‹‹በትኩረት ከተሠራ ከወንዶች በተሻለ ሴቶች የታክቲክ አረዳድ አላቸው›› Featured

11 Jan 2018

ከወጣት አሰልጣኞች ተርታ ይሰለፋል፡፡ እንደ ብዙሐኑ የስፖርት ሰዎች ወደ እግር ኳሱ የገባው በልጅነቱ ከአብሮ አደጎቹ ጋር የጨርቅ ኳስ በመግፋት ነው፡፡ ካደገበት ቢሾፍቱ ከተማ እስከ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊነት የደረሱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ወጥተዋል፡፡ እርሱ ግን ጉዳት በተጫዋችነት ብዙ እንዳይገፋ አድርጎታል፡፡ ጉዳቱን ተከትሎ ጫማውን የሰቀለው ፍሬው በተቃራኒው ብዕሩን በማንሳት የስፖርት ሳይንስ ትምህርት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ መማር ጀመረ፡፡ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ አካባቢው ላይ ወጣቶችን ሰብስቦ ሲያሰለጥን በመቆየት፤ ለብሔራዊ ቡድን ተመራጭ እስከመሆን የደረሱ እንደ አቤል ማሞ እና ሌሎች ተጫዋቾችን ለማሰልጠን ችሏል፡፡
የተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቢሾፍቱ ከተማን ለክረምት ወራት ቅድመ የውድድር ዝግጅት የሚመርጧት በመሆኑ የሚያ ሰለጥናቸውን ልጆች ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርጉ ዕድል አመቻችቶላቸዋል፡፡ ክለቦቹም የተሻለ ተስፋ ያላቸውን ወጣቶች እየወሰዱ ዕድል ይሰጧቸው ነበር፡፡ ይሄን የተመለከቱ የስፖርት ሰዎችም ፍሬውን ወደተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግር የሚችል የአሰልጣኝነት ዕድል ፈጠሩለት፡፡
በ2008 ዓ.ም ደደቢትን በአሰልጣኝነት በመቀላቀል የሴት እግር ኳስ ክለብ ማሰልጠን ጀምሯል፡፡ በክለቡ ብዙም ሳይቆይ የሁለት ዋንጫዎች ባለቤት ማድረግ በመቻሉ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ለመባል በቅቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሲዳማ ቡና ሴት እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሰልጣኝነት ጉዞ እና በአገሪቱ የሴቶች እግር ኳስ ደረጃ ዙሪያ ከአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ አሰልጣኝነት የገባኸው የስፖርት ሳይንስን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተምረህ ነው፤ ሳይንሱን መማርህ አሁን ለምትገኝበት አሰልጣኝነት ሕይወት ጠቅሞሃል?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ መማር ሰውን ይለውጣል፡፡ የድሮ እናቶች የሚወልዱት በቤት ነበር፤ አሁን ተቀይሯል፡፡ አሁን ምጧ የደረሰ እናት ወደ ሆስፒታል ነው የምትወሰደው፡፡ ምክንያቱም የሚመጣው አይታወቅምና በዘመናዊ ነገር ታምናለህ፡፡ በእርግጥ ድሮ ጥራት ያላቸው ብዙ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የእግር ኳስ ሳይንሱ ድሮ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሳይንሱ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች ይበልጥ ለማውጣት ያግዛል፡፡ ሳይንሱ በአብዛኛው ተጫዋቾች ከልጅነታቸው ጀምሮ ብቃታቸውን አውጥተው እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን እኔ ወደ ሲዳማ ቡና የገባሁት በወጣቶች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ከክለቡ ሃላፊዎች ጋር ተግባብቼ ነው፡፡
በእርግጥ በደደቢት ክለብ ሻምፒዮን ሆኜ ወደ ሲዳማ ቡና ስገባ በወጣቶች ላይ መስራቱ የሚፈጥረው ስጋት አለ፤ ምክንያቱም ሻምፖዮን ሆነህ ስትሄድ ሁሉም ስሙን መጠበቅ ይፈልጋል፡፡ እግር ኳስ ውለታ አያውቅም፡፡ ነገር ግን የክለቡ ፕሬዚዳንት ጋር ባደረግነው በቂ ውይይት ለማሰልጠን ተረክቤያለሁ፡፡ ሳይንሱን ለመማር የወሰንኩትም የኢትዮጵያ የሴቶችንም ሆነ የወንዶች ሊግ በቅርበት እከታተል ስለነበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ በተማሩ ሰዎች መመራት እንዳለበት አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሴቶች እግር ኳስ ላይ መስራት ለምን ምርጫህ አደረግክ?