የሌስተር ሲቲዎች «ሃንጎቨር» Featured

13 Feb 2017

አንዳንዶች «የሻምፒዮኖች ሃንጎቨር» እያሉ ይጠሩታል የሌስተር ሲቲዎችን ዓይነት ክስተት። ምክንያቱ ደግሞ በአንድ የጨዋታ ዓመት ዋንጫ አንስተው፤ አሸናፊነታቸውን በቅጡ ሳያጣጥሙ በቀጣዩ ዓመት ከወራጅ ቀጣና አፋፍ ላይ መገኘታቸው ነው። በ2015/16ቱ የውድድር ዓመት የቀበሮዎቹ ግስጋሴ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አዲስ ክስተት ለመሆኑ አመልካች ነበር። በዚያው ብቃታቸው ይቀጥላሉ የሚል ቅድመ ግምትም በያዝነው የፕሪምየር ሊግ ዓመት ከብዙዎች ዘንድ ሲሰነዘር ቆይቷል።

ክለቡ ዋንጫውን ከማንሳቱ ባሻገርም በአንድ ዓመት ብቻ በርካታ ደጋፊዎችን ከዓለም ዙሪያ ማሰባሰብ ችሎ ነበር። በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 38 የሊግ ጨዋታዎች 3ቱን ብቻ በመሸነፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ችሏል። ይህም የዓመቱ ምርጥ ክለብ አሰኝቶታል። ቀበሮዎቹ ባለፈው ዓመት ባልተጠበቀ መልኩ ከዋንጫው እንደደረሱ ሁሉ በዚህ የውድድር ዓመትም ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ወራጅ ቀጣናው እየተቃረቡ ናቸው። ትናንት በ25ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከስዋንሲ ሲቲ ጋር ከመገናኘቱ በፊት በ21 ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል። 

ለዚህ ድራማዊ ለሆነ የክለቡ ውድቀትም በአንዳንዶች ዘንድ የተለያዩ ግምቶች ይሰጣሉ። ከእነዚህም መካከል ሚዛን የሚደፋው ባለፈው ዓመት ደካማ አቋም ሲያሳዩ የቆዩት ክለቦች ራሳቸውን ማጠናከራቸው ነው። በተለይ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ የሚባሉት ቡድኖች በአሰልጣኝና በሌሎች ምክንያቶች የወረደ አቋም ማሳየታቸው፤ ክለቡ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ስኬታማ እንዲሆን አግዞታል። ዘንድሮ ክለቦቹ ቀድሞ የሚታወቁበትን አቋም መመለሳቸውም ቀበሮዎቹን ባለፈው ዓመት በነበሩበት ልክ እንዳይንቀ ሳቀሱ አድርጓቸዋል።

ሌላው በተለይ በክለቡ ውስጥ ቁልፍ ይባሉ የነበሩ ተጫዋቾች አቅም መቀዛቀዝና በአጥቂና ተከላካይ ክፍል ያለው መዳከም ነው። በተለይ የክለቡ የጀርባ አጥንት እና ያለፈው ዓመት ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን የተጎናጸፈው ጂሚ ቫርዲ ከብቃቱ በግማሽ አንሶ የተገኘበት ነበር። አምና 24ግቦችን በማስቆጠር በቀዳሚው ስፍራ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት 5ግቦችን ብቻ ከመረብ ማገናኘት ችሏል። ከቫርዲ ጋር ባላቸው ጥምረት ክለቡን ከውጤት እንዲደርስ ምክንያት ከሚባሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሪያድ ማህሬዝም በተመሳሳይ ካለፈው ዓመት የወረደ አቋም ያሳየበት ዓመት ሆኗል። የመሀል ክፍሉን ሚዛን በመጠበቅ እና የመልሶ ማጥቃት ሂደቱን በማቀላጠፍ የሚታወቀው ኒጎሎ ካንቴ ቼልሲን መቀላቀሉም ሌላኛው ለክለቡ የውጤት ማጣት አመክንዮነት በስፖርት ተንታኞች ሲነሳ ይደመጣል። ካንቴ አሁን ላይ ቼልሲ ሊጉን በሰፊ የነጥብ ልዩነት እንዲመራ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።   

የሌስተር ሲቲዎች ፊታውራሪ ክላውዲዎ ራኔሪም በዚሁ የክለቡ የውጤት ቀውስ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ሊገቡ ችለዋል። አሰልጣኙ ክለቡን ሳይጠበቅ የዋንጫ ባለቤት በማድረጋቸው ፊፋ በየዓመቱ የሚያበረክተውን የምርጥ አሰልጣኝነት ሽልማት ለግላቸው ወስደዋል። አሰልጣኙ በመልበሻ ክፍል ውስጥ ያለው የተጫዋቾቹ ስሜት እንደቀድሞው ነው ቢሉም የውጤት እጦት ግን እየተፈታተናቸው ነው። ይህም አሰልጣኙ በክለቡ የሚኖራቸውን ቆይታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ይሆናል።    

ብርሃን ፈይሳ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።