ሁለተኛው የብር ሜዳሊያ በማራቶን Featured

07 Aug 2017

አትሌት ታምራት ቶላ፤

ዓላማንና የህዝብ አደራን ተወጥቶ የወከሉትን ሃገር ባንዲራ እንዲውለበለብ ማድረግ የሚያስገኘውን እርካታ ለመግለጽ ምናልባትም አትሌት መሆንን ይጠይቃል። ምክንያቱም አትሌቶች በሚያጠልቋቸው ሜዳሊያዎች ሳይወሰን የሃገር ስምም በውድድር መድረኩ አብሮ ይነሳል።

ከአትሌቲክስ ውድድሮች ሁሉ ፈታኙና ረጅሙን ርቀት የሚሸፍነው ማራቶን ነው። 42 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ለድል ለመብቃት ደግሞ ከብቃትም በላይ ጽናት ዋነኛውን ቦታ ይይዛል። ማራቶንን በተደጋጋሚ ድል በማድረግ ታላቅነቱን ያስመሰከረው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ «ማራቶንን ስትሮጥ ውድድርህ ከሌሎች አትሌቶች ወይም ከሰዓቱ ጋር ሳይሆን ከርቀቱ ጋር ይሆናል» በሚል ይገልጸዋል። እያንዳንዷ የአትሌቱ እርምጃም የርቀቱን መጠናቀቅ ብቻም ሳይሆን ወደ ድሉ መቃረቡን ያመለክታል። በመሆኑም በማራቶን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ብቻም ሳይሆን ሮጦ መጨረስም ጀግና የሚለውን ስያሜ ያጎናጽፋል።

ኢትዮጵያ የዘመናት የአትሌቲክስ ስፖርት ተሳትፎዋ በረጅም ርቀት የተቃኘ ሆኖ እስካሁኑ ወቅት ዘልቋል። በእነዚህ ዓመታትም ፈታኙን ማራቶን የሚፈትኑ አትሌቶችን አፍርታ ለዓለም አበርክታለች። በውድድር መድረኮች ላይ የምታሳትፋቸው አትሌቶች የውድድር ድምቀት ብቻም ሳይሆኑ የድል ምልክቶች ናቸው። በዓለም ሻምፒዮና የማራቶን ድል ብቅ ጥልቅ እያለ ቢቆይም በቅርብ በተካሄዱት ሻምፒዮናዎች ላይ ግን የተሻለ ውጤት መታየት ችሏል።

እአአ በ1983 ሄልሲንኪ ባዘጋጀችው የመጀመሪያው የዓለም ሻምፒዮና የተሳተፈችው ኢትዮጵያ፤ ሜዳሊያውን አሀዱ ያለችው በማራቶን ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያዊው አትሌት ከበደ ባልቻ በአውስትራሊያዊው ሮበርት ዴ ካስቴሌ ቢቀደምም ጀርመናዊውን ዋልዴማር ሴርፒኒስኪን በማስከተል የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን ነበር ውድድሩን ያጠናቀቀው። በወቅቱ ኢትዮጵያ 1ሜዳሊያ ብቻ በማግኘትም ነበር ውድድሯን ያጠናቀቀችው። ነገር ግን ይህ ድል እአአ እስከ 2001 የኤድመንተን ሻምፒዮና ድረስ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ ቆይቷል።

ኤድመንተን ላይ የ23 ዓመቱ ወጣት አትሌት ገዛኸኝ አበራ ባልተጠበቀ መልኩ ሌሎቹን አስከትሎ በመግባቱ የወርቅ ሜዳሊያውን ለሃገሩ አስገኘ። እስካሁን በተካሄዱት የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይም ከገዛኸኝ ባነሰ እድሜ ማራቶንን ያሸነፈ አትሌት አልታየም። በወቅቱም የገዛኸኝ የማራቶን እንዲሁም የደራርቱ ቱሉ የ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎች ከሌሎቹ ጋር ተደምረው ኢትዮጵያን ከአፍሪካ 2ኛ ከዓለም ደግሞ 6ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓት ነበር። 

