‹‹ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ››- ለወረርሽኝ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ያስቻለ ሥርዓት

10 Jul 2018

ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ የበሽታ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለመቆጣጠርና ከተከሰተ በኋላም በቂ ምላሽ መስጠትን ዓላማ በማድረግ የተጀመረ የስልጠና ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረው በአሜሪካ አትላንታ በሚገኘው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል /CDC/ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአለም አቀፍ ደረጃ 65 የሚጠጉ ሃገራት የስልጠና ፕሮግራሙን እየሰጡ ሲሆን፣ስልጠናው በሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያም በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ለመቆጣጠር ሲባል ፕሮግራሙ አትላንታ /CDC/ በተደረገ ድጋፍ እ.ኤ.አ በ2009 እንደ ተጀመረ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በወቅቱ ስልጠናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ መስጠት የተጀመረ ሲሆን፣በዚህም 15 የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ተመርቀው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2015 ወዲህ ግን ኢቦላን የመሳሰሉ ለሃገሪቱ ብሎም ለዓለም የሚያሰጉ በሽታዎች መከሰታቸውን ተከትሎ የሥልጠና ፕሮግራሙን በሃገሪቱ ባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በማስፋፋት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ሰልጣኞችን ቁጥር ወደ 504 ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም ስልጠናውን በመስጠት ሀገሪቱን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስፍራ እንድትይዝ ያስችላታል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጤና ፅህፈት ቤት በጤና መኮንንነት የሚያገለግለው አቶ አንተነህ ጌታሁን የመጀመሪያውን የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ተከታትሎ ካጠናቀቀ በኋላ በቢሮ ደረጃ ብቻ ተገድበው ሲሰሩ የነበሩ ስራዎችን መስክ በማውጣትና ኅብረተሰቡ ዘንድ በመውረድ መስራት እንደሚቻል ተገንዝቧል፡፡እነዚህ ሥራዎች ፖሊሲ ለመቅረጽ ጭምር እንደሚያገለግሉ ተረድቷል፡፡
የኅብረተሰቡን የጤና ችግር በቅርበት ሆኖ የሚከታተል የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ የሚጠቅሰው አቶ አንተነህ፤ በተለይም በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ በሚችሉ በሽታዎች ላይ የሚደረገው ቅኝትና የዳሰሳ ሥርዓት መጠናከር ይኖርበታል ይላል፡፡ በሽታው ከተከሰተም በኋላ በአፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የማገገም ስራ መስራት እንዲቻል የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይናገራል፡፡
እንደ አቶ አንተነህ ገለፃ፤ የበሽታ ቅኝት የሚጀምረው በአብዛኛው ከማኅበረሰቡ እንደመሆኑ መጠን የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ታች በመውረድ ማኅበረሰቡን ማገልገል ይኖርባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ወደማኅበረሰቡ ቀርቦ በመስራት ረገድ የሚስተዋሉ ድክመቶችን ማስወገድ ይገባል፡፡
በቢሮ ደረጃም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ስራን በተመለከተ በአግባቡ አውቆ በመስራት በኩል የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ጠንካራ ተግባር ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡም የበሽታ ቅኝት ስራው ጥቅም ምን እንደሆነ ገና ያልተረዳ በመሆኑ ከጤና ተቋማት በመውጣት ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ መፍጠር፣የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስራ በአብዛኛው እንቅስቃሴ የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ በቂ ትራንስፖርት ሊመደብም ይገባል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው አቶ መዝገቡ የኋላ በትምህርት ቤት ቆይታው በዋናነት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ተብለው የሚጠቀሱ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የሚያስችለውን እውቀት ጨብጧል፤በተለይ የበሽታ ቅኝት ስራዎችን በማካሄድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ እንዴት መከላከልና የኅብረተሰቡን ጤና መጠበቅ እንደሚቻል ፣በሽታዎችን በተመለከተ መረጃዎችን በመሰብሰብ መረጃዎቹ ውሳኔ እንዲያገኙ ለሚመለከተው አካል እንዲደርሱ ለማድረግ የሚያስችለውን ዕውቀት ቀስሟል፡፡
የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ትምህርት በአብዛኛው የሚሰጠው ማኅበረሰቡ ዘንድ በመዝለቅ በመስክ ቆይታ በመሆኑ በዚህ ሂደት የበሽታ ቅኝት ስራ ይካሄዳል፡፡ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በዋናነት መረጃዎችን ማሰባሰብን ይጠይቃል፡፡
