«ፕሪሚየር ሊጉ የሚጀመርበት ቀን ካልተራዘመ ለእኛ በጣም አደጋ ነው»- አቶ በለጠ ዘውዴ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ Featured

01 Aug 2017

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የማህበራት ማደራጃና እውቅና ዳይሬክቶሬት ከተማ አቀፍ እውቅና ከሰጣቸው የስፖርት ማህበራት መካከል የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አንዱ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የተሰጠውን እውቅና መሰረት አድርጎ በከተማዋ ውስጥ እግር ኳስ ስፖርት ተመራጭና ተዘውታሪ እንዲሆን የማድረግና ታዳጊ ስፖርተኞችን የማፍራትና የማብቃት ሃላፊነት ተስጥቶታል።

   በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ከተማዋን የሚወክሉ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪዎች የማፍራትና ለክለቦቹ ሙያዊም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግም ከተጣለበት ሃላፊነቶች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ለዚህ ሃላፊነቱ ተግባራዊነትም፤በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ክለቦች መካከል በየዓመቱ የከፍተኛና የአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶችና የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮች ያዘጋጃል። ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር በመተባበር በዓመት አንድ ጊዜ የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫን ያስተናግዳል።

  አዲስ ዘመንም የፌዴሬሽኑን የዘንድሮ ዓመት ውድድሮች አተገባበር በሚመለከት ከስራ አስፈፀሚና የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢው ከአቶ በለጠ ዘውዴ ጋር ቆይታ አድርጓል።

   አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ የእግር ኳስ ስፖርት በከተማዋ ተመራጭና ተዘውታሪ እንዲሆን የክለቦችን ተሳታፊነት በማሳዳግ ረገድ ሃላፊነቱን እንዴት ተወጥቷል?

    በአቶ በለጠ፡- ፌዴሬሽኑ በከተማዋ ውስጥ እግር ኳስ ስፖርት ተመራጭና ተዘውታሪ እንዲሆን ለማድረግና ታዳጊ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለማብቃት ለተጫዋቾች የውድድር ዕድል ለመፍጠር በየዓመቱ የውስጥ ውድድር ያደርጋል። በዚህም በተለይ ክፍለ ከተሞች በስፖርቱ እንዲሳተፉ በማድረግ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ውጤታማ ተግባርም መፈፀም ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ከአንድ ክፍለ ከተማ ማለትም ከኮልፌ ክፍለ ከተማ በስተቀር አብዛኞቹ ብሄራዊ ሊግና በከፍተኛ ሊግ በወንድም በሴትም እየተካፈሉ ናቸው። ከዚህ በተጓዳኝ በርካታ የግል ክለቦች ወደ ውድድሩ እንዲመጡ ማድረግ ችለናል።

   አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ ቡድኖችን በመደገፍ ተተኪዎችን በማፍራት ረገድ ውስንነት እንዳለበት በዘርፉ ባለሙያዎችና ክለቦች ሲወቀስ ይሰማል፣ ይህን ምን ያህል ይስማሙበታል?

  አቶ በለጠ፡- ወቀሳው ትክክል ነው። ፌዴሬሽኑ ክለቦችን በተለያዩ መንገዶች የመደገፍ ሃላፊነት አለበት። ይሁንና በዚህ ረገድ የሰራቸው ሥራዎች ብዙም አይደሉም ለማለት እደፍራለሁ። ለክለቦቹ ሙያዊም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግም ረገድ ፌዴሬሽኑ ደግፏል ብዬ አላስብም። ከተማዋን የሚወክሉ ክለቦች ወደ ክልል ሻምፒዮና ሲሄዱ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ለሚወጡት መጠነኛ ድጋፍ በማድረግ ከመሸኘት በስተቀር በድጋፍ ደረጃ የሰራነው የለም። ይህም የሆነበት ምክንያት ፌዴሬሽኑ ክለቦች በበጀት እንዲጠናከሩ የማድረግ ስራ በብዛት ያለመስራቱም ጭምር ነው። በየዓመቱ የምናካሂዳቸውን ውድድሮች ስፖንሰር በመፈለግ ክለቦቹ የሚጠናከሩበትን አሰራር በመቅረፅ ረገድ ስራዎች አልተሰራም። ይህን ባለመስራታችንም በባለፈው ዓመት የተቋቋሙ ክለቦች ዘንድሮ ሲፈርሱ እናያለን።

