ስታዲየሙ ዝም ሲል Featured

11 Feb 2018

ዛሬ ስለ እግር ኳስ እንፅፋለን። ስንፅፍ ግን አሁን ከሚታየው እና በመረጃ ብዛት ናላን ከሚያዞረው የወቅቱ ፋሽን ገለል ብለን ነው። ይህን ስንል የሁሉም ቀልብ የሚያርፍበትን «ክቧን ኳስ» በተለየ የታሪክ እና የግል ምልከታ ላይ በማተኮር ሚስጥሯን ለማወቅ እንታትራለን ማለት ነው። ይህን ማግኘት የምንችለው ደግሞ የግዴታ አሁን በእግር ኳሱ ላይ ያለውን ፋሽን ወደኋላ ተወት አድርገን ባልተሄደበት መንገድ መጓዝ ስንችል እንደሆነ እናምናለን። መቼም ሳናምን አንፅፍም!
ምስጢር -1
በሆነ አጋጣሚ በአንድ ባዶ የእግር ኳስ ስታዲየም ውስጥ ተገኝታችሁ ታውቃላችሁ? ይህን አጋጣሚ ካላገኛችሁ ለማግኘት ሞክሩ። በስታዲየሙ ውስጥ እንደገባችሁ ቀጥታ ወደ መሀል ሜዳው ሂዱና ለትንሽ ደቂቃ ዝም ብላችሁ ቁሙ። እኔ እላችኋለሁ፤ ከዚህ በፊት ፀጥ ያለ አካባቢ አጋጥሟችሁ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ልክ በዚያ ስታዲየም ውስጥ እንዳለ ፀጥታ ሌላ የትም ሊኖር እንደማይችል በቦታው ስትሆኑ ትገነዘባላችሁ። ባዶነት እራሱ በስታዲየሙ ውስጥ ባዶ ይሆናል። ይህ የሚሆነው ግን ፍፁም ከእግር ኳስ የራቃችሁ እና በስታዲየሙ ውስጥ ቅንጣትም ትውስታ የሌላችሁ ከሆነ ብቻ ነው።
እስቲ ወደኋላ መለስ ብለን ታሪክ የሚያስታ ውሳቸውን ስታዲየሞች ሰው በተሞላባቸው ጊዜያቶች የደስታ ሲቃ እና የጠለቀ የሀዘን ስሜት ሲያስተናግዱ እንመልከት። ይህን ስንል ዶሴው እንድናስታውስ የሚያስገድደን የ1966ቱን የዓለም ዋንጫ ነው። የዌምብሌ ስታዲየም ተጉዛችሁ ብቻችሁን ስታዲየሙ ውስጥ ብትታደሙ የእግር ኳስ ፈጣሪዎቹን ድል በደጋፊዎቹ አስረሽ ምቺው እስካሁንም ድረስ ሲያስተጋባ ታደምጣላችሁ። ምዕራብ ጀርመንን በመርታት የድል ፅዋውን ከፍ ያደረገችው እንግሊዝ እና ዜጎቿ ደግሞ ሌላ የአለም ዋንጫ ድል እስካላጣጣሙ ድረስ በዚህ ስታዲየም ሲገኙ ይህ ድምፅ ያቃጭልባቸዋል። ሁልጊዜም የማይረሱት እና የሚያጣጥር የሲቃ ድምፅ የሚሆንባቸው ደግሞ የ1953 የሀንጋሪ የ6ለ3 ሽንፈት ነው።
60 አመታትን ወደኋላ መለስ ስንል የምንመለከተው ዌምብለይ ስታዲየም የአለም ዋንጫን ከማንሳት በላይ እንደ እሾህ የሚቆጠቁጥ ሽንፈት እንዳስተናገደ ነው። ድል ብቻ ሳይሆን መረታት በሜዳው ውስጥ እኔ እብስ እኔ እብስ እያሉ ሲሽቀዳደሙ ከጫጫታም በላይ የሆነ ግርታ በአይምሯችሁ ውስጥ ይከሰታል።
