‹‹ግንባታው ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ነው!›› - አቶ ቢልልኝ መቆያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ

29 Sep 2017

የግንባታው ባለቤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሆነውና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰንዳፋ በኬ አትሌቲክስ መንደር ከተከለለ ካለአገልግሎት 17ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ፌዴሬሽኑ በ2007 .10 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ የተወሰኑ ግንባታዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በሥራው መጓተት ምክንያት ብዙዎች ተጠቃሚ ሊሆኑበት አልቻሉም፡፡ የአትሌቲክስ መንደሩ ግንባታ በመዘግየቱ ምክንያትም ቦታው ለኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በኩል እንዲተላለፍ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ግንባታው ትልቅ በጀት ስለሚፈልግ በፍጥነት ሰርቼ ለማጠናቀቅ የሀብት ማሰባሰብ እቅዴን ተግባራዊ አድርጌ እሰራለሁ እያለ ይገኛል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣም የሰንደፋ አትሌቲክስ መንደር ግንባታንና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፦ አሁን በአገሪቱ ያለው የአትሌቲክስ ማእከላት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ቢልልኝ፦ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአራት ክልሎች የራሱ የስልጠና ማእከላት አሉት፡፡ በትግራይ ማይጨው፣ በአማራ ክልል ደብረ ብርሀን፣ በኦሮሚያ ክልል በቆጂና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሀገረ ሰላም ማሰልጠኛ ማእከላት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ማእከላት በዋናነት በክልሎቹ የሚደገፉ ሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የቴክኒክ፣ የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ በዚህም ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ ክልሎች በራሳቸው እንቅስቃሴዎች የገነቧቸው የስልጠና ማእከላት አሉ፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ላይ፣ በአማራ ክልል ሰከላ፣ ተንታና ፈረስ ቤት አካባቢ እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ በደቡብ ክልልም እንደዚሁ እንቅስቃሴ ያለ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ሱማሌ፣ ጋምቤላና በሌሎች ክልሎች በመዘዋወር ስልጠና ማእከላት መገንባት እንዳለባቸው ባስገነዘብነው አግባብ ወደ ግንባታ እየገቡ ይገኛሉ፡፡

አዲስ ዘመን፦ የሰንዳፋ በኬ አትሌቲክስ መንደር ግንባታና ያለበት ደረጃስ ምን ይመስላል?

አቶ ቢልልኝ፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሰንዳፋ በኬ አትሌቲክስ መንደርን ከ17ዓመት በፊት ቦታውን ተረክቦ አጥሮ የቆየ ሲሆን፤ ከ2007 .ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባትም ተችሏል፡፡ ወደ ሥራ ሲገባ ፕሮጀክቱ ትልቅ ስለሆነ በወቅቱ ከ300ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ስለነበር በፌዴሬሽኑ ብቻ መገንባት ስለማይቻል ባለን አቅም ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአትሌቶች ልምምድ የሚያገለግል ትራክ፣ አሸዋ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ከልምምድ በኋላ ስፖርተኞች የሚታጠቡበትና የሚጸዳዱበት ክፍሎች መስራት ተችሏል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የእስካሁኑ ክንዋኔ በቂ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ቢልልኝ፦ ይሄ በራሱ በቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ የአካባቢው ህዝብ ከጊዜው ቆይታ አንጻር ተገቢ በሆነ መንገድ አልተገነባም የሚል ጥያቄ አለው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርትም ይሄው ጥያቄ አለው፡፡ ስለዚህ አሁን እያደረግን ያለው በዚህ ዓመት ከመንግሥትም ድጋፍ ጠይቀን በተለይም ደግሞ የሀብት ማሰባሰብ ዘዴ ፈልገን በቅርቡ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አጸድቀን ወደ ሥራ ልንገባ ነው ያሰብነው፡፡ ይህ ማለት ለአትሌቲክስ ስፖርተኞች ማደሪያ የሚሆን ካምፕ እዚያው እንዲገነባና አትሌቶቹ የሚመገቡበት ክፍልና የመዝናኛ ክፍሎችን ተጨማሪ ሆነው እንዲሰሩ ወደ ሥራ እንዲገባ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በአንክሮ ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ ጉዳይ ከአቅም በላይ በመሆኑም ለኢ...ሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲደረግልን አቅርበናል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ወራት ተገቢውን የሀብት ማሰባሰብ ሥራና ድጋፍ መሰረት ያደረገ ሥራ እውን ማድረግ በሚያስችል መንገድ እንዲሰራ በእቅድ ውስጥ አካትተን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ጥቅምት መጀመሪያ አካባቢ በሚካሄደው የጠቅላላ ጉባኤ አጸድቀን ወደ ሥራ እንገባለን፡፡

