አሻጋሪዎቹ

13 Jun 2018

ትናንትና ያለፈችበትን አስቸጋሪ መንገድ ዞር ብላ ስታስብ ዛሬ ያለችበትን ህይወት ታመሰግናለች። ከዓመታት በፊት እግሮችዋ ለስደት ሲዘጋጁ ነገ መልካም እንደሚሆን ታስብ ነበር። የዛኔ ብቻዋን አልነበረችም። የልጅነት ጓዷ የትዳር አጋሯ ከጎኗ ነበር። በሱዳን ምድር ወልዳ ያሳደገቻቸው ሁለት ህጻናት ልጆችዋም ከጉያዋ ሳይርቁ ከእቅፏ ሳይወርዱ የአይኖችዋ ተስፋ ሆነዋታል።
ካሳዬነሽ መንገሻ ከትውልድ መንደሯ ርቃ ከሱዳኗ ካርቱም ዘልቃ ዓመታትን ስታሳልፍ እንደሌሎቹ የሀገሯ ልጆች ለራሷና ለባሏ የሚሆን ጥሪትን አላጣችም። ሰርታ መግባቷና በልታ ማደሯ ብቻ ግን በቂ ሆኖ አልተገኘም። ከዚህ በተሻለ ኑሮዋን ልትለውጥ ህይወቷንም ልታሻሽል ትሻለች። እሷ ኑሮን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ጥቂቶች ህይወታቸውን እንደለውጡ ሰምታለች። እሷም እንደነሱ ለመሆን በረሃውን አቋርጣና ባህሩን ተሻግራ መሄድ አለባት። ወደተስፋይቱ የህልመኞች ሀገር አውሮፓ።
ካሳዬነሽና ባለቤቷ ወደሚያስቡት የስደት ምድር ለመድረስ የሊቢያን ባህር መሻገር አለባቸው። ከዛ በፊት ግን በረሃማውን መንገድ በእግር፣ ቀጥሎም በመኪና ተጉዘው ከዳርቻው ሊደርሱ ግድ ነው። ይህን ለማድረግም አብረዋቸው ጉዞ የጀመሩ መንገደኞች ጥቂት አልነበሩም። እንደነሱ ባልናሚስት የሆኑ፣ ልጆች ያዘሉና ያቀፉ፣ ሌጣቸውን የሚኳትኑና ሌሎችም የስደቱን ጎዳና ተያይዘውታል።
ቀናት የፈጀው የበርሃ ጉዞ ተጠናቆ ሊቢያን ለመሻገር ከዳርቻው እንደተጠጉ ከስፍራው ያገኟቸው ባዕዳን በአበሾች ላይ የሚፈጽሙት ድርጊት የከፋ ሆነ። ድብደባውና ዝርፊያው፣ እስራትና እንግልቱም ብዙዎችን አሳዘነ። ይህን ያዩ ጥቂቶች የወገኖቻቸውን በደል አምኖ መቀበል ተሳናቸው። ወዲያውም ገጀራና ጠመንጃ የያዙ ጨካኞችን ሊጋፈጡ አንገት ለአንገት ተያያዙ። ድብደቡ፣ ትግልና ጨኸቱ ተባባሰ ። ጥቂት ቆይቶ ግን ከባዱ ፍልሚያ የህይወት ዋጋን አስከፈለ። በዕለቱ «ተደፈርን» ካሉ ባዕዳን አንድ ሰው ሞቶ የአራት ኢትዮጵያውያን ሬሳ በሰው ሀገር ምድር ላይ ተዘረረ።
ከአራቱ ሟቾች አንዱ የካሳዬ ባለቤት ነበር። የዛኔ ይህን ያየችው ወይዘሮ የሆነውን ሁሉ አምኖ ለመቀበል ተሳናት። የልጆችዋን አባት፣ ግማሽ አካሏን በቀነ ጎዶሎ ብትነጠቅ ሃዘኗ የከፋና የበረታ ሆነ። አሁን ወደመጣችበት የሱዳን ምድር ከመመለስ ሌላ ምርጫ የላትም። በውሳኔዋ ጸንታ ካርቱም ስትደርስም ከልጆችዋ በቀር የኔ የምትለው ተስፋ አልነበራትም። ያም ሆኖ ግን ሁለት ተጨማሪ ዓመታትን በባዕድ ሀገር መቆየት ነበረባት። እነዚህ ዓመታት ፈታኝና ከባድ ቢሆኑም ወደ ሀገሯ ለመግባት ምክንያት ሆነዋታልና ብዙ አልጠላቻቸውም። ከውሳኔዋ በኋላ ደግሞ በሀገር ላይ በሰላምና ጤና ሰርቶ ማደር እንደሚቻል አምናለች።
