የእግር ኳሱ መድረክ ወቀሳውም ሙገሳውም እንዲሰምር

15 May 2018

እግር ኳስ በአሁን ወቅት ስሜት መር ከሆነው መነቃቃቱ ባሻገር በዘመናዊ ሀሳቦችና የአስተዳደር ዘዴዎች እየተደገፈ የእድገት ማማው ላይ ደርሷል። አገራትም ዘመን አመጣሽና የጊዜው መገለጫ የሆኑ ስልቶችንና ዘመናዊ የቴክሎኖጂዎችን በመጠቀምና በተለያዩ ውድድሮች ላይ በመተግበር የስፖርቱን እድገት በማጣጣም ላይ ይገኛሉ።
የእነዚህ አገራት እግር ኳስና ውጤቱም በዘመናዊ የቪዲዮ የቴክሎኖጂዎች የታገዘ የተጤነና የተብራራ ትንታኔዎችና መረጃዎች ተደግፎ የሚቀርብ ነው። የክለቦች፣ ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች፣ የተጫዋቾች ውጤትና ብቃት እንዲሁም የእያንዳንዱ ጨዋታ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ተቀርጾ በምስል ተደግፎ ይቀርባል። ይህ እንደመሆኑም ወቀሳውም ሙገሳውም በመሰለኝ ሳይሆን በአግባቡ በተደራጀ መረጃና ማስረጃ መሰረት ባደረገ መልኩ ይተነተናል።
በእግር ካሱ ዓለም አሸናፊ ለመሆንና በሌሎች ላይ ከፍተኛ ብልጫ ለመውሰድ በተጫዋቾች ችሎታ ላይ የተመረኮዘ የቦታ አሰጣጥና የተጫዋቾች ተገቢ የሚና አተገባበር እንዲሁም ጠንካራ የአካል ብቃት ወሳኝ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የጨዋታውን ሂደት ማንበብ የግድ ነው። በመቅረጸ ምስል ተደግፈው የሚቀርቡ ትንታኔዎች ታዲያ አንድን ጨዋታ ለማንበብ ቀዳሚ አማራጭ ናቸው።
በእነዚህ በመቅረጸ ምስል ተደግፈው የሚቀርቡ ትንታኔዎች የተጫዋቾች ብቃት፣ የቡድኖች የማጥቃትና የመከላከል ሚዛን በዝርዝር መረጃ በጥልቀት ይተነተናል። ክለቦችም እንዴት እንዳሸነፉና እንዴት ሽንፈት እንደገጠማቸው የቡድኖችን ብሎም የተጫዋቾች የብቃት ደረጃ ቁጥራዊ በሆነና በተደራጀ መልኩ ይቀርባል።
በየጨዋታው የሚቆጠሩ ግቦች ሂደት፣ ተጫዋቾች ያሳዩት ደካማም ሆነ ጠንካራ እንቅስቃሴ፣ በጨዋታው ላይ የተሰሩ ያልተገቡ አጨዋወቶችን በዚህ ቴከኖሎጂ ድጋፍ አንድ በአንድ ተተንትነው ይቀርባሉ። የጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ምርጫ የሚከናወነው ይህንኑ የቴክሎኖጂ መረጃ በመከተል ነው። በተለይ አሰልጣኞች ጨዋታን የሚያሸንፉበት ሂሳባዊ ቀማር የሚሰሩትም እነዚህን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ ነው። በዚህ ረገድ የሚቀርቡ ትንታኔዎችም ቢሆኑ ክፍተቶችን ብቻ ለማሳያት የሚደራጁ አይደሉም። ድክመትና ጥንካሬዎች እንዲሁም የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም አመላካች እንጂ።
ከዚህ አንጻር የአገራችን ስፖርት ሲቃኝ ግን ኋላቀርና ባህላዊ ስለመሆኑ ምስክር አያሻውም። በተለይ የአገሪቱ እግር ኳስ ከልማዳዊ እሳቤ፤ ከተለመደ አካሄድ መውጣት አቅቶታል። በተለይ ከዘመኑ ጋር በመዘመን ቴከኖሎጂን ከመተግበር አንጻር እጅጉን ደካማ ነው። ኦፍሳይድና ኦንሳይድ አሊያም የግብ መስመርን ያለፉ ተጫዋቾችንና ኳሶችን ለመለየት የሚያስችል ቀርቶ ጨዋታዎች በመረጃ አስደገፎ የሚተነተን የቪዲዮ ቴከኖሎጂን መተግበር ጣር ሆኖበታል።
መሰል አሰራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ባለመቻሉም፤ የቡድኖችን ብሎም የተጫዋቾችን የብቃት ደረጃ በመረጃ ተደገፎ አይቀርብም። ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ትንታኔ የሚሰጥ አካልም ሆነ ተቋም የለም። በዚህም ምክንያት እግር ኳሳችን ባልተጤኑና ባልተብራሩ ትንታኔዎች የተደገፈ ሆኗል። ኳሳችን የሚተነተነው እውነትን መሰረት ባደረገ መረጃ ሳይሆን ከተንታኙ ፍላጎት ወይም ሌሎች በራሳቸው ሃሳብ ለራሳቸው ዓላማ በቀየሱት አቅጣጫ በመሆኑ የግለሰብ ፍላጎት አይሎ እውነት ይደበቃል።
