተባለ እንዲሞት ተደንግጓል። ከንቱ አስቦ ከንቱ የሚናገር ‘ዘመናይ’ ተብሎ እየተደነቀ ገዥ እንዲሆን፣ ቁም ነገር አስቦ ቁም ነገር የሚሠራ የተናቀ ሆኖ ተገዥ እንዲሆን ተመድቧል፡፡ ይገርምሃል! ይህን የማይረባ ልማድ ይህን በግፍ ላይ የተመሠረተ ክፉ ልማድ ተመልክተህ ‘እንዲህ ያለ ልማድ ሊኖር የማይገባው የሚችልም አይደለምና ይልቅ አወዳደቁ እንዳይከፋ ቀስ ብሎ እንዲለወጥ ማድረግ ይሻላል’ ብለህ የተናገርህ እንደሆነ እንደከሀዲ ተቆጥረህ የምትሰቀልበት ገመድ ይሰናዳልሃል» እያለ ያስረዳናል።
«ዝም ብለህ እያዘንህ ተመልካች የሆንህ እንደሆነም እንዲህ እንደእኔ ‘እብድ፣ ጉድ’ እያሉ ሰላምህን አሳጥተው ከማኅበር አስወጥተው፣ በዘመድ መሐል ባዳ፣ ተወልደህ ባደግህበት ሀገር እንግዳ ሆነህ እንድትኖር ያደርጉሃል። ደግሞኮ ይህን ሁሉ የሚያደርጉብህ ‘የጌታ ዘር ነን’ የሚሉት ሁሉንም ረግጠው እላይ የተቀመጡት ብቻ ቢሆኑ ‘ጥቅማቸው እንዳይጎድልባቸው ነው’ ትላለህ፡፡ ነገር ግን ባሮቹ፣ እጀ ሠሪዎቹ፣ ድሆቹ ሁሉ፣ ግፍ የሚሠራባቸው ሁሉ ከግፍ ሠሪዎች ጋር አንድ ላይ ተባብረው ሲፈርዱብህ ምን ትላለህ? ‘ከልማድ ጋር የማይስማማ እውነት ሁልጊዜ ሀሰት ነው’ የሚባለውን የማይረባ ተረት አስበህ ዝም ማለት ብቻ ነው፡፡ እየውልህ! በጠቅላላው የዚህ ልማድ እስረኞች ነን» እያለ ዕውነት መገለባበጧን እያስረዳ ይቀጥላል።
ቄስ ምሕረቱ፣ ቄስ ሞገሴና አባ ተክለ ሃይማኖት
ቄስ ምሕረቱ በሐይማኖት ምግባራቸው ትክክለኛ ያልነበሩ አሳሳች ነበሩ። «እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ» የተባሉ ካህናትና መነኮሳት ማጣፈጣቸው ቀርቶ ራሳቸው አልጫ ሲሆኑ፣ ብርሃንነታቸውን በጨለማነት ሲተኩ አያድርስ ነው።
ቄስ ምሕረቱ ከሰው ሕይወት ይልቅ የገንዘብ ፍቅር እንደሚበልጥባቸው የአቶ ቦጋለን መሞት ከእመት ውድነሽ ሲሰሙ የመለሱት መልስ ምስክር ይሆናል።
የአባ ምሕረቱን የሥነ ምግባር ደረጃ የአባ ቦጋለን ሬሳ እንዲያመጡ በሚልኳቸው ሰዎች በኩልም ማየት ይቻላል። ገብሬ የተባለ አገልጋያቸውን በተላላፊ በሽታ ነው የሞተ ወደተባለው የቦጋለ መብራቱ ሬሳ ወዳለበት ቤት ልላከው ወይስ ይቅር እያሉ ከተወዛገቡ በኋላ «ይሂድ ግዴለም፤ እግዚአብሔር ለእኔ ካለው ምንም አይሆንም፤ … መቼስ የሰው መፈረጃ ከመሆን የማይሻል የለም» እያሉ ሰው ምን ይለኛል በሚል ስሜት ብቻ መወጠራቸውን ያሳያል። ይህም ሐዲስ በሐይማኖታዊ ግብራቸው ሳይሆን በጥቅም የሚመሩ ሰዎች መኖራቸውን ሲያሳዩን ነው።።
ቄስ ሞገሴ ደግሞ ዕውቀት አጠር ስለነበሩ ድጋፋቸውም ሆነ ተቃውሟቸው የእምነቱን ሕግጋት የተከተለ ሳይሆን የፊታውራሪና የቀራቢዎቻቸው ዓይንና ግንባር ብቻ ነበር። ለጉዱ ካሣ አንዱ ራስ ምታትም እነፊታውራሪን ገሥጸው ወደበጎ ከመመለስ ይልቅ ለግፉ ተግባራት ተባባሪ የሆኑ እነአባ ሞገሴ መሆናቸው ነው። ጉዱ ካሣ ስለዘመናችን አባ ሞገሴዎችም እንዲህ የሚለን ይመስላል፡- «አባ ሞገሴ እንደምታውቋቸው የራሳቸው ሐሳብ የሌላቸው፣ የሰውን ሐሳብ ብቻ ከዓይኑና ከግንባሩ አይተው ለመተርጎም ችሎታ ያላቸው፣ ሆዳቸውን የሞላና በፈለገው መንገድ የሚመራቸው፣ ተግባራቸውን ለሆዳቸው የሸጡ የለወጡ ናቸው» እያለ ይወርፋቸዋል።
ከጉሊትና ከናሞራ ባላገሮች ተልከው የመጡት ሽማግሌ ሲናገሩም አባ ሞገሴ ፊታውራሪ ሲቆጡ አይተው «ዝም ይበሉ እርስዎ ምን ያሉ የሽማግሌ ባሕሪ የሌላቸው ናቸው እባካችሁ! እዚህ ጠብ ለመፍጠር የሰይጣን መላክተኛ ሆነው ነው የመጡት?» ማለታቸው የአባ ሞገሴን የወረደ ሥነምግባር ያሳያል። የሥነ ምግባር ትንተናውን ሙሉ የሚያደርገው አባ ሞገሴንና መሰሎቻቸውን ከቤተ ክህነት አውጥቶ ማየት ከተቻለ ብቻ መሆኑን ደግሞ አጥኚው ያስረዳሉ።
አባ ሞገሴዎች የሌሉ በት የማኅበረሰብ ክፍል ካለ ያ ማኅበረሰብ ከመለ ካውያን የጸዳ ስለሆነ ዕድለኛ ነው፡፡«መለካዊ» ማለት በሃይማኖት ስም የንጉሥን ፈቃድ ብቻ የሚፈጽም እግሩ ቤተ ክርስቲያን ልቡ ቤተ መንግሥት ያለ ጳጳስ ማለት ነው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች «ድርጓቸ ውም ሹመታቸውም ከንጉሡ በመሆኑ ፣ ብዙ ጊዜም ከነገሥታቱ ጋር ስለሚውሉ ምንም ዓይነት ችግር ቢያዩ በዝምታ ከማሳለፍ በቀር የሚቃወ ሙበትና የሚገሥጹበት አጋጣሚ አልነበረም» ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሐይማኖታዊ ግብራቸው በሀቀኝነት የሚቆሙ አይጠፉም። እንደዚህ አይነት ጊዜ ብዙ ጊዜ አለመግባባትና ችግር የሚፈጠረው ሹመ ትና ገንዘብን ንቀው በነበሩ አባቶች እና ለገን ዘብ ሲሉ በመነኮሱትና ክህነት በተቀበሉት መካ ከል ነበር።
ስለ አባ ተክለ ሃይ ማኖት ደግሞ «እየው ልህ! ቤተ እግዚአብሔር እንደዚህ ላሉት ሽፍቶች፣ እንደዚህ ላሉት ዘራፊዎች ዋሻ ሆነች! እየውልህ! ካህናታችን ከሐዋርያታችን የሚበዙት ከአለቆች ጀምሮ በመነኮሳቱ አልፎ እስከተራ ደብተሮች እስከዲያቆናቱ ድረስ አንዱ አስማት አድራጊ። አንዱ አስማት ፈቺ፣ ሌላው ጋኔን ስቦ አምጪ ሌላው አስወጪ፣ አንዱ መቅሰፍት አምጪ ሌላው ምሕረት አሰጪ ነን እያሉ ውሸታቸውን በየጥምጥማቸው በየቆባቸው በየደበሏቸው ሸሽገው ሊመሩት ሊያስተምሩት በተሰጣቸው መንጋ የሚጫወቱ ናቸው!። ታዲያ ከእነዚህ ጋር ማኅበርተኛ ሆኖ በአንድ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት በተቀደሰ ስሙ ማፌዝ አይደለም?። እየውልህ! ይህ ነው ከምወዳት ቤተ እግዚአብሔር ያራቀኝ! ሰው የሚለው ሌላ ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ ይህ ነው» እያለ በመጻህፉ ገጽ 428 ላይ ያስቀምጣቸዋል።