     እርግጥም ተተኪዎችን የማፍራት ችግር አለ። ይህም ምንም የማይካድ ነው። ባለፈው ዓመት 16 እና 12 ቡድን ተመዝግቦ ዘንድሮ ወደ ስምንትና ሰባት ከወረደ ተተኪዎች የማፍራት ችግር እንዳለብን የሚያሳይ ነው። ተተኪዎች የምናመጣበት መንገድ በራሱ ትክክል አይደለም። ታዳጊና ወጣቶች በስፖንሰር እንዲደገፉ ማድረግ የእኛ ስራ ነው። ታዳጊና ወጣቶች መጨረሻው ዓመት ላይ፤ቢያንስ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡትን ወይ በገንዝብ አሊያም በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ሲሆን ታዳጊና ወጣቶች ይመጣሉ።

   ሲፈርሱ ለምን ፈረሱ ብለን የምንገመግምበት ሂደት መኖር አለበት። በደጋፊ ማነስ ነው ወይንስ፤ በራሳችሁ ነው ብለን  የክለቦችን አመራር የማናገር ባህል የለንም። አንድ ቡድን ፈረሰ ፈረሰ ነው። የመመዝገቢያ ገንዘብ ከሆነ ችግሩ ይህን የምናግዝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።

   አዲስ ዘመን፡- በውድድሮቹ ላይ የሚስተዋለው የእድሜው ጉዳይ ተተኪዎቹን የማፍራት ሂደቱ ላይ የፈጠረው ጫና ይኖር ይሆን?

   አቶ በለጠ፡- በእርግጥም አንዳንድ አሰልጣኞች ተተኪን ለማፍራት ሳይሆን ትኩረት የሚያደርጉት ለውጤትና ውጤት ብቻ ነው። እኛ እየታዘብን ያለነውም ይህን ነው። በተተኪዎች ላይ ሰርተው ቢመጡ ውጤታማ እንደሚሆኑ አያውቁትም። አያምኑምም። ብዙ ጊዜ ከክለቦቹ የመገናኘት አጋጣሚው አለኝ። ታዳጊና ወጣት ይዘው የሚመጡ አሰልጣኞች ምንም ጥቅም አያገኙም።

  ይህ ምን ማለት ነው ለምሳሌ፤ባለፈው ዓመት አንድ ታዳጊና ወጣት ቡድን ይዞ የመጣ አሰልጣኝ ወይ በኒያላ በመብራት ሃይል አሊያም በመድን ወይም ሌላ ክለብ አምስትና ስድስት ተጫዋቾች ይወሰድበታል ። ተጫዋቾቹ ሲሄዱ ግን አሰልጣኙም ሆነ ክለቡ የሚያገኙት ጥቅም የለም።

   ክለቡ አሊያም አሰልጣኙ ለዓመታት የለፋባቸውን ተጫዋቾች ሌሎች ሲወስዱበት ቢያንስ ድጋፍ የሚያገኝበት መንገድ በመቀየስ ረገድ የተዘረጋ ነገር የለም። ይህ ችግርም ታዳጊ ቡድኖች እንዳይመጡና አሰልጣኞችም በታዳጊዎች ላይ መስራትን እንዳይመርጡና ተስፋ እንዲቆርጡ እያደረገ ነው። በመሆኑም የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከእነዚህ ክለቦች ጋር በመሆን ክለቦቹ የሚያፈራቸው ልጆች ወደ ትልልቅ ክለቦች ሲሄዱ ጥቅም የሚያገኙበትን መስመር መዘርጋት አለበት። ክክለቦቹ ጋር በመነጋገር አንድ ደንብና መመሪያና ማዘጋጀት የግድ ይለዋል።

  አዲስ ዘመን፡- ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ የከፍተኛና የአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶችና የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮች ያዘጋጃል፣የዘንድሮው ውድድር እንዴት ይቃኛል?

