«በእኔ ስም መንገድ በመሰየሙ ደስታዬ ወደር የለውም»- የክቡር ዶክተር አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ «የአባቴን ልፋትና ጥረት ሌላው ህብረተሰብ እንዲያውቅ አድርጌአለሁ»  - ጃገማ ዋሚ Featured

12 Jan 2018

ይህ በባለ ታሪኩ የሰማነው የእውነት የሆነ ታሪክ ነው፡፡ የአትሌቱ ሰፈር ነዋሪ የሆኑት ኮሎኔል ተክሉ የያዟትን ቮልስ መኪና ሲያሽከረክሩ ፈረንሳይ ኤምባሲ አካባቢ ቁልቁለቱ ላይ አትሌቱን ያዩትና ‹‹ ዋሚቾ ልሸኝህ?›› ይሉታል፡፡ ዋሚም ‹‹ እቸኩላለሁ›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ከመኪናዋ ቀድሞ የሚፈለገው ቦታ ላይ ሲደርስ፤ ዘግይታ የደረሰችዋን መኪና እያፌዘባት ‹‹ የአንተ ቆርቆሮ እንደማታዋጣህ አየህ!›› አለ፡፡ ኮሎኔሉ በንግግሩ ተደንቆ ማታ ላይ ግብዣ አደረገላቸው፡፡ ‹‹ዋሚ እቸኩላለሁ›› አለ ተብሎ እንደቀልድ እየተወራ ዘመናትን የተሻገረ እውነታ ሆኗል፡፡
እኛም «ዋሚ እቸኩላለሁ» አለ እየተባሉ ለዘመናት የሚወራላቸውን የክብር ዶክተር አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በህይወት እያሉ ሥራዎቻቸውን ለመዘከር ወድደን ከገና በዓል ማግስት ከቤታቸው ተገኘን፡፡ እኝህ ሰው ሩጫና ፉክክር በኢትዮጵያ በወጉ እንዲታወቅ ካደረጉ ጥቂት ፊታውራሪዎች መካከል ከዋነኞቹ ጎራ ስለመሰለፋቸው በርካቶች ያነሳሉ፡፡ መረጃዎችን ስናገላብጥ ይህን አገኘን፡፡
አበበ ቢቂላ የሮምን ማራቶን በባዶ እግሩ ፉት ብሎ ካጠናቀቀ በኋላ በድጋሜ 42 ኪሎ ሜትር እንደሚሮጥ ሯጭ ሰውነቱን ሲያፍታታ የተመለከቱ ጋዜጤኞች በመገረም «አይደክምህም እንዴ?» በማለት በአድናቆት ሲጠይቁት፤ የአበበ መልስ ይበልጥ አስደንግጧቸው ነበር፡፡ ጋዜጠኞቹ ጠጋ ብለው ሲጠይቁትም «እኔ የዓለም አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ሯጭ ነኝ» ሲል መለሰላቸው፡፡ «እንዴት? ኢትዮጵያ ካንተም የተሻለ ሯጭ አላትን?» ሲሉም በድጋሚ ጠየቁት፤
«አዎን እሱ ስለታመመ እኔ ወዲህ መጣሁ፤ ቢመጣ ኖሮ ጀግንነቱን ትመለከቱ ነበር!» ሲል አበበ መለሰላቸው፡፡ ጋዜጠኞችም ተገረሙ፡፡ ተገርመውም ወሬውን አራገቡት፡፡ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ሯጯ ድል አደረገች ሲሉም አጧጧፉት፡፡ አበበ ቢቂላ በኩራትና በአድናቆት አክብሮቱን የገለጸለት ታላቅ አትሌትም የክብር ዶክተር አትሌት ሻምበል ባሻ ዋሚ ቢራቱ ነበር፡፡
አንጋፋው የብስክሌት ተወዳዳሪ ገረመው ደንቦባም ‹‹ በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ውድድር ላይ ማንም ሰው ተከትሎት አይገባም ነበር፡፡ ቁመናው፣ ጥንካሬው፣ ብርታቱ፣ ሁሉ ነገሩ ለሩጫ የተፈጠረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀውንና እንዲህ በአድናቆት የሚመለከተውን ሩጫ በሚገባ ያስተዋወቀ ዋሚ ነው፡፡ በየቀኑ ከሱሉልታ አዲስ አበባ ጠዋትና ማታ ይሮጥ ነበር::›› ማለቱም በማይነጥፈው ታሪክ ተከትቧል፡፡
ከተለያዩ አካላት እውቅና እየጎረፈላቸው የሚገኙት ጀግናው አትሌት ዋሚ ቢራቱ በቅርቡ በአሮሚያ ክልል አዳማ ከወንጂ ማዞሪያ እስከ ፈጣን መንገድ መግቢያ ድረስ ያለው መንገድ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡ በህይወት እያሉ ይህንን ታሪክ ማየታችው ምን ያክል እንዳስደሰታቸው ለማወቅ ከእርሳቸውና ከ10ኛ ልጃቸው ጃገማ ዋሚ ጋር ቆይታ አደረግን፡፡
በህይወት እያሉ ይህ መደረጉ ምን ፈጠረብዎት? የመጀመሪያ ጥያቄያችን ነበር፡፡ ‹‹የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በእኔ ስም መንገድ በመሰየሙ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ተግባሩ ትክክለኛና የሚገባ ነው፡፡ ለዚህም ክልሉ ሊመሰገን ይገባል፡፡ በወቅቱ ማህበረሰቡ በድምቀት በተሞላበት ሁናቴ አቀባበል ስላደረገለኝ ትልቅ አክብሮትና ምስጋና አለኝ፡፡ የተደረገልኝ ነገር በሙሉ ከውስጤ እንዳይጠፋ ተደርጎ ተስሏል፡፡›› ፈገግታ በተሞላበት ፊትና ሲቃ በታጀበበት አንደበት የመለሱልን ነው፡፡
