የዓለም አቀፍ ውድድር ማነስ የስፖርቱ ፈታኝ ሥራ Featured

07 Dec 2017

የሜዳ ቴኒስ በዓለም ዙሪያ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ትኩረት እየሳበ የመጣ ስፖርት ነው፡፡ ስፖርቱ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ከማትረፉም በላፈ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚዘዋወርበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዓለም ከፍተኛ ትኩረት ከሚያገኙ ስፖርቶች መካከል የሆነው የሜዳ ቴኒስ በኢትዮጵያም ይዘወተራል፡፡

የሜዳ ቴኒስ ስፖርት በኢትዮጵያ ሲዘወተር ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በ1972 .ም የቴኒስ ስፖርት ፌዴሬሽን ከመቋቋሙ በፊት ተዘውታሪ የሆነው የሜዳ ቴኒስ ስፖርት በዓለም የሜዳ ቴኒስ ፌዴሬሽን ሳይመዘገብ በፊትም በወዳጅነት ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች እንደነበሩት ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የቴኒስ ፌዴሬሽን አባል በመሆን የተመዘገበችው ፌዴሬሽኑ ከተመሰረተ ከስምንት ዓመት በኋላ በ1980.ም ሲሆን፣ ስፖርቱ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል የስፖርቱ ቤተሰቦችን አነጋግረናል፡፡

ስለሺ ጌታቸው የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ ሲሆን፣ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኛ ነው፡፡ ከአሥር ዓመቱ ጀምሮ በበርካታ የአገር ውስጥ ውድድሮች ላይ ተካፍሏል፡፡ በአብዛኞቹም አሸናፊ በመሆን በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ አለው፡፡ ስለሺ የቦሌ 19 ሜዳ ቴኒስ ክለብ ተጫዋች ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ እ..አ በ2015 ኦልአፍሪካን ጌምስ ላይ ተሳትፏል፡፡ በውድድሩም ሦስተኛ ዙር ድረስ በመድረስ ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግቧል፡፡

ስለሺ ለውድድር በሄደበት ጊዜ ከተመለከተው የሌሎች አገራት የስፖርት እንቅስቃሴን ከኢትዮጵያ ጋር ለማወዳደርና ልዩነቱንም ለመግለጽ እንደሚከብድ ይገልጻል፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ በጣም ብዙ ልዩነት አለው፡፡ እንደ አገር ኢትዮጵያ ቴኒስ ስፖርትን ከሌሎች አፍሪካ አገራት ጋር ለማወዳደር ይከብዳል። በርካታ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ።

‹‹እኔ የብሄራዊ ቡድኑ ቁጥር ሁለት ተጫዋች ነኝ፤ ይህን ችሎታዬን ግን በራሴ ፍላጎት ያመጣሁት ነው፡፡ ትኩረት ሰጥቶ የያዘኝና ድጋፍ ያደረገ ፌዴሬሽን የለም›› የሚለው ስለሺ በተለይ ታዳጊዎችን ወደ ስፖርቱ ለመሳብ፣ ትክክለኛ ስልጠና በመስጠትና ለክለብና ለብሔራዊ ቡድን መመልመል ድረስ በርካታ የአሰራር ጉድለቶች መኖራቸውን ይናገራል፡፡

የአፍሪካ አገራት የቴኒስ ፌዴሬሽኖች ለተጫዋቾቹ የሚያደርጉትን ድጋፍ ስፖርተኞቹ ሲናገሩ ልዩነቱ እጅግ የሰፋ ነው ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ውድድር ሲኖር መሳተፍ ስለሚገባ ብቻ ለተሳትፎ እንደሚሰራና የውድድር መረጃዎች እንኳን በአግባቡ ለስፖርተኞቹ እንደማይደርስ ያመለክታል፡፡

ውድድሮች ከበዛ አንድ ወር አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ሁለት ሳምንት ሲቀር ዝግጅት ለማለት የማሳያስደፍር የድንገት ልምምድ በማድረግ ለውድድር እንደሚቀርቡም ነው የሚያስረዳው፡፡ ነገር ግን ቴኒስ ሰፊ ጊዜ የሚፈልግ ስፖርት መሆኑንና ለማንኛውም አይነት ውድድር በአንድ ወር ዝግጅት መወዳደር ከባድ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች አገራት ለአንድ ውድድር የሁለት ዓመት ዝግጅት እንደሚያደርጉም አስታውሷል፡፡