 በ2009ኙ የበርሊን ሻምፒዮና የበላይነቱ በኬንያዊያን አትሌቶች ቢያዝም ጸጋዬ ከበደ ግን የነሐስ ሜዳሊያውን በማጥለቅ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ችሏል። በዴጉ ሻምፒዮናም ሌላኛው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ሌላኛውን ነሐስ ሲያጠልቅ፤ በቀጣዩ የሞስኮ ሻምፒዮና ሌሊሳ ዴሲሳና ታደሰ ቶላ ዩጋንዳዊውን አትሌት ተከትለው የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል። ከሁለት ዓመት በፊት ቤጂንግ ባዘጋጀችው ሻምፒዮና ደግሞ አትሌት የማነ ጸጋዬ ሁለተኛውን ደረጃ በመያዝ የብር ሜዳሊያውን አግኝቷል።

   በሻምፒዮናው ተሳትፎ ሴቶች የሜዳሊያ ሰንጠረዡን የተቀላቀሉት እአአ በ2009 በርሊን ባዘጋጀችው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ነበር። በወቅቱ የቻይናና የጃፓን አትሌቶችን ተከትላ በመግባት የነሐስ ሜዳሊያውን ያጠለቀችው አትሌት አሰለፈች መርጊያ ናት። በቤጂንጉ ሻምፒዮና ደግሞ አትሌት ማሬ ዲባባ በርቀቱ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ በሴቶች ልታገኝ ችላለች። ኢትዮጵያ በማራቶን ካስመዘገበቻቸው 9ሜዳሊያዎች መካከልም 1የወርቅ፣ 3የብርና ሦስት ነሐስ በጥቅሉ 7ቱ ሜዳሊያዎች በወንዶች የተመዘገቡ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃም ባስመዘገቧቸው ሜዳሊያዎች 4ኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጡ ችለዋል። በሴቶች ደግሞ 2ሜዳሊያዎች ሊመዘገቡ ችለዋል።  

ያሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በእንግሊዟ የለንደን ከተማ መካሄድ በጀመረው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ኢትዮጵያዊያን የማራቶን አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል። በወንዶች አትሌት ታምራት ቶላ፣ ጸጋዬ መኮንን እና የማነ ጸጋዬ፤ በሴቶች ደግሞ ሻምፒዮናዋ ማሬ ዲባባ፣ ብርሃኔ ዲባባ፣ ሹሬ ደምሴ እንዲሁም አሰለፈች መርጊያ በርቀቱ ሃገራቸውን ወክለዋል።

ትናንት ቀትር ላይ በጀመረው የወንዶች ውድድርም ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የብር ሜዳሊያ በማግኘት የሜዳሊያዎቿን ቁጥር 3አድርሳለች። በውድድሩ ላይ ኬንያዊው ጆፈሪ ኪሩይ ቀዳሚ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቋል። በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድሮች ብልጫ ያላት ኬንያ፤ ጆፈሪ ኪሩይ አምስተኛው ሻምፒዮና የሆነ አትሌት ነው። አትሌቱ አሸናፊ ለመሆንም 2፡08፡27 የሆነ ሰዓትም ፈጅቶበታል። በወንዶች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር በወንዶች ክብረወሰኑን የያዘው እአአ በ2009ኙ የበርሊን ማራቶን በሃገሩ ልጅ አቤል ኪሩይ የተያዘው 2:06:54 ነው።

አትሌቱ ከውድድሩ በኋላ ለአይ ደብል ኤ ኤፍ በሰጠው አስተያየትም፤ በተለይ እስከ 35ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ተፎካካሪው የነበረው የኢትዮጵያዊው አትሌት እንቅስቃሴ ደከም ማለት አሸናፊ የመሆን ተስፋ ስለሰጠው ወደፊት መውጣቱን ገልጿል። ሻምፒዮና በመሆኑም ደስተኛነቱንና ህልሙን እውን ማድረጉን ነው ጨምሮ የገለጸው።  

እስከ 30ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ የአሸናፊነት ግምቱ በተለይ ወደ ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ ያዘነበለ ነበር። በተለይ አትሌቱ በዚህ ዓመት በተካሄደው የዱባይ ማራቶን 2፡04፡11 የሆነ ሰዓት ማስመዝገቡ ለሻምፒዮናው ከፍተኛ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት እንዲሰጠው አድርጓል። ሆኖም ታምራት ሻምፒዮን ለመሆን ብርቱ ፉክክር ቢያደርግም ኬንያዊውን አትሌት ተከትሎ 2፡09፡49 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ የብር ሜዳሊያውን የግሉ እድርጓል። ታንዛኒያዊው አልፎንስ ሲምቡ ደግሞ ከታምራት በ2ሰከንዶች ዘግይቶ  ሦስተኛ ሆኖ ውድድሩን ሊያጠናቅቅ ችሏል። 