አትሌቱ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የተደረገ ላቸው የእውቅና የማዕረግ ሽልማት እያስገረማቸው በህይወት እያሉ ባልጠበኩበት ወቅት ይህን ማየታቸው ዕድለኛ አድርጓቸዋል፡፡ ለእርሳቸው የተደረገው መልካም ተግባር የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህዝብ ብሎም የዓለም ማህበረሰብን በሙሉ የሚያስደስት ነው ብለውም ያምናሉ፡፡
‹‹ድሮ ስሄድ መኪና አልጠቀምም፤ መኪና እግሬ ነው፣ መሪ ዓይኔ ነው፣ አሁን ላይ መሪዬ ስለተበላሸች ወጣ ብዬ ለመግባት እቸገራለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በህይወቴ ሁሉም ነገር ስለተሳካልኝና እኔን እውቅና ሰጥተው ታሪኬ እንዲቆይ ላደረጉልኝ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ የማይሞት ታሪክ ተተክሎልኛል›› በማለት የመንገዱ ስያሜ በስማቸው በመሆኑ የፈጠረላቸውን ልዩ ደስታ ገልጸዋል፡፡
‹‹በእርግጥ ስፖርትንና የስፖርት ሜዳን አልጠገብኩም›› የሚሉት አትሌቱ፤ በቅርቡ በተካሄደው የታላቁ ሩጫ ላይ እሳተፋለሁ ብለው ሳይሳካላቸው መቅረቱን ነግረውናል፡፡ ሆኖም አሁንም ከሁለት ኪሎ ሜትር እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ለመወዳደር ዝግጁ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡
‹‹አዛውንቶች መወዳደር በሚችሉባቸው መድረኮች ላይ እሳተፋለሁ፡፡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ፍላጎቴን አውቆ ሊያሳትፈኝ ይችላል፡፡ በውድድር ቦታ ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ወጣቶችና ለአዛውንቶች ምሳሌ ለመሆን ጅምናስቲክ እየሠራሁና እያሠራሁ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ የደስታዬ ጫፍም ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔና ስፖርት በእጅጉ ተቆራኝተናል፤ ምናልባትም ስፖርት መሥራቴን የማቆመው ከዚህ ዓለም በሞት ስልይ ብቻ ይሆናል፡፡›› በማለትም የወደ ፊት ፍላጎታቸውን ጭምር አብራርተዋል፡፡
‹‹በየጊዜው ስለ እኔ የሚያወሩት የሚዲያ አካላትና ግለሰቦች እንዲሁም ተቋማት ይህንን ክብር እንዳገኝ ስላደረጉኝና የሁሉም ትብብር ስላለበት ምስጋዬ ወደር የለውም፡፡ ሚዲያዎች ድምፅ ባያሰሙልኝ ኖሮ ይህን ሁሉ ዕድል ባለገኘሁ ነበር፡፡ በህይወቴ ኖሬ ሁሉን በማየቴና በመስማቴ ከልብ የመነጨ ምስገና ይድረሳቸው፡፡ መንግሥትም ለሌላው ተምሳሌት የሚሆን ታሪክ ስላሰፈረልኝ እያመሰገንኩት ይህ ቀጣይነት ያለው ተግባር መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ይህን ክብር ያላገኙ ሌሎች አንጋፋ ስፖርተኞች እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡›› በማለትም ስሜታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጃገማ ዋሚ የክብር ዶክተር አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ 10ኛ ልጅ ሲሆን፤ ዋሚ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍረካ አትሌቲክስ አባት ናቸው ይላል፡፡