‹‹እኔም ሌሎቹም ቴኒስ ተጫዋቾች ስፖርቱን ወደን ስለጀመርነውና የፌዴሬሽኑንም የማንንም ድጋፍ ሳንጠብቅ እናዘወትራለን እንጂ ያለው የስፖርት አመራር ሥራ ለዝግጅት እንኳን የሚመች አይደለም›› ይላል፡፡ የአገር ውስጥ ውድድር በአብዛኛው በክለቦች እንደሚ ዘጋጅና በዓመት ወይም በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጁ አገራዊ ውድድሮች መኖራቸውን የሚናገረው ስለሺ፤ ስፖርቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ውድድር የሚያዘጋጁ ክለቦች ወጪ እንደሚበዛባቸው ይጠቁማል፡፡ የሚያዘጋጁት ውድድር አዘጋጆቹን ትርፋማ ሊያደርግ ቀርቶ ወጪውንም እንደማይመልስም ያመለክታል፡፡ ውድድር ለማዘጋጀት በቂ በጀት ኖሯቸው ሳይሆን የውድድር ቁጥር ለማብዛት አስበው እንደሚያዘጋጁ ነው የሚናገረው፡፡

የአገር ውስጥ ውድድርም ቢሆን ለውድድር ቢያንስ ለሁለት ወር በየቀኑ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የሚናገረው ስለሺ፤ ስፖርተኞች ለውድድር ሲዘጋጁ ከሚመጣ ወጪ በተጨማሪ የሚያወጡትን ጉልበት እየተኩ እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹በውድድር ብቻ ሳይሆን ለውድድር ዝግጅት ብቻ የምናወጣው በርካታ ወጪ አለ›› ሲልም ያክላል፡:

በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ሁሉም ተወዳዳሪዎች እንደማይወዳደሩ ጠቅሶ፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የሚወዳደሩ ስፖርተኞች በውድድር ተሳትፈው የላብ መተኪያ እንኳን የማያገኙ ከሆነ ለመወዳደር ፍላጎት እንደማይመጣና በተጨማሪም በዚህ መሰረት ክለቦችም ለሚያዘጋጁት ውድድር ገንዘብ ማውጣት እንጂ የሚገኝ ገቢ ባለመኖሩ ተጎጂዎች መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡

‹‹አንድ ተጫዋች ለአንድ ውድድር የሚያወጣው 20 ሺ ብር ድረስ ይደርሳል፡፡ ከአገር ውስጥ ውድድሮች ደግሞ ከፍተኛ ክፍያ ይከፈላል የሚባለው ቢጂአይ የሚያዘጋጀው ውድድር ነው፡፡ በውድድሩ ከፍተኛው ክፍያ ስምንት ሺ ብር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በማንኛውም ስሌት አዋጭ አይደለም፡፡ ጥቅሙም የውድድር ቁጥር ከመጨመር ባለፈ ተጠቃሚነትና ፋይዳው አነስተኛ ነው፡፡ ውድድርን ከመሳተፍ ያለፈ ፋይዳ የለውም›› ይላል፡፡

የአፍሪካ አገራት አሰራርን ሲገልጽም እንዳብራራው፤ የኬንያ ኢኮኖሚያዊ አቅም ከአፍሪካ አገሮች የተሻለ ከፍተኛ ሳይሆን ውድ የሆነውንም ስፖርት በቀላሉ ተዘውታሪ ማድረግ ተችሎም ሳይሆን የስፖርቱ ኃላፊዎች የተሻለ ነገር ስለሚሰሩ ነው፡፡ ውድድሮችን ማዘጋጀት ባይችሉም በርካታ ውድድሮችን ስፖንሰር አድራጊዎችን በማነጋገርና በማምጣት ለስፖርተኞቹ ጠንካራ የውድድር መድረክ መፍጠር ችለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮችንም አገራቸው ላይ እንዲዘጋጅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ጥረት አድርገው ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አንዴ የማዘጋጀት ዕድል ከተገኘ ስፖንሰር ማግኘት ደግሞ ቀላል ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ አሰራር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት አይሰራም፡፡ እንዲያውም ዓለም አቀፍ ውድድር ማምጣት እንደማይቻል ነው የሚታሰበው፡፡ የአፍሪካ አገራት ትልልቅ የቴኒስ ስፖርት ውድድሮችን የሚያዘጋጁት ከአምስት ባልበለጡ ሜዳዎች ላይ እንደሆነና ኢትዮጵያ ግን ከቴኒስ ሜዳ ቁጥርና ጥራት ፍራቻ ነው እንዳይባል እንኳን በቂ የሆነ ከአንድ በላይ ሜዳ ያላቸው ክለቦች ብቻ በቂ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ስለዚህ የስፖርቱ አመራር ላይ ያሉት ኃላፊዎች ያለውን ዕድል በመጠቀም አለመስራት ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ይጠቁማል፡፡

