«ዕድሜያችን ከ40 ዓመት በላይ ሲደርስ በዓመት አንድ ጊዜ የዓይን ምርመራ ማድረግ አለብን» Featured

12 Jun 2018

ዶክተር ሳዲክ ታጆ የመጀመሪያ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1996 ዓ.ም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዓይን ሕክምና ስፔሻላይዝ አድርገዋል።ወደ ካናዳ አቅንተውም በህጻናት ዓይን ሕክምና ሰብ-ስፔሻላይዝ አድርገዋል።አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የዓይን ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም፣ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የዓይን ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ዓይን ሐኪሞች ማሕበር ዋና ጸሐፊም ናቸው።
እኛም በዓይን ህመም መነሻ ፣ህክምናና መከላከያ መንገዶች ዙሪያ ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- ጤነኛ እይታ ወይም ጤነኛ ዓይን ሲባል ምን ማለት ነው?
ዶክተር ሳዲክ፡- ጤነኛ ዓይን ሶስት አራት ተግባራት ይኖሩታል።የመጀመሪያው የእይታ ልኬት ሲሆን ከፊት ለፊት፣ ከቅርብና ከርቀት በደንብ ማየት መቻል ሲሆን ይህ ተግባር በአካባቢያችን ያሉ ነገሮችን የምናይበት የአገልግሎት ዓይነት ነው።ሰዎች አካባቢያዊ ግንኙነታቸውን ከ 80 እስከ 90 በመቶ ዓይንን መሠረት በማድረግ ነው የሚያከናውኑት። ሁለተኛው የዓይን አገልግሎት የእይታ አድማስ ይባላል።ፊት ለፊት እየተመለከትን የጎንዮሽ እይታ የማከናወን ችሎታ ነው። ሦስተኛው የቀለም እይታ ሲሆን፣ የቀለማት ውህድ፣ መጠንና ድምቀታቸውን መለየት ስንችል ነው።አራተኛው የጥልቀት እይታ ነው።ይህ ማለት በሁለቱም ዓይኖች ጥቃቅን ነገሮችን በጥልቀት መጠናቸውንና የጎንዮሽ ስፋታቸውን የምንለይበት አቅም ነው።እናም አንድ ሰው እይታው ጤነኛ ነው ለማለት እነዚህን ተግባራት ያለእንከንና ችግር ማከናወን ሲችል ነው።
በዓይን ሕክምና መስፈርት አንድ ሰው የዓይን ሕክምና እርዳታ ከተደረገለት በኋላ ያለው እይታ ከሦስት ሜትር ያነሰ ከሆነ ዓይነ-ስውር ነው ይባላል።ሌላው የዓይነ-ስውርነት ብያኔ የእይታ አድማስ ወይም የጎንዮሽ እይታ መቀነስ ነው።በሌላ በኩል አንድ ሰው ከሦስት ሜትር በላይ ማየት እየቻለ የርቀትና የቅርብ እይታው ከቀነሰ የእይታ መቀነስ ይባላል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ በስርጭታቸው ወይም በሚያደርሱት ጉዳት ቀዳሚዎቹ የዓይን ሕመሞች የትኞቹ ናቸው?
