የባህር ሞገዱን የተራመዱ Featured

11 Jul 2018
ከዘጠኙ የኢትዮጵያ መርከቦች መካከል ባህር ዳር የሚል ስያሜ ያላት መርከብ ከዘጠኙ የኢትዮጵያ መርከቦች መካከል ባህር ዳር የሚል ስያሜ ያላት መርከብ

 

እያንዳንዱ ሙያ በራሱ ስነምግባርና ደንብ የተቃኘ ሲሆን፤ መልካም ፍሬ ይኖረዋል። በስሩ የሚገኙ ባለሙያዎችም ለተቀመጠው ህግና መመሪያ ተገዢ መሆን ሲችሉ ለበርካቶች አርአያ ይሆናሉ። ሁሌም በመልካም ስነምግባር የታነጸ ባለሙያ ደግሞ ስለትላንት የሚያወሳው ታሪክ ይኖራል። ሥራውን ለውጦ በሌላ ስፍራ ቢቀመጥ እንኳን ያለፈበት የህይወት መስመር የሚዘነጋ አይሆንም። የአዲስዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም ቀደም ሲል በመርከበኝነት ሙያ ያለፉና ዛሬም የትላንቱን ጊዜ በበጎ እያስታወሱ ትዝታቸውን ከሚያወጉ ባህረኞች ጋር ቆይታ አድርጋ ያካፈሏትን ተሞክሮ እንዲህ ታጋራናለች።

የትላንትናውን የህይወት መንገዱን ሲያስበው አሁን ለሚገኝበት መልካም ስብዕና መሰረት እንደሆነው ያምናል። በ1976 ዓ.ም በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለ እሱና ስድስት ጓደኞቹ ወደግሪክ አገር ተጓዙ። የዛኔ አገር ርቀው ባህር አቋርጠው የሄዱበት ዓላማ ታላቅ ኃላፊነትን የሚሻ፣ ማንነትንም የሚፈትን ሙያ ነበር። ከአራት ዓመታት በኋላ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ አገራቸው ለታላቅ ተልዕኮ ትፈልጋቸዋለች።
ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ ይታገሱ፤ ገና በአፍላነት ዕድሜው መርከበኛ ለመሆን ሲወስን የባህሩን ቆይታና አይቀሬዎቹን ስጋቶች አላጣቸውም። መቼም ቢሆን የባህር ላይ ነፍስ ከአስፈሪና ከአስደንጋጭ አጋጣሚዎች የራቀ እንደማይሆን ያውቃል። የመርከብ መስመጥና አደጋው፣ የማዕበሉ ወጀብና ግፊት፣ የአሳነባሪው ቁጣና የባህር ላይ ወንበዴዎች ክፋት ሁሉ አብረውት ይጓዛሉ።
መርከበኝነትን ሙያ አድርገው ሲቀበሉት ከእነዚህ እውነታዎች ጋር ተስማምቶ መጓዝ ግድ ይላል። አንዳንዴ በባህር ላይ ወራትን አልፈው ዓመታትን ሲሻገሩ ፣ ውስጣዊ ስሜት እንደውቅያኖስ አይረጋም። እንደ መርከብ እግርም በመልህቅ አይታሰርም። እንዲህ በሆነ ጊዜ ቤተሰብ በእጅጉ ይናፍቃል። የሀገርና የወገን ትዝታም ልክ እንደባህሩ ሽታ ውል እያለ ይፈታተናል።
መርከበኛው አድማሱ በግሪክ ቆይታውን አጠናቆ ሲመለስና ሙያውን አሀዱ ብሎ ሲጀምር ከእነዚህ ስሜቶች የራቀ አልነበረም። የዛኔ የመጀመሪያውን የሩቅ ምሥራቅ ጉዞ ያቀናባት «ነፃነት» የተባለችው መርከብ ነበረች። በዚህች መርከብ ተጉዞ ወደተነሳበት የአሰብ ወደብ ለመመለስም አራት ወር ተኩል ያህል እንደቆየ ያስታውሳል። በጉዞውም የጃፓን፣ የቻይና፣ የኮሪያ፣ የሲንጋፖር፣ የኬንያና ዳሬሰላም የባህር ወደቦችን አቋርጧል።
መርከበኞች በሚጓዙባቸው ሀገራት፤ በርካታ ስፍራዎችን የማየት ዕድሉ አላቸው። የሌሎች ባህልና ታሪክን ጨምሮ እንግዳ ሰዎችን ለማወቅም የቀረቡ ይሆናሉ። አድማሱና ጓደኞቹ ያዳበሩት ሙያዊ ስነምግባርና ጨዋነት ደግሞ ከብዙሃኑ ሲያስተዋውቃቸው ቆይቷል። የዚያኔው መርከበኛ በጉዞ ወቅት ሊያጋጥም በሚችል አደጋ የነበረውን አጋርነትና መተሳሰብ ዛሬም ድረስ አይዘነጋውም። በየመርከቡ የነበረው ወንድማማችነትና ፍቅርም በቋንቋና ባህል የሚለያየውን ባለሙያ አንድ አድርጎ የሚያሰባስብ ነበር።
ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ ሙያዊ ግዴታውን በብርታት ሲወጣ እንደቆየ ያስታውሳል። ከሁሉም በላይ ግን የቤተሰቡ ናፍቆትና ትዝታ ይፈታተነው እንደነበር አይሸሽግም። የዚያኔ እንደአሁኑ የሞባይል ስልክ በሁሉም እጅ አልገባም። በቀላሉ የቤተሰብን ደህንነት ጠይቆ ለማወቅ ይቸግራል። ይህን ለማድረግ የሚኖረው አማራጭ መርከቡ በቆመበት የወደብ ከተማ የመስመር ስልክ አፈላልጎ መደወል ብቻ ይሆናል። በወቅቱ ለአገር ቤት ስልክ የሚጠየቀው ወጪ ከፍተኛነት ኪስን የሚጎዳና ኢኮኖሚን የሚያራቁት ነበር።
ሁሌም ቢሆን የባህርን ሞገድና ተፈታታኝነቱን መቋቋም ሙያዊ ግዴታ ነው። ይህ አይቀሬ ትግልም ለአንድ ባህረኛ በቀላሉ የሚረሳ አይሆንም። መርከበኛ አድማሱም ይህን ስሜት በዋዛ መልመድ እንደማይቻል ዛሬም ድረስ የሚመሰክረው ነው።
የባህር ላይ ሞገድ ድንገት ቢነሳ መርከበኛው ተጓዥ ሥራውን በአግባቡ ሊወጣ ግድ ይለዋል። ከተፈጥሯዊ ፈተናዎችና ከራሱ ስሜት ጋር እየታገለም ሙያውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል። ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ በሲንጋፖር ጉዞ የባህር ላይ ወንበዴዎችን ድንበር የማቋረጥ አጋጣሚን ጭምር እንደተጋፈጡ ያስታውሳል።
መርከብ በተበላሸ ጊዜም ዕረፍትና እንቅልፍ ይሉት ነገር አይታሰብም። ከሰማይ በታች በሰፊው የባህር ሜዳ ላይ የቆመው ግኡዝ አካል ነፍስ ዘርቶ እስኪንቀሳቀስ በትጋት መረባረብ ያስፈልጋል። ይህ ዓይነቱ ጉዳይ ሲነሳ ቺፍ አድማሱ በሙያው አጋጣሚ የደረሰበትን እውነት ዛሬም ድረስ ያስታውሳል።
በአንድ ወቅት እሱና የሥራ ባልደረቦቹ አዲስ መርከብ ከሮተርዳም ወደብ ይረከቡና ጉዟቸውን በሲዊዝ ካናል ወደአሰብ ወደብ ያደርጋሉ። መርከቧ ለጉዞ አዲስ እንደመሆኗ አብረዋት ካሉት ባህረኞች ጋር በቀላሉ አልተግባባችም። የሚስተዋልባት የቴክኒክ ችግርም እምብዛም የሚያራምዳት አልሆነም። የመርከቧ ያልተለመደ ባህርይ ለሁሉም መርከበኞች የእራስ ምታት ቢሆን ጤንነቷን ለመመለስ ትግሉ ተጀመረ። ዕረፍት አልባው ትንቅንቅም በስጋት ታጅቦ የአዕምሮና ጉልበት ዋጋን አስከፈለ።
ቺፍ አድማሱ ለአንድ ዓመት ያህል በባህር ላይ ትግል ከገጠመችው መርከብ ሌላ «በተአምር ተረፍኩበት» የሚለውን አይረሴ አደጋ መቼም ቢሆን አይረሳውም። ወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተጀመረበት1990 ዓ.ም ነበር። በዚህ ጊዜ አሰብ ወደብ የቆመችውና እሱ የነበረባት መርከብ በከባድ መሳሪያ ትመታለች። በመርከቧ ላይ ያጋጠመው ጉዳት የላቀ መሆኑ በውስጧ የነበሩት ይተርፋሉ የሚባልበት አልነበረም። ቺፍ አድማሱና ባልደረቦቹ ግን ያለምንም ችግር በህይወት መኖራቸው ታወቀ። ለእሱ ይህ ተአምር አሁንም ድረስ በእጅጉ የሚያስገርመው ነውና ፈጣሪውን ደጋግሞ ያመሰግናል።