ጥረት ተደርጎ ውድድሮችን ወደ አገር ማምጣት ካልተቻለ ስፖንሰር ማግኘት እንደማይቻል የሚናገረው ስለሺ፤ ውድድሮችን ለማምጣት ሳይሰራ የስፖንሰር እጦት ለስፖርቱ ችግር ነው ማለት እንደማይገባ ይገልጻል፡፡ ውድድሮችን ወደ አገር ለማምጣት ተግቶ የሚሰራ ጠፍቶ እንጂ የስፖርተኛ እጥረት፣ የብቃት ማነስ፣ የመወዳደሪያ ሜዳ ማጣትም አይደለም፡፡ መሟላት የሚገባቸው ሁሉም ተሟልተውና ስፖርተኛውም ዝግጁ ሆኖ በፌዴሬሽኑ የአሰራር ችግር ምክንያት ውድድሮች ወደ አገር እንዳይመጡ ምክንያት መሆኑን ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያ ያላት ሌሎች የአፍሪካ አገራት ካሏቸው ስፖርተኛና የስፖርት ማዘውተሪያ ያነሰ ሳይሆን ለምን ትልቅ ውድድሮችን ማምጣት አልተቻለም የሚለው ፌዴሬሽኑ ሊጠየቅና ሊሰራበት እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡

አቶ አሰግድ ኃይለስላሴ የኢትዮጵያ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነው፡፡ አሰግድ በቴኒስ ስፖርት ተሳትፎው ከተጫዋችነት እስከ አሰልጣኝነት 25 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በቴኒስ ስፖርት መሳተፍ የጀመረበት የ80ዎቹ ጊዜ የነበረው የስፖርቱ እንቅስቃሴ በፉክክር የተሞላ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ በሚደረጉ የዞናል ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የመሳተፍ እድል አግኝቷል፡፡ በህብረተሰቡም ዘንድ ከፍተኛ ፍቅር የነበረውና ብቃትና ፍላጎት ያላቸው ተጫዋቾች ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉና ከአስር በላይ ክለቦችም እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡

በጊዜው የአገር ውስጥ ውድድሩ በአራት የእድሜ ደረጃ በመከፋፈል ከመቶ በላይ ተወዳዳሪዎች የነበሩት ሲሆን፣ በጊዜው ወጣት እና ዋና ብሔራዊ ቡድን በሚል ተከፍሎ ስፖርተኞች ጥሩ ስልጠና ይሰጣቸው እንደነበርም ይገልጻል፡፡ ቀስ በቀስ ግን የቴኒስ ስፖርት መቀዛቀዝ እየታየበት መምጣቱን ይናገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ያሉት ስፖርተኞችን የሚተኩ ከስር ማፍራት ባለመቻሉ፣ የነበሩትም ጠንካራ ስፖርተኞች ለውድድር በሚሄዱበት ጊዜ በዛው መቅረት እንዲሁም በጊዜው ለስፖርቱ መቀዛቀዝ ትኩረት ሰጥቶ ችግሮቹን ለማቃለል የሚሰራ አካል ባለመኖሩ ነው፡፡

