ብርታትን በተግባር Featured

12 Jul 2018
ወጣት ማንዴላ ገብረመድህን፤ ወጣት ማንዴላ ገብረመድህን፤ ፎቶ፡- ማህሌት አብዱል

አርባምንጭ ከተማ ሲቀላ በሚባል አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ዕድሜው ለጨዋታ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የመኪና ፍቅር ያደረበት ሲሆን፤ በአካባቢያቸው ማንኛውም ተሽከርካሪ ባለፈ ቁጥር እየተከተሉ መሮጥ የቀን ተቀን ተግባራቸው ነበር፡፡ ወጣት ማንዴላ ገብረመድህንና ጓደኞቹ፡፡ በተለይም በጎረቤታቸው የሚኖር አንድ የፖሊስ ባልደረባ መኪና እስካሁን ድረስ አትዘነጋውም፡፡ ግለሰቡ ለህፃናቱ ፍቅር ስለነበረው መኪናው ላይ ሲወጡ ምንም አይላቸውም ነበር፡፡ እንዳውም ገና በለጋ ዕድሜያቸው መኪና መንዳትና ሲበላሽ እንዴት መጠገን እንደሚቻል ልምድ እንዲቀስሙ ያደርጋቸው እንደነበር ነው የሚገልፀው፡፡ እነርሱም በተራቸው መኪናውን በማጠብ ወሮታውን ይከፍሉ እንደነበረም ይገልፃል፡፡
«እንግዲህ ያኔ የጀመረው የመኪና እና የብረታ ብረት ፍቅሬ አድጎ ኮሌጅ ስገባም ቀዳሚ ያደረጉት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ነበር» የሚለው ወጣት ማንዴላ በኮሌጅ ቆይታውም የኦቶሞቲቭ ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሌሎች መሰል ዘርፎች ላይ ሥልጠና መውሰዱን ይጠቅሳል፡፡ ውጤቱ ጥሩ በመሆኑም እዛው በመምህርነት ተቀጥሮ መሥራት ይጀምራል፡፡ ግን ተቀጥሮ መሥራቱ ስላላረካው አምስት ሺ ብር አጠራቅሞ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ባቋቋመው ማህበር አማካኝነት የብረታ ብረት ሥራዎችን ማከናወን ጀመረ፡፡ በዚህም ለአካባቢው ህብረተሰብ ፈጠራ የታከለባቸው የብረታብረት ውጤቶችን በማቅረብ ተቀባይነትን ማፍራት ችሏል፡፡
ብዙም ሳይቆይ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተወዳድሮ በመግባት ረዳት ቴክኒሽያን ሆኖ ማገልገሉን ቀጠለ፡፡ ገና ከለጋነቱ ጀምሮ ተሽከርካሪን አወላልቆ መልሶ የመገጣጠም ልምዱ አድጎና ዳብሮ በአንድ ጎን በተቀጠረበት የሙያ መስክ በሌላ በኩል ደግሞ በምርምር ሥራው የመምህራኑን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት የሚያስደስተው መሆኑን የሚገልፀው ወጣቱ በተለይም የዩኒቨርሲቲውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ የቆየውን የዝንጀሮ ጥቃት መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሠራ፤ ይኸውም የዝንጀሮ ወጥመድ ነበር፡፡

ወጣት ሰላማዊት ወልደሚካኤል፤


በዚህም ሥራው በዩኒቨርሲቲው ገንዘብና የነፃ ትምህርት ዕድል ተቸረው፡፡ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜም በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ተምሮ ሰሞኑን ለመመረቅ በቅቷል፡፡ አርባምንጭ ያፈራችው ይኸው ተመራማሪ ወጣት በመመረቂያ ሥራውም አዲስ ቴክኖሎጂን በማምጣት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ አንቱታን አግኝቷል፡፡ የራሱን 50ሺ ብር አውጥቶ የሞተር ሳይክል ሞተር በመጠቀም የሠራት ባለአራት እግር ተሽከርካሪ በምርቃቱ እለት በተመራቂ ቤተሰብና በመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ፊት አብራው ተመርቃለች፡፡
እንደወጣት ማንዴላ ገለፃ፤ በመመረቂያ ሥራው ያበረከታት ይህችው ተሽከርካሪ ከሌሎች የሚለያት አንድም ከሞተር ሳይክል ከተወሰደ ሞተር መሠራቷ ሲሆን፤ ሌሎች አካሏም በቀላል ዋጋ መገጣጠም መቻሏ ነው፡፡ አጠቃላይ ወጪዋም 70 ሺ ብር አይበልጥም፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት አንድ ባጃጅ ለመግዛት አገሪቱ ከምታወጣው 140ሺ ብር አኳያ ሲነፃፀር በግማሽ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም የውጭ ምንዛሪን በመታደግ ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡
ወደፊት በፋይናንስ የሚደግፈው ካገኘ ተሽከርካሪውን የበለጠ በማዘመን ለገበያ በስፋት ለማቅረብ አልሟል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የከተማዋ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መጠነኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና ዩኒቨርሲቲው ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚመደብለት በጀት ባለመኖሩ የምርምር ሥራዎች ለህብረተሰቡ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል መቸገሩን ያነሳል፡፡ በዚህም ምክንያት የምርምር ሥራዎች የሼልፍ ላይ አድማቂዎች እንዳይሆኑ ስጋት ያለ መሆኑን ጠቅሶ፤ የሚመለከታቸው አካላት ለእርሱ መሰል ወጣት ተመራማሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ነው የሚጠይቀው፡፡
ወጣት ማንዴላ ዋጋ ከፍሎ የሰራት ተሽከርካሪ እውን ሆና ማየቱ በራሱ ትልቅ የአዕምሮ እርካታ እንደፈጠረለት ያስረዳል፡፡ «ከኪሴ ያወጣሁት ወጪም ሆነ ሳልተኛ ያደርኩበት ጊዜ አሁን ላይ ምንም ትዝ አይለኝም፤ የእኔ ትልቁ ትርፍ ልክ እንደወላጅ ሁሉ አይኔን በአይኔ ማየቴ ነው» ሲል ይገልፃል፡፡ ለዚህ ያበቃውም ቁልፉ ምስጢር አስቀድሞ መክሊቱን ለይቶ ከግብ እንዲደርስ ያለመታከት መስራቱን ነው፡፡ በዚህም ካፒታሉን ከአምስት ሺ ተነስቶ አሁን ላይ 1ነጥብ 5ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ያሉትን ሁለት ተሽከርካሪዎችና ማሽኖቹን ሳይጨምር እንደሆነ ነው የጠቀሰው፡፡
«በእርግጥ» ይላል ወጣቱ ስለ አላማ ፅናትና ግብን መምታት ሲናገር፡፡ «በእርግጥ ማንኛውም ወጣት ትልቅ ራዕይ ቢኖረውም ከጎኑ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አያጣም፤ በተለይ ራዕዩን ተረድቶ የሚደግፍ ማግኘት አዳጋች ሊሆንበት ይችላል» ይላል፡፡ ነገር ግን ችግሮችን ሁሉ በፅናት ማለፍ ከቻሉ የማይደረስበት ነገር እንደሌላ ያምናል፡፡ በመሆኑም ልክ እንደእርሱ ሁሉ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች የትዕግስት ፍሬ ጣፋጭ መሆንዋን ተገንዝበው የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮት በፅናት ሊጋፈጡት እንደሚገባ ነው የመከረው፡፡
ወጣት ሰላማዊት ወልደሚካኤልም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ካስመረቃቸው ተማሪዎች አንዷ ናት፡፡ ወጣቷ በተከታታይ ሦስት ዓመታት በትጋት በማጥናቷ 3ነጥብ 98 በማምጣት ከሁሉም ተማሪዎች በመላቅ የዓመቱን የወርቅ ሜዳሊያም ሆነ ዋንጫ ወስዳለች፡፡
ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሲዳማ ዞን ይርጋለም ከተማ ውስጥ ተወልዳ ማደጓን የምታስረዳው ወጣት ሰላማዊት ቤተሰቦቿ እንደአብዛኛው የገጠር ነዋሪ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶአደሮች መሆናቸውን ትገልፃለች፡፡ «ቤተሰቦቼ ምንም እንኳ ቀለም የቀሰሙ ቢሆኑም ገፍተው ባለመማራቸው ምክንያት ኑራቸው ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ዓይነት ነበር» ትላለች፡፡ ይህ ቁጭት ያሳደረባቸውም የሰላማዊት ቤተሰቦች ታዲያ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው ልጆቻቸውን ተግተው ያስተምራሉ፡፡ በተለይም አባቷ ልዩ ክትትልና ድጋፍ ያደርጉላት እንደነበር ትጠቅሳለች፡፡
ሴት ልጅ በመሆንዋ ምክንያት ብቻ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ በቤት ውስጥ የማይደርስባት መሆኑን የምትገልፀው ወጣት ሰላማዊት መላ ትኩረቷን ትምህርቷ ላይ ብቻ እንድታደርግም ይገፋፏት እንደነበር ታስረዳለች፡፡ « እነርሱ ተምረው ምንም ሳላላገኙ ያጡትን ነገር በእኔ የማየት ፍላጎት ስለነበራቸው ከትምህርት ቤት እንደመጣሁ ምንም ሥራ አልታዘዝም፤ ይልቁንም እንዳጠና ብቻ ነው የሚያስገድዱኝ» ትላለች፡፡ ይህም አወንታዊ ጫና በአንደኛ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ሰቃይ ተማሪ ሆና እንድትዘልቅ ትልቅ ሚና መጫወቱን ታስረዳለች፡፡ አሁን ለደረሰችበት ስኬትም የወላጆቿ ሚና ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ታምናለች፡፡