ቀደም ሲል ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሲሆን የቆየው በቢሮ ውስጥ ብቻ እንደነበር አስታውሶ፣‹‹በአሁኑ ወቅት መሬት ላይ በመውረድ ሥራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ፕሮግራሙ በተለይ የኅብረተሰቡን ጤና አስቀድሞ እንዲጠበቅ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡›› ይላል፡፡
ከዚህ በፊት በአብዛኛው በሽታዎች ከተከሰቱ በኋላ ስራዎች ይሰሩ እንደነበር የሚጠቅሰው አቶ መዝገቡ፤ በአሁኑ ወቅት ግን በሽታዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ የሚያስችሉት የቅኝት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ለሃገሪቷ እንደ ዋና ስጋት ሊሆኑ በሚችሉ በሽታዎች ላይ ትኩረት በማድረግም የቅኝት ስራው የበለጠ መጠናከር እንደሚኖርበት ይጠቁማል፡፡
እንደ አቶ መዝገቡ ማብራሪያ፤ በቅኝት ሥርዓቱ በየጊዜው የሚገኙ መረጃዎች ጠቃሚ ግብአት ሊሆኑ ስለሚችሉ ለሚመለከተው አካል በማድረስ የመረጃ ሥርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ይህም በሽታዎች እንዳይከሰቱ በእጅጉ ይረዳል፡፡ በሽታው ቢከሰትም ወዲያውኑ መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሰው ሃብት ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ እንደሚገልፁት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት ሃገር በመሆኗ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም ማቋቋም አስፈልጓል፡፡ ሌላው ፕሮግራሙ ያስፈለገበት ምክንያት በሃገሪቱ እ.ኤ.አ በ2009 የተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ጠንካራ የበሽታ መከላከል አቅም መገንባትና መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ካላት የመልክአ ምድር አቀማመጥና የሕዝብ ብዛት አንፃር በርካታ በሽታዎች ሊያጋጥሟት ይችላሉ፡፡››ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በጎረቤት ሃገራት ጠንካራ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም አለመኖርም ትልቅ ስጋት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎችን በብዛትም በጥራትም መፍጠር ካልተቻለ ሀገሪቷ የበሽታ አደጋ ውስጥ ትገባለች ተብሎ እንደሚታሰብ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የሥልጠና ፕሮግራሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ ጅማ ፣ ሃሮማያ ፣ሃዋሳ ፣መቀሌ፣ጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲስፋፋ ተደርጓል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለጻ፤ በሀገሪቱ ያለው የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ቁጥር በቂ ባለመሆኑ ፣እ.ኤ.አ እስከ 2019 ባለሙያዎቹን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለሙያዎችን በማፍራት ሂደትም የጥራት ችግሮች መኖራቸው ታውቋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም በርካታ ተግባሮችን ለማከናወን ተሞክሯል፡፡ የአገልግሎት ጥራትን በተመለከተ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች በትክክል ለቦታው የሚመጠኑ እንዲሆኑና በስራ ላይ እንዲሰማሩ ማህበር መፍጠር እንደሚገባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
‹‹የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ስራ የሚለካው በሽታ ከሌለ በመሆኑ በኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራሞች የተሰሩ ስራዎችን ለመዘርዘር ቁጥሮችን መጥቀስ አያስፈልግም›› የሚሉት ዶክተር ጌታቸው ፣ ለዚህም ምክንያቱ በሽታው እንዳይኖር ከተደረገ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያው ወይም የበሽታ ቅኝት ሥርዓቱ ጠንካራ ነው ማለት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ በሽታ ከተከሰተ ደግሞ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ስራ የሚለካው በሽታው የባሰ አደጋ ሳያስከትል መቆጣጠር በመቻሉ እንደሆነም ጠቀመው፣ችግሩ በሰፊው ከመጣ ደግሞ በሽታውን ለመከላከል ሙሉ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለፃ፤በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች መሸጋገሪያቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ማድረጋቸው ፣ሃገሪቷ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ፣ በጎረቤት ሃገራት ያለው የበሽታ ቅኝት ሥርዓት ደካማ መሆን፣ ኢትዮጵያ ታዳጊ ሃገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የጤና ሥርዓቷ ጠንካራ ባለመሆኑ ለአጣዳፊና ተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ እድሏ ሰፊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለአለም ስጋት የሆኑት የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎች በሀገሪቷ እስካሁን አለመከሰታቸው ጠንካራ የበሽታ ቅኝት ስርዓት መዘርጋቱን ያመለክታል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሰው ሃብት አስተዳደር ልማት ዳይሬክቶሬት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂና የኅብረተሰብ ጤና ፕሮግራሞች አስተባባሪ ዶክተር ታጠቅ ቦጋለ በበኩላቸው እንደሚያብራሩት፤የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም በዋናነት ያስፈለገው በሃገሪቷ ያለውን የበሽታዎች ቅኝት ሥርዓት ለማሻሻል የላቀ ክህሎት ያላቸው የኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በሃገሪቱ ወረርሽኞች፣የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ አፋጣኝ ርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል ታስቦ ነው፡፡
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ አነስተኛ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ቁጥር እንደነበራት የሚያስታውሱት አስተባባሪው፤ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ በቀጣይም ከሕዝቡ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ባለሙያ ማሰልጠን ካልተቻለ ኢቦላን የመሳሰሉ በሽታዎች በሃገሪቱ ቢከሰቱ በቀላሉ ለመመከት አዳጋች እንደሚሆን ጠቁመው፣ ባለሙያዎቹን በጥራትም ሆነ በብዛት ማፍራት ከተቻለም በሽታዎቹ ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስቀድሞ መሆኑን ለማሳወቅና እንዳይመጡ ለመከላከል ብሎም ከተከሰቱም በኋላ ምላሽ ለመስጠትና ለመከላከል ያስችላል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
አስተባባሪው እንደሚሉት፤ፕሮግራሙ በሃገሪቱ የድርቅ አደጋ በተከሰተበት ወቅት ሰፊ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ከሃገር ውስጥም አልፎ በሴራሊዮንና ላይቤሪያ በተከሰተው የኢቦላ በሽታ ላይም ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተከስቶ የነበረውን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ለማቆም የምላሽ ስራ ተከናውኖበታል፡፡ በዚህ ረገድ የስምንቱም ዩኒቨርሲቲዎች የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ሰልጣኞች በሃገር ደረጃ ለተደረገው ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሃገሪቱ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ዜጎችን ከማስተናገዷ አኳያ እስካሁን ኢቦላን በመሳሰሉ ከባድ ተላላፊ በሽታዎች አለመጠቃቷ ፕሮግራሙ ካመጣቸው ስኬቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን አስተባባሪው ጠቅሰው፤ ለዚህም ስኬት የኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች በተለይም በአየር መንገድ አካባቢ ጠንካራ የበሽታ ቅኝት ሥርዓት መዘርጋታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ይላሉ፡፡ በክልል ደረጃም ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ ድንገተኛና አጣዳፊ የኅብረተሰብ በሽታዎችን ከመከላከል አንፃር የቅኝት ሥርዓቱ ከፍተኛ መሻሻሎችን ማምጣቱን ጠቅሰው፣ የበሽታዎች ቅኝት ሥርዓቱን አስቀድሞ ማጠናከር በመቻሉም በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች አስጊ የሆኑ በሽታዎች በሃገሪቱ እንዳይከሰቱ ማድረግ ማስቻሉን ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በፕሮግራሙ ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎችም ከሃገራቸው በዘለለ ላይቤሪያና ሴራሊዮን በመሳሰሉ የአፍሪካ ሃገራት በመሄድ ድጋፍ በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ይጠቁማሉ፡፡
ተማሪዎቹ በአብዛኛው ማኅበረሰቡ ውስጥ በመግባትና በመስክ ላይ የሚሰሩበት ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው፣ከዚህ አንጻር በሃገር ደረጃ ካሉት 72 የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ጣቢያዎች መኪናዎች ያሏቸው አርባዎቹ ብቻ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ይህ አንድ ተግዳሮት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ የአሜሪካ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተው፣ይህ ድጋፍ እየቀነሰ እንደሚሄድና መንግስት ለፕሮግራሙ ከሰጠው ትኩረት ጎን ለጎን የገንዘብም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስራ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ በኢትዮጵያ በሚገባ ታይቷል፡፡ይህንን ከሀገሪቱ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፖሊሲ አኳያ ውጤት እያስገኘ ያለ እንደ አህጉርም ተጠቃሽ ለመሆን የበቃ ፕሮግራም መንግስት በቀጥታ በመደገፍ የተሽከርካሪና እና የገንዘብ ችግሩን መፍታት ይኖርበታል፡፡ይህ ድጋፍ ተላላፊ በሽታዎች ተከስተው ከሚያስከፍሉት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ሚዛን የሚደፋ መሆኑን በመረዳት መስራት ከመንግሥት በኩል ይጠበቃል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።