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- በወንዶችም በሴቶችም እግር ኳስ ላይ ብትሰራ አሰልጣኝነት ሁሌም ያው ነው፡፡ ለውጥ የለውም፡፡ ሴቶች እግር ኳስ ላይ የሚገባውን ያህል አልተሰራም እንጂ ቢሰራ ኖሮ ከወንዶች ያልተናነሰ አቅም አላቸው፡፡ ሴቶች ታክቲካል የሆኑ ስልጠናዎችን የመረዳት አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስልጠናን የመረዳት አቅማቸውና ስነምግባራቸውም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በደደቢት በነበረኝ ቆይታም እነ ወይንሸት፣ ብርቱካን፣ ሎዛ፣ ውባለም እንዲሁም ኤደን የነበራቸው የታክቲክ አረዳድ ከፍተኛ እንደነበር አስተውዬአለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሴቶች ከወንዶች የተሻለ የታክቲክ አረዳድ ካላቸው የሴቶች እግር ኳስ ለምን በዚያው መጠን መሻሻል አላሳየም?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- አንድ ወላጅ ቤተሰቡን በአግባቡ መምራት ካልቻለ ችግሩ የልጆቹ ሳይሆን የወላጅ ነው፡፡ ምንም ያህል እውቀቱ ቢኖርም እግር ኳስ ላይ ከታች ጀምሮ ካልተሰራ በስተቀር ስፖርቱን ማሳደግ አይቻልም፡፡ ተጫዋቾቻችን ሁሉም ነገር እያላቸው እግር ኳሱ ላይ ባሉ የመሪዎች ችግር ምክንያት አላደገም፡፡ ይህም የሴቶቹ ጥረት ፍሬ እንዳያፈራ ያደርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዳጠቃ ላይ የሴቶች እግር ኳስ በተለይም ከብሔራዊ ቡድን ውጤት አንፃር አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- የሴቶች እግር ኳስ በተመለከተ በብሔራዊ ቡድንም ይሁን በክለብ ደረጃ የሚሰጠው ትኩረት እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ የወንዶች ክለብ ከሌለ የሴቶች ክለብ የማይኖርበት ሁኔታ ይበዛል፡፡ በእርግጥ አሁን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶቹን ቡድን ሲበትን የሴቶችን ቡድን ማቆየቱ እንደ መልካም ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሴቶች ቡድን የሚሰጠውን አይነት ትኩረት ሌሎች ክለቦችም መስጠት አለባቸው፡፡ በክለብ ደረጃ የሴቶች እግር ኳስ በራሱ መቆም አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሴቶች እግር ኳስ የክለቦች ውድድር በየጊዜው የሚኖረው መሻሻል አጠያያቂ ቢሆንም በውድድር ደረጃ ሳይቋረጥ ዘልቋል፤ ይሄ ምን ያህል እግር ኳሱን ጠቅሞታል?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- ውድድሩ መኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይበልጥ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በፉክክሩ ላይ የተመጣጠነ ትኩረት የለም፡፡ አንዳንዶቹ ክለቦች ከትጥቅ ጀምሮ የሚያስፈልጓቸው ግብዓቶች ተሟልቶላቸው የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ግን ተመጣጣኝ ያልሆነ አነስተኛ ትኩረት ያገኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ በብሔራዊ ቡድን የሚመጣው ውጤት የክለቦች ነፀብራቅ ነው፡፡ ክለብ ላይ ጥሩ ውድድር ሳታደርግ የምትመጣ ተጫዋች ብሔራዊ ቡድን ላይ የሚፈለግባትን አስተዋፅኦ ልታበረክት አትችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሰልጣኝነት ቆይታህ ክልሎች ብቁ ተጫዋቾችን ከማፍራት አንጻር የሚያደርጉትን ጥረት እንዴት ትመዝነዋ ለህ?
አሰልጣኝ ፍሬው፡- ሁሉም ክልሎች የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡የሴቶችን ፕሪምየር ሊግ ከተመለ ከትከው ግን አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከደቡብ ብሄርና ብሄረሰቦች ክልል የመጡ ናቸው፡፡ በደደቢት እና ንግድ ባንክ ክለቦች ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች ከዚህ ክልል ወጥተዋል፡፡ ክልሉ ውስጥ እግር ኳስ ባህል ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ዘላቂነት ላይ ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡ አምና ከክልሉ ወረዳ የተወጣጡ 17 ልጆችን ይዤ ነው ስሳተፍ የነበረው፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ስድስት ልጆች ጨምሬ በአጠቃላይ ከ28 ተጫዋች 23 ልጆች ከወረዳ ነው ያሳደኩት፡፡ ከነዚህም ውስጥ ደግሞ የተሻለ ብቃት ያላቸው ልጆች የተሻለ ክፍያ ወዳላቸው ክለቦች ተዘዋውረዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ !
አሰልጣኝ ፍሬው፡- እኔም አመሰግናለሁ !

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።