«ለዋንጫው» ከቼልሲ የተሻለ ማን አለ? Featured

17 Feb 2017

የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች እና የእግር ኳስ ተንታኝ ጋሪ ኔቭል  ቼልሲ በቀጣይ ጨዋታዎች ነጥብ የሚጥልበት አጋጣሚ ቢኖርም፤ ተፎካካሪ ክለቦች ግን የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ እንደሚቸገሩ ተናገረ። በሌላ በኩል ደግሞ የቼልሲ ክለብ የመስመር ተጫዋች የሆነው ፔድሮ አሁንም ድረስ  ክለቡ ከተፎካካሪዎቹ ያለውን የስምንት ነጥብ ርቀት አስጠብቆ ለመጓዝ ሠፊ ዕድል እንዳለው ገልጿል።

ጋሪ ኔቭል ቼልሲን ለማቆም እየተጣጣሩ ያሉትን ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ቶተንሀምን ተስፋ የሚያመነምን አስተያየቱን ሲሰጥ «አሁን ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ቼልሲን ለማቆም በቀጣይ ታሪካዊ የሆነ  እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠይቅ ነው» በማለት ቀሪ ጨዋታዎችን በጥንቃቄ አሸንፎ ቼልሲ ነጥብ እንዲጥል መጠበቅ በጣም ከባድ ጉዞ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።

ሰማያዊዎቹ ተከታታይ 13 ጨዋታዎችን በማሸነፍ ሊጉን በሠፊ የነጥብ ልዩነት መምራት ችለዋል። እስከአሁን ድረስ ቼልሲን በነጥብ የቀረበው ክለብ አልተገኘም። ባሳለፍነው ሳምንት ከበርንሌ ጋር አቻ  በመውጣቱ ሁለት ነጥቦችን መጣል ችሎ ነበር። በዚህም ማንችስተር ሲቲ ተጋጣሚውን በመርታት ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት 8 ሊያደርሰው ችሏል። በቀጣይ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት 13 ጨዋታዎች ይቀራሉ። በዚህም ቼልሲ ከባድ ጨዋታዎች ያጋጥሙታል። በድል መወጣት የሚችል ከሆነ እና ያለው የነጥብ ልዩነትም አስጠብቆ የሚቆይ ከሆነ ግን ዋንጫውን የማያነሳበት ምክንያት አይኖርም።

 ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ቶተንሀምን እና ማንችስተር ዩናይትድ ቼልሲ ነጥብ ጥሎ ልዩነታቸውን ለማጥበብ የሚችሉበትን አጋጣሚ እየተጠባበቁ ቢሆንም በእጃቸው ያለውን ዕድል በተደጋጋሚ ሲያባክኑ ቆይተዋል። ለ8 ጊዜያት የፕሪሚየርሊጉን ዋንጫ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ማንሳት የቻለው ጋሪ ኔቭል ለስካይ ስፖርት በሰጠው አስተያየት « እኔ ቼልሲ ነጥብ እየጣለ ተፎካካሪዎቹ ደግሞ ልዩነቱን እያጠበቡ ይመጣሉ የሚል ግምት የለኝም። ቼልሲን ለማቆም እነዚህ ክለቦች በተከታታይ 13 እና 14 ጨዋታዎችን ማለትም የቀሩትን ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። ቼልሲ ግን 3 እና አራት ጨዋታዎችን ቢሸነፍም በተከታታይ በርካታ ጨዋታዎችን በዚህ ዓመት ሲያሸንፍ ማየት ችለናል። በእኔ ግምት ሌሎች ክለቦች በዚህ የውድድር ዓመት የሚደግሙት አይመስለኝም።

«በዘንድሮው ዓመት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ቼልሲ ተመራጭ ክለብ ነው። ነገር ግን ቁልፍ ተጫዋቾቹን ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩ ሀቅ ነው። ይህ ድሉን እንዳያጣጥም እንቅፋት ሊሆነው እንደሚችልም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ግን አጋጣሚው ሊከሰትም ላይከሰትም የሚችል ነው። በዚህ የተነሳም ሠፊ ዕድል አለው» ማለቱ የኔቭል ግምት ወደ ቼልሲ አዘንብሏል።