ዶክተር ሳዲክ፡- ኢትዮጵያ በዓለም ከፍተኛ የእይታ መቀነስና ዓይነ-ስውርነት ከሚከሰትባቸው አገራት ሦስተኛዋ ነች።እ.ኤ.አ 2006 ላይ የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው አንድ ነጥብ ስድስት በመቶ የአገራችን ህዝብ ዓይነ-ስውር ነው።ይህ ማለት ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማው ላይ ችግሩ አለ ማለት ነው።
ከዚህ ውስጥ ዋነኛው የዓይነ ስውርነት አጋላጭ ምክንያት የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሲሆን በሁለተኝነት ትራኮማና ተያያዥ ችግሮች ናቸው።ግላኮማ ሌላኛው የዓይነ-ስውርነት ምክንያት ሲሆን አራተኛውና በመነጽር ሊስተካከል የሚችለው የአነጣጥሮ ማየት ችግሮች ናቸው።
አሁን በአገሪቱ 800 ሺ ሰዎች በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ለዓይነ-ስውርነት የተዳረጉ ሲሆን ችግሩም ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣ ብርሃን ተቀባይ ሌንሱ ላይ እየተፈጠረ የሚመጣ ጠባሳን ተከትሎ የሚከሰት ነው። እናም ችግሩ በማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የሚያጋጥም ነው።
ትራኮማን ብንወሰድ ኢትዮጵያ በዓለም በሽታው በከፍተኛ መጠን ካለባቸው አገራት ውስጥ አንዷ ነች።ችግሩም በአካባቢና በግል ንፅህና ጉድለት በማይታዩ ባክቴሪያዎች የሚመጣ ተላላፊ የሆነ በሽታ ሲሆን በዋናነት ህፃናትና እናቶችን ያጠቃል።ሰዎች በአካባቢያቸው ንፅህናቸውን የሚጠብቁበት በቂ ውሃ ካላገኙ፣ የበሽታ ተጠቂ ይሆናሉ። በሽታው ከእድገት ጋርም ይያያዛል።
ግላኮማ ዓይናችን ውስጥ ያለው ግፊት እየጨመረ ሲሄድ ከውስጥ ብርሃን የሚቀበለው የዓይን ነርቭ ሲጎዳ የሚከሰት የዓይነ-ስውርነት ምክንያት ነው።ህመሙ በዋናነት በዘር የሚተላለፍ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የህፃናት እይታ መቀነስና ዓይነ-ስውርነት ከፍተኛ ከሆነባቸው አገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ነች።ቁጥሩ ዜሮ ነጥብ አምስት ሲሆን፤ይህ ማለት ከአንድ ሺ ህጻናት ውስጥ አምስቱ ዓይነ-ስውርነት አላቸው ማለት ነው።
ህጻናት ላይ የሚከሰት የዓይን ሞራ ግርዶሽ ለዓይነ-ስውርነት የሚዳርግ ሲሆን በመነጽር ሊስተካከል የሚችል አነጣጥሮ የማየት ችግርም በቫይታሚን «ኤ» እጥረት፣ በትራኮማ አልያም በአደጋ ምክንያት የሚፈጠረው የዓይን ብሌን ጠባሳ መጣልም ህጻናትን ለእይታ መቀነስና ለዓይነ-ስውርነት እየዳረጉ ከሚገኙ ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት የዓይን ሕክምና ተደራሽነትና ጥራት ደረጃ ምን ላይ ይገኛል?
ዶክተር ሳዲክ፡- ችግሩ በጣም ግዙፍ ነው። የኢትዮጵያን የዓይን ሕክምና በሐኪሞች ቁጥር ማነስና በተደራሽነት በኩል ሰፊ ክፍተት አለበት። በዚህ ምክንያት ደግሞ 1 ነጥብ 6 በመቶ የዓይነ-ስውርነት መጠን አለ። በዓለም የጤና ድርጅት መስፈርት አገሪቱ በትንሹ 3ሺ የዓይን ሐኪሞች ሊኖራት የሚገባ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 140 የዓይን ሐኪሞች ብቻ ናቸው ያሉት ።ይሄ ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ከተጠቀሱት የዓይን ሐኪሞች 70 ወይም 80 በመቶዎቹ በከተሞች ውስጥ ያሉ በመሆኑ እንደ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና አፋር ቋሚ የሆነ የዓይን ሕክምና እንዳይሰጥ ሆኗል።
ይህንን ችግር ለመፍታትም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰለጥኑ ሐኪሞች ቁጥር እንዲጨምር ማድረግ፣ በተለይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ እያደረገም ነው።
በሌላ በኩልም ማህበሩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአምስት ዓመት የዓይን ሕክምና ፍኖተ-ካርታ እንዲቀረፅ በጋራ ሰርቷል።በዓይን ጤና ላይ የሚስተዋለው ሌላ ትልቅ ችግር ሕክምናው በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተንጠለጠለ መሆኑ ስለሆነ ችግሩን ለመፍታትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር አብረን እየሠራን ነው።
መንግስት ለዓይን ሕክምና ተገቢ ትኩረት አልሠጠም።ፖሊሲ አውጪዎች ላይ የምናየው «አይነ-ስውርነት አይገድልም» የሚል አንድ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ።ነገር ግን ዓይነ-ስውርነት እንደሚገድል በኔፓልና ህንድ የተሰሩ ጥናቶች አሉ።ዓይነ-ስውርነት በራሱ ብቻ የሰዎችን የዕድሜ ጣራ ይቀንሳል። የድህነት ምክንያትም ነው። ዓይነ-ስውርነት በዜሮ ነጥብ አንድ በመቶ በጨመረ ቁጥር አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) በ15 በመቶ ይቀንሳል። ስለዚህ ዓይነ-ስውርነትና እድገት በጣም የተያያዙ ናቸው።
በአንዲት አገር ዓይነ-ስውርነት በጨመረ ቁጥር የልማት ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።ችግሩ ያለባቸው ሰዎች ከምጣኔ-ሃብቱ፣ ከጤና አገልግሎቱና ከማሕበራዊ መስተጋብሩ ይገለላሉ።
አዲስ ዘመን፡- በክትባት መከላከል የሚቻሉ የዓይን በሽታዎች አሉ?