አሁን ያለው የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ከዚህ ቀደም የነበረበትን ያህል ባይሆንም ከ2000.ም ጀምሮ በሁለት ከተማ መስተዳድሮችና በአምስት ክልሎች ላይ የስፖርት እንቅስቃሴው እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ተስፋፍቶ የሚገኘው በአዲስ አበባ መሆኑን አልሸሸገም፡፡ ይህ ደግሞ ስፖርቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን ተዘውታሪነትና ህዝባዊነት እንዲቀጥል አላስቻለም፡፡ ስፖርቱ አዲስ አበባ ላይ በስፋት መዘውተሩ እንደ አገር ያለው ተዘውታሪነት ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳም ይጠቁማሉ፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዓመት አራት ያህል ውድድሮችን ቢያዘጋጅም በቂ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ውድድሮች በአብዛኛው አዲስ አበባ ላይ መካሄዳቸውና በክልል ያሉ ክለቦች ለውድድር ዝግጅትና አዲስ አበባ በመምጣት ለመወዳደር አቅም እንደሚገድባቸው ይናገራል፡፡ ከክልሎች በመምጣት በክለቦች የሚዘጋጀውን ውድድርም በግል ለመሳተፍ አዋጭ አይደለም፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሜዳ ቴኒስ ስፖርቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም የሚያስገኘውም ጥቅም የዚያን ያህል ትልቅ መሆኑን በመጠቆም የኢትዮጵያ ሜዳ ቴኒስ ስፖርት ግን በተገላቢጦሽ ከጥቅሙ ይልቅ ወጪው ከፍተኛ መሆኑን ይናገራል፡፡ ስፖርቱን በቀላሉ ለማዘውተር እንደሌላው ስፖርት ቁሳቁስ በቀላል አለመገኘት ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ አንድ የቴኒስ ስፖርተኛ የልምምድ ቁሳቁስን ለማሟላት ብቻ 50ሺ ብር በላይ እንደሚስ ፈልግም ይጠቁማል፡፡

‹‹የአህጉር ውድድሮችን እንድንሳተፍ በየዓመቱ የሚላክ የውድድር የጊዜ ሰሌዳ አለ፡፡ የጊዜ ሰሌዳው በየእድሜ ደረጃው ምን ያህል ተወዳዳሪ ማሳተፍ እንደሚቻልም የሚገልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ ከ12 ዓመት በታች አራት ታዳጊዎችን ማሳተፍ እንደሚቻል ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ግን የተቀመጠውን ያህል ተሳታፊ መላክ ስለማይቻል በግማሽ በመቀነስ ከእያንዳንዱ ዕድሜ ደረጃ በመቀላቀል ይላካል፡፡ ይህ የሆነው ወጪውን መሸፈን ስለማይቻል ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ግን ወጪያቸውን የሚቀንሱበት መንገድ አላቸው፡፡ በባቡርና በመኪና በመጓዝ መወዳደር ስለሚችሉ፡፡ እኛ ግን የአየር ትራንስፖርት ወጪው ብቻ ከፍተኛ አቅም የሚጠይቅ ነው›› በማለት በእንደነዚህ ዓይነት ዕድሎች ሌሎች አገራት በርካታ ውድድሮችን ለመካፈል ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያ በተጨማሪም የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ያለበት ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ ትኩረት መነፈጉን እንደሚያሳይ ይናገራል፡፡ ስፖርቱ የነበረውን ህዝባዊነትና ተዘውታሪነት እንደነበረው ለመጨመር ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም ያመለክታል፡፡ ስፖርቱን ለማበረታታትና በቂ ውድድሮችን በአገር ውስጥ ለማዘጋጀት የግለሰቦች ጥረት መጨመር እንደሚገባም ሳይጠቁሙ አላለፈም፡፡ እንዲሁም በዋናነት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዜብ ወልደስላሴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቴኒስ ስፖርት አቅም ያላቸው ስፖርተኞች እንዳሏት ይናገራሉ፡፡ ሜዳ ቴኒስ ስፖርት በኢትዮጵያ እውቅናው አሁንም ሰፊ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ በክልሎች የታዳጊ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ወይዘሮ አዜብ እንደሚናገሩት፤ የክልሎች የቴኒስ ስፖርት በታዳጊ ፕሮጀክቶች እኩል ቁጥራቸው እያደገ ነው፡፡ በየዓመቱ በሚደረጉ አገር አቀፍ የወጣቶችና የታዳጊ ውድድሮች ላይም የክልሎች ተሳትፎና ውጤትም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ካለው የስፖርት እንቅስቃሴ አንጻር በቂ የማዘውተሪያ ስፍራ መኖሩንም ይገልጻሉ፡፡

