ከመርሃግብር ያልዘለለው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ Featured

12 Oct 2017

ተፎካካሪ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እንዲፈጠር ጠንካራ ፕሪምየር ሊግ ያስፈልጋል፤

 

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ 16ኛ ዓመት የልደት ሻማውን ያበራል፡፡ ሊጉ ከ1994 .ም ጀምሮ ሲካሄድ ቢቆይም ለውጡ አዝጋሚ ነበር፡፡ ክለቦች ከወንዶች ቡድኖቻቸው ጎን ለጎን የሴቶችን ቡድን መያዝ ግዴታ ከሆነበት ካለፉት ሰባት ዓመት በኋላ ግን በአንፃራዊነት መሻሻሎች እንደታዩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት 22 ቡድኖች ይሳተፋሉ፡፡ ለመሆኑ የሊጉ የእስካሁን ጉዞና ለብሔራዊ ቡድኑ ያበረከተው አስተዋፅዖ እንዲሁም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮቹ ምን ይመስላል? በዚህ ውድድር ዓመት መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮችስ?

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሴቶች ቡድን እና ከ17 ዓመት በታች የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሆነችው ሰላም ዘራይ የሴቶች እግር ኳስ ከዚህ ቀደም ይካሄድ የነበረው ውድድር ቡድኖች በብዛት አነስተኛ በመሆናቸው ውድድር ለማካሄድ ብቻ በማሰብ እንደነበር ታስታው ሳለች፡፡ ውድድሩ ለብሄራዊ ቡድኑ ጠቀሜታ ባይኖረውም በትንሹ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞችና ቡድኖችን ከመጥቀም እንደማያልፍም ትገልጻለች፡፡

ካለፉት ሁለት ዓመታት በኋላ ግን የውድድር መርሆቹ እየተቀያየሩ ማሸነፍና ጥሩ አቋም መያዝን የሚጠይቅ ውድድር ላይ መደረሱንም ትናገራለች፡፡ ይህ የፕሪምየር ሊግ ውድድር እየተሻሻለ መምጣቱ ፉክክር እንዲኖር እድል በመፍጠሩ ጥራት ላይ ለማተኮር እንዲቻል እድል ፈጥሯል የሚል እምነት አላት፡፡ ይህ ደግሞ የተሻለ ብሄራዊ ቡድን እንዲኖር አስተዋፅዖ የጎላ ነው ትላለች፡፡

የሴቶች እግር ኳስ ከዚህ በፊት ብሔራዊ ቡድኑ ተጠቃሚ ባይሆንም አሁን ግን መወዳደር ብቻ ሳይሆን መውጣት መውረድ በመኖሩ እንዲሁም በቡድኖች ቁጥር፣ በክፍያና በጥራት እያደገ በመምጣቱ የተሻለ ፉክክር እንዲኖር አስችሎታል፡፡ ሁል ጊዜም የተሻለ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር በተሻለ ፉክክር ውስጥ ያለፉ ብቁ ስፖርተኞች አስፈላጊ በመሆናቸው የሊጉ ቡድኖች ፉክክር መጠናከር ብሔራዊ ቡድኑም አዳዲስ ተጫዋቾችን እንዲያገኝ አማራጭ ያሰፋል፡፡

አሰልጠኝ ሰላም እንደምትለው ሴቶች በእግር ኳሱ እንደ ‹‹ሁለተኛ ዜጋ›› ነው እየታዩ ያሉት፡፡ ማለትም ማንኛውም የስፖርት አስፈላጊ ድጋፎች እኩል ለሴቶቹም አለመደረጉ፣ የሴቶች ስፖርት ትኩረት አሁንም አናሳ መሆን ምክንያት ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በሂደት በስፖርቱ ውስጥ ባሉ ሴት ስፖርተኞች ጥረት የሚስተካከል መሆኑንም ትጠቁማለች፡፡