ስለእኝህ አስመሳይ ሰው ወይም አባ ተክለሃይማኖት የቀረበው ምጸታዊ ገለጻ ቤተ እግዚአብሔርን ተጠግተው በሚያረክሱት የካህናት አባላት ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ ሂስ ነው። ጉዱ ካሣ ስለብዙኀኑ ካህናት ምግባረ ብልሹነት ለበዛብህ ሲነግረው የነበረውን በተግባር የሚያሳይ ነው። ሰብለ የአባ ተክለሃይማኖትን የመነኩሴ ደበሎና ቆብ መግፈፍ በአንድ በኩል ትእምርታዊ ሆኖ እናገኘዋለን። አባ ተክለሃይማኖት የማይገባቸውን ሃይማኖታዊ ክብር በአስመሳይነት ስለተጎናጸፉ ያን በመግፈፍ እውነተኛ ማንነታቸውን የማጋለጥ ሚና ሲኖረው፣ ያ የተጨማለቁበት ትውኪያ ደግሞ የኃጢአታቸውን፣ የርኩሰታቸውን፣ የዝቅጠታቸውን መጠን ማሳያ ነው።
እንደ አቶ ምንዋጋው ማብራሪያ፤ ይህን የአባ ተክለ ሃይማኖትን «ቤተ እግዚአብሔርን ተጠግተው በሚያረክሱት የካህናት አባላት» ማሳያ ብቻ አድርጎ ማቆም አያስፈልግም። ይልቁንም እርሳቸውን «ቤተ መንግሥትን ተጠግተው» ያልተገባ ሥራ በሚሠሩ የካቢኔ አባላትም መመሰል ይቻላል። ይህ የዘመናችን መንፈስ መገለጫ ስለሆነ ደግሞ ዘረኝነት፣ ጉቦኝነት፣ ሴሰኝነትና ዕብሪት አድርገን ልንተረጉመው እንችላለን።
አበጀ በለውና ነጋዴው ዓሊ ጅብሪል
አበጀ በለው በፊታውራሪና በሹማምንታቸው የሚፈጸመው ግፍ ሲበዛ ተመልክቶ ለብዙኀኑ መብት መጠበቅ ሲል የሸፈተ ገበሬ ነው። ሊዘርፉ የሄዱትን ፊታውራሪ ከማረካቸው በኋላ የሚናገራቸው ነገርም ይህን ዓላማውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። እርሳቸው ተማርከውም እንኳ ባልተረታ መንፈሳቸው አበጀ በለውን «ሕዝቡን ያሳመጽህ ሽፍታ ነህ» ቢሉትም አበጀ ግን ሲመልስላቸው ዕውነቱን ያግታቸው ነበር።
«ሥልጣንን በዙሪያቸው አጥረው በሥልጣን ውስጥ ተሸሽገው ድሀ የሚዘርፉትን፣ ድሀ የሚቀሙትን፣ በራሳቸው ወንጀል ድሀ አስረው የሚገድሉትን ግፈኞች ሽፍቶች እቃወም ነበር እንጂ ሽፍታ አልነበርሁም። እቤቴ ተቀምጨ ባለሥልጣኖች የሚሠሩትን ግፍ በሕግ ለመቃወም ስላልቻልሁ ቤቴን ትቼ መሰደዴ ሽፍታ አያሰኘኝም። አብረውኝ ሰባት ዓመት በዱር በገደሉ የተንከራተቱት ብዙዎች ስለሆኑ አንዱን በአጋጣሚ አግኝተው ቢጠይቁት እንኳን የሰው የከብት ደም ሲፈስ ማየት የማልወድ መሆኔን ይነግርዎታል። ደም ሲፈስ ከማየቱም ደግሞ የድሀ ሕይወትና ንብረት እንዲጠበቅበት የተሠራው ሕግና የተሰጠው ሥልጣን ተጣሞና ተቆልምሞ ለድሀ ሕይወት ማጥፊያ፣ ለንብረት መዝረፊያ፣ ለአመጽ መፈጸሚያ ሲሆን ማየት ከሁሉ የበለጠ ያስጠላኛል፤ በጣም ያንገፈግፈኛል» እያለ የልቡን ይነግራቸዋል። ይህም በገሃዱ አለም የሚታዩ ለህዝብ ሲሉ የሚታገሉ ሰዎችን ያስታውሰናል።
ነጋዴው ዓሊ ጅብሪል በበኩሉ የንግድ ሥነ ምግባር የሌለውና ለህዝቡ ሲሉ በሚታገሉ ግለሰቦች ጋር አንድ አገር ላይ የሚኖር አስከፊ ሰው ነው። «የገበያ ሽብር ለሌባ ይበጃል» እንደሚባለው ሁሉ የንግድ ሥነ ምግባር ሲጠፋ ነጋዴዎች ሁሉ ሕጋውያን ቀማኞች ይሆናሉ። በዛብህ አዲስ አበባ ወደጉለሌ ሲሄድ ሁለት የጎጃም ነጋዴዎች ሲነጋገሩ ያደመጣቸውን እናንሳ «አሁንኮ ዐሊ ጅብሪል ቆዳችንን መዝንልንና ዋጋ እንነጋገር ብንለው አንድ ጊዜ ‘ሚዛኑ ተሰብሯል’ አንድ ጊዜ ‘መዛኙ ታሟል’ እያለ ዛሬ ነገ የሚለን ፋሲካ እስኪደርስለት ነው» አለ አንዱ ነጋዴ። «ፋሲካ ሚዛን ይሆናል ወይስ መዛኝ?» አለ ሁለተኛው፡፡ «የለም ‘ዛሬ ነገ እያልሁ ፋሲጋ እስኪለግት ካቆየኋቸው ለማጫረት ጊዜ ያጥራቸውና በርካሽ ዋጋ ጥለውልኝ ይሄዳሉ’ ብሎ ነው እንጂ» እያሉ ስለ ዓሊ መጥፎ ስነምግባር አውርተዋል። ይህም ዝም ብሎ ከመጻህፉ ውስጥ የተገኘ አይደለም እንደውም የዘመናችንን የንግድ መንፈስ የሚወክል ይመስላል።
የቦጋለ መብራቱን ቻይነት
ቦጋለ ትዕግስተኛና ቻይ በመሆኑ ደግሞ ለትዳሩ መቆም አቅም ሰጠው። ችግር ሳይሸነፉለት ሲለምዱት ከእርሱ ጋር እየታገሉ እየወደቁ እየተነሡ ሲኖሩ ጥሩ ነው። ከችግር ጋር ሲታገል የኖረ ቆዳው ይወፍራል፤ ጅማቱ ይጠነክራል፤ ጡንቻው ይደነድናል፤ የተጣለበትን ሸክም ሁሉ መሸከም ይችላል፤ የገጠመውን ሁሉ ያሸንፋል። ስለዚህ እድሜ ላሳዳጊያቸው፣ እድሜ ለአስተማሪያቸው፣ እድሜ ለችግር፣ ቦጋለ መብራቱን ቆዳቸውን አወፍሮ፣ ጅማታቸውን አጠንክሮ ትግል እያስተማረ አደንድኗቸዋል። ስድብና ቁጣ፣ የንቀትና የግልምጫ ውሽንፍር እንዳይገባቸው አድርጎ ሁሉን እንዳመሉ እንዲችሉ አድርጎ ላነፃቸው ለቀረጻቸው እድሜ ለችግር አቶ ቦጋለ ሁሉንም ቻይ ነበሩ። ይህ የአቶ ቦጋለ መቻል ትዕግሥታቸውና መሸነፍን እንደውርደት አለመቁጠራቸው ከእመት ውድነሽ ይቅር ባይነት ጋር የተቆጡበትንና ምርር ብለው ያለቀሱበትን ቶሎ የሚረሱ ከመሆናቸው ጋር አንድ ላይ ሆኖ ጠቅሟቸዋል። ይህም ጊዜ ባለፈ መጠን ባልና ሚስት እንዲቻቻሉ፣ ባሕርይ ለባሕርይ እንዲተዋወቁ፣ ለፍሬ እንዲበቁ ‘ማን አለው? ማን አላት?’ እየተባባሉ እንዲተሳሰቡ አድርጎ ትዳራቸውን አጸናላቸው። በዚህ ገጸባህሪም ውስጥ በትዳር እና በማህበረሰብ ውስጥ የትዕግስትንና የጽናትን ተምሳሌትነት መማር እንደሚቻል አጥኚው ያስረዳሉ።
የቀኛዝማች አካሉ «ጽርየት» (ለሌሎች ክብር መኖር)
ቀኛዝማች አካሉ ፊታውራሪ መሸሻን በጣም ይወዷቸዋል። ትውልዳቸውም እኩል ነው። ፊታውራሪ መሸሻና የፊታውራሪ አሰጌ ግጭት በሆነ ጊዜ ደግሞ ቀኛዝማች የራሳቸውን ክብር ረስተው የፊታውራሪ አገልጋያቸው ለመሆን የቆረጡ ሰው መሆናቸው በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ባይሆን ኖሮ የመሰንበቻው ሁኔታቸው የፊታውራሪ አሰጌ ወገን አስመስሎ ባስጠረጠራቸው ነበር። በወሬው ሁሉ የፊታውራሪ መሸሻ ጀግንነትና የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪነት ሲነሣ ጥርሳቸው ሌሎችን ለመምሰል ያክል ቢስቅም ግንባራቸው ሲቋጠር ወይም አንዳንድ ምክንያት ፈጥረው ከዘመድ መሐል ተነሥተው ሲወጡ ወይም ሌሎቹ የሚያደርጉትን ሁሉ በማድረግና ባለማድረግ መሐከል መቁረጥ አቅቷቸው ሲያመነቱ ይታዩ ነበር።