  አቶ በለጠ፡- ፌዴሬሽኑ በከተማዋ የሚስተዋለውን የተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾች ችግር ለመቅረፍ እና ለተጫዋቾች የውድድር ዕድል ለመፍጠር በየዓመቱ የውስጥ ውድድር ያካሂዳል። ምንም እንኳን የዘንድሮው ውድድር ከባለፉት ዓመት በተሳታፊዎች ቁጥሩ ቢቀንስም፤ክለቦችም በእጅጉ ተዘጋጅተው የተወዳደሩበት፤ አስደሳችና እስከመጨረሻዋ ቀን ድረስ በነጥብ ተቀራራቢ ክለቦች የተሳተፉበት ነው። ውጤታቸው የተቀራረበ በመሆኑ በጎል ለመለየት እስገመገደድ ደርሰናል። እኛም ውድድሮቹ በህግና ደንብ እንዲመሩ ከማድረግ በስነምግባር የታነፀ ስፖርተኛ ከማፍራት አንፃር እንደ ውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ብዙ ርቀቶች ሄደናል። ውድድሩንም በቅርበት ተከታትለነዋል።

  ይህን ስንል ግን ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። በዘንድሮ ዓመት የገጠመን ፈተና በጣም ከባድ ነው። ከአቅምና ውጤት ጋር ተያይዞ ያቋረጡ ቡድኖች ገጥመውናል። በዓመት አንድ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር የምናወጣቸው ደንቦች በደንብ ግንዛቤ ፈጥረን በየጊዜው ለክለቦቻችን ማሳወቁ ላይ እጥረቶች ነበሩብን። ይህ ባለመሆኑ የገጠሙን ችግሮችም አሉ።

  የዘንድሮው ውድድር ከባለፉት ዓመት በተሳታፊዎች ቁጥሩ ቀንሷል። ባለፈው ዓመት ወጣት 16 ታዳጊ 12 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን ዘንድሮ 8 ወጣት 7 ታዳጊ ብቻ ነው። የክለቦች ተሳትፎ የቀነሰበት ትልቅ ምክንያት ፌዴሬሽኑ የምዝገባ ገንዘብ ማሻሻሉና መጨመሩ ነው። ይህም  ክለቦች የመመዝገቢያ ክፍያ እጥረት እንዲያጋጥማቸውና ከውድድር ውጪ እንዲሆኑ የተሳታፊዎቹ ቁጥር እንዲቀንስ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

  ከዚህ በተጓዳኝ የእድሜ ጉዳይ አለ። እኛ እድሜ የምናጣራው እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በምርመራ አይደለም። በእይታ ነው። ይህ እንደመሆኑ ልትሳሳት ትችላለህ። በጣም እድሜያቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን ይዘው በመቅረባቸው ምክንያት በርካታ ክለቦች ብዙ ልጆች ይወድቁባቸዋል። አሰልጣኞች ቀድመው ልጆችን አዘጋጀተው የመምጣት ነገር የለም። ይህ በቀጣይ አንድ መፍትሄ የሚያሻው ጉዳይ ነው።

  አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮው ውድድር ለክለቦች ከፍተኛ ራስ ምታት ከሆኑ ችግሮች ቀዳሚው የሆነውን የሜዳ ችግር እንዴት ይገልፁታል?

   አቶ በለጠ፡- ዘንድሮ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም መዘጋት ጨዋታዎችን በጃን ሜዳ እንድናካሂድና ከባድ ፈተና እንዲገጥመን ምክንያት ሆኗል። ጃንሜዳ ለተጫዋቾች ምቹ አይደለም። ለጉዳት የሚያጋልጥ ነው። ሜዳው በተለይ ለሴቶች እጅግ ፈተና ነው። ልብስ መቀየሪያ ቦታ እንኳን ማግኘት አይችሉም። ሴቶች የሚቀይሩበት ቦታ እያጡ ሲቸገሩ ይታያል። ሰርቪስ ያለው ምናልባት እዛው ውስጥ ሊቀይር ይችላል። ይህን ስታይ በእጀጉ ታዝናለህ።

   በሜዳዎቻችን ለውድድር አመቺ ያለመሆን ምክንያት ተመልካችና ተጫዋቾቹ የማይለዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ተጫዋቾች ለቅጣት የሚዳረጉት፤ተመልካችና ተጫዋቹን መለየት ስላልተቻለ ነው። አራተኛ ዳኛና ኮሚሽነሩም፤ በተመልካች ተውጠው እያጣናቸው እንቸገራለን። ሜዳው ትልቅ ስለሆነ ለታዳጊዎች አይመችም። ለታዳጊዎች የሚሆን ሜዳ የለም።

  አዲስ ዘመን፡- የዳኞች ችግርንስ?

