ሁለት የፊፋ ባለሙያዎች ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

12 Mar 2018

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫውን እያራዘመ መጋቢት ወር ላይ ደርሷል። አሰልቺ የሆነው ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ መራዘሙን አስመልክቶም የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) ሁለት ባለሙያዎችን እንደሚልክ ሶከር ኢትዮጵያ በዘገባው አስነብቧል።
አወዛጋቢውና አሰልቺው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ በጥቅምት ወር መካሄድ ቢኖርበትም በተለያየ ምክንያት እየተራዘመ ወራትን አሳልፏል። ምርጫው ባለፈው ጥር ወር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን ለፊፋና ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ቀድሞ እንዲያሳውቅ ቢጠየቅም ባለማሳወቁ ምክንያት በየካቲት ወር ይካሄዳል የተባለው ምርጫ በድጋሚ ሊራዘም መቻሉን ፊፋ በላከው ደብዳቤ ማሳወቁ ይታወሳል።
ዓለም አቀፉ አካልም የምርጫ ሂደቱ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመገምገም ሁለት ባለሙያዎችን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልክ የታወቀ ሲሆን፤ ስምና የሥራ ድርሻቸው ግን እስካሁን ግልጽ እንዳልተደረገ ዘገባው ያሳያል።
ዛሬ አዲስ አበባ የሚገቡት እነዚህ ባለሙያዎች ለምን ያህል ቀን የማጣራት ሥራቸውን እንደሚያከናውኑም አልታወቀም። ነገር ግን በምርጫው ዙሪያ የሚመለከታቸውን አካላት እስካሁን ባለው የምርጫ ሂደት እና አሉ በሚባሉ ችግሮች ላይ ተንተርሰው ያነጋግራሉ። በሚያደርጉት ማጣራት መነሻነትም ምርጫው መቼ እንደሚደረግ እና ስለሚኖረው አጠቃላይ ነገር ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ብርሃን ፈይሳ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።