ምክንያቱ ሌሎቹ የማያውቁትን የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪ አለመሆን እርሳቸው ያውቁ ስለነበረ ነው። ነገር ግን ተነስተው ዘራፍ አላሉም። ይህም ለሌሎች ክብር መኖር የመሰለ ህይወትን ያሳየናል። አቶ ምንዋጋው ሲያጠቃልሉም በአጠቃላይ ፍቅር እስከመቃብር ላይ ያሉ ገጸባህሪያትን ብንመለከት የአሁኑ ዘመንም የማህበረሰቡ ነጸብራቅ ሆነው እናገኛቸዋለን። የሐዲስን ማኅበራዊ ሂስ በታላላቆቹ ገጸባህሪያት ብቻ ሳይሆን በታናናሾቹም ላይ የሚያሳይ በመሆኑ ለዘመናት ቢነገርለት የማይሰለች ልብወለድ ነው። በመሆኑም ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ በስራቸው ለማህበረሰቡ መስታወት ሆነዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

የዓውደ ርዕይ ማድመቂያዎች

 

በባህል ዘርፍ የሚመራመሩ ሰዎች እንደሚሉት ባህል ማለት የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ነው፡፡ ይሄ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ስለባህል ግልጽ ያልሆነ ግን ሌላ ትርጉም አለ፡፡ ተመራማሪዎቹ የሚሉት ባህል ማለት ያለፈ ሳይሆን አሁን እየተተገበረ ያለ ነው፡፡ የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ነው ሲባል ያ ማህበረሰብ ያንን ባህል እየተገበረው መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ በፊት ይጠቀምበት የነበረውን ከሆነ የሚያሳየው ቅርስ እንጅ መገለጫው አይደለም፡፡ ያ ማህበረሰብ አሁን ሌላ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ይህኛው የባህል ትርጉም አሁን ላይ ግልጽ ሆኖ የሚሰራበት አይመስልም፡፡
አሁን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል ብዙ ወቀሳ እየተነሳበት ነው፡፡ የሚሰራው ሥራም የሚያስወቅስ ነው፡፡ ብዙም ሳንሄድ የሚዘጋጁ የባህል መድረኮችን ማየት በቂ ነው፡፡ ከፌዴራሉ የባህልና ቱሪዝም ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ያሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፤ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ዓመት ጠብቆ ፓናል ከማዘጋጀትና የተጠኑ ጥናቶች ፓናሉ ላይ ከማወያየት ባለፈ ሚናቸው ምን መሆን አንዳለበት የሚያስቡ አይመስሉም፡፡
በየጊዜው የባህል ፌስቲቫሎች ይዘጋጃሉ፡፡ በሚዘጋጁት ፌስቲቫል ላይ የሚቀርቡት ዕቃዎችና አልባሳት ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸው ሳይሆኑ በፎቶ ብቻ ያሉ ናቸው፡፡ በአካል ያሉ ዕቃዎችም አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሳይሆኑ ለዓውደ ርዕይ ብቻ የሚወጡ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ባህል ሳይሆን ቤተ መዘክር (ሙዚየም) ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብሄራዊ ሙዚየም ውስጥ ቢቀመጡ ይሻላል፡፡
ጥያቄው እነዚህ ዕቃዎች ለምን ዓውደ ርዕይ ላይ ይቀርባሉ? አይደለም፤ ዳሩ ግን የባህል ማዕከላት ሥራ መሆን ያለበት ኅብረሰተቡ እነዚህን ዕቃዎች አውቋቸው መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ ሥራ መስራት ነው፡፡ ራሳቸው አዘጋጆቹ እኮ የባህል ልብስ የሚለብሱት ለዚያ መድረክ ብቻ ነው፡፡ እነዚያን የባህል ዕቃዎችና አልባሳት የማየት ዕድል ያለው ዓውደ ርዕዩ የተዘጋጀበት ቦታ የሄደ ሰው ብቻ ነው፡፡ ወይም ደግሞ በቴሌቪዥን ተቀርጸው የማየት ዕድል ያለው ነው፡፡
ባህርዳር ከተማ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከልና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጀው የባህል ፌስቲቫል ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ወደ ሙሉዓለም የባህል ማዕከል ሲገቡ ገና መግቢያው በር ላይ ግራና ቀኝ የተተከሉ ድንኳኖች ይታያሉ፡፡ ወደ ድንኳኖች ሲገባ ከባህል አልባሳት ጀምሮ ብዙ የባህል የመገልገያ ዕቃዎችና ጌጣጌጦች ይታያሉ፡፡ ዕቃዎችንም ብዙ ሰዎች ይሸምታሉ፤ ይጎበኛሉ፤ እኔ ግን በድንኳኑ ውስጥ ጉብኝት የሆኑብኝ ዕቃዎቹ ሳይሆኑ ሰዎቹ ነበሩ፡፡
34 ድንኳኑ ውስጥ ያሉ የዓውደ ርዕይ ዕቃዎች ለዕይታ ብቻ ሳይሆን ለሽያጭ የቀረቡ ናቸው፡፡ የሚጎበኙት ሰዎች ግን ዋጋ የሚጠይቁ እንዳይመስላችሁ! በዋጋ ከሚከራከረው ይልቅ ‹‹ይሄ ደግሞ ምንድነው፣ የየት አገር ባህል ነው፣ ለምን ያገለግላል?›› እያለ የሚጠይቀው ይበልጣል፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ! ኢትዮጵያዊ ሆኖ የባህል መሳሪያው የራሱ መሆኑን የማያውቅ በዝቷል ማለት ነው፡፡ ‹‹የአንዱን ብሄረሰብ አካባቢ የሌላው ብሄረሰብ ላያውቀው ይችላል›› እንዳትሉኝ! ከጎጃም አካባቢ መጥተው የጎጃምን ዕቃ የሚጠይቁ፤ ከኦሮሞ መጥተው የኦሮሞን የባህል ዕቃ የሚጠይቁ ናቸው ያጋጠሙኝ፡፡ ይሄ ማለት እንግዲህ ባህል ላይ በዓመት አንድ ጊዜ ዕቃዎችን ለዓውደ ርዕይ ከማውጣትና ከአዳራሽ ውስጥ ከማክበር በስተቀር ምንም አልተሰራም ማለት ነው፡፡