በማንኛውም ጨዋታ የተጫዋቾች ብቃት፣ የቡድኖች የማጥቃትና የመከላከል ሚዛን በዝርዝር መረጃ በጥልቅ ትንታኔ የተደገፈ አይደለም። አሁን አሁን በዘልማድና ድፍረት ከመናገር በዘለለ ከጨዋታው ተጨባጭ ሁኔታ ጥሩ ተጫዋች ማን ነበር? የሚለው አይታወቅም። ዝርዝር የስፖርት ትንታኔዎችን የሚሰጡትም ቢሆን በመላ ምት ነው።
በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም መሰል ትንታኔ ሲሰጡ እናስተውላልን። ይሁንና ይህ ክዋኔ በተደራጀ መረጃና ማስረጃ የተደገፈ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ የአንድ ወገን ስሜት ያጋደለበት ግላዊ ፍላጎትና ስሜት የሚንፀባረቅበት ሆኖ ይታያል። ወቀሳውም ሙገሳውም በአግባቡ በተደራጀ መረጃና ማስረጃ የተቀመረ አይደለም። በዚህም ውጤት የማጣት ምክንያትን ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ፊቱን አዙሯል።
የሌሎች አገራት ተሞክሮ ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳየን ክለቦች የተፎካካሪነት አቅማቸውን የሚያጎለብቱት እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ የነበራቸውን ጥንካሬና ድክመት በአግባቡ ሲገመግሙ ብሎም ሲያውቁት ነው። የአገራችን አብዛኞቹ ክለቦች በአንፃሩ እንዴት እንዳሸነፉና እንዴት ሽንፈት እንደገጠማቸው ማብራሪያ ለመስጠት የሚቸገሩ ናቸው።
አንድ ክለብ ሲያሸንፍም ሆነ ሲሸነፍ ለምን? የሚለውን ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ የለም። የጎብዝናንውም ሆነ የስንፍናውን መጠን የሚያውቅ የለም። በመረጃ አስደግፎ ብዙዎችን ማሳመን አልተለመደም። ተጫዋቾች በእለቱ ያሳዩትን የተለየ ክህሎት አንድ በአንድ አይዳሰስም። ክለቡ በቀደመ ጨዋታው ያስከበረው የበላይነት አሊያም ያስጠበቀው ክብር በቅጡ አይታወቅም። ካለፈው ጨዋታ ምን እንደተማረ መናገር የሚችል ክለብ የለም። የያኔው ድክመት ለዛሬው ማስተማሪያ ሲሆነው አይታይም።
ማሸነፍን እንዴት እንደሚመጣ አልያም ሽንፈት በምን ምክንያት እንደሚከሰት እንዴት መብለጥና ማሸነፍ እንደሚቻል በቅጡ የሚያስረዳ የለም። ውጤት ሲጠፋ ምክንያት ፍልጎ መደርደር ሰፍኗል። በዚህም ድክመት ለማሻሻል ሳይችል ሌላ ጨዋታ ስለሚደረግ ትርጉም አልባነቱ እየጎላም ነው። በሽንፈት የቆሰለው ክለብ ድክመቱን የሚያውቅበት መንገድ የለውም። ካለፈው መማር የማይፈልግ ያለፈ ስህተትን ለመድገም የተዘጋጀ ነው። ከትላንት የሚማር ነገን ያርማል። የትላንቱን ጥሩ ይዞ እንዲቀጥልና መጥፎውን እንዲያርም ያግዘዋል።
መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ታዲያ የዘልማድ አካሄድና አሰራሮችን መቀየር ትክክለኛነት ይሆናል። በተለይ ጨዋታዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዙበት በዚህ ወቅት የተለያየ ፍላጎት ግላዊ እሳቤ ካላቸው አካላት የሚመነጭ አስተያየትና ትንታኔዎች መቆም አለባቸው።
የክለቦችን ጠንካራና ደካማ ጎን እንዲሁም ክፍተቶች፣ መንስኤ በትክክለኛ መረጃ አስደግፎ ለአድማጭ ተመልካች ማቅረብ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ እግር ኳሳችን ሁሌም ከዘመኑ ጋር መታደስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍባቸውን መንገዶች በመፈለግ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። ምክንያት ከመደርደር ይልቅ ክለቦች እንዴት እንዳሸነፉ እና እንዴት ሽንፈት እንዳጋጠመው ማብራሪያ የሚሰጥ የቴክኒክ ዳይሬክተር አሰልጣኝ በሌለበት አገር መሰል በመረጃ የተደገፈ ትንታኔ ፋይዳው አጠያያቂ አይደለም።
