የሲቲ ካፑ ማሳረጊያ Featured

13 Feb 2018

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በገቢ ራሱን ለማጠናከር፣ክለቦች ራሳቸውን እንዲፈትሹና ተጫዋቾቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ዕድል ለመፍጠር የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድርን በየዓመቱ እንደሚያካሂድ ይታወቃል።ዘንድሮ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የተካሄደው 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የተዋጣለትና ፌዴሬሽኑ ያልጠበቀውንና በሲቲካፑ ውድድር ታሪክ ሪከርድ የሆነ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የተገኘበትም ነው።
ስድስት የአዲስ አበባ ክለቦችና ሁለት ተጋባዥ ክለቦች ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2010 ድረስ የተፋለሙበት ይህ ውድድር በመጨረሻው የዋንጫ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናንና ቅዱስ ጊዮርጊስን አገናኝቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አሸናፊነት መጠቃለሉ ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በከተማዋ ለሚገኙ ተሳታፊ ክለቦች ከውድድሩ ገቢ ድርሻቸውን ያከፋፈለበትን የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት በጁፒተር ሆቴል አካሂዷል። በሥነ-ሥርዓቱ ፌዴሬሽኑ ለተለያዩ አካላት እውቅና ከማበርከቱ ባሻገር ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የገዛውን የ100 ሺ ብር ቦንድም ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስረክቧል። የክለቦቹ ተወካዮች በበኩላቸው ክለቦች በቅድመ ውድድር ራሳቸውን የሚመለከቱበት መልካም አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ያስረዳሉ።
የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ፌዴሬሽኑ በከተማዋ ለሚገኙ የሲቲ ካፑ ተሳታፊ ስድስት ክለቦች ከአንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺ ብር በላይ አከፋፍሏል።
በሥነ-ሥርዓቱ የውድድሩ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ 500 ሺ ብር በመውሰድ ቀዳሚ ሲሆን፣ በሁለተኝነት የጨረሰው ኢትዮጵያ ቡና 433 ሺ ብር ተረክቧል። ውድድሩን በሦስተኝነትና አራተኝነት ያጠናቀቁት ኢትዮ ኤሌክትሪክና መከላከያ ስፖርት ክለቦች እያንዳንዳቸው 133 ሺ ብር፣አምስተኛና ስድስተኛ በመሆን የጨረሱት የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ክለብና ደደቢት ስፖርት ክለብ እያንዳንዳቸው 100 ሺ ብር ተረክበዋል።
የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በእግር ኳስ ውስጥ ባለፉ ሰዎች የተደራጀ መሆኑ አንድ የውድድሩ ስኬታማነት ምስጢር መሆኑን አቶ በለጠ ይናገራሉ። «ሕብረተሰቡ ስለውድድሩ በቂ መረጃ እንዲያገኝ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የፈጠርነው ግንኙነትና ተጋባዥ ክለቦች ሻምፒዮን ከሆኑ ዋንጫውን መውሰድ ይችላሉ» የሚል አዲስ ደንብ ይዘን መቅረባችን ሌሎች የስኬቱ ምንጭ ናቸው» ሲሉ ሰብሳቢው ይገልጻሉ፡፡
በተለይ የደንቡ መሻሻል ተጋባዥ ክለቦች አሸናፊ ለመሆን እንዲጫወቱ ስላደረጋቸው ፉክክሩን ከሚጠበቀው በላይ አድርጎታል የሚል ሃሳብም ይሰጣሉ። በውድድሩ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ውድድሮች ያልነበረው የጨዋታው ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ መደረጉ ለውድድሩ ድምቀት የራሱ አስተዋፅኦ እንደነበረው ይገልጻሉ።
ክለባቸው በየዓመቱ የሲቲካፕ ውድድሩ ተሳታፊ መሆኑንና ውድድሩ ክለቦች በዝግ ጅት ሂደት እያሉ መካሄዱ ከአዳዲስና ነባር ተጫዋቾች ተሰላፊዎችን ለመለየት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው የሚናገሩት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ዮሴፍ ፣የዘንድሮው ውድድርም የክለቡ ደጋፊዎች በትኩረት የተመለከቱትና ውጤቱም የሚደነቅ እንደሆነም ይናገራሉ።
አቶ ጌታቸው ክለቡ ካለፉት ዓመታት የተሻለ የገንዘብ ድርሻ ማግኘቱን ተናግረው፥በቀጣይ ክለባቸው ከውድድሩ ተሳትፎ የሚያገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተዘጋጀ መሆኑን ይጠቁማሉ።
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ግርማ አስራት በበኩላቸው፣«የሲቲ ካፑ ውድድር በከተማዋ ለሚገኙ ክለቦች ወሳኝ ውድድር ነው፣በቅድመ ዝግጅት የሚገኙ የፕሪሚር ሊጉና ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ክለቦችን ተጠቃሚ ያደርጋል»ይላሉ።
አቶ ግርማ እንደሚያስረዱት፤ውድድሩ አዳዲስ ተጫዋቾች የሚታዩበት፣ነባር ተጫዋቾች አቋማቸው የሚገመገምበት ነው።ከዚህ ባሻገር በከተማዋ የሚገኙ ክለቦችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ውድድር በመሆኑ ለከተማዋ የእግር ኳስ ዕድገት ወሳኝ ነው።በተለይ በቀጣይ አስሩም ክፍለ ከተሞች ለሚያቋቁሟቸው የእግር ኳስ ክለቦች መጠናከር እገዛው ተጠቃሽ ነው።
በሥነ-ሥርዓቱ ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊድያ ታፈሰ በፌደሬሽኑ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።ፌዴሬሽኑ በቅርቡ የጤና መጓደል አጋጥሟቸው በመታከም ላይ ለሚገኙት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ስዩም አባተ የእውቅና ሽልማትና የ10ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል።
ፌዴሬሽኑ የዘንድሮውን ገቢ በከተማዋ እግር ኳስ ተኮር ሥራዎችን እንደሚያካሂድበት የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ በለጠ ማብራሪያ፤የተለያዩ የውስጥ ውድድሮችን የሚያካሂድባቸውን የጃን ሜዳ ቁጥር ሁለትና ሦስት ሜዳዎችን አስጠርጓል።የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረትን ለመቀነስ ከከተማዋ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ ጋር በመተባበር ምቹ በማድረግ ውድድሮችን ለማስፋት በየክፍለ ከተማው ያሉት ሜዳዎችን ለማስተካከል እየተዘጋጀ ይገኛል።የዳኞችና የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን አቅሙን ለማጠናከርም ሙያተኞችን ለመቅጠርም አስቧል።
የጊዜያዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ፌዴሬሽኑ በ13ኛው ውድድር የሲቲካፑን ጥራት የሚያሳድጉ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ለመምጣት ማሰቡን ይናገራሉ።እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፌዴሬሽኑ በሚቀጥለው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር የሌሎች አገራት እግር ኳስ ክለቦችን በመጋበዝ የውድድሩ ተሳታፊ ለማድረግ አስቧል።የሲቲ ካፑ ተጋባዥ የክልል ክለቦች ከስታዲየም ገቢ የገንዘብ ድርሻ እንዲያገኙ ለማድረግም አቅዷል።

በሪሁ ብርሃነ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።