  አቶ በለጠ፡- የዳኞች ጉዳይ የራሱ ኮሚቴ አለው። ይሁንና እንደ ውድድርና ስነ ስርዓት ጥራት ያለው ዳኛ እንዲመደብልን እንፈልጋለን። ውድድራችን በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲያልቁ እንፈልጋለን። ፌዴሬሽኑ በርካታ ዳኞችን እያወጣ ነው። የዳኞች ችግር የለበትም። ይሁንና አንዳንድ ዳኞች ቦታ ይመርጣሉ። አበበ ቢቂላ ማጫወትና ጃን ሜዳ ማጫወት ልዩነት አለው። አብዛኞቹ ዳኞቻችን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎች ይያዛሉ። ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅድሚያ የሚሉት አለ።

  የዳኞች ክፍያ ሌላኛውና ትልቁ ችግር ነው። ዳኞች በሚፈለገው መልኩ መጥተው እንዳያጫውቱ የሚያደርገው የክፍያው ሁኔታ ነው። ክፍያው የተሻለ በመሆኑ የግል ውድድር ማወዳደር ይመርጣሉ። ዳኞቻችን የውጭ ውድድሮች እያወዳደሩ ማለትም ባይሆን ለራስ ቅድሚያ ቢሰጡ የተሻለ ነው። ዳኞችን በማብቃት ረገድ፤ተከታታይ ስልጠና የመስጠት ችግርም አለብን። ባለፈው ዓመት አንድ ድርጅት መቶ ዳኞችን ለማሰልጠን ጥያቄ ቢያቀርብም ተፈፃሚ አልሆነም።

   ዳኞች ቢመደቡም እንኳን እንደ ጃንሜዳ በመሳሰሉ ቦታዎች የዳኞች የልብስ መቀየሪያና ማስቀመጫ የለም። ከፍለው ካልሆነ ሻወር የሚወስዱበት ቦታ እንኳን የለም። እንደ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አይደለም። ትጥቅና ንብረታቸውን የሚያስቀምጡት ሜዳ ላይ ነው። ይወሰድባቸዋል። ይህ በራሱ ትልቅ ችግር ነው። ውድድሩን ያማረና የደመቀ ለማድረግ መሰል ችግሮች ቅድሚያ ማስተካከል  ያስፈልጋል። ለዚህም ከወጣቶችና ስፖርት እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ መነጋገር የግድ ይላል።

  አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮም ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች የሚያፈሩ ቡድኖች እምብዛም አልተመለከትንም፤ ለሴት ቡድኖች እጥረት መንስኤና መፍትሄ የሚሉት ምን ይሆን?

  አቶ በለጠ፡- ፌዴሬሽኑ የሚያደርገው ተጨማሪ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በሴቶች ደረጃ ክለብ አቋቁሞ የማምጣት ክፍተኛ ችግር አለ። የግል ክለቦችና አሰልጣኞች በራሳቸው በየሰፈሩ የያዛቸው ካልሆኑ በስተቀር ክፍለ ከተሞች ያላቸው ተሳትፎ በጣም ደካማ ነው። ክለብ ያላቸው ክፍለ ከተሞች በጣም አነስተኛ ናቸው።

  ምንም እንኳን የዘንድሮው ውድድር ተሳታፊዎች ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ምንም ልዩነት ባያሳይም፤ ውጤታማነቱም ፉክክሩም በጣም አነስተኛ ነው። የዘንድሮው ውድድር የተጠናቀቀው በአካዳሚና በቂርቆስ የበላይነት ነው። ቀሪዎቹ ስድስት ቡድኖች የትራንስፖርት እንኳን የላቸውም። ትጥቅ አሟልተው አይመጡም። ምግብ አያገኙም። ከውሃ አንፃር እንኳን የሚያገኙት አልነበረም።