ወይዘሮ ይታይሽ አታላይ ይባላሉ፡፡ በዓውደ ርዕዩ ላይ የባህል ዕቃዎችን ለሚጎበኘው ያስጎበኛሉ ለሚገዛውም ይሸጣሉ፡፡ ከያዟቸው የባህል ዕቃዎች ውስጥ ለመዋቢያ የሚሆኑት ብቻ ሲሸጡ ሌሎች ዕቃዎች ግን ለምን እንደሚያግለግሉ የሚጠይቃቸው ይበዛል፡፡ እኔም ከጠያቂዎች ሆንኩና አንድ ዕቃ አንስቼ ጠየቅኳቸው፡፡ ከቀንድ የሚዘጋጅ የጠላ ወይም የጠጅ መጠጫ ነው፡፡ ዕቃው በቀላሉ አይሰበርም፤ ወድቆ የመዳን ጥንካሬ አለው፡፡ ይህን ዕቃ ግን እንደ ቅርስ እየጎበኙ ከመሄድ በስተቀር ማንም አይገዛውም፡፡ በየቤቱ ውስጥ በቀላሉ የሚሰባበር ብርጭቆ አለ፤ ይህ ጠንካራ የአገር ስሪት ዕቃ ግን የለም፡፡
ከዚህ ይልቅ ወይዘሮ ይታይሽ እየሸጡ ያሉት የመዋቢያና የጌጣጌጥ ዕቃዎችን ነው፡፡ ለሽታ የሚሆነው ጭስ ይሸጣል፤ ስሪቱ በዘመናዊ መንገድ ቢሆንም የባህል ጭስ ተጨምሮበት ያለው የሽቶ ዓይነት ይሸጣል፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉት ዕቃዎች ግን የሙዚየም ዕቃዎች ሆነዋል፡፡


ወደሌላኛው ድንኳን ገባሁ፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ ስሙም አዲስ የሆነ የባህል ዕቃ አገኘሁ፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የባህል እሴቶች ልማት ባለሙያ አቶ ሃይሌ ሞላ ስለእቃዎቹ ነገሩኝ፡፡ ‹‹እርኮት›› የሚባል አንድ የመገልገያ ዕቃ አሳዩኝ፡፡ ይህ ዕቃ የውሃ መጠጫ ነው፡፡ የሚዘጋጀው ከስፌት ነው፡፡ በዚህ ዕቃ ውስጥ የተቀመጠ ውሃ ልክ በዘመነኛው ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ውስጥ እንደማስቀመጥ ማለት ነው፡፡ ውሃውን ያቀዘቅዘዋል፡፡ እስኪ ይህን ነገር ከዘመናዊው ብርጭቆ ጋር እናነጻጽረው፡፡ የብርጭቆ ውሃ ወዲያውኑ ካልተጠጣ እየቀዘቀዘ ሳይሆን እየሞቀ ነው የሚሄደው፡፡
ሌሎችም ዕቃዎች አሉ፡፡ ሴቶች ሹሩባ ተሰርተው እንዳይበላሽባቸው የሚንተራሱት ትራስ በባህላዊ መንገድ የተሠራ ነው፤ ብርኩማ ይባላል፤ ከቆዳ ይዘጋጃል፡፡ ብዙ የጌጣጌጥ ዕቃዎችም አሉ፡፡ እያንዳንዳቸው ዕቃዎች የየራሳቸው ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ እጅ ላይ የሚደረጉ፣ አንገት ላይ የሚደረጉ፣ ጸጉር ላይ የሚደረጉ፣ እግር ላይ የሚደረጉ፡፡ እነዚህ ጌጣጌጦች ሲደረጉ ዝም ብሎ ለመዋቢያነት ብቻ እንዳይመስላችሁ! ሁሉም የየራሳቸው ትርጓሜ አላቸው፡፡ የታጨች ሴት የምታደርገው፣ ያገባች ሴት የምታደርገው፣ ገና ልጅአገረድ የሆነች ኮረዳ የምታደርገው ነው፡፡ ባህሉን የሚያውቅ ሰው ያደረገችውን አይቶ ልጅቷ ያገባችና ያላገባች መሆኑን ያውቃል ማለት ነው፡፡ ይሄም ልክ በዘመነኛው ቀለበት አይቶ እንደሚፈረጀው ማለት ነው፡፡
አሁን ላይ የምናያቸው ዘመናዊ የመገልገያ ዕቃዎች ከመኖራቸው በፊት ሁሉም በባህላዊ መንገድ ነበሩ፡፡ እዚህ ድንኳን ውስጥ ከእንጨት የተዘጋጀ የጸጉር ማበጠሪያ አለ፣ ከእንጨት የተዘጋጀ ማንኪያ አለ፣ ከእንጨት የተዘጋጀ ገበቴ አለ… ብዙ ከእንጨት የተዘጋጁ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ዕቃዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ዛሬም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ የባህልን ጥበብነት፣ የባህልን የቴክኖሎጂ መነሻነት በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡ ያንን የእንጨት ማንኪያ የሰራ ሰው ዘመናዊውን ማንኪያ አይቶ የማያውቅ ነው፡፡ ገበቴ ከእንጨት ሲያዘጋጁ የፕላስቲኩ ሳፋ ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ የእንጨት የጸጉር ማበጠሪያ ሲሰራ ዘመናዊው ማበጠሪያ አልታሰበም፡፡
ከእንጨት ከሚዘጋጁ የመገልገያ ዕቃዎች ውስጥ ገበቴ ወይም በአንዳንድ አካባቢዎች አጠራር ቆሪ የሚባለውን እንመልከት፡፡ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ይህን ትልቅ ዕቃ ከእንጨት ለማዘጋጀት ማሰብ በራሱ ጥበብ ነው፡፡ እንጨት እንደዚያ አይነት ጥልቀት ያለው ዕቃ ይወጣዋል ብለው መጀመራቸው፡፡ ገበቴውን ተሰርቶ ካበቃ በኋላ ያየ ሰው ከእንጨት የተዘጋጀ ነው ብሎ ማንም አያምንም፡፡ ይህን ሲሠሩ ምንም አይነት ዘመናዊ ማሽን አልተጠቀሙም፤ መጥረቢያ ብቻ በቂ ነው፡፡
ይህ የእንጨት ገበቴ (ቆሪ) ብዙ አግልግሎችን ይሰጣል፡፡ አግልግሎቱም እንደየ ገበቴው አሰራርና መጠን ይለያያል፡፡ አንዳንዱ ገበቴ ከመሃሉ ላይ ሌላ ገበቴ ይኖረዋል(ልክ በቤት ውስጥ እንዳሉ ክፍሎች ማለት ነው)፡፡ የዚህ አይነት ገበቴ ለመመገቢያነት ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ ገንፎ ሲበላ የገበቴው መሃል ክፍል ላይ የገንፎው ማባያ ይቀመጣል፡፡ ገንፎው ዳርዳሩን ይሆናል፡፡ ሌላም ምግብ ቢሆን እንደ አስፈላጊነቱ ምግቦችን በገበቴው ክፍል ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ እንዲያውም ይሄ ነገር በትልልቅ ሆቴሎች ራሱ ቢለመድ ጥሩ ነበር፡፡
የጌጣጌጥ ዕቃዎችንም እንይ፡፡ ሴቶች ጸጉራቸው እንዳይበላሽ በአተኛኘትም ይሁን በሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ዛሬም እናያለን፡፡ ይህ በባህላዊው አሰራር ምቹ የሆነ የትራስ አይነት ነበረው፡፡ ሰውነትን የማይጎዳ ከቆዳ የሚዘጋጅ ትራስ ለዚህ አግልግሎት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ከባህል ዕቃዎች ውስጥ ሌላው ‹‹ማጨብጨቢያ›› የሚባለው ነው፡፡ ይህም ከእንጨት የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህኛውን ለማስረዳትስ ዘመነኛውን ማስቀደም ሳይሻል አይቀርም፡፡ በፍርድ ቤት ወይም በአንዳንድ ቢሮዎች ውስጥ አለቆች ጸሐፊዎቻቸውን ለመጥራት የሚጠቀሟትን ‹‹ጭርርርር!›› የምትል ነገር ታውቋታላችሁ አይደል? እንግዲህ እሷ ምናልባት ፈረንጅ የሰራት ልትሆን ትችላለች፡፡ ማንም ይሰራት ማን ግን በአገራችን ውስጥ መጀመሪያ ከእንጨት ተሰርታ ነበር፡፡ አገልግሎቷም እንደዚሁ በድምጽ ለመግባባት ነው፡፡ የእንጨቷ ግን ሌላም ተደራቢ አገልግሎት አላት፡፡ በጨዋታ ጊዜ ለጭብጨባ ማድመቂያም ትሆናለች፡፡