አሁንም እዛው ስታዲየም ውስጥ ነን ። ነገር ግን በሌላ ሰፍራ የሚገኝ የእግር ኳስ ቤት። ብራዚል ማራካኛ ስታዲየም እንገኛለን። ይህ ወቅት ለብራዚላዊያን፤ ሊያውም እግር ኳስን በቅንጦት ለሚጫወቷት ደቡብ አሜሪካውያን እንደ ዱብዳ የሚቆጠር ጊዜ ነው። በቡድን ድልድል ውስጥ የነጥብ ብልጫ ያለው ብቻ የአለም ዋንጫውን በሚያነሳበት የጊዜው ውድድር፤ ለፍፃሜው ከኡራጋይ ጋር የገጠመችው ብራዚል ብልጫ ወስዳ ድልን ለመጎናፀፍ አለመሸነፍ ብቻ ይበቃት ነበር። ይህ አልሆነም። በባላጋራዋ የ2ለ1 ሽንፈት ተከናነበች። የምትጓጓለትን ዋንጫ በግዳጅ ተነጠቀች።
ብራዚላውያን በሌሎች የአለም ዋንጫ ድሎች ቁስላቸው ቢሽርላቸውም የማራካኛ ስታዲየም ግን እስካሁንም ድረስ በዝምታ ውስጥ የሀዘን እንጉርጉሮን ያዜማሉ። ዝም ሲል ብሶት ይተናነቃቸዋል። በአርጀንቲናም ይሄ ታሪክ ያው ነው። በቦነስ አይረስ የሚገኘው ባለ አራት መአዘኑ የቦምቦኔራ ስታዲየም የድል እና ሽንፈት ከበሮ ሲደለቅበት ግማሽ ክፍለ ዘመን አለፈው። በዚህ ጉዳይ ላይ የሜክሲኮው አዝካ ስታዲየም ተመሳሳይ ድምፅ ያስተጋባል። በባህላዊው የአገሬው ሚጥሚጣ እንደመለብለብ አይነት ሀዘን። ደግሞም በድል ቃጠሎውን እንደማጥፋት። ይህ ሁሉ ግን በዝምታው ውስጥ ብቻ የሚደመጥ ድምፅ ነው።
ወደ ጣሊያኗ ሚላን ልውሰዳችሁ። ጊውሴፔ ሜዛ ስታዲዮም። እግር ኳስን ተጫውተው ያለፉ ጥበበኛ መንፈሶች ምሽት ምሽት ኳስን ከመረብ እንደሚያገናኙበት አንዳች ነገር ስታዲዮሙን ስታዩ ይነግራችኋል። ዳኛው የተሰራውን ጥፋት ለማስቆም «ፊሽካውን» እንደሚያፈነዳበት ጥርጥር የለውም። ይሄ ስታዲየም ዝም ቢል እንኳን ዝም አይልም። ምክንያቱም ብዙ የፈንጠዝያ እና ቅስም የሚሰብር የእግር ኳስ ክስተቶችን አስተናግዷል። እያንዳንዱ የስታዲየሙ ጥጋት ዘመን የሚያስታውሰው ታሪክ አለው። በዚህኛው ጎን ከመቀመጫ ብድግ የሚያስብል አስደናቂ ጎል ተመልካቹ ሲያይ፤ በሌላኛው ጎን ደግሞ እጅን አፍ ላይ አስጭኖ አይን የሚያስፈጥጥ መሳት የሌለበት ግብ ተቆጥሯል።
ታዲያ ይሄን ሁሉ ታሪክ ተሸክሞ የሳን ሴሮው ስታዲየም እንዴት ዝም ሊል ይችላል። ቢያንስ ቢያንስ አፍ አውጥቶ ባይናገር በጥሞና ለተመለከተው ሁሉ አንዳች የሚከብድ መንፈስ አንደረበበበት በሚስጥር ያሳብቃል እንጂ። አሊያማ ከሳውዳረቢያው ከ«ኪንግ ፉዓድ» ስታዲየም ምን ይለየዋል። በበረሀ መሀል እንዳለው። ከበረሀው በላይ በረሀ እንደሆነው። የተመልካች ድርቅ በየጊዜው እንደሚመታው። በዚህ ስታዲየም ውስጥ ኳስ ማንከባለል ቅሪላ ከመግፋት አይተናነስም። ኳስ ያለ ተመልካች እንዲህ ውበቷን ታጣለች እንዴ? ኳስ ያለ የሚያስገመግም የድጋፍ ድምፅ እና ቁጣ ብቻዋን የምታወጣው ድምፅ ከመደበርም በላይ ይቀፋል። እንደገና ደግሞ ምንም ታሪክ ያልተሰራበት ባዶ ስታዲየም ከውሃ ማጠራቀሚያ ጋን የተለየ ቁስ አለመሆኑን ነገርየውን ልብ ብሎ ለታዘበው በቂ ግንዛቤን ያገኝበታል። ከኪንግ ፋዓድ ስታዲየም ውጪ የዘረዘርናቸው ሜዳዎች ግን ድቡልቡሏ የእግር ኳስ ከፀሀይ እና ከጨረቃ እኩል ገዝፋ እንድትታይ ውበት ደርበውላታል።
