እንስቶች ያደመቁት ሩጫ Featured

12 Mar 2018

ስፖርት በየትኛውም ጉዳይ ውስጥ በመግባት ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚችል ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል። የስፖርት አውዶች በርካታ ሰዎችን በአንድ የሚያገናኙ እንደመሆኑ መልዕክትን ለማስተላለፍ በምቹነታቸው አቻ አይገኝላቸውም። ከዚህ ባሻገር ስፖርት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ሁነት እንደመሆኑ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ እጁን በማስገባት አጋርነቱን በማሳየት ዘመናትን ዘልቋል፤ በማሳየት ላይም ይገኛል።
የአትሌቲክስ ስፖርት መናኸሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ፤ ስፖርት የማህበራዊ እሴቶች አጋር መሆኑን ከሚያሳይባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የሆነውም «የሴቶች ቀንን» አስመልክቶ የሚካሄደው የሩጫ ውድድር ነው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ውድድሮች በትልቅነቱ ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዘው ሴቶችን ብቻ የሚያሳትፈው የ«ቅድሚያ ለሴቶች» ሩጫ ውድድር ነው። በውድድሩም ላይ የሴቶችን እኩልነት በተመለከተ መልዕክት የሚተላለፍበት ሲሆን፤ የዘንድሮ ሩጫም «ከጥቃት ነጻ ህይወት መብቴ ነው!» በሚል መሪ ቃል ታጅቦ ትናንት ተካሂዷል።
ቅድሚያ ለሴቶች የሩጫ ውድድር መካሄድ የጀመረው በ1996 ዓ.ም ሲሆን፤ ሴቶችን ብቻ እያሳተፈ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ ተካሂዷል። ይህ ውድድር ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለማክበርና ለመዘከር፣ ህብረተሰቡ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ጫና በማስቀረት በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ ለእንስት አትሌቶች ስኬት ዕውቅና ለመስጠት እንዲሁም ለውጥ በማምጣት ረገድ ያላቸውን ሚና የመደገፍና መልእክቶችን የማስተላለፍ ዓላማ ያለው ነው።
ይህንን ዓላማ የተገነዘቡ አጋር አካላት ለውድድሩ ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ሴቶችን የሚያነሳሱና ለሀገራቸው የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ የሚያመላክቱ መልዕክቶችንም ያስተላልፉበታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ17ቱ የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ አንዱ፤ ለጾታ እኩልነት ትኩረት በመስጠት ጾታዊ ጥቃቶችን ማስቆም ነው። በመሆኑም ከቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል። በየዓመቱ የሴቶች ቀንን ወይም «ማርች 8»ን በማስመልከት የሚካሄደው ይህ ውድድርም በተሳታፊ ቁጥር እያደገ፤ ትናንት12ሺ ሴቶች ተካፍለውበታል።
ባለፉት ዓመታት ከዚህ ውድድር በመነሳትም በርካቶች በኦሊምፒክና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ሊወክሉ ችለዋል። ከእነዚህ ታዋቂ አትሌቶች መካከልም አሰለፈች መርጊያ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ ጃለኒ ያኒ፣ ረሂማ ከድር፣ ሱሌ ኡቱራ፣ ማሚቱ ዳስካን እንዲሁም በለንደን ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷን ቲኪ ገላናን መጥቀስ ይቻላል።
በትናንቱ ውድድር ላይም እናቶች፣ ወጣቶች፣ ታዳጊና ህጻናት እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ሴቶች በሰንደቅ ዓላማ ታጅበው፣ በአገር ባህል ዲዛይን ልብሶቻቸውን አሳምረው፣ ፊታቸውንና ሌሎች አካላቸውን በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም አቅልመው ውድድሩን አድምቀውታል። ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው፣ ሠራተኞች ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት፣ የትንንሽ ሴት ልጆቻቸውን እጅ የያዙና ጨቅላ ህጻናትን በጋሪ የሚገፉ እናቶችም፤ በተመሳሳይ ካናቴራ ደምቀው፤ በጠዋቱ ነበር ከሩጫው ጎዳና የተሰባሰቡት።
በውድድሩ ላይም ከ200 በላይ የሚሆኑ ታዋቂ እና ጀማሪ አትሌቶችን ጨምሮ በአራት ዘርፎች ውድድሩ ተካሂዷል። በተምሳሌት ሴቶች፣ በዲፕሎማቶች እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት በተውጣጡ ተሳታፊዎች መካከልም ፉክክሩ ተደርጓል። በተጨማሪም 15 ዲፕሎማቶች፣ ሁለት ኡጋንዳውያን አትሌቶች እና 11አውስትራሊያውያን ተሳታፊዎች ነበሩ። የሩጫው ተሳታፊዎችም ከአትላስ ሆቴል በመነሳት፤ በኤድናሞል አደባባይ፣ በቦሌ ድልድይ፣ ዓለም ህንጻ፣ ደሳለን ሆቴል በማድረግ የ5ኪሎ ሜትሩን ውድድር ሸፍነዋል።