ምን ዋጋ አለው እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች የዓውደ ርዕይ ዕቃዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከማንኛውም ቤት ውስጥ የምናገኛቸው አልሆኑም፡፡ እንኳን ዕቃዎችን ማግኘት የዕቃዎችን ስም ማወቅ ራሱ ብርቅ ሆኗል፡፡ ዕቃዎቹ ብቻ ሳይሆን ስማቸውም ሙዚየም ሊገባ ነው፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ዕቃዎች በሱቅ ውስጥስ ይገኙ ይሆን? በባህርዳር ከተማ ውስጥ በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ወደሚገኙ የባህል ዕቃ መሸጫዎች አመራሁ፡፡ ወጣት ሙሴ ልዑለቃል በአንደኛዋ የባህል ዕቃዎች ሱቅ ውስጥ አገኘሁት፡፡ ወጣት ሙሴ እንደሚለው ከባህል ዕቃዎች ውስጥ የሚሸጠው አልባሳት ብቻ ነው፡፡ በሱቁ ውስጥ የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎችን ጨምሮ የጌጣጌጥና የተለያዩ የቅርጻቅርጾች አሉ፡፡ የሀውልትና የነገስታት ቅርጻቅርጾች አልፎ አልፎ የሚሸጡ ሲሆን የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎች ደግሞ በጣም አልፎ አልፎ ይሸጣሉ፡፡ ከእንጨት የተዘጋጁ የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎች ግን ጭራሹንም እንደማይሸጡ አጫወተኝ ፡፡
እነዚህ የቴክኖሎጂ መነሻ የሆኑ የባህል ዕቃዎቻችን የዓውደ ርዕይ ማድመቂያ ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡ እኛም እንደ ፈረንጅ ‹‹ይሄ ምንድነው?›› እያልን መጠየቅ ጀምረናል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ገና ብዙ ዕቃዎችና የፈጠራ ሥራዎች ወደ ሙዚየም ይገባሉ፡፡ ሙዚየም የገባ ዕቃ ባህል ሳይሆን ቅርስ ነው፡፡ ይህ ነገር ከመሆኑ በፊት የባህልና ቱሪዝም አካላት ከታይታ ያለፈ ሥራ ሊሰሩ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

 

70 ዓመታትን በጥበብ

 

የሙዚቃ ግጥም ጸሐፊ፣ የቴአትር ባለሙያ፣ የፊልምና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ተዋናይ ነው። ኮሜዲነትም ይሞክራል። በተለይ በዓላት ወቅት ከቴሌቪዥን መስኮት ላይ በኢትዮጵያ አልባሳት አሸብርቆ መታየት የተለመደ ነው። በጦር ሠራዊት፣ በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ባንድ ውስጥም እየተዘዋወረ  ሰርቷል። የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የኪነት ቡድን መስራችና የቴአትር አሰልጣኝ  ነበር። የከፍተኛ፣ የቀበሌ በሚባሉ የኪነት ቡድኖች ውስጥ በመዘዋወር የተለያዩ የኪነጥበብ ስልጠናዎችን ሰጥቷል። በትራንፔት ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት ይታወቃሉ። የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን አርቲስት ተረፈ ለማ።  አርቲስት ተረፈ የሰባ ሰባት ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ነው። አንተ ብለን አንድናወራው ስለወደደ  አክብሮታችን እንደተጠበቀ ሆኖ አንተ እያልን እንቀጥላለን። መልካም ንባብ!

«ተረፈ ቁራ»
ቀጨኔ መድኃኒዓለም ማርገጃ አካባቢ ሄደው ተረፈ ለማ ብለው ቢጠይቁ ማንም ሊነግርዎት አይችልም። ምንም እንኳን ውልደቱና ዕድገቱ እዚያ ቢሆንም «ተረፈ ቁራ» ካሉ እርሱን የማያገናኝዎ አይኖርም። ቤተሰቡ ያወጡለት ተረፈ ለማ ቢሆንም በቅጽል ስሙ ተረፈ ቁራ እየተባለ ይጠራል። ተረፈ የሚለው ስም የወጣለት ትልቅ ምክንያት ነበረው። በ1933 ዓ.ም ታኀሣሥ 29 የተወለደው በሰባት ወሩ ነበር። ከመንታው ጋር ነበር ሆስፒታል ውስጥ እናቱ በጭንቅ የተገላገለችው።
በወቅቱ ማንም ይተርፋል ብሎ አላመነም፤ በተለይ መንታው ሲሞት ከዛሬ ነገ ይሞታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ግን መዳን ከፈጣሪ ተቸረውና ሳይሞት ቀረ። ይህንን የተመለከቱት አባቱም «ተረፈልኝ» ለማለት ፈለጉና ተረፈ የሚል ስም አወጡለት። የአካባቢው ሰው ግን ተረፈ ቁራው በማለት ይጠራዋል። ቅጽል ስሙን ያገኘው ደግሞ በሚሰራቸው ተግባራትና ባለው ጥቁር መልክ የተነሳ ነበር። ስለዚህም ቁራ በጣም ይበራል፤ እርሱም በጣም ፈጣን ሯጭ በመሆኑ ከልጅነቱ ጀምረው የአባቱን ስም ትተው ተረፈ ቁራ ሲሉ ይጠሩታል።
ህጻኑ ተረፈ በልጅነቱ ምርጥ የሚባሉ የጭቃ ላይ ስዕሎችን መሳል የሚወድ ሲሆን፤ ሸርተቴ፣ ሩጫ፣እግር ኳስ ከሚጫወታቸው የጨዋታ ዓይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይ በእንጨት ሰበራ ማንም የሚችለው አልነበረም። እንደውም በአንድ ወቅት አንድ በዓል ላይ ቤተሰቦቹ ባይፈቅዱለትም ገንዘብ ለማግኘት ሲል በርከት ያለ እንጨት ሰብስቦ ችቦ ሰርቶ በመሸጥ በእጁ ይዞት የማያውቅን ገንዘብ መያዙን ያስታውሳል። አዲስ ዓመት ላይ ልብሱን ሽክ የሚያደርገውም በሚለቅመው እንጨትና በሚሰራቸው ችቦዎች ሽያጭ ነበር። በተለይ መጀመሪያ አካባቢ እንዲህ ሲያደርግ ከቤተሰብ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ያስታውሳል። ይሁንና ለልብስ የሚወጣ ወጪን ለመቀነስና እነርሱን ለማገዝ ሲል እንደሚያደርገው ሲያስረዳቸው ፈቀዱለትና ብዙ ጊዜ ሳያስቸግር የራሱን ልብስ መግዛት ጀመረ።