  ለአብነት በዚህ ዓመት ጉለሌ፤ አራዳ፣ የካ፤ተሳትፈዋል። ልጆቹ ስሙን ይዘው ይሳተፉ እንጂ አንድም የተደረገላቸው ድጋፍ የለም።የመመዝገቢያ ክፍያውን የሸፈኑት እንኳን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አቃቤ ነዋይ የሆኑት ኢንጂነር ሃይለእየሱስ ፍስሃ ናቸው። ይህ ባይሆን እነዚህም ክለቦች የመወዳደር ሁኔታ አይታሰብም ነበር።

  ሴቶች ላይ በጣም መስራት አለብን። የወጣቶችና ስፖርትም በዚህ ረገድ ሊያግዘን ይገባል። የሴቶች ቡድን የሌላቸው ክፍለ ከተሞች፤ቡድን እንዲያቋቁሙ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም አስፈላጊው ህግና መመሪያ መተግበር አለበት። የማስገደዱ ነገር እንዳይኖር ደግሞ አብዛኞቹ የግል ክለቦች ናቸው። እነዚህን ክለቦች ሴት እንዲይዙ ማስገደድ ይቸግረናል። ወንዶችን ለመያዝም እየተንገዳገዱ ነው። ይሁንና የሌላቸውን ክፍለ ከተሞችን ብናስገድድ በዚህም ውጤታማ እንሆናለን ችግሩን ማስወገድ እንችላለን ብዬ እምናለሁ። ይህ ካልሆነ ለመላ ኢትዮጵያ እንኳን የምናሳትፋቸው ልጆች  እናጣለን ብዬ አስባለሁ።

   አዲስ ዘመን፡-በአገር አቀፍ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የአዲስ አበባ ከተማ ውጤት እየራቀው ነው ዘንድሮስ በውጤት ደረጃ ምን ይጠበቃል?

  አቶ በለጠ፡- በ2006 በአዋሳ የተካሄደው ሻምፒዮና የተጠናቀቀው በአዲስ አበባ የበላይነት ነው። የካ ሻምፒዮን ከሆነበት ከዚህ ውድድር ወዲህ ግን በውጤት ደረጃ ድክመቶች ታይተዋል። ላለፉት ዓመታት በሌሎች ክልሎች ተበልጠናል። ዘንድሮ ግን ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣መርካቶ አካባቢ እና ናኖ ሆርቦ ቡድኖች አዲስ አበባን በመወከል በአገር አቀፍ የክልሎች ሻምፒዮና ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪ በመሆን የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ አምናለሁ። ለዚህም በቂ ዝግጅት አድርገናል።

  አዲስ ዘመን፡- የፌዴሬሽኑ ትኩረት ለክልል ክለቦች ሻምፒዮን ከተማዋን የሚወክላት ክለብ ማፍራት ላይ ብቻ ነው የሚባለውስ?

  አቶ በለጠ፡- ይህን ካነሳን በጣም ከባድ ነው። የእኛ የመጨረሻ ግባቸው ይመስለኛል። ግን አይደለም። ብሄራዊ ሊግ ላይ የሚገኙ ክለቦችን እንኳን ሰብስበን አናውቅም። ለአብነት ዘንድሮ የካ ከፍተኛ ሊግ ገብቷል። የካ ከፍተኛ ሊግ መግባት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ይመለከተዋል። ችግራቸውንም ይሁን ሌሎች ጉዳዮች አዋይተናቸው አናውቅም። ይህ ትልቅ ክፍተት ነው።

  ይሁንና ክለቦች ፕሪሚየር ሊግ ሲገቡ የፌዴሬሽኑ ተሳትፎ ውስን ይሆናል። በክለቡ ቦርድ ውስጥ እንኳን ውክልና ሊኖረው ይገባል። የእኛ መብትና ባለቤትነት ምንድነው ብለን እንኳን መጠየቅ አልቻልንም።ይህ ሊስተካከል ይገባል።