አዲስ ዘመን፦ የሰንዳፋ በኬ አትሌቲክስ መንደሩን በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ነበር እቅድ የተያዘው?

አቶ ቢልልኝ፦ ግንባታው ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ማከናወን አይቻልም፡፡ ሥራው በጣም ትልቅ ነው፤ ስታዲየምም ስላለው ከ300ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ፕሮጀክት በአንድ ጊዜ ተገንብቶ ያልቃል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በካፒታል በጀት የሚገነባ አይደለም፡፡ ፌዴሬሽኑ ያለው አቅም ውስን ነው፡፡ ስለዚህ በሂደት ቀስ እያለ የሚጠናቀቅበት መንገድ ነው የሚታሰበው፡፡ ነገር ግን አሁን በዋናነት አትሌቶቻችን ልምምድ የሚሰሩበት የሻወርና የመጸዳጃ አገልግሎት የሚያገኙበት፣ የምግብ አገልግሎትና የማደሪያ አገልግሎት የሚያገኙበትና ተገቢ በሆነ መንገድ ልምምድ እንዲያደርጉበት የታሰበ እንጂ በዚህ ጊዜ ያልቃል ተብሎ የታሰበ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ድጋፍና እርዳታ እየተፈለገ የሚሰራ እንጂ በእቅድ ውስጥ አካትተን በዚህ ጊዜ ይሰራል የሚል ሥራ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፦ እስካሁን በማን ወጪ ነው እየተሰራ ያለው? እስካሁን ላለው ግንባታስ ምን ያህል ወጪ ተደርጓል?

አቶ ቢልልኝ፦ እስ ካሁን እየተሰራ ያለው በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው ሥራ አስፈጻሚ ከአስር ዓመት በፊት ገንዘቡ ወጪ ሆኖ መታጠር ችሏል፡፡ ቦታው በክፍያ ጥበቃ እየተካሄደለትም ነው፡፡ ባለፈው 2007 .ም ግን 10 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገን የግንባታ ሥራው እየተከናወነ ነው ያለው፡፡ የዚህም ምንጩ ፌዴሬሽኑ ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን ሥራውን ከፍ ባለ ሁኔታ ለመስራት የመንግሥት፣ የህዝብ እንዲሁም የባለሀብቱም ድጋፍ ያስፈልጋል፤ በተቻለ መጠን ሥራው እንዲያድግ በዚህ ዓመት ጠንክረን እንሰራለን ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ግንባታው አሁን ባለበት ደረጃ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ምንድነው? የተሰራው ትራክስ?

አቶ ቢልልኝ፦ ትራኩ በግንባታ ላይ ስለሆነ ኮንትራክተሮቹ እያሉ ሌላ ልምምድ አይደረግም፤ ምክንያቱም በግንባታ ላይ በመሆኑና ለመሮጫ ብቁ በሆነ መንገድ ስላላለቀ፡፡ ይህም በደንብ ለልምምድ በሚያገለግል መንገድ እንዲሰራ ያስችላል፡፡ መሀል ላይ ያለው የሳር ተከላውና የፍሳሽ ቦታው የመጸዳጃ ቤትና የሻወር አገልግሎቶች ግንባታ ግን አልቋል፡፡

አዲስ ዘመን፦ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረውስ መቼ ነው?