«አምስት ሳንቲም በወቅቱ ልዩ ቦታ ነበራት፤ ከስንት ትግል በኋላም ነው ለሽልማት ተብላ እጄ ላይ የምትገባው። ለዚያውም እንደማባበያነትና ላደረኩት ነገር ክፍያ ይሆን ዘንድ። ስለዚህም ይህ ሳንቲም አለመልመዴ ለነገሮች ትኩረት እንድሰጥ እረድቶኛል» የሚለው አርቲስት ተረፈ፤ ለቤተሰቡ ዘጠነኛ ልጅ ነው። አጠቃላይ 13 ልጆች ሲሆኑ፤ አባቱ ቄስ ለማ ወልደመስቀል ይባላሉ። እናቱ ደግሞ እማሆይ ወለተስላሴ አብዬ ናቸው። አባቱ እጅግ ሲበዛ ፀሎተኛና ዓለማዊ ነገር ብዙ የማይወዱ በቀያቸው አንቱ የተባሉና ሰው አክባሪ አዛውንት ናቸው። እናቱም እንደዚያው የቤት እመቤትና በአካባቢው ሰው የሚወደዱ ናቸው።
የዛን ጊዜው ህጻን የዛሬው የ77 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አርቲስት ተረፈ በዓላት ላይ ልዩ ልዩ ትዕይንቶች፣ ጭፈራዎች፣ ዘፈኖች ሲቀርቡ ሲመለከት ሁልጊዜ ይሳብ ነበር። ከህሊናው መቼም ቢሆን የማይወጣውና ልቡ ወደ የሚወደው ደግሞ ቀይ ካባ፣ ሰማያዊ ከረባትና ነጭ ሱሪ ለብሰው የተለያዩ ማራኪ ትይንቶችን የሚያቀርቡ ሰልፈኞችን ሲመለከት ነው። ይህ ደግሞ ቀልቡ ወደ ጠራው ሙያ ለመቀላቀል መነሻ ሆኖታል። እነርሱን መሆን ሁልጊዜም ያስባል። ሰልፈኛ ሙዚቃ የሚያሰሙዋቸው ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን በመከተልም በየአደባባዩ ተከትሏቸው ይሮጥ ነበር። «ሳይደግስ አይጣላ» እንዲሉ አንደኛው ወንድሙ በአገር ፍቅር ቴአትር ይሰራ ነበርና ይዞት እየሄደ የቴአትር ፍቅር እንዲኖረውና የሙዚቃ ጥማቱን እንዲያረካ ያግዘው ነበር።
በቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ በሚሰሯቸው ድራማዎችም አቅሙን አሳይቷል። ብቻውንም ሳይቀር ጥላሸት እየተቀባ ተዋናይ ለመሆን የሚያደርገው ግብ ግብ ፍቅሩ ይበልጥ እንዲያይል አስችሎት እንደነበር ያስታውሳል። የአባቱ ካህን መሆን ደግሞ ከቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ቅዳሴ እንዳይቀር ያስገድደው ነበር። በዚህም ዳዊት ደግሟል፤ ቅኔም መዝረፍም ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ውጥኑ እስኪሳካ ድረስ ብቻ ነበር በመንፈሳዊ ትምህርቶች ውስጥ የቆየው። ምክንያቱም እርሱ ዲያቆን መሆን አይፈልግም። የዘወትር ፍላጎቱ ዘመናዊ ትምህርት መማርና ሙዚቀኛ መሆን ነው። ይህ ደግሞ በተለይ ከታላቅ ወንድሙ ጋር ያጣላቸው ነበር። ወንድሙ እንዲማር አይፈልግም፤ ሙዚቀኛ ሆኖም ማየትን አይሻም።
ለአርቲስት ተረፈ፤ አባተ መኩሪያና መላኩ አሻግሬ የሁልጊዜ አርአያዎቹና የሚወዳቸው ሰዎች ሲሆኑ፤ የልጅነት ምኞቱ እነርሱን መሆን እንደነበር ይናገራል።
ጥበብን ፍለጋ
ወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት መማር እምነትን ያስቀይራል ተብሎ የሚታመንበት ነበር። ስለዚህም አባቱ በምንም መልኩ ከቤተክርስቲያን ትምህርት እንዲርቅና ዘመናዊ ትምህርት እንዲማር አይፈልጉም ነበር። እናት ግን ምንም እንኳን የተማሩ ባይሆኑም ዘመናዊ ትምህርት መማር እንደሚለውጠው ያስባሉ። ስለዚህም ፍላጎቱ እንዲሳካ ባላቸውን በማሳመን አመሃ ደስታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገባ ዕድሉን አመቻቹለት። የስድስተኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስዶም ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ሰባተኛ ክፍልን እንዲቀጥል ተደረገ። ስምንተኛ ክፍልንም ተከታተለ። ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስዶ ካጠናቀቀ በኋላ ግን ትምህርቱ መቀጠል አልቻለም። ምክንያቱ ደግሞ የኪነጥበብ ፍቅሩ አይሎበት ወደ ሀረር በመሄዱ ነበር።
ሀረር የሚገኘው የጦሩ የሙዚቃ ክፍል ሙዚቀኞችን ይቀጥራል የሚል ወሬ ሲሰማ ሳያቅማማ ነበር ወደማያውቃት ሀረር የተጓዘው። ትምህርቱም ቢዚህ ቆመ። ሆኖም በተለያዩ የውትድርና ሙያዎችና የኪነጥበብ ሥራዎች ስልጠናዎችን ወስዷል።
አፍንጫና ከእጅ ጋር በማገናኘት ድምጽ በማውጣት እርስ በርስ ይናበቡ እንደነበርና ለእያንዳንዷ ድምጽ ልዩ ባህሪ እንደነበራቸው አይዘነጋውም። ዛሬ ድረስም በዚህ የመግባቢያ ዘዴ መጠቀም እንደሚችል ይናገራል። በሌላ በኩል በፖሊስ የህግ ትምህርት፣ የጦር መሳሪያና የሙዚቃ መሳሪያ ትምህርትም ወስዷል።
ጥበብን መጠማት የፈጠረው ዙረት
አርቲስት ተረፈ ሥራውን ሀ ብሎ የጀመረው ገና ተማሪ እያለ ነበር። ሰባራ ባቡር ዲ ብረታብረት ክፍሌ ደስታ የሚባል ብረታብረት ድርጅት ውስጥ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠረው። ከዚያ ወደ ሀረር አመራና ሀረር ጦር ውስጥ ሙዚቀኛ ሆነ። በ35 ብር ደመወዝም ከ1953 እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ በልዩ ልዩ ክፍል እየተዘዋወረ ሰራ። በዚህ መስሪያ ቤት ሀርሞኒካና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫወት ነበር። ይህንን የተመለከቱ የጦሩ መሪዎች ሌላ ዕድል አመቻቹለት። ይኸውም ጦሩን ማዝናናት አለበት ተባለና ወደ ኡጋዴን እንዲላክ ተደረገ። በትንሹም ቢሆን ደመወዙ ከፍ አለ። ግን በረሃ ስለነበር ከባድ ፈተና ነበረበት። እንዲህ እንዲህ እያለም ዓመታት ተቆጠሩ።