  እኛ የምንሰራው ክ/ከተማዋን የሚወክል ክለብ ለፕሪሚየር ሊጉም ሆነ በሌሎች መድረኮች ለማበርከት ነው። ትኩረታቸው ለክልል ክለቦች ሻምፒዮና ለመሳተፍ ብቻ ነው የሚባለው ሃቅ ነው። ዓመታዊ ስራችንን እንገምግም ብለን ብንቀመጥ የሚበዛው የውድድሩ ነው። ፌዴሬሽኑ ዘንድሮ 77 ቡድኖች አወዳደረ። አራትና አምስት ክለቦች በክክል ክለቦች ሻምፒዮና ላከ። ይህ አይደለም ግባችን። ግቡ ሊሆን የሚገባው እነዚህን የሚተካ ሌላ ማምጣት ላይ ነው። የእኛ የመጨረሻ እሳቤ ውድድር ጨረስን ላክንም በሚቀጥለው ዓመት የገባው ይገባል። የወደቀው መልሶ ይወዳደራል። ይህ መሆን የለበትም።  ከክልል ክለቦች ሻምፒዮናውን ተሻግረው ወደ ሊጉ መግባት  የቻሉ ክለቦችን በሙያም ሆነ በሌሎች አስተዋፅኦዎች ተከታትሎ መደገፍ ይኖርብናል።

አዲስ ዘመን፤የዘንድሮው ሲቲ ካፕ የውድድር መርሃ ግብር ከፕሪሚየር ሊጉ ጅማሮ ጋር ይጋጫል፤ይህን አስባችሁበታል?

   አቶ በለጠ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክተሮች በኩል ስልክ ተደውሎ መስከረም 28 እና 29 የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር እንደሚካሄድና ጥቅምት አራት ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉ  እንደሚጀመር ተነግሮኛል። እኔም ለሚመለከተው አካል አሳውቄ አለሁ።

   የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ በተለምዶው የሲቲ ካፕ ውድድሩን የሚያካሂደው ከመስከረም 25  እስከ ጥቅምት15 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የፌዴሬሽኑ ገቢም በዓመት አንድ ጊዜ በሚያካሂደው በዚሁ የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ  ዋነኛ መሰረቱን ያቆመ ነው። ፌዴሬሽኑ በራሱ በጀት የሚንቀሳቀስ ነው። ከመንግስት የሚያገኘው በጀት የለም። በፊት የሚደረግለት ድጎማ አሁን ቀርቷል። ይህ ገቢ ቢቋረጥ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ቆመ ማለት ነው።ይህ ለእኛ እጅግ አደጋ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥቅምት አራት ካካሄደ እኛ መቼ ውድድር ልናካሂድ ነው? ይህ መታሰብ ያለበት ይመስለኛል።

  አዲስ ዘመን፡- ይህ ከሆነ እናንተ የውድድራችሁን መርሃ ግብር ለምን አላስተካ ከላችሁም?

   አቶ በለጠ፡- ይህን ማድረግ አይችልም። ምክንያቱ ደግሞ የአየሩ ሁኔታ ነው። እንደሚታወቀው መሰከረም የዝናብ ወቅት ነው። ሰው ከፍሎ ገብቶ ውድድር መቋረጥ የለበትም። ሜዳዎች አይደርቁም። ሳሩ የሚታጨድበት ወቅት ነው። በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዳናካሂድም እድሳት ላይ ነው።

  ከአየር በተጓዷኝ መስከረም ለፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የእረፍት ወቅታቸው ነው። ቅድመ ልምምድ የሚሰሩበት ወቅት ነው። ጥቅምት ውስጥ ማካሄዳችንም ብዙ ጠቀሜታ አለው። ክለቦችም ብዙ ተዘጋጅተው  እንዲመጡና ለሊጉ ጅማሮ የቀረበ እንደመሆኑ ራሳቸውን የሚፈትሹበት አጋጣሚ ይፈጥራል።

  አዲስ ዘመን፡- የውድድር መርሃ ግብሩን ስታዘጋጁ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ትነጋገራላችሁ? ዘንድሮ ፌዴሬሽኑ በውሳኔው ቢፀና ውድድሩ ሳይካሄድ ይቀራል ማለት ነው?