በየክልሉ የቴኒስ ስፖርት ጽህፈት ቤቶች መኖራቸው ክለቦች በያሉበት ክልል ውድድሮች እንዲያገኙና የተሻለ ስፖርቱን ተዘውታሪነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ውድድሮችም ቁጥር መጨመሩን በመጠቆም፤ የደረጃ ውድድር፣ በየሁለት ዓመት የሚካሄድ የክለቦች ቻምፒዮና በየዓመቱ የሚካሄድ፣ አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ውድድር፣ የግልና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውድድር እና በሁለት ዓመት አገር አቀፍ የትምህርት ቤት ውድድሮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ውድድሮቹን ለማካሄድና ስፖርቱን ህዝባዊነት ለመጨመር እየሰሩ እንደሆነና በየጊዜው አበረታች ለውጦች መኖራቸውን ወይዘሮ አዜብ ይጠቁማሉ፡፡ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ስፖርቱን የሚያውቁትና ተወዳዳሪ የነበሩ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ስፖርቱን በቅርበት ስለሚያውቁ ችግሮቹ ላይ በትኩረት እንዲሰራ እንደሚያግዝ ይናገራሉ፡፡

ስፖርቱን በገንዘብ የሚደግፍ አካል በብዛት እንደሌለና ስፖርተኞቹ በተናጠል ስፖንሰር በመፈለግ እንደሚንቀሳቀሱ ይጠቁማሉ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አካላት ስፖርተኞቹ የውጭ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ዕድል ሲገጥማቸው የጉዞ ትኬት የማፈላለግ የመሳሰሉ ከገንዘብ ውጪ በተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ ዕድሎችን ያመቻቻሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የዓለም የቴኒስ ስፖርት ፌዴሬሽን ልምድ ላላቸው ተጫዋቾች የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ማንኛውንም እርዳታ እንደማያደ ርጉና ድጋፍ የሚሰጥ ከሆነም ለጀማሪ ታዳጊዎች አነስተኛ ቁሳቁስ ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የአሰልጣኝና የዳኝነት ስልጠናም ቢሆን በክፍያ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡ ማንኛውንም የስፖርቱን ዓለም አቀፍ ስብሰባ የሚካፈል ኃላፊ ወጪውን በግል እንዲሸፍን እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ለስፖርተኞቹ ስኬት በርካታ ውድድሮች ላይ መሳተፍ አስፈላጊ እንደሆነና ተጫዋቾቹ በርካታ ውድድር ባደረጉ ቁጥር ስፖንሰር የማግኘት ዕድላቸውንም እንደሚያሰፋ ያምናሉ፡፡ ውድድሩ በግል ደረጃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በስፋት መወዳደርን የሚጠይቅ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡

‹‹የዓለም አቀፍ የሜዳ ቴኒስ አሰራርን እኛ አንከተልም፡፡ ለምሳሌ የአምስት ዓመት የውድድር ዕቅድ ይሰጠናል፡፡ ዕቅዱ 100 ውድድር መሳተፍን የሚጠይቅ ነው፡፡ እኛ ግን ያንን ያህል ውድድር አንሳተፍም፡፡ የምንሳተፈው ውድድር ከፍተኛው ሁለት ነው፡፡ ውድድሩም ከዞንና ከአፍሪካ አያልፍም›› በማለት የዓለም አቀፍ ቴኒስ ፌዴሬሽን አሰራርን እንደማይከተሉ ይገልፃሉ፡፡ በምትኩ ግን የአምስት ዓመት እቅድ ማዘጋጀታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሜዳ ቴኒስ ፌዴሬሽን ትኩረት ውድድር ሳይሆን ስፖርቱን በአገር ውስጥ ማስፋፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ዋናው ትኩረታችን ስፖርቱን በአገር ውስጥ ማስፋፋት እንጂ ለአንድና ሁለት ልምድ ያለውን ተጫዋች ትልልቅ ውድድር ላይ በማሳተፍ የመንግሥት በጀትን ውድድር ላይ እንዲባክን አናደርግም፡፡ ልምድ ያላቸው ስፖርተኞች ስፖንሰር በማፈላለግ በግላቸው መወዳደር ይችላሉ›› በማለት በዓለም አቀፉ ሥርዓት መሰረት ልምድ ያላቸውን ስፖርተኞች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ማሳተፍ አለመሆኑን ወይዘሮ አዜብ ገልጸዋል፡፡

 

ሰላማዊት ንጉሴ

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።