አቶ ቢልልኝ፦ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው ሲጠናቀቅ ነው፡፡ ምናልባት በዚህ ዓመት ከኮንትራክተሮቹ ጋር በመነጋገር በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ባለበትም ቦታ ቢሆን ወደ ተግባር እንዲገባና የአካባቢውንም ወጣቶች እንዲያገለግል ለማድረግ አጠናክረን እንሰራለን፡፡ በተለይ ትልቁ ነገር የካምፕ ሥራ ሲሆን፤ እሱን ለመስራት ሀብት ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ደጋግሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሀብቱን ከተለያዩ አካላት ድጋፍ ካገኘን በቀጥታ በዚህ ዓመት ሥራ ይጀምራል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የተቀመጠ የዲዛይን ሥራ አለ?

አቶ ቢልልኝ፦ በማደሪያ ካምፕ ደረጃ ዲዛይን መጀመሪያ አይደለም የተሰራው፡፡ በዚህም ይህንን መከለስ ስለሚያስፈልግ መጀመሪያ ገንዘቡን የማሰባሰብ ሥራ መስራት አለብን በሚል ጎን ለጎን የዲዛይን ሥራው እየተሰራ በዚህ ዓመት ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ይገባል በሚል ነው የሥራ አስፈጻሚው አቅጣጫውን ያስቀመጠው፡፡

አዲስ ዘመን፦ የአትሌቲክስ መንደሩን ሰንዳፋ ላይ ለመገንባት ሲታቀድ ለአትሌቶች አመቺ ስፍራ መሆኑ ተጠንቶ ነው?

አቶ ቢልልኝ፦ ቦታው ስለተገኘ ብቻ አይደለም እዛ እንዲሰራ የተደረገው፡፡ ቦታው ለአትሌቲክስ በጣም የተመቸ በተራራ ሰንሰለት እስከ እንጦጦ ድረስ የተያያዘ ሲሆን፤ የተራራ ልምምዶችን ለማድረግ የሚያስችልና በሁሉ ነግር ምቹ የሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ተጠንቶ ጥያቄ የቀረበለትና ባለሙያዎች አይተውት ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገ ነው፡፡ አንደኛ ከከተማው ቢያንስ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ውስጥ ገባ ያለ ርቀት ሲሆን፤ ስለዚህም ማእከላዊ ቦታም ነው፡፡ ለአዲስ አበባም ቅርብ በመሆኑ አትሌቶች ወደ ቦታው ሄደው ልምምድ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ በብሄራዊ ደረጃ ተመርጠው ካምፕ ከሚገቡት ውጭ ያሉትም አትሌቶች ልምምድ አድርገውና ሌሎች አገልግሎቶችን አግኝተው መመለስ ይችላሉ፡፡

አዲስ ዘመን፦ የአትሌቲክስ መንደሩ ግንባታ መከናወን ምን አይነት ስፖርታዊ ጥያቄዎችን መመለስ ይችላል?

አቶ ቢልልኝ፦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ትልቅ የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር አለበት፡፡ አትሌቶቻችንም በብዛት ከተማ ውስጥ ነው የሚሰሩት፡፡ ስለዚህ የአትሌቲክስ መንደሩ መገንባት የማዘውተሪያ ስፍራ ችግርን ይፈታል ማለት ነው፡፡ አትሌቶችም ተገቢ በሆነ መንገድ ንጹህ የሆነ አየር እያገኙ መስራት ይችላሉ፡፡ በሌላ መልኩ ካምፑ ከተሰራ እዚያ አካባቢ የጅምናዚየምና የምግብ አገልግሎት እንዲሁም ተገቢ በሆነ መንገድ እዚያው አድረው ውለው አገልግሎት ማግኘት ስለሚያስ ችላቸው ሲጠናቀቅ ይህንንና መሰል መልሶችን መስጠት ይችላል፡፡ ይህም በአገሪቱ የሚፈለገውን የተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት እንዲሁም ውጤታችን ሳይንጠባጠብና ሳይቆራረጥ ከምንፈልገው ግብ ላይ እንድንደርስ የሚያስችል ትልቅ ቦታ ነው፡፡ በመሆኑም ስፍራው የህዝብ ሀብት እንደመሆኑ መንግሥትና ፌዴሬሽን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ትልቅ ርብርብ ሊያደርግበት ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ቢልልኝ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 

አዲሱ ገረመው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።