በጎዳና ላይ ሩጫዎችና ሃገር አቋራጭ ውድድሮች ታዋቂው ታምራት ቶላ፤ በ2015 የጉያንግ የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን፤ ያለፈው ዓመት በካርዲፍ የዓለም ግማሽ ማራቶን 2ኛ በመሆን የብር ተሸላሚ ነበር። በሪዮ ዴ ጄኔሮ በተካሄደው ኦሊምፒክ ላይም በ10ሺ ሜትር ተሳትፎ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኑም የሚታወስ ነው።

ከውድድሩ በኋላ አትሌቱ በሰጠው አስተያየትም፤ እስከ 30ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ለአሸናፊነት የሚያበቃው ፉክክር ቢያደርግም፤ ከዚያ በኋላ የህመም ስሜት እንደተሰማው ገልጿል። ህመሙን ተቋቁሞ ለመሮጥ ጥረት ቢያደርግም በኬንያዊው አትሌት መበለጡንና ከህመሙ ጋር እየታገለ ውድድሩን ሊያጠናቅቅ መቻሉን ገልጿል። ከህመሙ ጋር ተዳምሮ የከርቮቹ መብዛትም ውድድሩን ፈታኝ አድርጎበት እንደነበረም ነው የገለጸው። አትሌቱ ከዚህ ቀደምም በጉዳት ላይ መቆየቱን አስታውሷል።

ከወንዶቹ ውድድር በኋላ የተጀመረው የሴቶች ውድድር እጅግ ከፍተኛ ፉክክር የታየበትም ነበር። በተለይ እስከ መጨረሻዎቹ ኪሎ ሜትሮች ድረስ የምሥራቅ አፍሪካዊያኑ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን፤ አሸናፊ የምትሆነውን አትሌት ሊለይ በማይቻል ሁኔታም የከረረ ፉክክር ታይቷል። በዚህ ውድድር ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ማሬ ዲባባ፣ ብርሃኔ ዲባባ፣ ሹሬ ደምሴ እንዲሁም አሰለፈች መርጊያ ነበሩ።

በተለይ የቤጂንግ ሻምፒዮና አሸናፊዋ አትሌት ማሬ ዲባባ ለዚህ ውድድር በቀጥታ ተሳታፊ እንደመሆኗ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷት ነበር። የሁለት ጊዜ የማራቶን ሻምፒዮናዋ ኬንያዊቷ አትሌት ኤድና ኪፕላጋትም ፈተና ትሆናለች የሚል ቅድመ ግምት አግኝታ ነበር ማሬ። እአአ 2009 የበርሊን ሻምፒዮና ሦስተኛ በመሆን የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አሰለፈች መርጊያም፤ በውድድር መድረኩ ያላትን ልምድ ተጠቅማ የሜዳሊያ ሰንረዥ ውስጥ ትገባለች የሚል ተስፋ ተጥሎባት ነበር። ሹሬ ደምሴና ብርሃኔ ዲባባም በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም በማራቶን ውድድሮች ያሳዩት ብቃት ለአሸናፊነት እንደሚያበቃቸው ተጠብቆ ነበር።

ሆኖም  በትውልድ ኬንያዊቷና ለባህሬን የምትሮጠዋ አትሌት ሮዝ ቼሊሞ እና ኬንያዊቷ ኤድና ኪፕላጋት ቀድመው በመውጣት ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ፤ በባህሬናዊቷ አትሌት 2:27:11በሆነ ሰዓት በመግባት አሸናፊ በመሆን ውድድሩ ሊጠናቀቅ ችሏል። ኬንያዊቷ አትሌት በ7ሰከንዶች ዘግይታ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያውን የግሏ ስታደርግ አሜሪካዊቷ አትሌት አሚ ክራግ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

ኢትዮጵያዊቷ ሹሬ ደምሴ 5ኛ ስትሆን፤ ማሬ ዲባባ8ኛ፣ ብርሃኔ ዲባባ 10ኛ እንዲሁም  አሰለፈች መርጊያ 12ኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል። እስከ ትናንት በነበረው ውጤት መሰረት ኢትዮጵያ በ1ወርቅና በሁለት ብር በአጠቃላይ ሦስት ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ብርሃን ፈይሳ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።