ፀሐይ ገመቹ በ15ኛው የቅድሚያ ለሴቶች የ5ኪሎ ሜትር ሩጫ በግሏ በመሳተፍ አንደኛ ሆና የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀች አትሌት ናት። ለሦስት ጊዜያት ተሳትፋ በዚህኛው ውድድር አሸናፊ በመሆኗ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማትም ነው የምትገልጸው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ውድድሮች ላይ የተሳተፈችው አትሌቷ የሴቶች ሩጫ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰጣት ትጠቁማለች። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ውድድር እንደነበር የጠቀሰችው አትሌቷ፤ ከዚህ በኋላ ለአገሯ መሮጥ እንደምትፈልግም ትናገራለች።
ውድድሩ ከተጀመረ ጀምሮ ለ15ዓመታት ተሳታፊ የሆነችው የውብነሽ ቁምላቸው፤ አካል ጉዳተኛ ብትሆንም ከ35ደቂቃ በታች በመግባት የምስክር ወረቀት አግኝታለች። በየዓመቱ ድምቀቱ እየጨመረና አጓጊ እየሆነ ያለ ውድድር መሆኑን ገልጻ መሰል መልእክት አስተላላፊና አዝናኝ የውድድር መድረኮች ተጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም እንደሆነ ትገልጻለች። በተለይ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ መቻላቸውን ማሳየት እንዳለባቸውም ጥሪዋን አስተላልፋለች።
የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋር፤ ውድድሩ ከመነሻው ጀምሮ ባሉት 15ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት እና ለውጥ በማሳየት እንደቀጠለ ትገልጻለች። ውድድሩ መልዕክትን ከማስተላለፉ ባሻገር ትልልቅ የሚባሉ ሴት አትሌቶችን ማፍራት ችሏል፤ ከዚህ በኋላም በርካታ አትሌቶችን ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ለማብቃት ያስችላል። ከዚህ ባሻገር ሴቶች የሚገናኙበት፣ የሚወያዩበትና አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበት የውድድር መድረክ በመሆኑ ተጽዕኖ መፍጠር እና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማምጣት የሚችል ውድድር መሆኑን ታብራራለች።
በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት የኡጋንዳ ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል፤ ከአውስትራሊያም በተመሳሳይ አትሌቶችን ማሳተፍ ተችሏል። ከዚህ በኋላም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ስም ያላቸውን ሴት አትሌቶችን ለመጋበዝ መታቀዱን አትሌቷ ትገልጻለች። መሰረት ጨምራም «ይህ ውድድር ከዚህ በላይ አድጎ እና ጎልብቶ ዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሆን ምኞቴ ነው፤ በመሆኑም ሴቶች በውድድሩ ላይ ተካፈሉ» የሚል አስተያየቷን ሰጥታለች።
በዘንድሮው የUN 2018 ቅድሚያ ለሴቶች ውድድርን በግሏ የተሳተፈችው አትሌት ፀሐይ ገመቹ የገባችበት ሰዓት 16፡05፡52 ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው የሱር ኮንስትራክሽን አትሌቷ ደባሽ ኪላል 16፡09፡16 በሆነ ሰዓት ውድድሯን በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። ሌላኛዋ የግል ተወዳዳሪ የኔነሽ ጥላሁን ደግሞ 16፡09፡48 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ውድድሯን አጠናቃለች። በታዋቂ ሰዎች ዘርፍ አርቲስት አምለሰት ሙጬ፣ አሰልጣኝ መሰረት ማኔ እና አርቲስት ሄዋን(ጃኖ) ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ የተዘጋጀላቸውን ሽልማትም ወስደዋል።
ለአሸናፊዎች በአጠቃላይ 70ሺ ብር የተዘጋጀ ሲሆን፤ አንደኛ የወጣችው አትሌት ከሜዳሊያ እና ዋንጫ ሽልማት ባሻገር የ15ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላታል። የተምሳሌት ሴቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ አምባሳደሮች እና ቲ-ሸርቶቻቸውን ያስዋቡ ተወዳዳሪዎችም የተለያዩ ሽልማትን አግኝተዋል። 5ኪሎ ሜትሩን በ35 ደቂቃዎች ለገቡት ተሳታፊዎችም ከሜዳሊያ በተጓዳኝ የሴቶች ውድድር በጎ ፍቃድ አምባሳደር የሆነችው አትሌት መሰረት ደፋር ፊርማ ያለበት የምስክር ወረቀት ወስደዋል። ከውድድሩ በኋላም ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜግነት ያላቸው አርቲስቶች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ ተሳታፊዎችን አዝናንተዋል።

ብርሃን ፈይሳ 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።