‹‹በሴቶች እግር ኳስ ውስጥ ጥሩም ይሁን መጥፎ ውጤት የመጣው ስፖርቱ ውስጥ ባሉት ተጫዋቾች ነው›› አሰልጠኝ ሰላም፤ በስፖርቱ ፍቅርና በራስ ጥረት እዚህ የደረሰ ስፖርት አሁንም እየተሰጠ ያለው ትኩረት በቂ አይደለም፡፡ በእግር ኳስ ስፖርት ለውጥ ለማምጣት ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅ ነገር ግን አሁንም በአንድ አካል ጥረት ብቻ የትም አያደርስም፡፡ ‹‹በሴቶች እግር ኳስ የተፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ጊዜ ይፈጃል ግን እስካሁን በቂ ትኩረት እንኳን መስጠት ካልተቻለ ጊዜው ሳይሰራበት እየራቀ ይመጣል›› በማለት ጥቃቅን ነገሮችን ከስር እየፈቱ ማለፍ ካልተቻለ ለችግሮቹ ቀጣይነት እድል እንደሚፈጥር ትጠቁማለች፡፡

በሴቶች እግር ኳስ ተተኪ አሳሳቢነት በየአካባቢው የሴት እግር ኳስ ታዳጊ ቡድኖች አለመኖርና የፕሪምየር ሊግ ቡድኖችም ተጨማሪ ተተኪ ሁለተኛ ቡድን አለማዘጋጀታቸው አሁንም ለእግር ኳሱ ፈተና እየሆነ እንደሚቀጥል ትጠቁማለች፡፡ ሁሉም የሴቶች ቡድኖች ፕሪምየር ሊጉ ላይ መወዳደር ስለሚችሉ ከታች ስላለው ውድድር አለማሰብና ታዳጊዎቹም ከትልልቆቹ ጋር በአንድ ሊግ በአንድ ቡድን የመወዳደር እድል ፈጥሯል፡፡ በየአካባቢው የታዳጊ የሴቶች ፕሮጀክቶች እንዳይኖሩ የሚያደርገው ዋና ምክንያት የምትለው ደግሞ ታዳጊ ሴቶችን ወደ እግር ኳስ አምኖ የሚልክ ቤተሰብ አለመኖሩ ነው፡፡

‹‹አሁን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር 22 ደርሷል፡፡ ከወንዶቹ የቡድን ብዛት ላይ በመደረሱ ቁጥርን ከመጨመር ይልቅ እቅድ በማውጣት ጥራትና በተለይ ተተኪዎችን ማፍራቱ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡ ጥሩ ተጫዋቾችን ማፍራት የሚቻለው ከወዲሁ መዘጋጀት ሲቻል ነው›› በማለት ትገልጻለች፡፡

ሰላም እንደምትገልፀው የሴቶች ቡድኖች አሁንም በወንድ ቡድኖች ላይ የመንጠላጠል ሁኔታዎች አሉ፡፡ የወንዶች ቡድን ጥሩ ውጤት ላይ አይደለም ማለት የሴቶቹም ተመሳሳይ ነው ብሎ መወሰንን እስኪያመጣ ድረስ የሴቶቹ ቡድኖች በወንዶቹ ላይ መንጠልጠላቸው አሁንም በዓላማ እንዳይሰሩ ችግር ፈጥሯል፡፡ ‹‹በፌዴሬሽን እንዲሁም ቡድኖችም የሚመሩት በወንዶች እንደመሆኑ ከሚሰጣቸው ትኩረት አንፃር ሁሉም ቡድኖች የመፍረስ እድል አላቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሴቶች እግር ኳስ ደካማ ጎን ነው›› ትላለች፡፡

በሴቶች እግር ኳስ ላይ ያለው ዋና ችግር የምትለው በቂ ገንዘብ ለቡድኖቹ የሚመድብ አካል ቢገኝም በሙሉ እርግጠኛ ባለመሆኑና አሁንም ድረስ ያለው በሴቶች እግር ኳስ ላይ ያለመተማመን ሁኔታ ለስፖርቱ ስጋት መሆኑን ትናገራለች፡፡ በዚህ ምክንያት በሴቶች እግር ኳስ ላይ ያለው አመለካከትና መተማመን አስተማማኝ አልሆነም፡፡

‹‹የሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች በቁጥር ጨምረዋል፤ በጥራትም ቢሆን እየተሻሻለ ነው፡፡ በቂና የመጨረሻ ግብ ባይሆንም ጥሩ የሚባል ውድድር ጊዜ ላይ መድረሳችን መልካም አጋጣሚ ነው›› በማለት አሁንም የበለጠ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በአንድ ወይም በሁለት ቡድኖች የበላይነት ብቻ ተወስኖ ይጠናቀቅ ስለነበር በዓመቱ መጀመሪያ ጨዋታዎች አሸናፊውን መለየት የሚቻልበት ጊዜ እደነበር ብዙዎች እንደ ሚስማሙበት ይናገራል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው፤ እስካሁን የተገኘው ማንኛውም ውጤት በተጫዋቾቹ የግል ጥረት የመጣ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከዚህ ቀደም ትኩረት የማይሰጠው የነበረው የሴቶች እግር ኳስ አሁን አሁን ትኩረት መስጠት በትንሹም ቢሆን መጀመሩ ፕሪምየር ሊጉ ለውጥ ማምጣት እዲችል አድርጓል፡፡

በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች እየተሻሻሉ የመምጣቱን ውጤት በብሄራዊ ቡድኑ ያሳዩትን እንቅስቃሴና የተመዘገቡ ውጤቶችን ማየት እንደሚበቃ ይናገራል፡፡ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች መቋቋም ለዋናው ብሄራዊ ቡድንና ለክለቦች ያለው ጠቀሜታ እንደማያጠያይቅም ይናገራል፡፡ አለዚያ ተተኪ ቡድንን መጠበቅ እንደማይቻል ይጠቁማል፡፡

አሰልጣኝ ብርሃኑ ብሄራዊ ቡድኑን ባሰለጠነበት ጊዜ ካስተዋለው በመነሳት፤ ከዚህ በፊት ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ቢቻልም ውጤቱ የመጣው ግን አፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ እንደ እቅድ ተይዞ ለረጅም ጊዜ ተሰርቶበት ሳይሆን በልጆቹ የስፖርቱ ፍቅርና በራሳቸው ጥረት የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ ያለፈውን የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ እንደ ግብ አድርጎ ቢሰራም መልካም ተሞክሮ እንደሚሆን በመናገር አሁንም ተከታታይ ስራዎችን በማቀድ መስራት ላይ ትልቅ ክፍተት መኖሩን ይጠቁማል፡፡

‹‹እስከ አሁን ድረስ ከቁጥር የሚገባ ድጋፍ ሳይደረግላቸው እዚህ መድረሳቸው ይበቃል›› የሚለው አሰልጣኙ፤ ከዚህ በኋላ ግን ሊታገዙ እንደሚገባ ያብራራል፡፡ ተጫዋቾቹ አቅማቸውን መጠቀም የሚችሉበት የዕድሜ ክልልን በጥንካሬ እንዲሰሩና ሀገርም ከእነሱ መጠቀም እንድትችል ከተፈለገ ጊዜ ሳይወሰድ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፡፡ አሁን ያሉት አብዛኛዎቹ የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ረዥም ጊዜ የተጫወቱ በመሆናቸው እነርሱን የሚተኩትን ማፍራቱ ላይ አሁንም እየተተኮረ አለመሆኑ ችግሩ እንዲቀጥል ዕድል የሰጠ ነው፡፡

ብርሃኑ እደሚናገረው ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች መቋቋማቸው ጥሩ ሆኖ፤ ነገር ግን እነርሱም ከፕሪምየር ሊጉ ቡድኖች ውስጥ ከሚጫወቱት ውስጥ መምረጡ አሁንም አስተማመኝ አይደለም፡፡ እንዲሁም ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን መስርቶ ቋሚ የሆነ ውድድሮችን የማያገኙ ከሆነ ትርጉም የለውም፡፡ ጨዋታዎች ሲኖሩ ብቻ ተጫዋቾቹን መሰብሰብ ሳይሆን በእድሜያቸው እኩል እንዲወዳደሩ ውድድሮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ከፕሪምየር ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ከ17 እና 20 ዓመት በታች መርጦ በማጫወት መፍትሄ አይገኝም፡፡ በእድሜያቸው ልክ የስፖርቱን ስርዓት እንዲማሩ ሳይደረግ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ መሳተፋቸው ችግሩ ለብሔራዊ ቡድኑም የሚተርፍ ነው፡፡ ‹‹ተጫዋቾቹ ከስር ጀምሮ ራሳቸውን እያስተካከሉ እንዲመጡ ስርዓት ካልተዘረጋ አሁንም ለተሳትፎ ብቻ ተጫዋቾችን አፈላልጎ በማሰባሰብ በአንድ ተጫዋች በመመርኮዝ ሶስት ቡድን ማቋቋሙ ችግሩን ማስቀጠል ነው›› ይላል፡፡

