ቼስ ስፖርትን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማስፋፋት Featured

17 Feb 2017

ኢትዮጵያ እና የቼስ ስፖርት የረጅም ዓመት ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ቼስ ስፖርት ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት «ሰንጠረዥ» በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይዘወተር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የቼስ ስፖርት አካላዊ በሆነው እንቅስቃሴና ውድድር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚሰጥ ሁለንተናዊ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑም  ስፖርቱን  በሚያዘወትሩ ሰዎች ተወዳጅ አድርጎታል፡፡

  ኢትዮጵያ በላልይበላ እና የአክሱም ሀውልት ቅርሶቿ እንደምትታወቀው ሁሉ በቼስ ስፖርትም ቀዳሚ ሀገር መሆኗን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የቼስ ስፖርት አጀማመርን በተመለከተ በእንግሊዝ ሀገር በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ባትጠቀስም ሪቻርድ ፓንክረስት በጻፉት የቼስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የቼስ ስፖርት ቀድሞ በተጀመረባቸውና ጨዋታው ከሚዘወተርባቸው ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን  አመልክተዋል፡፡ ሌሎችም የጥናት ውጤቶች ይህንኑ ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡

   ስፖርቱ በሀገሪቱ ረጅም ታሪክ ያለውን ያህል በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉን በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይነገራል፡፡ ትኩረት አጥቶ የነበረውና በደካማ ደረጃ እንደሆነ የተነገረለትን የቼስ ስፖርት ጨዋታ ወደተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የለውጥ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል፡፡ በሀገሪቷ የቼስ ስፖርት ጨዋታ እንዲስፋፋና እንዲያድግ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለማሳደግ የአሰልጣኝነት እና የዳኝነት ስልጠናዎችን በመስጠት ሙያዊ ብቃት ላይ የመጀመሪያውን ትኩረት አድርጓል፡፡

   ፌዴሬሽኑ ከክልሎችና ከአዲስ አበባ ከተማ ለተውጣጡ ከ20 በላይ ለሆኑ ባለሙያዎች የዳኝነት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ የስፖርት ሳይንስ መምህራን ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ስልጠናው ምሁራንን ማዕከል ያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

      በዚሁ መሠረትም ከ30 የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 54 የስፖርት ሳይንስ መምህራን አዲስ አበባ በሚገኘው ፌዴራል ቴክኒክ እና ሙያ ኢኒስቲትዩት ከየካቲት 6 ቀን 2009ዓ.ም ጀምሮ ስልጠናውን  እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ከሚገኙት ሠልጣኞች መካከልም  ሴት መምህራን እንደሚገኙበት ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

       ስልጠናውን ከሚሰጡት መካከል ዋና አሰልጣኝ የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ቼስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አባልና በግላቸው በቼስ ስፖርት ላይ በርካታ ምርምሮችን እያደረጉ የሚገኙት ኢንስትራክተር ቶፊቅ በርሄ እንዳስረዱት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በቼስ ስፖርት ውጤታማ አልነበረችም፣አሁን ግን ስፖርቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ጠንካራ ሥራ አስፈጻሚዎችና ጠንካራ ኦፊሰር መመደቡ ስፖርቱ ትኩረት ማግኘቱን ያሳያል፡፡ የቼስ ስፖርት እንዲዘወተር እና በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚደረጉት ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡«የቼስ ስፖርት ወደባለቤቶቹ ምሁራን ተመልሷል» ኢንስትራክተር ቶፊቅ የስፖርት ምሁራን የቼስ ስፖርትን መጀመራቸው ከስፖርታዊ ውድድሩ በተጓዳኝ ሀገሪቱ በርካታ ተመራማሪዎችን የማፍራት አቅም እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በቼስ ስፖርት ከዓለም 125ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ እንደነበር የተናገሩት ኢንስትራክተር ቶፊቅ በአሁኑ ጊዜ ግን በተሰጠው ትኩረት የተሻለ ዕድገት እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

   «ቼስ ስፖርት ከወድድር ባለፈ ለሀገሪቱ ዕድገት ቁልፍ  በሆኑት ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከተዘወተረ  በርካታ ተመራማሪዎችን የማፍራት አቅም ይፈጥር ላታል፡፡» ያሉት አሰልጣኙ ቼስ ስፖርትን በትምህርት ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠቀም ቀዳሚ የሆነችው አርመኒያ አስር ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ከ22ሺህ በላይ ተመራማሪዎችን ማፍራት መቻሏን ለአብነት አንስተዋል፡፡

       ኢንስትራክተር ቶፊቅ አክለውም ቼስ ስፖርትን ለመጫወት ሁሉንም የሚያሳትፍ ገደብ የሌለው መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ ደግሞ ስፖርቱን ለማስፋፋት ማነቆ የሆነውን የስፖርቱን ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራዎች እንዲጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ «ይህንን ስልጠና ለመስጠት ሁለት ወር ተዘጋጅቼያለሁ፡፡ ሰልጣኞቹ የስፖርት ሳይንስ ምሁራን መሆናቸው ሃሳቡን በቀላሉ እንዲረዱት አስችሏቸዋል፡፡ በስልጠናው ላይ ከመጀመሪያ ድግሪ እስከ ፒኤችዲ የትምህርት ደረጃ ያላቸው መምህራን ተሳትፈዋል፡፡» በማለት አሰልጣኙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