ቺፍ አድማሱ ከሦስት ጉልቻ በኋላ ተመልሶ ወደባህር መጓዝ ፈተና ሆኖበት ቆይቷል። ከትዳር አጋሩ ለመለየትም ስሜቱ ቀላል እንዳልነበረ ትዝ ይለዋል። አጋጣሚ ሆኖ ከጋብቻው በኋላ በመርከበኝነት ህይወት አለመዝለቁ የመለያየትን ሰቀቀንና ጭንቀት እንዳይደጋግመው አግዞታል።
ዛሬ ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ የአራት ልጆች አባት ነው። በኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ተቋም በመምህርነት ሙያ እያገለገለ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በምህንድስና ሙያው በነበረው ታላቅ ተሳትፎ ከሀገራችን አስራአንድ መርከቦች መሀል የዘጠኙን ግንባታ በእሱ መሪነት አጠናቋል። ይህ መሆኑ ደግሞ በሙያው የሚኮራበት ተግባር ነውና ሁሌም ደስ ይለዋል።
ካፒቴን ጌትነት አባይ፤ አሁንም ቢሆን የባህር ላይ ቆይታውን የመርከብ ትዝታውንና የሥራ ላይ ፍቅሩን አይረሳም። ዛሬም የጥቁር ባህር ትዝታ፣ በዓይኑ ውል ይልበታል። የውቅያኖሱ ንፋስ፣ የማዕበሉ አረፋና ወጀብም ከጆሮው ሽው ይላል። ለእሱ ባህረኝነት ክቡር ሙያው ነው። ከዓመታት በኋላ ልክ እንደዛሬ የሚያስበው የህይወት ጥሪ።
ከዚህ ቀደም ያለፈበትን የመርከበኝነት ሙያ የሚያስታውሰው በተለየ ትዝታ ነው። እኤአ የመጀመሪያ ዲግሪውን በኒዮቲካል ሳይንስ ከህንድ አገር ከወሰደ በኋላ ሙያውን የጀመረው በተለማማጅ መሪ መኮንንነት ወደ ሀገሩ ተመልሶ ነበር። የዛኔ አድማስና አባይ ወንዝ የሚባሉ ሁለት መርከቦች ነበሩ። ካፒቴኑ መርከቦቹን ያወቃቸው በሙያው አጋጣሚ ነበርና ከእነሱ ጋር ለመዝለቅ የቀረበ ነበር።
የመጀመሪያው የባህር ጉዞ ከአሰብ ጂቡቲ ወደ ምጽዋ ቀጥሎም አውሮፓ ሆነ። በጀርመን የብሬመን ሀመን ወደብ ከነበረው ቆይታ በኋላም ወደ ሀምቡርግ፣ ሰሜን ኢንግላንድ፣ ሮተርዳምና ባርሴሎና አቀና። በባህር መንገዱ ሲመላለስ ሁሌም መድረሻው አሰብ ወደብ ነበር። ረጅሙን የባህር መስመር ያለማቋረጥ ሲጓዙ ለቀናት ውሃ ላይ መቆየት ይኖራል። በየሀገራቱ በሚገኙ ወደቦች ላይ አረፍ ብለውም የመልስ ጉዞን መጀመር የተለመደ ነው።
አንዳንዴ ወደቦችን አቋርጠው ሲሄዱ ከተሞችን በቅርበት ያገኛሉ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ነጋዴዎች መርከቡ ድረስ ዘልቀው እንዲጎበኟቸው የማድረግ አጋጣሚ ይኖረዋል። እነሱም ቢሆኑ በደረሱበት ከተማ ወርደው ገበያውን ተዘዋውሮ መመልከትን ለምደዋል። ካፒቴን ጌትነት በሠራው አጋጣሚ በርካታ የባህር መስመሮችን አልፏል። ጥቂት በማይባሉ ወደቦች አርፎም የብዙዎችን ባህልና ታሪክ ማወቅ ችሏል። አልፎ አልፎ ደግሞ ምንም ከተማና ወደብ ሳይገኝ ቀናትን የሚገፉበት ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም። ከፒቴኑ ለዚህ የሚጠቀሰው አካባቢ ወደ ሩቅ ምሥራቅ የሚደረገውን አሰልቺ ጉዞ ነው። ከጂቡቲ ስሪላንካ፣ ሲንጋፖርና ማላካ የሚደረገው ማቋረጥም ምንም ዓይነት ከተማ የማይታይበት ጉዞ እንደሆነ ያስታውሳል። በተለማማጅ መኮንንነት የቆየው መርከበኛ ከእነዚህ ሁሉ የጉዞ ተሞክሮዎች በኋላ ሙያውን በተጨማሪ ስልጠናዎች አዳበረ። ጥንካሬው እውን ሆኖ ሲመሰከርም የሦስተኛ መሪ መኮንን ካፒቴን ማዕረግን አገኘ።