ኢትዮጵያ ስትደርስ ለቤተሰቦችዋና ለወገኗ የሚተርፍ ጥሪት አልነበራትም። ልጆችዋ በዕድሜና በቁመታቸው ጨምረዋል። ለወደፊቱ ማንነታቸው ያኖረችላቸው ቋጠሮ ግን የለም። ይህን ስታውቅ ባገኘችው ስራ ልትሰማራ ከውሳኔ ደረሰች። የመስራት ብርታትና ፍላጎቷም ከብዙ እያደረሰ ያውላት ጀመር።
ካሳዬ በነበራት የቧንቧ ጥገና ሙያና በሌሎችም ስራዎች ስትሮጥ መዋልን ለመደች። ከሁሉም ግን በአንድ ወቅት ያገኘችው የስራ ዘርፍ የስደት ተመላሿን ወይዘሮ ቀልብ ገዛ። በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የከፋ ጉዳት ለመታደግ የድርሻዋን የማበርከት መልካምነት ቢገባት፣ ከሁሉም ምርጫዎችዋ የልቧ ሚዛን ለዚህኛው ሲያደላ ተሰማት።
እሷ የኑሮን ውጣ ውረድና የህይወትን ዋጋ ጠንቅቃ ታውቃለች። በዕድሜዋ የተማረችውም ከዚሁ ዓላማ ጋር የሚዛመድ ሆኖ አግኝታዋለች። በበጎ ፍቃደኝነት ተመዝግባና ተገቢውን የመንገድ ደህንነት ስልጠና ወስዳ ስራውን ስትጀምር ለዚህ ድንቅ ዓላማ መታጨቷ በእጅጉ አስደሰታት። አሁን ላይ ካሳዬነሽን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የፈለገ አያጣትም። ዘወትር ማለዳ በደንብ ልብሷ ሆና ወጪ ወራጁን ስታስተናብር ትታያለች። ይህን ስታደርግም መልካም ሥራዋ የገባቸው እግረኞች በወጉ ይታዘዟታል። ዓላማዋ የገባቸው አሽከርካሪዎችም ለደንብና ህጉ ተገዥ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩዋታል።
አንዳንዴ እሷንና መሰሎችዋን መስማት የማይፈልጉ የመንገድ ተጠቃሚዎች በሚፈጥሩት ስህተት የአደጋ ሰለባ መሆናቸው በእጅጉ ያሳዝናታል። ይህን ስታስብም አንድ ቀን የሆነውን ክፉ አጋጣሚ ሁሌም አትዘነጋም። በዚህ ቀን ምሽት መሀል አስፓልት ለማቋረጥ ጉዞ ከጀመረ አንድ ወጣት ጋር አይን ለአይን ተጋጠመች። ወጣቱ በኪሱ ካለ የእጅ ስልክ ጫፍ የተገናኘ ማዳመጫ በጆሮዎቹ ሰክቶ ወደ መሀል አስፓልቱ ቀርቧል። በሙዚቃው እየተዝናና ስለመሆኑ ከሚያደርገው ድርጊትና እንቅስቃሴ ተረድታለች።
እንዲህ አይነቱ ያልተገባ ድርጊት ሲያጋጥም አይቶ ማለፍን የማታውቀው ካሳዬ ልጁ በአግባቡ እንዲጓዝና ትኩረቱን ለመንገዱ ብቻ እንዲሰጥ ልትመክረው ሞከረች። ወጣቱ የምትለውን ቢረዳም ምክሯን መቀበል አልፈለገም። እንደውም ስድብና ማመናጨቅ አክሎበት እንደነበረው መጓዝን ቀጠለ። በዚህ አካሄዱ ግን ብዙ አልተራመደም። ከፊት ለፊቱ ሲበር በመጣ መኪና ክፉኛ ተገጭቶ ህይወቱን ተነጠቀ።