  አቶ በለጠ፡- እነርሱ ፕሮግራም ያወጣሉ። ይህ ከሆነ በኋላ እኛ በደብዳቤ ፅፈን ቀናችሁን አሸጋሽጉልን የመባባል ነው ያለው። በየዓመቱ መነጋገር አያስፈልግም። በዚህ መልኩ ሳይካሄድ የቀረበት ጊዜ የለም። እስካሁን አጋጥሞኝ አያውቅም። ባለፈው ዓመት በዛ ችግር ውስጥ ሆነን እንኳን ውድድሩን አዘጋጅተናል። ውድድር ማካሄድ ብቻም ሳይሆን ከውጭ ክለብ ለመጋበዝ ጥረት አድርገናል። በእርግጥ በ2008 ውድድር ዓመትም ውድድሩን ወደዚህ አምጥቶብን ነበር። በመነጋገርና በመወያየት ለጉዳዩ እልባት ስጥተናል።

  ሲቲ ካፕ የፌዴሬሽኑ ትልቅ ገቢ ነው። ይህን ገቢ ማግኘት ካልተቻለ ክለቦቻችን ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህን ውድድር አላካሄድንም ማለትም በቀጣይ ዓመት የሚከናወኑ ተግባራት ይቀንሳሉ ማለት ነው። በመሆኑም የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ራሱን ችሎ እንዲቆም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ማገዝ አለበት። ይህ ጉዳይ የእኛ ብቻም ሳይሆን የወጣቶችን ስፖርትም ጭምር ነው። ፌዴሬሽኑ የሚጠናከረው በዚህ ገቢ በመሆኑ ቢሮው በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የማገዝ ግዴታ አለበት።

  ፌዴሬሽኑም ውድድሩን መግፋት አለበት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በእርግጠኝነት ይገፋሉ ብዬ አስባለሁ። ሁላችንም የምንሰራው ለስፖርቱ ነው። ክልሎች ደግሞ የራሳቸውን  ገቢ ለማጠናከር እና ስፖርቱን ለማስፋፋት ገቢ ያስፈልጋቸዋል። እኛም ብቻ አይደለንም የምናካሂደው። ደቡብም ያካሂዳል። ደቡብም ሲቲ ካፕ ውድድር አለ። ቢያንስ  እስከ ጥቅምት15 ድረስ ያለውን ጊዜ ለክልሎች መተው አለበት።

  አዲስ ዘመን፡- ስፖርታዊ ውድድሮች በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆሙ ከስፖርተኞቹ ጥረት በስተጀርባ ጠንካራ የገንዘብ አቅም ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው፤ውድድሮችን የመሸጥና ስፖንሰሮችን የማፈላለግ አቅምና አቋማችሁስ?

   አቶ በለጠ፡- በዓመቱ መጀመሪያ የሚካሄደው የሲቲ ካፕ ውድድር የከተማው ዋንጫ ላይ ከምናገኘው ገቢና ከምናገኘው ስፖንሰር ውጪ በዚህ ደረጃ የምንሄድባቸው ርቀቶች የሉም። የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መስራት አለበት ብዬ የማምነውም ውድድሮችን መሸጥና ስፖንሰሮችን ማፍራት ላይ ነው። ይሁንና ፌዴሬሽኑም ክለቦችም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ለመዘርጋት የሄድንበት ርቀት የለም። ውስንነት አለበት። ይህን ችግር ለማስወገድ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የተቋቋመ ኮሚቴ አለ። የስፖንሰር ሺፕ ኮሚቴ ይሰኛል። ይህ ኮሚቴ ስራውን በአግባቡ መስራት አለበት። እኛ አለመስራታችንና የድርጅቶችን በር ለማነኳኳት ካለመሄዳችን በስተቀር፤ በርካታ ድርጅቶችም ይህን ውድድር ይፈልጋሉ። ሄደን እምቢ ያለን አካል የለም።

   ውድድሩን በመሸጥ የተሳትፎ ክፍያን እንኳን ማስቀረት ይቻላል። ቢያንስ ክፍያው ይቀንስላቸዋል። በእርግጠኝነት በርካታ ክለቦች ይመዘገባሉ። ታዳጊ ወጣቶች ማምጣትና ተተኪዎች መፍራት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመስግናለሁ።

አቶ በለጠ ፡- እኔም እመሰግናለሁ።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።