የአባቴን የአትሌቲክስ ህይወት አሁን ስናነሳ የሩጫ ዘመኑ 65 ዓመት ያክል ነው፡፡ በእነዚህ በርካታ ዓመታት በአትሌቲክሱ ጸንቶ ቆይቷል፡፡ እኔ ከዚህ በፊት የእርሱን ልፋትና ጥረት ሌላው ህብረተሰብ እንዲያውቀው አድርጌአለሁ፡፡ መጋቢት 11 እስከ 15 1996 ዓ.ም ‹‹ዋሚና አትሌቲክስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት›› በሚል መሪ ቃል፡፡ በአዲስ አበባ ብሄራዊ ሙዚየም ላይ የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን አዘጋጅቼ ነበር ይላል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጋር አያይዤ በዓለም ላይ ያለ ማቋረጥ ረጅም ጊዜ የሮጠ በማለት ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የዓለም የሳቅ ንጉሥ በላቸው ግርማና አባቴ የተሳተፈበትን የሰባት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ማዘጋጀት እንደቻለ ገልጾልናል፡፡
ዋሚን ልዩ የሚያደርገው በሁሉም ርቀት የሩጫ ውድድር ላይ መሳተፉ ነው፡፡ 1ሺህ አምስት መቶ ሜትር፣ 3ሺህ ሜትር፣ አምስት ኪሎ ሜትር፣ አስር ኪሎ ሜትር አገር አቋራጭ፣ 21ኪሎ ሜትር፣ 32ኪሎሜትር ሙሉ ማራቶን 42ኪሎ ሜትር ድረስ ሮጧል፡፡ ይህንን ሁሉ መሳተፉ ትልቅ የጥንካሬ መንፈስ ስላለው ነው የሚለው ልጃቸው፤ ትውልዱ እንዲያውቀውና እንዲያስታውሰው በኤግዚቢሽን መልክ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለውለታዎች እነማን እንደነበሩ የሚጠቁም መርሀ ግብር ማዘጋጀቱንም ጠቅሷል፡፡ ከእዚህ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አመጣጥን የሚገልጽና ሻለቃ ዋሚ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በተለያዩ ዶክመንቶች እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡ የዋሚ ጽናትና ትዕግስት ዛሬም ድረስ መኖሩን የሚናገረው ጃገማ፤ እስከ አሁን ድረስ ከስፖርት አለመለየታቸውንና በእዚህ ዕድሜያቸው ለማመን የሚያስቸግሩ ጅምናስቲኮች እንደሚሠሩም ጠቁሟል፡፡
ጃገማ፤‹‹አባቴ በአካል ሲታይ ያረጀ ይምሰል እንጂ አዕምሮው ግን አሁንም አላረጀም፡፡ በእንዲህ አይነት መልኩ ላለ ሰው ደግሞ ክብር መስጠት ከሰውየውም አልፎ ለአክባሪውም ደስታን ይፈጥራል፡፡ ለአንድ ቤት መቆም ወሳኝ መሰረት ነውና መሰረትን ማሰብ ያስፈልጋል፤ ስለዚህ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ያደረገውን አስተዋጽኦ በመመልከት የተደረገለት ነገር ሁሉ የሚመጥነው ተግባር ነው›› ሲል ያብራራል፡፡
ጃገማ በአባቱ ስም መንገድ መሰየሙን አስመልክቶ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ፤ ‹‹የአዳማ ከንቲባና አመራሮች ሁሉ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ይህንን የተቀደሰ ሃሳብ በተግባር ማዋላቸው የሚያስመሰግን ሥራ ነው፡፡ መንገዱ በእርሱ ስም መሰየሙ እንደቤተሰብ ሁላችንንም አስደስቶናል፡፡ ከእኛም አልፎ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የስፖርት ቤተሰቡን ያስደሰተ ተግባርነው፡፡ በእርግጥ መቶኛ ዓመቱ በሚከበርበት ወቅት የአደባባይ ስያሜ እንዲኖር ደብዳቤ ማዘጋጃ ቤት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ በአደማ የተደረገው ግን ሳይታሰብ ድንገታዊ ነበረ፡፡ ይህም ምን ያህል ለእርሱ ትልቅ ቦታ እንደሰጡት የሚያሳይ ነው፡፡›› ሲልም ስሜቱን ገልጿል፡፡
