ስፖርት ለሁሉም ከውድድርነት ባሻገር

06 Dec 2017

አቶ ዘነበ ተሰማ፤

 

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር ጥሩ የመዝናኛ ምንጭ ነው። ከመዝናኛነቱ ባሻገር በሽታ የመከላከል አቅምን በማጠናከር ረገድ ያለውን ሚና ተራማጅ እንደሆነ ይነገራል። ሌላው ዘርፍ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች በአገር ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ያለው ፋይዳ ተጠቃሽ መሆኑን የዘርፍ ምሁራን ይናገራሉ። በአጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አምራችና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እገዛው ከፍተኛ እንደሆነ ያመላክታሉ።

የዘርፍን ተሻጋሪ ፋይዳ ተረድቶ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በአፍሪካ ያለው ልምድ ከሌላው ዓለም አንፃር ዝቅተኛ ስፍራ እንደሚይዝ መረጃዎች ያመለክታሉ። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ስፖርቱን ልምድ የማድረግ ባህል አነስተኛ ነው፡፡ ልምዱን ተደራሽ ለማድረግ ጥረቶች ቢደረጉም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት እምብዛም ሆኖ ይስተዋላል። እንቅስቃሴውን ለማድረግ ቢጣርም በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያብራራሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ ተሰማ፤ በአገሪቱም ሆነ በአዲስ አበባ የስፖርት እንቅስቃሴ የማድረጉ ልማድ እምብዛም ነው። ይህን ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዕድሜው ትንሽ ቢሆንም «ስፖርት ለሁሉ» የውድድር መድረክ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

ፕሬዚዳንቱ፤ እንደሚያብራሩት በስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማሳተፍ የስፖርቱን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና የዜጎችን ምርታማነት ለማረጋገጥ የጎላ ሚና አለው፡፡ ስፖርት ለሁሉም ይሄንኑ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ከስምንት ዓመት በፊት በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ለማዳረስ በሚል ሃሳብ ተቋቁሟል። የተቋቋመው ኮሚቴ ውድድሮችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል።

ህብረተሰብ በሚኖርበት፣ በሚሠራበት፣ በሚማርበት፣ በሚያስተምርበት ቦታ ሁሉ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናውን እንዲጠብቅ ያደርጋል። ይህንኑ መሰረት በማድረግም የሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ሁለት ዓላማዎችን አንግበዋል። አንደኛው እያንዳንዱ ዜጋ ጤንነቱን በስፖርት እንዲጠብቅና እራሱን ከተለያዩ በሽታዎች እንዲታደግ ማስቻል ነው። ሁለተኛው የአንዱ ተቋም ከሌሎች ተቋም ሠራተኞች የልምድ ልውውጥ በማድረግ የተቀላጠፈና መልካም ግንኙነት ያለበት የሥራ ቦታን መፍጠር የስፖርት ለሁሉም ሌላው ዓላማ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ።

የስፖርት ለሁሉም ያለፉት ሰባት

ዓመታት ጉዞ

አቶ ዘነበ፤ የስፖርት ለሁሉም ማህበረሰብ የስፖርት ተሳትፎውን በማጠናከር ረገድ ሚናውን በመወጣት አንድ ዕርምጃ ተራምዷል። ቅንጅታዊ አሠራርን በማጎልበት ረገድ ለውጦች አሉ። በተለይም በአነስተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልምድን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደርስበትን አጋጣሚ ለመፍጠር እንደመንደርደሪያ የሆነ ውጤት ታይቷል። ለዚህም በማሳያነት ስፖርት ለሁሉም ሲጠነሰስ አስር ያህል ተሳታፊ ቡድኖች ብቻ በመያዘ ሲሆን፤ አሁን ከ60 በላይ ተቋማት ከ99 በላይ ቡድኖች በውድድሩ ተሳታፊ ናቸው። ነገር ግን አሁንም የከተማው ህብረተሰብ በስፖርት ልማትና ተሳትፎ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል።

«ባለፉት ሰባት ዓመታት አነስተኛ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልምድን ስፖርት ለሁሉም ባከናወናቸው ውድድሮቹ ማነቃቃት ተችሏል። በነበረው የውድድር ጉዞ የጤና ተቋማት፣ አርቲስቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፤ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቃማት ተሳታፊ ነበሩ። ይህ እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አብራርተዋል።