ወጣት ሰላማዊት እንደምትገልፀው፤ ምንም እንኳን የሁለተኛ ደረጃ እስከምታጠናቅቅ ድረስ ተሸላሚ ተማሪ ብትሆንም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተፈትና ውጤቷ የጠበቀችውን ያህል ሆኖ አላገኘችውም፡፡ ይህም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ በፈለገችው የትምህርት ዘርፍ እንድትማር እንቅፋት ስለሆነባት በወቅቱ ልቧ ክፉኛ ተሰብሮ እንደነበር አትሸሽግም፡፡ «የግብርና ትምህርት ክፍል ሲደርሰኝ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ነገር ግን ያለኝ አማራጭ ያገኘሁትን መውደድ ስለነበር የተመደብኩበትን የግብርና ትምህርት መስክ ለመውደድ ተገደድኩ» ትላለች፡፡
በትምህርት ክፍሉ ደግሞ «አግሪካልቸራል ቢዝነስ» ዘርፍ የተሻለ መስሎ ስለታያት ቀዳሚ ምርጫዋ አድርጋው ባለፉት ሦስት ዓመታት በትጋት በማጥናት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ «በዚህ ትምህርት ክፍል ከገባሁ በኋላ የፈራሁትን ያህል መጥፎ ሆኖ አላገኘሁትም፤ እንዳውም ትምህርቱን እየወደድኩት ሦስቱንም ዓመት በፍቅር ነበር የተማርኩት፡፡ በዚህም አመለካከቴ ሁሉ ተቀየረ» በማለት ትገልፃለች፡፡
የወጣቷ የመመረቂያ ሥራ ዋና መጠንጠኛ በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ ባሉ ቲማቲም አምራች ገበሬዎች ዙሪያ ሲሆን፤ በዋናነትም አርሶአደሮቹ በሚያመርቱት የቲማቲም ምርት ለምን ተገቢ ጥቅም እንዳላገኙና በገበያ ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ቁልፍ ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ ይዳስሳል፡፡ «በጥናቴ በዋናነት የለየሁት አንዱ ጉዳይ ከአርሶ አደሮች ይልቅ በገበያው ሰንሰለት ላይ ያሉ ደላሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ቲማቲም በባህሪው ቶሎ የሚበላሽ በመሆኑ ደላሎቹ ማሳው ድረስ መጥተው በሚያቀርቡላቸው የወረደ ሂሳብ ሳይደራደሩ የሚሸጡበት ሁኔታ መኖሩን አይቻለሁ» ትላለች፡፡
በሌላ በኩልም አካባቢው አብዛኛው ፍራፍሬ አምራች እንደመሆኑ ቲማቲምን እንደተደራቢ ሰብል በማየት ለምርቱ ጥራትና ብዛት እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጡ ትገልፃለች፡፡ እንዲሁም ምንም እንኳ የአካባቢው ስነምህዳርና የአየር ፀባይ ምቹ ቢሆንም መሬቱ በተባይ የሚጠቃ በመሆኑ ምርትና ምርታማነቱን ይዞት መቆየቱን በጥናቷ ለማረጋገጥ ችላለች፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል በምን መልኩና እንዴት አርሶአደሮቹን ሊደግፍ እንደሚገባ ምክረሃሳቧን በመጠቆም ያከናወነችው ይኸው የመመረቂያ ሥራ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ ለሽልማት አሳጭቷል፡፡
የሰላማዊት የወደፊት ህልሟ በተለይም የገበሬ ልጅ እንደመሆንዋ የወላጆቿን የግብርና ሥራ ማዘመን ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የምታመርታቸው ምርቶች በገበያው ላይ ተወዳዳሪ ይሆኑ ዘንድ አዳዲስ አሰራሮችን ለመከተል አቅዳለች፡፡ በዚህም የእርሷንም ሆነ የቤተሰቦቿን ህይወት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ቆርጣ ተነስታለች፡፡ ለጋነቷም ሆነ ሴትነቷ ሳይበግራትም በአገሯ ኢኮኖሚ ላይ የበኩሏን ድርሻ ለመወጣትም ፅናትን ሰንቃ ይዛለች፡፡
ልክ እንደዚህ ሁለት ወጣቶች ሁሉ ሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች ህልማቸውን ለማሳካት መትጋትና በአገራቸው ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ የየራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብርታትና ፅናትን መላበስ ይጠይቃል፡፡በተለይም የውስጣቸውን ጥሪና መክሊታቸውን በማዳመጥ መንግሥት ለወጣቶች ያመቻቸውን ልዩ ዕድል ሳያቅማሙ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ወላጆች፣ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችም ቢሆኑ የነገ አገር ተረካቢ ትውልዶች መሆናቸውን ተገንዝበው የወጣቶችን ራዕይ ከግብ ለማድረስ ከጎናቸው መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።