ለጉብኝት በሚል ኮሎኔል ቶላ በዳኔ ጋር ወደ ሀረር ተመለሰ። ግን ዳግመኛ ወደ ኡጋዴን እንዲመለስ አልተደረገም። ምክንያቱም በዚህ ቢያገለግል የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላል ተብሎ ታመነበትና እዚሁ እንዲቆይ ተደረገ። በጦር ሠራዊት የሙዚቃ ሥራ ውስጥም ተመደበ። ነገር ግን የጉርምስና ነገር አየለና ሥራው ደበረው። ስለዚህም አመመኝ በማለት ሥራውን ለቀቀ። ግን አልሸሹም ዘወር አሉ ሆነና ነገሩ ከሀረር ሳይርቅ በሙዚቃው ዘርፍ ለማገልገል ምስራቅ በረኛ ፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ በ1960ዎቹ ተቀጠረ። እስከ ለውጡ ድረስም አገለገለ።
አርቲስት ተረፈ በ1966 ዓ.ም ስጋቱ እየሰፋ በመምጣቱና ለኑሮም ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ግርግሩን ተጋፈጠ። ምርጫ መጣናም ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ተብለው ከተመለመሉት መካከል አጃቢ በመሆን አዲስ አበባ ተላከ። ይሁንና የእርሱ ሥራ ሙዚቀኛና የኪነጥበብ ሰው መሆን ብቻ ነው። የተላከበት አላማ ደግሞ በተቃራኒው ሆነ። ግድ ፖለቲከኛ መሆን ይጠበቅበታል። ንግግሩ፣ ተግባሩም፤ ክየናውም ሆነ እንቅስቃሴው ፖለቲካ ብቻ ማድረግ አለበት። «ባልመጣሁ ኖሮ» እስኪል አስመርሮት እንደነበር ያስታውሳል። ይሁን እንጂ በመጨረሻ አንድ ነገር ተከሰተ። ሀረር ውስጥ በሙዚቃው ዘርፍ ምን ያህል ሲያዝናና እንደነበር የሚያውቀውን ሰው አገኘ። መቶ አለቃ ፍስሃ ገዳ የሚባል ሰው፤ የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አጃቢና ፕሮቶኮል ኃላፊ ነው። ከዚያም ሳያመልጠው «እባክህ ከዚህ ክፍል ቀይረኝ፤ ሥራው ከብዶኛል። ፍላጎቴንም ማሟላት አልቻልኩም» ይለዋል። መቶ አለቃ ፍሰሃም «ትንሽ ጠብቅ ቦታ ይፈለግልሃል» ብሎ ከተለየው በኋላ የተወሰኑ ወራት አልፈው ደርግ ገብቶ መንግሥት ቅየራ በመደረጉ የተነሳ ወደ መንግሥት ንብረትነት የተዘዋወረው ብሔራዊ ሀብት ልማት የሚባል ድርጅትን በሚሊተሪ ውስጥ ሆኖ እንዲመራ ዕድሉ ሰጠው። ተቆጣጣሪ እንዲሆንና ኑሮውም አስኮ ጫማ ፋብሪካ ውስጥ እንዲያደርግ አገዘው። ለእርሱ ግን ይህም ቢሆን ምቹ አልነበረም። ከፖለቲካው አልተላቀቀም። ሠራተኛውም ቢሆን ሊቀበለው አልቻለም፤ «የደርግ አሽከር» እያሉ ሲያሽሟ ጥጡበት መልቀቅን ፈለገ። የሥራ ማስታወቂ ያዎችንም መከታተሉን አጧጧፈው። በተለይም ከኪነጥበቡ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ማስታወቂያዎችን አዘውትሮ ይመለከት ነበር።
ይህ ጥረቱ ተሳካና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሙዚቀኛ መቅጠር እንደሚፈልግ ሰማ። ወዲያው ወደቦታው አመራ፣ ተመዘገበ፣ ለፈተናም ቀረበ። ግን በውስጡ ብዙ ፍራቻዎች ነበሩበት። ምክንያቱም ሁሉም ተወዳዳሪዎች የትምህርት ደረጃቸው ከስምንተኛ ክፍል በላይ ናቸው። ምንም እንኳን አቅሙና እውቀቱ ቢኖረውም የትምህርት ደረጃው የሚጥለው መስሎ ተሰምቶት ነበር። ስለዚህም «ከሆነ ይሆናል ካልሆነም እዚያው እሰራለሁ» በማለት ሁለት ሃሳብ ይዞ ለውድድር ቀረበ።
ከእነ ተሾመ አንዳርጋቸው፣ ከእነ ፈቃዱ ተክለማርያም፣ ከእነ ገለታ ተክለጻዲቅ፣ ከእነ ወለላ አሰፋና መሰል አንጋፋ አርቲስቶች እኩል ቆመ። የሚያቀርቡት የመወዳደሪያ መስፈርት ስሜት ፈጣሪ ግጥም ከስሜት ጋር በተዋሃደ መድረክ ላይ መተግበር ነው። ከተዋቂ ቴአትሮች ውስጥ አንዱን መርጦ መቅረብም ሌላው ፈተና ነው። ወንደሰን ገብረየሱስ፣ ተፈሪ ብዙአየሁና ወጋየሁ ንጋቱ የወቅቱ ፈታኞች ነበሩ። አርቲስት ተረፈም እስካሁን አልረሳሁትም የሚለውን የአቤ ጉበኛ ግጥም እንዲህ በማለት አቀረበ።

አርቲስት ተረፈ ለማ


«በጣም ያስገርማል ወሬ ድፍረትህ
በሥራ በለጥኩኝ እኔ ማለትህ
በእኔ በስራ እንጂ አለም ያደገችው
መቼ በወሬ ነው ጥበብ የጎላችው
ያ ትልቁ መጽሐፍ ለሰው ልጅ የሚለው
ለፍተህ፣ ጥረት፣ ግረህ በላብህ ብላ ነው
አይገባህም እንጂ ወሬኛ እምትኖረው
እሹሹ ጌታዬ ነገር ስትፈትል ነው
ይህቺን አቅርቤያለሁ መቀጠር ጥሩ ነው» ብሎ ሲጨርስ ወዲያው እንዲቀጠር ተፈቀደለት። በ45 ብር ደመወዝ ኮንትራት ሠራተኛ ሆነና ከሚወደው ሙያና ከሚወዳቸው አርቲስቶች ጋር ተቀላቀለ። የቤቱ መሰረት፤ የኑሮውን ቀዳዳ መሙያም ማዘጋጃ ቤትን አደረገ። በዚህ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቴአትር ለማቅረብ መድረክ ላይ የወጣው «ባለካባ ባለዳባ» በሚለው ሲሆን፤ «መቃብር ቆፋሪው»፣ «ሳር ሲነድ»፣ «ኦቴሎ»፣ «መልዕክተ»፣ «መቅድም» እያለ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተሰሩ ቴአትሮችን በአብዛኛው ከአጃቢ ተዋናይነት እስከ ዋና ተዋናይነት ሰራ።
አርቲስት ተረፈ የተለያዩ የዘፈን ግጥሞችንም ቢሆን ማዘጋጃ ቤት እያለ ይጽፍ ነበር። ለምሳሌ የሚገጥማቸውን የዘፈን ግጥሞች «ድሮም ገበሬ ነኝ» በጸጋዬ ዘርፉ፣ «አራሹ ግብረ ሃይል» በትረ ወልደ አማኑኤል እና ሌሎች ግጥሞች በእነ ተሾመ ወልዴ መሰል ዘፋኞች ለመድረክ በቅቷል። በየጊዜው ለተለያዩ ቴአትሮችና ፊልሞች ማጀቢያ የሚሆኑ የዘፈን ግጥሞችንም ይጽፍ እንደነበር ይናገራል። በተመሳሳይ እንደ «ቤት አከራዩ»፣ «ያልተሄደበት መንገድ»፣ «እንቅፋት» ና የመሳሰሉት ላይ በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ላይ ሰርቷል። በፊልምም ቢሆን «የእናት ዋጋ»፣ «ሀግዕዝ»፣ «መክሊት»፣ «አንጥረኛው»ና «ፍርሃት» በሚሉት ላይ የትወና አቅሙን አሳይቶባቸዋል። በኮሜዲያንም ሆኖ ሰርቷል።
ቅሬታ