የስፖርተኛው ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከሚኖረው የሰው ብዛት አንጻር ለውጡ ዘገምተኛ ነው። የኮሚቴው ፍላጎት እያንዳንዱ ተቋም እና በአስሩም ክፍለ ከተሞች የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ ቢሆንም ካለው የበጀት ችግር አኳያ በታሰበው ደረጃ መሄድ አልተቻለም። በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ ተሳታፊዎች የእራሳቸውን ወጪ በእራሳቸው አቅም እንዲሸፍኑ በማድረግ እና አጋር ድርጅቶችን በማፈላለግ ከችግሩ ለመውጣት እየተሞከረ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ይገልጻሉ።

የተሳትፎ ጉዳይ እንደ ጉድለት

የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ፤ ከዚህ በተጓዳኝ የተሳታፊውን ቁጥር ለማብዛት የተሠራውንና በቀጣይነት የሚሠሩትን ሥራዎች መኖራቸውንም ያነሳሉ። በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ በመውረድ ነዋሪዎች የእራሳቸውን ቡድን ማሳተፍ በሚፈልጉት የስፖርት ዓይነት ተሳታፊ እንዲያደርጉ እስከ መቀስቀስ ተሠርቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን አሠልጣኞችን በመቅጠር ህብረተሰቡ በአካባቢው በቀላሉ እና በነፃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስልጠና እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች ተሠርተዋል።

በስፖርት ለሁሉም እቅድ ውስጥ ተካትተው ከሚሠሩ ተግባራት መካከል በዋናነት ትኩረት የተሰጠው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው። ማህበረሰቡ ከስፖርት ሳይገለል በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሠራበት አካባቢ ተገቢ የሆኑ የስፖርት ዓይነቶችን በመሥራት ጥረት ማድረግ እንዲችል ግንዛቤ ተሰጥቷል፡፡ በከተማዋ በሚገኙ አስር ክፍለ ከተሞች በተዋቀሩ ኮሚቴዎች አማካኝነት ሥራው ተደራሽ በማድረግ ስኬታማ ሥራ እንደሚሠሩ አብራርተዋል።

የስምንተኛው የውድድር ምዕራፍ ቅድመ ዝግጅት

«ስፖርት ለሁሉም ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ቀጥሎ ይካሄዳል» ያሉት አቶ ዘነበ ውድድሩን በተለየ እና በተሻለ ደረጃ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ በፊት የነበሩትን ተሳታፊ ተቋማትንም ሆነ አካላት ቁጥር ለማብዛት የተሠሩ ሥራዎች በመኖራቸው የዘንድሮው «ስፖርት ለሁሉም» ውድድር ተሳታፊ ተቋማትም ሆኑ ቡድኖች ቁጥር ከባለፉት ውድድሮች ያሻቅባል ተብሎ እንደሚጠበቅ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በነበረው ውድድር ያጋጠመውን ችግር ከመቅረፍ አኳያም ዝግጅት ተደርጓል። ባለፈው ውድድር በቂ የማወዳደሪያ ስፍራ አለመኖር አንዱ ችግር ነበር፡፡ በወቅቱም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ችግሩን ለመቅረፍ የትምህርት ቤቶችንና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ሜዳዎችን በማስፈቀድ ውድድሮች ሳይስተጓጎሉ እንዲካሄዱ ለማድረግ ችሏል፡፡ ይህ ችግር በስምንተኛው ስፖርት ለሁሉም ውድድር ላይ እንዳይደገም ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። ዝግ የነበሩት የስፖርት ሜዳዎች ዘንድሮ ክፍት እንዲሆኑ ተደርገዋል ብለዋል።

የሴቶች ተሳትፎ መጨመር

አቶ ዘነበ ስፖርቱን ተደራሽ በማድረግ ሂደት የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው። በተቻለን መጠን የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ተሳታፊ ተቋማት ሴቶችን እንዲያነሳሱ እና እንዲያበረታቱ በማድረግ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ከነበረው ተሳትፎ በላቀ ሁኔታ የሴቶች ተሳትፎ ይኖራል። በውድድሩ የሚሳተፉ ተቋማትም ሆኑ ቡድኖች ገና እየተመዘገቡ በመሆኑ አሁን ላይ ይህን ያህል ተሳታፊ ይኖራል የሚለውን ለማስቀመጥ አዳጋች ነው። አጠቃላይ ምዝገባው እስከ ታኅሣሥ 30 ይጠናቀቃል የሚል ግምት አለ። በዚያን ወቅት የተሳታፊውን ቁጥርም ሆነ የውድድሩን መጀመሪያ ቀን እናሳውቃለን ብለዋል።

 

ዳንኤል ዘነበ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።