ካሳዬ ተሽከርካሪዎችን ከእግረኞች ስትዳኝ በምትውልበት ጎዳና ብዙ ያጋጥማታል። አደጋን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ሃላፊነትን መጋራት የሁሉም ድርሻ እንደሆነ ታውቃለች። ብዙ ግዜ ግን አንዳንድ እግረኞች ይህን እየተረዱም ለህግ ተገዥ መሆንን አይፈልጉም። እሷ ለስራ በምትሰማራበት የሜክሲኮ አደባባይ እግረኞች በዜብራ (በእግረኛ መሻገሪያ) ለማሻገር በገመድ አጥር እስከመስራት ተደርሷል። ይህም ሆኖ ግን ገመዱን ሾልከው የሚሄዱና ‹‹ለምን ተጠየቅን?›› በማለት ለመማታት የሚጋበዙ መንገደኞች አይጠፉም። በዜብራ ከሚሻገሩት መካከልም ስልክ እያወሩ፣ ሙዚቃ እያዳመጡና በሃሳብ እየተከዙ የሚሄዱ እግረኞች ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባታል።
ወጣት አዲሱ መኮንንም ልክ እንደወይዘሮ ካሳዬነሽ ሁሉ በበጎ ፍቃደኝነት የመንገድ ትራፊክ ደህንንቱን ሲያግዝ ይውላል። አዲሱ በመንገድ ላይ እንቅስቃሴው ከብዙ እግረኞችና አሽከርካሪዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚው የሰፋ ነው። በዚህ ሂደትም የበርካታ ሰዎች ባህርይ ከማስገረም አልፎ እስከማሳዘን አድርሶታል። እንደ እሱ ትዝብት አንዳንዱ ማድረግ የሚገባውን ትቶ ህገወጥ አካሄድን ይከተላል። ይህ መጥፎ ልማድ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ብዙዎች ህገ ወጥነትን በመከተል ስህተት ሲፈፅሙ ይታያል፡፡
አዲሱ እግረኞችን ለማሻገር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከበርካታ አሽከርካሪዎች ጋር ይገናኛል። በስራው አጋጣሚም አብዛኛዎቹ ሾፌሮች ሥነሥርዓት ያላቸውና ለህግ ተገዢዎች መሆናቸውን አስተውሏል። ጥቂቶቹ ደግሞ ከበጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ ይልቅ ለትራፊክ ፖሊሶች ብቻ ሲታዘዙ ይመለከታል። እንዲህ አይነቱ አመለካከት ያላቸውም የትራፊክ ደንቡን ለማክበር ፍቃደኞች አይደሉም። ስህተት ፈጽመው እንዲቆሙ ሲጠየቁም ተሳድበውና አመናጭቀው ለመሄድ ይፈጥናሉ።
ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ስነምግባር የሚስ ተዋልባቸው አሽከርካሪዎች አደጋ ለማስከተል የፈጠኑ መሆናቸውን የሚያምነው አዲሱ፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ በሰሩት ስህተት የሚፀፀቱት ውለው አድረው ይቅርታ ለመጠየቅ እንደሚመጡ ይናገራል። ብዙ ጊዜ ስልክ እያወሩ መንገድ የሚያቋርጡ እግረኞችም ድርጊታቸው ስህተት መሆኑ እንዲነገራቸው አይፈልጉም።
እንዲህ ለማድረግ የሞከረ አሻጋሪ ሲኖር ስድብ አልያም ቦክስና እርግጫ ሊደርስበት ይችላል። አዲሱን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የትራፊክ አጋዦች ወጣት እንደመሆናቸው አንዳንዴ በመንገድ የሚያጋጥሙ ያልተገቡ ግብግቦችን ታግሶ ለማለፍ አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል። እንዲህ ሲሆን ሌሎቹ በመካከለል በመግባትና ነገሩን በማስገንዘብ ስለሚያስተምሩ የየዕለቱ ተሞክሯቸው ትምህርት እየሆናቸው ማለፍን ለምደውታል።