አርቲስት ተረፈ ማዘጋጃ ቤት የሰራ ሰው የሚታወቅበትና ልዩ መረጃ የሚታይበት ስርዓት አለመኖሩ ሁሌም እንደሚያናድደው ይናገራል። ለዚህም ደግሞ እርሱን ጨምሮ ሌሎች ተዋቂ አርቲስቶች እንዲደበቁ በማድረጉ ብዙ ሥራዎች ላይ እንዳይሳተፉ ገድቧቸው ነበር። ለሌላ ሥራ ለመታጨት ዕድሉ አይኖራቸውም። ሌሎች ቴአትር ቤቶች በሥራቸው የሚሰሩ አርቲስቶች ሙሉ መረጃ አላቸው። ስለሰዎቹ ለማወቅ ሲፈለግም ያንን አንብቦ ለመምረጥና ለሥራ ለመመልመልም ምቹ ይሆናል። ማዘጋጃ ቴአትር ቤት ግን ምንም አይነት መረጃዎች ስለሌሉት በዚህ ተጠቃሚ የሚሆን አርቲስት አይኖርም። ስለነሱም ማወቅ የሚፈልግ ሰው ቢመጣ ባለታሪኩን ወይም ስለእርሱ የሚያውቁትን ሰዎች ካልጠየቀ በስተቀር ምንም ማወቅ አይችልም። ይህ ደግሞ በህይወቴ ከሚያሳዝነኝ ነገር አንዱ ነው ይላል። ሌላው ምንም እንኳን በማዘጋጃ ቤቱ ከዓመት በላይ ቢያገለግልም ቋሚ ለመሆን የሚሰራው ሥራ እጅግ እንደፈተነው አይረሳ ውም። ቦታውን ለማግኘት መጸዳጃ ቤት መጥረግ፤ ሸረሪት ያደራበትን አቧራ መጥረግ የመጀመሪያ ሥራውእንደነበር አይዘነጋውም ። ውትድርና ላይ ሆኖ ከጉልበቱ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ጥይት መመታቱ ያለመዳን ስሜት የተሰማውን ቀንን አይረሳውም። ከዚያ ውጪ የሚያሳዝነውም ሆነ የገጠመው ፈተና እንዳልነበር ነው የሚናገረው።
ገጠመኝ
አርቲስት ተረፈ በርካታ ገጠመኞች ባሳለፈው 77 ዓመታት ውስጥ አሉት። ነገር ግን ሁለቱን ብቻ እናንሳ። የመጀመሪያው በ1970ዎቹ አካባቢ የገጠመው የማይረሳው ትዝታው ሲሆን፤ በሰለሞን ክፍሌ የተደረሰ «መስኮት» የተሰኘ የቴሌቪዥን ድራማ ለመስራት በዝግጅት ላይ ሳሉ በቀረጻ ወቅት ሽጉጥ ያስፈልጋልና በወቅቱ ለማግኘት ይቸገራሉ። ከዚያም አዘጋጁ ከሆነ ሰው ይቀበልና ለተረፈ ይሰጠዋል። ሽጉጡ የተሰጠው ተረፈም አርቴፊሻል ስለመሰለው እንደለመደው ለመጠቀም ይሞክራል። በመጀመሪያ የተደረደሩ ተዋናዮችን እያስፈራራ ያስኬዳል። ግን አይተኩስም። በመጨረሻ ግን ጌታሁን ሀይሉ የሚባለው ላይ አነጣጥሮ ያልተፈተሸ ሽጉጡን ይተኩሳል። ግን የተተኮሰበት ሰው በመሸሹ እርሱም ተርፎ ተረፈንም ከተጠያቂነት አውጥቶታል። ዛሬም ድረስ የተተኮሰበት ሰው «ገለኸኝ ነበር እኮ» እያለ እንደሚያነሳበት ይናገራል።
ሌላው ገጠመኝ አስመራ ለሥራ በሄደበት የተከሰተው ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። በአንድ ጊዜ እስከመሳሪያቸው ለመላክ መስሪያ ቤቱ ይቸገራል። ስለዚህም ግማሹ ቡድን ቀድሞ ሄዶ ዝግጅት እንዲያደርግ ያዛል። ከዚያም ሁለተኛ ቡድን በዝግጅቱ ወቅት ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ አውሮፕላኑ በመበላሸቱ የተነሳ ይቆያል። ሰውም ዝግጅቱ ይቀርባል ብሎ ይጠባበቃል።
የሥራ ባልደረቦቻቸው በአየር ችግር ምክንያት አውሮፕላኑ ለማረፍ ተቸግሮ ሰዓታትን በአየር ላይ ያሳልፋሉ። በዚህ ጊዜ ካሁን አሁን ሞቱ፤ ተከሰከሰ የሚል ወሬ ይደርሰናል እያሉ በስጋት ሰዓታትን አሳለፉ። ሁሉም በእየእምነቱ መጸለይ ጀመረ። ከሰዓታት በኋላም ፀሎታቸው ተሰማና ምንም ሳይሆኑ አውሮፕላኑ በሰላም አረፈ። ሰዎቹም ወደ ሥራቸው ገቡ። ስለዚህም እነርሱም ራሳቸውን ለመሰብሰብና ጓደኞቻቸውን ለማረጋጋት ሲሉ ቀኑን ያሳለፉበትን ጊዜ እስካሁን ያስታውሰዋል። እንደውም አንዷ ጓደኛቸው የጥር ስላሴን እንደምትዘክር አጫውቶናል።
ሽልማት
ኡጋዴን ሄዶ እያለ በቀላል ሚዛን የስፖርት ውድድር ተመርጦ ሜዳሊያ አግኝቷል። እንደውም አፍንጫው ተሰብሮ እንደነበር ያስታውሳል። በጦር ሠራዊት ሲሰራ የተዋጊ ምልክት ተሰጥቶታል። በማዘጋጃ ቤት ደግሞ በ35 ዓመት አገልግሎቱ የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። በፊልም ሥራዎችም እንዲሁ ከ35 በላይ የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል። በቴአትርም በተለያዩ ጊዜያት የምስክር ወረቀቶች ተበርክቶለታል። በተለይ «በማዶ ለማዶ» በተሰኘው ቴአትር ከምስክር ወረቀቱ ባሻገር የአምስት መቶ ብር ተሸላሚ ሆኖ ነበር።
ውሃ አጣጭ
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ በኪነጥበቡ ዘርፍ የሰራው አርቲስት ተረፈ፤ ከአገር ውጪ በጀርመን፤ በሆላንድ፣ ፈረንሳይና ሌሎች አገሮች ዞሯል። በዚህም አገሩ ከሌሎች አገራት በምን እንደምትለይ ለይቶ ያውቃል። ስለዚህም ልጆቹን ሁል ጊዜ የሚያስተምረው አገር ወዳድነትን ነው። በአገር ውስጥ በነበረው ቆይታ ሚስት አግብቶ ነበር። ከእርሷም ሁለት ልጆችን አፍርቷል። አሁንም ድረስ ከልጆቹ ጋር ይጠያየቃል።
ሁለተኛዋ ባለቤቱ አሁን አብራው ያለችው ስትሆን፤ ማዘጋጃ ቴአትር ቤት የዳረለት ልዩ ሚስቱ ናት። ግንኙነታቸው የጀመረው ግን በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሰራ በነበረበት ወቅት ነው። ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል ጸሐፊው እንድትሆን ተቀጠረችለት። በዚህም ትህትናዋ፣ እንክብካቤዋና ያላት የሰው ፍቅር ልቡን ረታው። አፈቀራትና ሊያገባት ወሰነ። ፈቃዷንም ጠይቆ ለዚህ የሚያምር የትዳር ህይወት በቁ። ዛሬ የአንዲት ሴትና ሦስት ወንድ ልጆች አባትና እናት ሆነዋል። ሁሉም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። አርክቴክት ልጁ ግን ሁልጊዜ የእርሱን ፈለግ መከተል ትፈልጋለች። እናም የዳንስ ፍቅር ስላላት በእርሱ ክሊፕ ለማውጣት እየጣረች እንደምትገኝ በወጋችን መካከል ነግሮናል።
«ኪነጥበብ ግብረገብነትን ያስተምራል፤ ባህልን ያሳውቃል። ከባህል ውጪ ላለ ተግባር እንዳንቆም ያሳስባል። ይሁንና ወጣቱ ገንዘብ ተኮር እየሆነ በመምጣቱ የተነሳ የኪነጥበብ ፍቅሩንና ግብረገብነቱን እየተወ ስለመጣ ከአንጋፎቹ ይህንን ይማርና ህይወቱ ያድርገው፤ ይኑርበትም። ከእኔና ከቤተሰቦቼ የሚተላለፈውም ይህ ግብረገብነት ነውና ሌሎችም እንዲያደርጉት ፍላጎቴ ነው» በሚለው መልዕክቱ ረጅሙን የህይወት ቅኝት ቋጨን። ሰላም!

ፅጌረዳ ጫንያለው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።