ሁልጊዜም ቢሆን እነዚህ ስታዲየሞቹ ጨዋታዎችን ሲያስተናግዱ በባለሜዳው ደጋፊዎች ያሸበርቃሉ። ልክ እንደ ንጉስ ቤተ መንግስት «ካስትል» ግርማ ሞገሳቸው በእጥፍ ይጨምራል። ባላንጣዎች ጥቂት ስፍራ ይፈቀድላቸዋል። ሆኖም ድምፃቸው ካሉበት ቦታ ግዘፎ ነስቶ መላው ስታዲየም ውስጥ ይንሰራፋል። ነጩ የሜዳ መስመር ሁለቱን ባላጋራዎች ጨዋታው እስኪጀመር እንደ ድንበር ይለያቸዋል። ሁል ጊዜም በግራና በቀኝ ያሉት የግብ አግዳሚዎች ጀርባ ያሉ ደጋፊዎች የሚቀመጡባቸው ቦታዎች የአደጋ ቀጣና ይባላሉ «danger zone» በደጋፊዎቹ ጩኸት በረኛች እጃቸው ኳስን ከመያዝ ትቦዝናለች። አጥቂዎች እግራቸው ቄጤማ ይሆናል። የበረታ የድል ፅዋውን ሲጎነጭ፤ ሌላኛው መሪር ሽንፈትን ይከናነባል። አንገት ለአንገት የተናነቁት ተከባብረው በእኩል ውጤት ይለያያሉ። ስታዲየሞች ያኔ ነው ከባዶነት ተነስተው ታሪክ መሸከም የሚጀምሩት።
ምስጢር -2
እግር ኳስ ከሰላማዊ ጦርነት የዘለለ አጋጣሚን ያስተናግዳል። መጫወት ከመሸናነፍ ጋር ሲደበላለቅ የክብር ጉዳይ ይመጣል። ድንገት መሀል ሜዳ ላይ ግጭት ይፈጠራል። ደጋፊዎች በወንበር ይፈነካከታሉ። ከጨዋታው በኋላ በሚፈጠር ግጭት በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ የሰው ልጅ ህይወት ይቀጠፋል። ኳስ ድምፅ፣ ትንፋሽ፣ ጉልበት ብቻ ሳይሆን ደም ይከፈልባታል። እግር እንክት ብሎ እስከወዲያኛው ላይመለስ ይሰናበታል። ልብ መሮጥ ደክሟት መሀል ሜዳ ላይ ቀጥ ብላ እስከወዲያኛው አለምን ትሰናበታለች። አለም ላይ ግጭትን ያስነሳሉ ተብለው እሹሩሩ ከሚባሉት ሀይማኖት እና ፖለቲካ ባልተናነሰ በእግር ኳስ ጨዋታ ብቻ ስፍራዎች የጦርነት አውድማ ይሆናሉ። አንዳንዶች እንዲያውም ጠንከር ያለ ብያኔ ሲሰጡ «በእግር ኳስ ግጭትና ጥላቻ አይፈጠርም ማለት መሀረብ እንባን አይጠርግም ብሎ እንደመከራከር ነው» በማለት ይደመድማሉ።
እስቲ ይሄን ጉዳይ ጠንከር አድርጎ ወደሚያስረዳን እንድ ታሪክ እንመለስ። ጊዜው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1969 ነበር። ሁንዱራስ እና ኤል ሳልቫዶር በሚባሉ ሁለት በጣም ደሀና ሚጢጢዬ የመካከለኛው አሜሪካ አገራት ቅልጥ ያለ ጦርነት
ተነሳ።

ዳግም ከበደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።