‹‹ለሴቶች እግር ኳስ ትኩረት አልተሰጠም ወይም በቂ አይደለም የምንለው እስካሁን ድረስ በፕሪምር ሊጉና በብሄራዊ ቡድኖቹ ላይ እየታየ ያለው ስራ በተጫዋቾቹ ጥረት የመጣ በመሆኑ ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ከሚያደርጉት ጥረትና ከሚሰሩት ስራ አንፃር የተሰጠው ትኩረት በጣም ትንሽ ነው፤ አንድ ቡድን ብቻ ተይዞ ስለ ዘላቂነት ማሰብ ስለማይቻል ተተኪ ስለማፍራት የማይታሰብ ከሆነ ቅብብሎሹ ላይ ስራው የሚቆምበት ጊዜ ይመጣል፤ ባለው ላይ ተተኪ እያፈራን የማንሄድ ከሆነ ሁሌም ከአዲስ እንደገና እየጀመሩ መሄድ ነው የሚሆነው ስራችን›› ይላል፡፡

ተተኪዎች ላይ መስራት ዛሬ ነገ የማያስብል ስራ አይደለም፡፡ ብርሃኑ ጨምሮም ተተኪዎች ላይ የማይሰራ ከሆነና በማቀድ አንድ ተብሎ አሁን ካልተጀመረ ስፖርቱ ባለበት እየረገጠ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ለመድረስ 30 እና 40 ዓመት እንደ ቀላል መፍጀቱ እንደማይቀር ያስገነዝባል፡፡ ተተኪዎችን በማፍራት በኩል ትኩረት መስጠት ከቡድኖች ይጀምራል በማለት ስራው የሁሉም አካላት ድርሻ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

‹‹ሊስተካከል የሚገባው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተለመደ የመጣው በማንኛውም ደረጃ ከሰፈርና ወረዳ አንስቶ እስከ ትልልቅ ውድድሮችን ላይ ሁሌም ውጤት ይጠበቃል ያለ ተከታታይ ስራና ድጋፍ ለትንሹም ለትልቁም ውድድር ሁሌም ውጤት አምጡ ማለት ስለ ውጤት አለመረዳት ነው፤ ውጤት የሚለው ጥያቄና ያለ ድጋፍ ውጤት ከዳር ሆኖ ውጤት የላቸውም መባሉ ነው የሴቶችን እግር ኳስ ተፅዕኖ ያሳደረበት፤ በገንዘብም ድጋፍ ለማግኘት ሲሞከር እንቅፋት የሆነው ሁሉም ለውጥ ለማምጣት መጀመርን ሳይሆን በማንኛውም ሁኔታ ውጤትን መፈለጉ ነው›› ይላል፡፡

ብርሃኑ ለሴቶች እግር ኳስ የሚሰጠው ትኩረት አሁን አሁን በክለቦች በኩል መሻሻል እያሳየ መሆኑን በመጥቀስ ተጫዋቾቹ በትኩረት ስፖርቱ ላይ እንዲያተኩሩ የክፍያ መጠኑ መጨመሩ መልካም ነው በማለት የክለቦቹም ትኩረት በቂ አይደለም፡፡ የዚህ ዓመት ውድድር በሁለት ተከፍሎ በመካሄዱ ጥሩ ፉክክር እንዲኖር ስለሚያስችል በቅድሚያ በቂ ዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልግና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሴቶች ሊግን በደንብ ሊያስተዋውቅ እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡ ከወንዶቹ ጋር በማወዳደር ሳይሆን የሴቶች እግር ኳስም የራሱን መልካም ነገሮች እንዳሉትና አጉልቶ ለመውጣት በከፍተኛ ሁኔታ ሊተዋወቅ ይገባል፡፡

ብርሃኑ እንደሚጠቁመው የፕሪምየር ሊጉ መጠናከር የብሄራዊ ቡድኑም ጥቅም ነውና በፕሪምየር ሊግ ብቻ ተወስኖ ያለው የሴቶች እግር ኳስ የውድድር መድረኮችን ማብዛት ይገባል፡፡ የሴቶችን እግር ኳስ በማስተዋወቁ በኩል የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የሚያዘጋጃቸውን ውድድሮች እንዲሁም የሲቲ ካፕ ጨዋታዎችን ለሴቶች ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡ ፕሪምየር ሊጉን ለማስተዋወቅ የሚያግዙ ማንኛውንም እድሎች በመጠቀም የተሻለ ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል፡፡ ፌዴሬሽኑ የሴቶችን እግር ኳስ በከፍተኛ ደረጃ ቢያስተዋውቅ ገንዘብ አያስገኝም ብለው የሚርቁ አጋሮችን የመመለስ እድል ያገኛል፡፡