ባህር ማለት በባህርይው ቋሚ የሚባል አይደለም። ዛሬ ሰላማዊ ቢሆን ነገ ሊለወጥና ሊቆጣ ይችላል። ዝምታና እርጋታው ደፍርሶም በማዕበልና ወጀብ መታጀቡ የተለመደ ነው። ካፒቴን ጌትነትም በመርከበኝነት ህይወት የመጀመሪያው ጥንካሬ ከባህር እንቅስቃሴ ጋር መላመድ እንደሆነ ይናገራል። ከውሃ ጋር ጓደኛ እስኪሆኑ ስሜቱን መዋሀድ ግን ቀላል የሚባል አይሆንም።
ባህር ላይ ሲገኙ ማዞር፣ ማቅለሽለሽና በእጅጉ መረበሽ አይቀርም። አንዳንዴም ችግሩ ከዚህ ያለፈና የጠነከረ ሊሆን ይችላል። ይህ በሆነ ጊዜ ብዙዎች መርከበኝነት በቃን፤ እንደውም ይቅርብን ሊሉ ይችላሉ። ይህ ስሜት ውቅያኖስ ላይ ሲሆን ደግሞ በእጅጉ የበረታና የሚያስቸግር ይሆናል። ሆኖም ሙያውን ተዋህደው ከባህር ሲወዳጁ ድንገቴው አጋጣሚ የዘወትር ትዕይንት ሆኖ ይቀጥላል።
ካፒቴን ጌትነት ባለፈባቸው የባህር መስመሮች ከበርካታ ህዝቦች ጋር ተዋውቋል። ይህ አጋጣሚም ባህልና ልምዳቸው እሱ ከኖረበት ማንንት መራቁን አሳውቆታል። በተመሳሳይ በእነዚህ ስፍራዎች ያገኙት ባዕዳንም መልክና ቁመናው ያስገርማቸዋል። ጸጉሩን እየነኩና እየዳሰሱም በልዩነቱ ይገረማሉ። ጠቆር የሚሉ ባልንጀሮቹን ሲያስተውሉ ደግሞ የመልካቸው ቀለም እንደሚለቅ ገምተው በሙከራ ማረጋገጥን ይሻሉ።
የባህረኛ አለባበስ ዓለም አቀፍ ገጽታን የተላበሰ ነው። ካፒቴን ጌትነትም በሀገሩ ንግድ መርከብ ላይ በሚሠራበት ጊዜ ሰማያዊ ኮትና ሱሪ በነጭ ሸሚዝ ይለብስ ነበር። አለባበሱ እንደየደረጃና ማዕረጉ የሚለያይ ቢሆንም በባህር ጉዞ በተለይም በወደብ አቅራቢያ አለባበሱን የማሟላት ግዴታ እንደነበር ያስታውሳል። አሁን ላይ ግን በአንዳንድ ታላላቅ ድርጅቶች ላይ ይህ አሠራር እየቀረ መሆኑን አስተውሏል።
ካፒቴን ጌትነት ትዳር የመሰረተው ሁለተኛ መሪ መኮንን በሆነበት ጊዜ ነበር። ባህረኝነት ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ፈታኝ እንደሆነም ከህይወት ልምዱ አረጋግጧል። በተለይ የልጆች አስተዳደግንና ሙያዊ ግዴታዎቹን በአንድ ሚዛን ለማስቀመጥ እንደሚከብድ ያስተዋለው እውነታ ሆኗል። እንደሱ ዕምነትም የአንድ ባህረኛ ከባዱ እራስ ምታት ከቤተሰብ ተነጥሎ የሚያሳልፋቸው የብቸኝነት ጊዜያቶች ናቸው።
ዛሬ ላይ ካፒቴን ጌትነት ከባህር ላይ ውሎ አያድርም። ልክ እንደትላንቱም ወደሌሎች ሀገራት ለማቋረጥ በመርከብ ላይ አይገኝም። ይሁን እንጂ አሁንም ከሚወደው ሙያ አልራቀም። በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛል። በርካታ ጊዜውን በማሪታይን ባለስልጣን በማድረግም አስፈላጊውን ስልጠና እያበረከተ ነው። ትላንት ባለፈበት ጉዞ ያካበተውን ዕውቀት ለሌሎች ማበርከት ግድ ብሎታልና ለዚህ በመታደሉ ከልቡ ይደሰታል።
ሁለቱም መርከበኞች ትላንትን በሞገዱ ላይ ተራምደዋል። ባህር ወደቡን ተሻግረውም በማዕበል ወጀቡ ተፈትነዋል። ዛሬም ግን ያለፉበትን መንገድ የሚያወሱት ልክ እንደዛሬ ታሪክ በቅርበት ሆነው ነው። አሁንም ደማቁ የሙያ ማህተማቸው በውስጣቸው መፍዘዝ አልጀመረምና።

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።