‹‹እንኳን ለዜጎቻችን ቀርቶ ለውጭ ዜጎች ስም እየተሰጠ ነው›› የሚለው ጃገማ፤ በተለይ አገር ቤት ውስጥ ያሉና ለአገር ትልቅ ውለታ የዋሉ ሰዎችን ማሰብ ልምድ መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡ የተጀመረው ሥራም እግረ መንገዱን ታሪክን ከማቆየቱ ባሻገር ለባለ ታሪኮች በብርና በቁሳቁስ የማይተመን ደስታን ሊሰጣቸው እንደሚችል ገለጿል፡፡ ተግባሩ ቀጣይነት ኖሮት በሁሉም ቦታ መታወስ የሚገባቸው ባለ ታሪኮች እንዲታወሱበትም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የአባቱ ጥንካሬ ብዙ ነገርን ያስተማርው ጃገማ፤ የአባቱን ታሪክ በተቻለው መጠን በምስል በመቅረጽና በጽሑፍ በማዘጋጀት ታሪኩ ሳይሸራረፍና በክብር እንዲቀመጥ እያደረገ ሲሆን፤ ጃገማ እንዳለውም፤ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ ዋሚ አንድ ምዕተ ዓመት ከአንድ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ከቤታቸው ወጥተው ያዩዋቸው ሰዎች እስከአሁን በህይወት መኖራቸው ያስገርማቸዋል፡፡ ይህም ለሰዎቹ ልዩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ለእርሱም ቢሆን ጽናትን፣ የአገር ፍቅርን፣ ሰው አክባሪነቱን፣ ሠርቼ አልጠገብኩም ባይነትን እንዲሰርጽበት አድርጓል፡፡ ለጊዜ ዋጋ ከመስጠታቸው የተነሳ የዱሮ ትዝታዎችን የሚናገሩት ቀንን ጠቅሰው መሆኑ ደግሞ ምን ያክል አሁንም ድረስ አዕምሯቸው ብሩህ እንደሆነ ያሳያልም ይላል፡፡
ዋሚ ቢራቱ ታዋቂዎቹን ማሞ ወልዴንና አበበ ቢቂላን አሠልጥነዋል፡፡ ሁሉም ከእርሳቸው የማያልቅ ፍቅርን ተምረዋል፡፡ ትልቅ ተስፋን የሰነቁና ህልማቸውንም ማሳካት የቻሉ የአገር ባለውለታም ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው በእንዲህ ዓይነት መልኩ በስነ አዕምሮው ዝግጁ ከሆነ ያሰበበት መድረስ ይችላልም ባይ ናቸው፡፡ እነርሱ የአትሌቲክሱ መሰረት ናቸው መልካም ዘርንም ዘርተዋል፡፡የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ታሪክ የሠሩና የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ እንዲውለበለብ ያደረጉትን አርአያ አድርጎ መከተል ይገበዋልም ይላሉ፡፡
ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ስድስት ወንዶችን አምስት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ከእነዚህም 27 የልጅ ልጅ እና 20 የልጅ ልጅ ልጅ ማየት ችለዋል፡፡እርሳቸው አሁን ጡረተኛ ናቸው፡፡ የዓይንና የጆሮ ችግር ካልሆነ በቀር ጤንነታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ በእርሳቸው ውስጥ ያለው ጥንካሬ ግን ጡረታ አልወጣሁም እያስባላቸው ነው፡፡ ጡረታ ከወጡ በኋላም ልጆችን በማማከር፣ በማሰልጠንና በማወዳደር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ዝግጅት ክፍሉም በህይወት ያሉ እንቁዎቻችንን ካለፉ በኋላ መዘከሩ እንዳለ ሆኖ በህይወት እያሉ ማስታወስና እውቅናመስጠት ከገንዘብ ይልቅ ትልቅ የመንፈስ እርካታ ስላለው፤ ይህ ዓይነቱ ተግባር በሌሎችም አካባቢዎች ቢሰፋና ቢደጋጋም ለሌላው ተነሳሽነትን ይፈጥራል እንላለን፡፡
ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በተለያዩ የሩጫ መድረክ ላይ አገራቸውን ያስጠሩ ድሎችን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በ1ሺ500፣ 3ሺ፣ 5ሺ፣ 10ሺ፣ 21ኪሜ፣ 25ኪሜ፣ በ32ኪ.ሜ በአገር አቋራጭ እና የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ 51 የወርቅ፣ 44 የብር እና 30 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡ 21 ሰርተፍኬት፣ 4 ዲፕሎማ እና ከ40 በላይ ዋንጫዎችን ወስደዋል። በተለያየ ወቅትም የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አስችለዋል። የሶምሶማ ሩጫ በአገራችን እንዲለመድ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውም በታሪካቸው ተቀምጧል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።