የደደቢት የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ጌጡ ተሾመ፤ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ጥሩ ሊባል የሚችል መሻሻልና ለውጥ ማየቱን ይገልጻል፡፡ ማሳያ ነው የሚለውም የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በየጊዜው የሚያደርጋቸው ጨዋታዎችና ውጤቶች ነው፡፡ ተጫዋቾቹ በአቅማቸው ጥረት በማድረግ የሚፎካከሩ እና በፕሪምየር ሊጉም ጥሩ የሚባል ፉክክር እያደረጉ ነው የሚል እምነት አለው፡፡

ካለፈው የሴቶች እግር ኳስ ውድድሮች ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት መመልከት የሚቻለው ፉክክሩ እየጠበበ በሁለት ቡድኖች መካከል ብቻ የተወሰነ መምጣቱን ነው፡፡ አሁን ግን ሁሉም ቡድኖች እኩል የሚባል ተቀራራቢ አቅምና ፉክክር ላይ እየደረሱ መጥተዋል፡፡

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተተኪ ለማፍራት እንዲያግዝ የሴቶች የታዳጊ ፕሮጅክቶች ቁጥር የለም እስከሚባል ደረጃ መገኘቱ ትልቅ ፈተና እንደሆነበት ይናገራል፡፡ ጫናውም ከባድ መሆኑን ከሊጉ ጨዋታዎች ማስተዋል እደሚቻልም ነው የሚጠቁመው፡፡ በሴቶች እግር ኳስ ተተኪ የሚሆኑ ልጆችን የሚይዝ ባለመኖሩ አሁንም የተተኪ እጥረት በሴቶቹም እግር ኳስ ዋነኛ ችግር እየሆነ እዲሄድ ያደርጋል፡፡ በሁሉም ቡድን ከዋናው ቡድን ውጪ ታዳጊዎችን በመያዝ በታዳጊዎችም መካከል ውድድር እንዲኖር ማድረግ ቢለመድ ቢቻል ተተኪ ማግኘቱ ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ይጠቁማል፡፡

የሴቶቹ ቡድን ላይ ያለው ትኩረት ገና አሁን መሻሻል እያሳየ ቢሆንም ከረዥም ጥረት በኋላ የመጣ በመሆኑ በተተኪዎችም በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት ታዳጊዎች ማፍራት የረዥም ጊዜ ስራን ስለሚጠይቅ ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ ካልሆነ ግን ለችግሮቹ አስቀድሞ መፍትሄ ማምጣት እየተቻለ አሁንም ለእያንዳንዱ ችግር ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ለመፍትሄ መሯሯጡ እንደማያዋጣና ከአሁኑ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ ጊዜን ተጠቅሞ በአግባቡ በማቀድ ስፖርቱን ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል፡፡

በአጠቃላይ የስፖርቱ ባለሙያዎቹ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለብሔራዊ ቡድን ያለውን አስተዋፅዖ ለመጨመርና ካለፈው ጊዜ ልምድ በመውሰድ መስተካከል የሚችሉትን በማስተካከልና የተሻለ ውድድር እንዲኖር ያግዛል ያሉትን ጠቁመዋል፡፡ የሴቶች እግር ኳስ ትኩረት እንዲያገኝ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በሴቶች እግር ኳስ ላይ የሚታዩትን ጥሩ ስራዎች በማጉላት ተከታታይ ስራ ቢሰሩ መልካም ነው፡፡

2010 .ም የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ስለሚካሄድ የተሻለ ፉክክሮች እንዲታዩ እድል ስለሚፈጥር እንደ ተፈለገ የሚቀየረው የጨዋታ ሰዓትን ሊስተካከል ይገባል፡፡ እንዲሁም ተተኪዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት መስጠት፣ የሴቶችን እግር ኳስ ማስተዋወቅ፣ በስፖርቱ ሴቶች እንደ ‹‹ሁለተኛ ዜጋ›› መቆጠራቸው ቀርቶ እኩል እድል ይሰጥ እና በተጫዋቾቹ ጥረት ላይ ብቻ በመመስረት ውጤት መጠበቅ ይቁም ይላሉ፡፡

 

ሰላማዊት ንጉሤ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።