    ኢትዮጵያ በቅርቡ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድርን በጅማ ከተማ ለማካሄድ ኃላፊነት መውሰዷ ለስፖርቱ የሰጠችውን ትኩረት እንደሚያሳይ የጠቆሙት አሰልጣኙ፣ ለሀገሪቱ የልማት ህዳሴ እውን መሆን ከፍተኛውን ድርሻ የሚወጡት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ቼስ ስፖርትን በማስፋፋትም በኩል ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ስልጠናውን በመውሰድ ላይ የሚገኙት ምሁራን ወደየመጡበት ትምህርት ተቋማት ሲመለሱ ክለቦችን ከማቋቋም ጀምሮ ቼስን ለማስፋፋት ጥረት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

    «ቼስ ተጫዋች በባህሪው ለሚያጋጥሙት ችግሮች ፈጣን መፍትሔ የመስጠት አቅም ያለው ነው፡፡ ቼስ ከአካል ንክኪ ይልቅ በአዕምሮ ንክኪ ላይ የተመሠረተ በሳል አስተሳሰብን የሚጠይቅ ስፖርት ነው» ያሉት ኢንስትራክተር ቶፊቅ ምሁራኑ ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው ሲመለሱ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ችግር ፈቺ ትውልድ በማፍራት በኩል ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

       የስልጠናው አስተባባሪና ሰልጣኝ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ሥራ አስፈጻሚ አባልና ዋና ፀሐፊ አቶ መስፍን ወንድወሰን በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል «የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር» በሚል ስያሜ ሲጠራ እንደነበርና ከዚህ ዓመት ጀምሮ ደግሞ «የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር» ተብሎ እንደሚጠራ ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚካሄዱ  ስፖርቶችን በማስፋፋት ሥራዎች ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡ ማህበሩ ሥልጠናዎችንም ይሰጣል፡፡

  «በየትምህርት ተቋማቱ ምርምሮችን መሥራት እና በተለይ አዳዲስ ስፖርቶችን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የማህበሩ ዓላማ እና ተግባር ነው፡፡» ያሉት ዋና ፀሐፊው አቶ መስፍን ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሚሳተፉበት ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ደግሞ አዳዲስ የስፖርት ዓይነቶች የሚተዋወቁበት ዕድል እየተፈጠረ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

   ዋና ጸሐፊው እንዳሉት ቼስ ስፖርት በትምህርት ተቋማት ሳይዘወተር የቆየ ስፖርት ነው፡፡ አሁን እየተሰጠ ባለው ስልጠና ችግሩ እንደሚቀረፍ እምነት ተይዟል፡፡ ሰልጣኞቹ ከስልጠና በኋላ ወደየመጡበት ትምህርት ተቋማት ሲመለሱ ተተኪ ተጫዋቾችን ከማፍራት ባሻገር የታዳጊ ፕሮጀክት ጣቢያዎችን በመደገፍ ቼስን ለማስፋፋት በርትተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

       በስልጠናው የተሳተፉትን የትምህርት ተቋማት አስመልክተው አቶ መስፍን እንደገለጹልን በስልጠናው እንዲሳተፉ በደብዳቤ ለ38 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥሪ ቢደረግም ከመካከላቸው  አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች አልተሳተፉም፡፡ ማህበሩ በየዓመቱ በሚያካሂደው የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ቼስን ጨምሮ በ14 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች እንደሚካሄዱም ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ሰልጣኞቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በተግባር ማዋላቸውንም ከትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

        «ከአሁን በፊት ቼስ ተጫውቼ አላውቅም፡፡ ስልጠናውን ስወስድ ግን ቼስ አዕምሮን የማስፋት እና የማሰብ አቅምን የሚያሳድግ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡» ያሉት ደግሞ በስልጠናው ላይ አክሱም ዩኒቨርሲቲን በመወከል እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ለምለም ወልደጊዮርጊስ የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና በቀጣይ በሌሎች ስልጠናዎች ከታገዘ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

       አቶ ለምለም አክለውም በዚህ ስልጠና ላይ ለመሳተፍ በፍቃደኝነት መምጣታቸውን ገልጸው፣ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ለተቋሙ ተማሪዎች፣ ደጋፊ ሠራተኞች እና መምህራን እንደሚያስተላልፉ አመልክተዋል፡፡ በሀገር አቀፉ የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ዩኒቨርሲቲያቸው ጠንካራ የሆነ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀርብ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

        የወሎ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ መምህርቷ ቅድስት ቢያድግልኝም በሰጠችው አስተያየት ቀደም ሲል ስለ ቼስ ስፖርት እውቀቱ አልነበራትም፡፡ ከስልጠናው ብዙ እውቀት እንዳገኘችና ከዚህ በኋላ ለቼስ ስፖርት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጻለች፡፡ ስፖርቱ ለተለያየ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግራለች፡፡

     የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የስፖርቱ ባለቤት የሆኑት ምሁራን በትምህርት ተቋማቸው ውስጥ እንዲያዘወትሩት እየሰጠ ያለው ስልጠና እስከ ነገ ድረስ እንደሚቀጥል ከወጣው መርሐግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ስልጠና ባሻገር ለትምህርት ተቋማቱ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  

ታምራት አበራ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002410899
TodayToday5140
YesterdayYesterday7537
This_WeekThis_Week14570
This_MonthThis_Month100001
All_DaysAll_Days2410899

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።