ሰማያዊዎቹ በያዝነው ዓመት ለሦስት ጊዜ ብቻ ነው ሽንፈት ያጋጠማቸው። ከአጠቃላይ 25 ሳምንቶች ውስጥ ደግሞ 19ኙን በድል አጠናቀዋል። በጠንካራ የተከላካይ ስብስብ የሚጠበቀው የግብ መስመራቸውም ጥቂት ጎሎችን ነው ያስተናገደው።

በተመሳሳይ ዜና ቼልሲ ያሳለፍነውን ሳምንት ጨዋታ ከበርንሌይ ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱን ተከትሎ፤ የአቻነቷን ግብ ያስቆጠረው የመስመር ተጫዋቹ ፔድሮ «አሁንም ዋንጫውን ለመብላት እና በሠፊ የነጥብ ልዩነት ሊጉን ለመምራት ዕድል አለን» በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። ቼልሲ ከበርንሌይ ጋር ያሳለፍነው ዕሁድ ብዙም የማያስደስት የጨዋታ ጊዜ ነው። የላንክሻዬሩ ክለብ በርንሌይ የቼልሲን የግብ ክልል ሲፈትሽ አምሽቷል። ዕለቱ ብርዳማና ዝናባማ ስለነበር ለቼልሲ ተጫዋቾች ጨዋታውን ከባድ አድርጎባቸው ነበር።

ያሳለፍነው ሰኞ ዕለት ማንችስተር ሲቲ ቦርንማውዝን 2ለ0 ካሸነፈ በኋላ ከቼልሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ8 አውርዶታል። ሆኖም ግን ፔድሮ አሁንም ከምንም ጊዜ በተሻለ ድሉ የኛ ነው የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል። «በተቻለን አቅም በጣም ጥቂት ነጥቦችን ብቻ ነው መጣል የሚኖርብን። አሁንም ዕድሉ አለን። ነገር ግን በእንግሊዝ ሊግ ቀድሞ ዋንጫውን ይሄኛው ክለብ ይበላዋል ብሎ ለመገመት በጣም ከባድ ነው። እንደሚታወቀው በጣም ከባድ ተፎካካሪዎች ናቸው ያሉን። ማንችስተር ሲቲ፣ቶተንሀም እና ሊቨርፑል ጠንካራ ክለቦች ናቸው። እኛም ግን ከነርሱ በተሻለ ጥንካሬ ላይ እንገኛለን» ሲል ተናግሯል።

 ፔድሮ በዘንድሮው ዓመት ለቼልሲ 9 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ባሳለፍነው ዓመት ተጫዋቾች 8 ግቦችን ብቻ ነበር ማስቆጠር የቻለው። በአጠቃላይ ከባርሴሎና ወደ ቼልሲ ከመጣ ጀምሮ 50 ግቦችን በስሙ ማስመዝገብ ችሏል። እንደ ፔድሮ እምነት ለቼልሲ የዘንድሮው ዘመን ጥሩ መሆን አንቶኒዮ ኮንቴ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። እርሱም በአሰልጣኙ ስር መሆኑ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ እንደረዳው ይናገራል። «በጨዋታዎች ላይ ዕድል አግኝቻለሁ። ሁሉም የቡድኑ አባላት ጥሩ ብቃት ላይ ይገኛሉ። ባገኘሁት አጋጣሚ ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረት አደርጋለሁ። ይሄ ደግሞ ለእኔም ሆነ ለቡድኔ መልካም ነው። በራሴና በቡድኑ የዘንድሮ አቋም ምቾት ተሰምቶኛል። ዋንጫውንም እናነሳለን» በማለት በሙሉ የራስ መተማመን ተናግሯል።

አሁን ቼልሲ ሊጉን በ60 ነጥብ ሲመራ ተከታዩ ማንችስተር ሲቲ 52 ነጥብ አለው። ቶተንሀም እና አርሰናል በእኩል 50 ነጥብ በግብ ተበላልጠው 3ተኛ እና 4ተኛ ናቸው። ነገ ቼልሲ  ከስዋንሴ ሲቲ ጋር ሲገናኝ ፤ ቶተናም ከስቶክ ሲቲ ዕሁድ ዕለት ይጫወታሉ። ማንችስተር ሲቲ እና ማንችስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት ጨዋታ ቀኑ በውል ባይታወቅም  ለሌላ ጊዜ ተዘዋውሯል። በተመሳሳይ አርሰናል ከሳውዝ ሀምፕተን የሚያደርጉት ጨዋታም ተዘዋውሯል።

ዳግም ከበደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።