በትልቁ ሊያስማማን የሚችለው በእርግጥ እግር ኳስ ላይ የቱንም ያህል ቴክኖሎጂ መጠቀም ቢቻል እንኳ ፍፁም ማድረግ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በእግር ኳስ ኡደት ሁሌም ፍፁምነት ስለማይኖር ፡፡
ይሁንና ስፖርቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ በርካታ ለውጦችን ማምጣትና ስሜታዊ የሚደርጉ ችግሮችን መቀነስ ይቻላል፡፡ ተጠያቂነትና ግልጸኝነት ያሰፍናል። ምን ተሰርቷል ምን አልተሠራም ተብሎ ከውጤቱ መገኘት አልያም መታጣት ጀርባ ኃላፊነት መውስድ ያለበት በይፋ ይለያል።
ስፖርቱን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ በተለይ በመቅረፀ ምስል ትንታኔ ማስደገፍ ወቀሳውንም ሙገሳውንም በመሰለኝና በደሳለኝ ከመግለፅ ይልቅ በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ያደርገዋል። የአንድ ሰው ተጠያቂነት አሊያም በዳኞች ላይ የሚነሱ ሰበቦች መቆሚያ ያገኛል። የተጣመመውን ማቃናት ይቻላል። እግር ኳሱን ከውዝግብ ማጥራትም እንደዛው።
ይህ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእግር ኳስ ትንታኔም የእያንዳንዱን ጨዋታና የተጫዋቾች እንቅስቃሴ በመተንተን ለብሄራዊ ቡድንም ሆነ ሌሎች ጨዋታዎች በሚመረጡ ተጫዋቾች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረት ያግዛል። እግር ኳሳችንን ዘመናዊ ለማድረግና ሊጋችንንም ለማስተዋወቅ ብሎም ተጫዋቾቻችን ከሀገር ውጪ የመጫወት እድልንም ለማስፋት ይጠቅማል፡፡ እንደ አጠቃላይ ይህን ማድረግም የሀገሪቱን እግር ኳስ በዘመናዊ አሰራር ወደፊት እንዲራመድ ያደርገዋል። ለሀገራችን እግርኳስ መነቃቃት አይነተኛ ሚና ይጫወታል።
የአገሪቱን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ቢሆን ይህ በመቅረጸ ምስል ተደግፎ የሚሰጥ ትንታኔ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ከ3 ዓመት በፊት የቡድኖችን የእግር ኳስ አቀራረብ በዘመናዊ መልኩ ለማስተንተንና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ (R&D GROUP) ከተባለ ተቋም ጋር የፊርማ ስምምነት ማድረጉ የቴክኖሎጂውን ጠቀሜታ መረዳቱን ያሳያል። ሆኖም ዓመታትን ተሻግሮም ውጤቱ አደባባይ አልወጣም።
በእርግጥ የዘንድሮውን ዓመት ከሌላው የውድድር ጊዜያት ለየት የሚያደርገው በመቅረጸ ምስል ተደግፎ የሚሰጥ ትንታኔ፤ ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ጨምሮ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ በኢትዮ ፉትቦል ሶሊሽን መመልከት ተችሏል። ይህም ይበል የሚያሰኝ ነው።
አሁንም ቢሆን ስለ እግር ኳሳችን ለውጥ የምንጨነቅ ከሆነ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ ብሎም የክለቦቻችንን ደረጃና እግር ኳሳዊ አቀራረብን ከፍ ለማድረግ ያልዘመነው እግር ኳሳችን አስቀድሞ እንዲዘምን ማድረግ የግድ ይለናል።
ይህን ለማድረግ ደግሞ አቅም በፈቀደ መልኩ ቴክኖሎጂዎችን ማስተግበር አሊያም ለማስተግበር የሚመጥኑ ሙያተኞች ማሳተፍና ማበረታታት የግድ ይለናል። ምክንያቱም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ መደረግ ያለበትን አለማድረግ ስህተት ነው። መሰል ተግባራት ለመተግበር ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ ሲሆንም መንግሥት እጁን ሊያስገባና እገዛ ሊያደርግ ይገባል። እንደ እኔ በእግር ኳሱ መድረክ ወቀሳውም ሙገሳውም እንዲሰምር ብሎም እግር ኳሳችን በዚህ መልኩ ቢታይና ቢደገፍ መልካም ይመስለኛል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።