ዶክተር ሳዲክ፡- ቀጥታ በክትባት የምንከላከላቸው የዓይን ህመሞች የሉም።ነገር ግን ህፃናት የሚያጋጥማቸው የቫይታሚን «ኤ» እጥረት የሚመጣ ዓይነ-ስውርነት አለ።እሱን ለመከላከል መንግስት የሚያደርገው የቫይታሚን «ኤ» እንክብል ዕደላ አለ።እርሱም የዓይን ብሌን ጠባሳን ብሎም ዓይነ-ስውርነትን ለመከላከል ይረዳል።ትራኮማ በስፋት በሚታይባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች በየስድስት ወሩ መድኃኒት ይሰጣል።መድኃኒቱ የበሽታውን መዛመት ይቀንሰዋል።
አዲስ ዘመን፡- የሕብረተሰቡ የዓይን ጤንነት አጠባበቅ ልምድና ግንዛቤ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
ዶክተር ሳዲክ፡- ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ሰው የግዴታ የመነፅር እርዳታ የሚያስፈልገው ቢሆንም የሕብረተሰባችን እውቀትና የግንዛቤ ማነስ ተገቢ ያልሆኑ አመለካከቶች በዓይን ሕክምናው ላይ ተግዳሮት ሆነው ቀጥለዋል። ለአብነት ሰዎች ዕድሜያቸው መጨመር ምክንያት እይታቸው እየቀነሰ ሲመጣ ከዛሬ ነገ እያሉ ሳይታከሙ ይቆያሉ።የዕድሜ መግፋትን ተከትሎ የሚመጣ ነው በማለት ችግሩን የመቀበል ዝንባሌ ይታያል።ነገር ግን በመነፅር የሚስተካከሉ ችግሮች ስላሉ በቶሎ ወደ ህክምና መሄዱ አዋጭ ነው።
በሌላ በኩልም የግንዛቤ ችግሩ በሕብረተሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን የዓይን ሐኪም ባልሆኑ የጤና ባለሙያዎች ጭምር የሚስተዋል ነው ። በቅርብ ያደረግነው የህጻናት የዓይን ካንሰርን የሚመለከት ጥናት እንደሚያሳየው 50 በመቶዎቹ የችግሩ ተጠቂዎች የሚዘገዩት የጤና ባለሙያዎች በተገቢው ወቅት የአይናቸውን የእይታ መጠን ያለመለካታቸው ሲሆን ሌላው ህፃናት ላይ መነፅር ሲታዘዝ የሕብረተሰብ የመቀበል ችግር ይጠቀሳል። በዚህ ምክንያት ተገቢው ክትትል ሳይደረግ ይቀራል።
ከዚህ በተጨማሪ በሰሜንና ደቡብ ኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ልማዳዊ ዓይንን የመብጣት ድርጊቶች ለዓይን ጤና ችግር መባባስ ምክንያት ናቸው ።
አዲስ ዘመን፡- መጨረሻ ላይ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?
ዶክተር ሳዲክ፡- ቅድም እንዳልኩት ከአካባቢያችን ካለን መስተጋብርና ግንኙነት ውስጥ ከ80 እስከ 90 በመቶ እይታን መሠረት ያደረገ ነው።ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።ሰዎች ሳይታመሙና ዓይናቸው ላይ ችግር ሳይፈጠር በየጊዜው ምርመራን ማድረግ መልመድ አለባቸው። በተለይ ዕድሜያችን ከ40 ዓመት በላይ ሲደርስ በትንሹ በዓመት አንድ ጊዜ የመታየት ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል ። መንግስትም በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ዓይነ-ስውርነት ከልማት ጋር ልማትም ከዓይነ-ስውርነት ጋር ስለሚገናኙ ሕክምናውን በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በቂ በጀት መመደብ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩልም መንግስት ችግሩን ለማቃለል በዓይን ሕክምና ላይ ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅርበት መሥራትና የመሪነት ሚናውን መወጣት ይጠበቅበታል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።