ሁሉም በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጄንሲ በኩል የተሰጠውን የትራፊክ ደህንነት ስልጠና በአግባቡ የተከታተሉ ናቸው። ለሚያበረክቱት በጎ አስተዋጽኦም ለኪስ ተብሎ የሚሰጣቸውን ክፍያ ለተለያዩ ጉዳዮቻቸው እንደሚያውሉት ይናገራሉ። ወጣት አዲሱም በግማሽ ቀን ውሎው ከሚያገኘው ጥቂት ገቢ ትምህርቱን ይማራል። በቀሪው ጊዜም ለአቅሙ በሚመጥን ስራ ላይ ተሰማርቶ ራሱንና ቤተሰቦቹን እየጠቀመ ይገኛል።
አዲሱ ማንም ሰው ካሰበውና ካቀደው ዓላማ ለመድረስ በሰላም ወጥቶ መመለሱ ግድ እንደሚለው ያምናል። በየቀኑ በትራፊክ አደጋ እየረገፈ ያለው ህብረተሰብም ለህግና ሥርዓት ተገዢ ቢሆን ጠቀሜታው ለራሱ ብቻ አለመሆኑን ይናገራል። ‹‹ብዙዎች እንደወጡ ለመቅረታቸው ምክንያቱ የራሳቸውም ስህተት ስለመሆኑ ለሌሎች ትምህርት መሆን ይገባዋል›› የሚለው ወጣቱ ይህን እውነት ደግሞ በየቀኑ ከሚቆምበት መንገድና ከሚያገኛቸው በርካታ ሰዎች ማንነት ሊረዳው መቻሉን ይናገራል።
ወጣት አቡበከር ሁሴንም በየቀኑ የትራፊክ ማስተናበሩን ተግባር ሲከውን ይውላል። አቡበከር እሱን ጨምሮ ሌሎች ጓደኞቹ እያደረጉ ባሉት አስተዋጽኦ በርካቶች ጥሩ ግንዛቤ እንዳተረፉ ይገልፃል። ‹‹አብዛኛዎቹ መኪናን ተዳፍሮ ለመሻገር የሚፈሩ በመሆናቸው በሚደረግላቸው ትብብር ምስጋናና ምርቃትን የሚቸሩ ናቸው። ጥቂቶቹም አስቀድሞ ለትራፊክ ህጉ በቂ ግንዛቤ ቢኖራቸውም ሁሌም የሚባሉትን አክብረውና ጊዜ ወስደው ስለሚጠቀሙ ህግ አክባሪዎች ናቸው›› ይላል።
አቡበከር መንገድ በሚዘጋጋና መኪኖች በሚበረክቱበት ወቅት እግረኞች ግራ መጋባትና መዋከብ እንደሚያገጥማቸው ይገልጻል። ይህን ጊዜ አሻጋሪዎቹ ወጣቶች በራሳቸው ስልትና ቅልጥፍና መጨናነቁን በማቃለል በአግባቡ የማስተናበሩን ተግባር ይከውናሉ። ይህን ለማድረግ ግን እግረኞችም ሆኑ አሽከርካሪዎች ስነ ምግባርን የተላበሱ ሊሆኑ ይገባል።
እንደወጣቱ ዕምነት ቀድሞ ከነበረው አመለካከት አሁን ያለው ግንዛቤ የተሻለ ነው፡፡ በፊት መንገድ ጥሰው በእምቢተኝነት የሚያልፉ አሽከርካሪዎችና እግረኞች ዛሬ የሚደረግላቸውን ስለሚያዩና ጠቀሜታውን ስላወቁ ለመተባበር ፍቃደኛ ናቸው፡፡ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ባልተገባ ስነምግባር በሚፈጽሙት የሴኮንድ ስህተት ዳግም የማይተካው ህይወት በከንቱ ይጠፋል፡፡ እግረኞችም በመዘናጋት በሚፈጠር ስህተት ለአደጋ ላለመጋለጥ መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ህይወት አንዴ ካለፈች ዳግም ስለማትገኝ ሁሉም ለራሱ፣ ለሌላውና ለብዙሃኑ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።